Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትአሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌና የቻን ቆይታቸው

አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌና የቻን ቆይታቸው

ቀን:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ሩዋንዳ እየተካሔደ ካለው 4ኛው የቻን ውድድር ቆይታውን አጠናቆ ተመልሷል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ሌሎችም ሰባት አገሮች ወደ ሩብ ፍፃሜ አልገቡም፡፡ ከእነዚህ አገሮች ውስጥ ናይጄሪያና ሞሮኮ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን በዴሞክራቲክ ኮንጎ 3ለ0፣ ከካሜሩን ጋር 0ለ0 እና በአንጎላ አቻው ደግሞ 2ለ1 ተሸንፎ አምስት ጎል ተቆጥሮበት አንድ ጎል አስቆጥሮ በአንድ ነጥብ የምድቡን የመጨረሻ ደረጃ ይዞ ከአራተኛው የቻን ሻምፒዮና ውጪ ሆኗል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ በኃላፊነታቸው መቀጠል አለባቸው የለባቸውም የሚሉ ሁለት ዓይነት አመለካከቶች ሲደመጥ ሰንብቷል፤ እየተደመጠም ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአገሪቱ ረዥም የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ የኅብረተሰቡን ቀልብ የሚገዛና የውጤት ረሐቡን የሚያስታግስ የተሟላ ቁመና ያለው ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት የሚደረጉ ጥረቶችን በሁለት መሠረታዊ ነጥቦች በመክፈል የሚመለከቱት አሉ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ መሠረታዊ ለውጥ ካልተካሔደበት በስተቀር አሠልጣኝ በመለዋወጥ ለውጥና ዕድገት እንደማይመጣ፣ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ ለእግር ኳሱ የሚመጥን የሰው አቅም መጠቀም እስካልተቻለ ድረስ ለውጥ አይደለም የለውጥ እንጥፍጣፊ እንኳ እንደማይታይ ያምናሉ፡፡

እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች ብዙ ጊዜ ስለአገሪቱ እግር ኳስ ውድቀት ሲነገርና ሲተች የሚደመጠው ብሔራዊ ቡድኑ ሽንፈት ሲያጋጥመው ብቻ ነው፣ ሆኖም ለአንድ ብሔራዊ ቡድን እንደ ግብዓት መታየት ያለባቸው ነገሮች ላይ ግን ትኩረት አይደረግም ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጀምሮ በክለቦችና በሥራቸው በሚገኙ ቡድኖች እግር ኳሱ በሚፈልገው መጠን መዋቅራዊ አደረጃጀቶቻቸው ትክክል ነው ወይ? የሚባሉት መሠረታዊ ነጥቦች ላይም ያን ያህል ክርክርና ትችት እንደማይደመጥ ጭምር በመግለጽ መሠረት በሌለው እግር ኳስ ላይ መተራመስና መተቻቸት ብቻውን የትም እንደማያደርስ ጭምር ያክላሉ፡፡

በብሔራዊ ቡድኑ ወቅታዊ ጉዳይና የቻን ቆይታውን አስመልክቶ አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌና የቡድን መሪ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ባለፈው ሐሙስ ጥር 19 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫው ለተነሱ ጥያቄዎች አሠልጣኙ የሰጡትን መልሶች እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

ጥያቄ፡- ብሔራዊ ቡድኑን በዋና አሠልጣኝነት ሲረከቡ ካለፈው የተሻለ ውጤት የማላመጣ ከሆነ በራሴ ጊዜ ከኃላፊነቴ እለቃለሁ ብለው ነበር፡፡ አሁን ላይ የተጠበቀው ውጤት አልመጣም፡፡ ከዚህ አኳያ በቀጣይ ምን ያስባሉ? ሩዋንዳ በነበሩበት ወቅት በተለይ ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ሽንፈት በኋላ በቂ ዝግጅት እንዳላደረጉ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም እርስዎና ቡድንዎ ወደ ሩዋንዳ ከማምራቱ በፊት በቂና ጥሩ ዝግጅት ማድረግዎን መናገርዎ ይታወሳል ምን አስተያየት አለዎት?

አሠልጣኝ ዮሐንስ፡- ብሔራዊ ቡድኑ ሆቴል ተሰባስቦ የሚያደርገው ዝግጅት ብቻውን የተሟላ ዝግጅት ብለን ልንጠራው አንችልም፡፡ የወዳጅነት ጨዋታዎች የዝግጅት አካል መሆናቸው መዘንጋት የለብንም፡፡ ከዚህ አኳያ ከያዝናቸው 23 ተጨዋቾች ውስጥ በአንድ የወዳጅነት ጨዋታ የተመለከትናቸው 13 ብቻ ናቸው፡፡ የቀሩትን ሌላ የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚኖር ተነግሮን ስለነበረ አልሞከርናቸውም፡፡ ይህንን ስል ምክንያት ለመደርደር ሳይሆን የሆነውን እውነት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ካለፈው የተሻለ ውጤት ካላመጣሁ እለቃለሁ ማለቴን አልክድም፡፡ ወደፊትም ቃሌ እንደተጠበቀ ነው፤ ውጤቱ የተሻለ አይደለም የሚል ካለ በተጨባጭ ማስረጃ መነጋገርና መተማመን እንችላለን፡፡

ጥያቄ፡- ቡድኑ በተቃራኒ ቡድን ላይ ጫና በመፍጠር የጎል ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ክፍተት ታይቶበታል፡፡ በተለይ ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ጋር ጎልቶ መታየቱ ግልጽ ነበር፡፡ ችግሮቹን ቢገልጹልን?

አሠልጣኝ ዮሐንስ፡- ጎል በማስቆጠር ደረጃ እንደተባለው የአገሪቱ ችግር ከሆነ ቆይቷል፡፡ ይህም ማለት ግን በአገሪቱ የሚገኙ የፊት መስመር ተጨዋቾች (አጥቂዎች) ጎል ማስቆጠር እየቻሉ ነገር ግን ላለማስቆጠር ፍላጎት ስለሌላቸው አይደለም፡፡ የአገሪቱ እግር ኳስ ደረጃ ነፀብራቅ ነው፡፡ ጎል አስቆጣሪና ፈጣሪ ተጨዋቾች በአንድ ሳምንት ዝግጅት ቀርቶ በወራትም መፍጠር አይቻልም፡፡ ሒደቱ ራሱን የቻለ ልማት ነው፡፡ አሁንም መሥራት ይኖርብናል፡፡ ችግሩ በቻን ውድድር ላይ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ዋንጫ፣ በዓለም ዋንጫና በቻን ማጣሪያዎች በግልጽ የተመለከትነው እውነት ነው፡፡ በብዛት ጎል ሲያስቆጥሩ የተመለከትናቸው ተጨዋቾች የመሐልና የኋላ መስመር ተጨዋቾች ናቸው፡፡ ይህን ስል አሁን አጥቂዎች ሥራቸውን አልሠሩም እያልኩ አይደለም፡፡ መፍትሔውና ሁላችንም እውነትም የአገሪቱን እግር ኳስ እናሳድጋለን ብለን ካመንን ተተኪ ወጣቶች ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ከማንኛውም አካል ጋር ልዩነት መኖሩ እንደተጠበቀ አብሬ ለመሥራት ዝግጁ ነኝ፡፡ በውጤት ደረጃ ስለሚባለው አሁንም እደግመዋለሁ፣ በሴካፋም ሆነ በቻን ካለፈው የተሻለ ውጤት አስመዝግቤያለሁ፡፡ በማስረጃ መነጋገር ይቻላል፡፡ በቂ ነው በፍፁም፤ ገና ብዙ መሥራት ይኖርብናል፡፡

ጥያቄ፡- በቻን ውድድር የጨዋታ ቁጥሮች መተንተኛ ዘዴ (ፕሮዞን) መሠረት የኢትዮጵያ ቡድን ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ቡድኑ የሚያጠቃ እንዳልሆነ ያሳያል ምንድነው አስተያየትዎ?

አሠልጣኝ ዮሐንስ፡- በዲሞክራቲክ ኮንጎ ሙሉ ለሙሉ ተበልጠን ነው የተሸነፍነው፡፡ ለቀጣዮቹ ጨዋታ ግን በነበረን ጊዜ በጨዋታው አጠቃላይ ይዘት ላይ ከተጨዋቾቹ ጋራ በግልጽ በመነጋገር ለሁለተኛውና ሦስተኛው ጨዋታ በምንችለው መጠን በራሳችን ክልል ስህተቶችን ሳንፈጽም በተለይ ከካሜሩን ጋር በተደረገው ጨዋታ ነጥብ ተጋርተን ለመውጣት ችለናል፡፡ ምንም እንኳ በአንጎላ ብንሸነፍም ጎሎችን በመፍጠር ደረጃ ከካሜሩኑም ጨዋታ የተሻሉ ዕድሎችን ፈጥረን ነበር፡፡ ይህ የአቋም ለውጥ ከተጋጣሚዎቻችን አንፃር ሳይሆን በራሳችን ቡድን ውስጥ መሻሻሎች እንደነበሩ ነው የተረዳነው፡፡ ግልጽ ለማድረግ የራሳችንን ሥራ እያሻሻልን መምጣታችንን ተመልክተናል፡፡

ጥያቄ፡- በድምር ውጤት 5ለ1 ተሸንፎ የተመለሰ ቡድን በምን መመዘኛ ነው ማሻሻል አሳይቷል ማለት የሚቻለው?

አሠልጣኝ ዮሐንስ፡- የጨዋታውን ዳታ መመልከት ይቻላል፡፡ እየተናገርኩ ያለሁት ከሌሎች አንፃር ሳይሆን ከአገራችን እግር ኳስ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት  ቡድኔ ከጨዋታ ጨዋታ እያደረገ የመጣውን እንቅስቃሴ ነው፡፡ እርግጥ ነው ተጋጣሚዎቻችን ከእኛ የተሻሉ ናቸው፡፡ በእንቅስቃሴው ብቻ ሳይሆን በደረጃቸውም ይበልጡናል፡፡ ከዚህ በመነሳት ለተጨዋቾቼ ክብር እሰጣለሁ፡፡

ጥያቄ፡- የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር እርስዎ በቻን ያስመዘገቡትን ውጤት ተከትሎ ውጤታማ እንዳልሆኑ በዚህም የስፖርት ቤተሰቡ እንዳዘነ፣ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጉዳይን ተመልክቶ የሕዝቡን እንባ ማበስ የሚችል ውሳኔ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡ ይህንን እንዴት ይመለከቱታል?

አሠልጣኝ ዮሐንስ፡- የብሔራዊ ቡድኑና የቴክኒክ ዲፓርትመንቱ የሥራ ድርሻና ኃላፊነት የተለያየ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ሆኖም የዲፓርትመንቱ ኃላፊ ስለእኔ ጉዳይ ተናግረው ከሆነ መታየት ያለበት በአስተዳደራዊ ጉዳይ በመሆኑ ምንም ማለት አልችልም፡፡ እርግጥ ነው ጋዜጣውን አላነበብኩትም፡፡ ከተመለስኩ በኋላ ግን የግል ሰብእናዬን የሚነካ ሆኖ ካገኘሁት ግን ጉዳዩን በሕግ ለመመልከት የምገደድበት ሁኔታ ይኖራል፡፡

ጥያቄ፡- እርስዎ ቡድኑን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ በተጨዋቾቹ ውስጥ የተመለከቱት ለውጥ ካለ?

አሠልጣኝ ዮሐንስ፡- በትልቁ ማንሳት የምፈልገው የተጨዋቾች ዲሲፕሊን ነው፡፡ ቡድኑ እስከ ዛሬ ድረስ ከ20 ያላነሱ ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡ በዚህ ሁሉ ጨዋታ በቀይ ካርድ ያጣነው ተጨዋች አንድ ብቻ ነው፡፡ ይህን የምልበት ምክንያት ደግሞ ብዙዎቹ ተጨዋቾች ለኢንተርናሽናል ጨዋታ አዲስ ናቸው፡፡ አዲስ ስል ከዕድሜ ጋር እንዳይገናኝ እሰጋለሁ፣ ከዚህ አኳያ ትልቅ ለውጥ አድርጌ እወስዳለሁ፡፡ ሌላው ከነባር ተጨዋቾች ባልተናነሰ አዳዲስና ወጣት ልንላቸው የምንችላቸው እንደነ አስቻለው ታማነ፣ ካቾች ፓኖም፣ ራምኬሎ ሎክ፣ ተካልኝ ደጀኔ፣ ቢኒያም በላይና ሌሎችም በብሔራዊ ቡድን ደረጃ መጫወት የቻሉት በዚህ ብሔራዊ ቡድን ነው፡፡ በአጭር ጊዜ የተገኙ ወጣቶች ናቸው፡፡ በአካል ብቃት ደረጃም ቢሆን እንደ ጨዋታው ብዛት በቀላሉ ለጉዳት አልተዳረጉም፡፡ ይህ በራሱ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ የምንፈልገውን ያህል ባይሆንም የማሸነፍ ሥነልቦናና የቡድን ውህደቱም ከብዙ በጥቂቱ መጥቀስ እችላለሁ፡፡

ጥያቄ፡- ወደ ኃላፊነት ከመጡ ጀምሮ ትክክለኛውን ቁጥር መናገር ባይቻልም ወደ 80 የሚደርሱ ተጨዋቾችን ተመልክተዋል፡፡ ለሚቀጥለው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያስ ቻን ላይ የታዩት ልጆች ይቀጥላሉ ወይስ እንደተለመደው አዳዲስ ተጨዋቾች የሚመጡበት ሁኔታ ይኖር ይሆን?

አሠልጣኝ ዮሐንስ፡- እኔ እስከማውቀው ድረስ እስካሁን ለሦስት ዓይነት ውድድሮች ወደ 70 የሚጠጉ ተጨዋቾችን ሞክረናል፡፡ ውድድሮቹ ሴካፋን ሳይጨምር የዓለም ዋንጫና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ እንዲሁም የቻን ዋንጫ ማጣሪያ በተመሳሳይ ሰለነበረብን ነው፡፡ እስካሁን ባለው 16 ቡድኖች ለሚሳተፉበት ለቻን ውድድር በቅተናል፡፡ ለዚህም 30 ተጨዋቾችን መርጠን 23 ተጠቅመናል፡፡ ወደፊትስ ለሚለው በግሌ ቀደም ሲል እንደተናገርኩት የማምነው በወቅታዊ አቋምና አቋም ብቻ ነው፡፡ ይኼ የእግር ኳሱም ቋንቋ ነው፡፡ ሌላ ምንም ምስጢር የለውም፡፡ ብሔራዊ ቡድን የአገር ጉዳይ እስከሆነ ድረስ አቅሙ አለኝ የሚል ኢትዮጵያዊ ተጨዋች ሁሉ እኩል መብት ተሰጥቶት ሊታይ ይገባል፡፡ ወሳኙና መሠረታዊው ነገር አቅምን ማሳየት ብቻ ነው፡፡

ጥያቄ፡- በሦስት ጨዋታ 18 ተጨዋቾችን ተጠቅመዋል፡፡ ይኼ ቡድኑ ቋሚ 11 የሚባል ተጨዋች እንደሌለው ያሳያል?

አሠልጣኝ ዮሐንስ፡- ጋቶች ፓኖምና በረኛው አቤል ማሞ በመጎዳታቸው ሁለት ልጆችን ለመቀየር ከመገደዳችን ውጪ ጉዳት በሌለበት የተጠቀምንባቸው 16 ተጨዋቾችን ነው፡፡ በሦስት ጨዋታ አምስት ልጆች መቀየሩ ነውሩ ምኑ ላይ ነው፤ ለዚህ ከታላላቆቹ የእንግሊዝ ክለቦች አርሰናል በሳውዝሀምተን 4ለ0 በተሸነፈ ማግስት ቬንገር በቀጣዩ ጨዋታ አራት ተጨዋቾችን ቀይረው ማስገባታቸውን መዘንጋት ያለብን አይመስለኝም፡፡

ጥያቄ፡- በቻን ውድድር ላይ የተሻለ ነገር እንደተሠራ አሠልጣኙም ሆኑ የቡድን መሪው እየተናገራችሁት ነው፡፡ ሕዝቡ ደግሞ በቡድኑ ውጤት ከፍተኛ ተቃውሞ እያሰማ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በዚህ መግለጫ ስንጠብቅ የነበረው አሠልጣኙ በራሳቸው ጊዜ ለቅቄያለሁ እንደሚሉ ነበር፡፡

አሠልጣኝ ዮሐንስ፡- የምንነጋገረው ስለእግር ኳስ ነው፡፡ እየተጠየቅኩት ያለው ደግሞ የሰዎች የግል አስተያየት ነው፡፡ እኔም የግሌ አስተያየት አለኝ፡፡ አንተም (ጠያቂው) በተመሳሳይ የግል አመለካከት ይኖርሃል፡፡ ስለዚህ ሰዎችም የግል አስተያየታቸውን በፈለጉት ዓይነትና መጠን ሊያንፀባርቁ ይችላሉ፣ መብታቸውም ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት የተለያየ አመለካከትና አስተሳሰብ ከሌለ ወደ ትክክለኛው የመፍትሔ አቅጣጫ መሔድ አይቻልም፡፡ የተለያዩ አመለካከቶች ያስፈልጋሉ፡፡ የምመራው የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚወክለውን ብሔራዊ ቡድን ነው፡፡ ታዲያ እንዴት ነው ሕዝብ ተመሳሳይ አመለካከት እንዲኖረው የምጠብቀው? ከፊሉ የብሔራዊ ቡድኑን ወቅታዊ ውጤት እንደማይመቸው ሁሉ በሌላ በኩል ደግሞ አይዟችሁ በርቱ የሚሉ አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለሚወክለው ብሔራዊ ቡድን የፈለገው ትችትና አስተያየት የመሰንዘር ሙሉ መብት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንንም ወደን ሳይሆን በግድ መቀበልና ማስተካከል ይጠበቅብናል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዮሐንስ ሳሕሌ ያደረገው ማን ነው? ታዲያ ይኼ ከሆነ ዮሐንስ ሳሕሌ ላይ እየተነሳበት ያለው ትችትና ወቀሳ ለአገሪቱ እግር ኳስ እስከሆነ ድረስ የማይቀበልበት ምክንያት ለምንድነው? መቀበል ይኖርበታል፡፡ በባህርዳርና በሐዋሳ እንዲሁም በአዲስ አበባ ስታዲዮም የተመለከትነው ተመልካች ያረጋገጠልን ይህንኑ ነው፡፡ በግሌ ምስጋናዬ ላቅ ያለ ነው፡፡ ልዩነቶቻችን እንዳሉ ሆኖ በአገር ጉዳይ አንድ መሆን ስንችል ነው ወደ ትክክለኛው ዕድገት የምናመራው፡፡ አሁንም እደግመዋለሁ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ወደተሻለ አቅጣጫ የሚወስድ ሐሳብ ካለው ሰው ጋር አብሬ ለመሥራት በማንኛውም ጊዜና ወቅት ዝግጁ ነኝ፡፡ ለእግር ኳሱ ዕድገት ከሆነ ማለቴ ነው፡፡ ምክንያቱም የተቀበልኩት የሕዝብና የአገር አደራ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሊቆረቆር ይገባዋል፡፡ አገሩ ነው፤ ባንዲራው ነው፤ እግር ኳሱ ወደምንፈልገው ዕድገት እንዲመጣ ከፈለግን እግር ኳሱን በሚመለከቱ በተለያዩ ሐሳቦች ዙሪያ ቻሌንጅ መደራረግ ያስፈልጋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...