Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የኢሕአዴግ ፀባይ እኛን መተንበይ የማንችል መሪዎች አድርጎ ነው ያስቀመጠን››

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፣ የመድረክ ፕሬዚዳንት

ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የተቃውሞ ፖለቲካ ጎራውን በመምራት ላለፉት 25 ዓመታት በአገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ከፍተኛ የሆነ ሚና የተጫወቱ ፖለቲከኛ ናቸው፡፡ ከሽግግር መንግሥቱ ምሥረታ ጀምሮ የተለያዩ ኅብረቶችንና የፓርቲዎችን ስብስብ በመምራት የሚታወቁ ፖለቲከኛም ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅትም የአራት ፓርቲዎች ስብስብ የሆነው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት በአገሪቱ የፖለቲካ ውጣ ውረድና በተቃዋሚ ፓርቲዎች ተጠናክሮ አለመውጣት፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ስለተከሰተው ድርቅና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ነአምን አሸናፊ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከሽግግር መንግሥቱ ጊዜ ጀምሮ ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡ በአጠቃላይ የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር ባለፉት 25 ዓመታት ያለፈበትን መንገድ እንዴት ይገልጹታል? ውጤትና ፈተናዎቹስ ምን ይመስሉ ነበር?

ፕሮፌሰር በየነ፡- የተነሳው ጥያቄ ውስብስብ የሆነ መልስ የሚሻ ነው፡፡ አንደኛ እዚህ አገር የሚያስማማ ዓይነት ለውጥ ለማምጣት ከማመን ተነስቶ የፖለቲካ መድረክ ላይ የመጣ መንግሥት ወይም አመራር የያዘ ፓርቲ የለም፡፡ ለውጥ ማምጣት ስንል በዘመናዊ መልኩ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሚባለው መተማመን የሚቻልበት የፖለቲካ ምኅዳር ለመፍጠር እምነት ያለው ፓርቲ ሥልጣን አልያዘም፡፡ የችግሮቹ ሁሉ እናት ይህ ነው፡፡ ይህ እምነት እስከሌለ ድረስ ያየናው ያለፉት 25 ዓመታት ሙሉ ቅንነት የላቸውም፡፡ በፖለቲካ ቅንነት ምናምን ማለት የዋህ ያሰኛል፡፡ ፖለቲካ ከሥልጣን ጋር ተቆራኝቶ ስለሚታይ ብዙ ጊዜ ለሥልጣን ሽኩቻ የሚነሳ ጥያቄና አስተያየት ነው ሊባልም ይችላል፡፡ ያም ሆኖ ግን በጣም ጎልቶ የወጣና እኔ በግሌ እርግጠኛ የሆንኩበት ኢሕአዴግ በብልጣብልጥነት፣ በማጭበርበር፣ በማታለልና በማስመሰል ሥልጣን ላይ ቆይቶ በረሃ በነበሩ ጊዜ የታያቸውን አንዳንድ ህልሞችን፣ ከህልምም በላይ አልፎ ቅዥቶችን ተግባራዊ አደርጋለሁ ብሎ ሙሉ ለሙሉ ራሱን ተገዥ የማድረግና የቀረውን ደግሞ ያለማዳመጥ ነገር ጎልቶ የወጣ ነው፡፡ ችግሩ እዚያ ላይ ነው፡፡ አንደኛ ደርግ ዝም ብሎ እንደ እምቧይ ካብ መውደቅ አልነበረበትም፡፡ በድርድር ከሥልጣን መወገድ የነበረበት አካል ነው፡፡ ችግሩ እዚያ ላይ ነው ያለው፡፡ የኃይለ ሥላሴ ሥርዓትም በድርድርና የተሰጠውን አስተያየት ተቀብሎ ቢሆን ኖሮ ደርግን የመሰለ ጭራቅ ባልመጣ ነበር፡፡ ኢሕአዴጎችም ሥልጣን ላይ ሲወጡ ተደራድረውና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ብቃት ያላቸው ፓርቲዎችን፣ ግለሰቦችንና እንቅስቃሴዎችን ዋጋ መስጠት ነበረባቸው፡፡ ስለዚህ በድርድር ያልመጣ ለውጥ በመሆኑ የአሸናፊ ፍትሕ ሆኖ ነው ያየነው፡፡

ለአንድ ችግር መፍትሔ ለማግኘት ሁለት ወገን ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን እነሱ ደርግን አሸንፈናል አሉ፡፡ መደረግ ያለበትን ነገር የራሳቸውን አቋም ለጠፉ፡፡ ብትወዱም ባትወዱም የምትከተሉት ይህንን ነው አሉ፡፡ ይህ ነገር ትክክል አይደለም፡፡ ቻርተሩ ላይ የተስማማነው ይህንን አይደለም ብለን ከኢሕአዴግ ውጪ ያለነው ለመንቀሳቀስ ሞከርን፡፡ ከአቶ መለስ ጋር ለመገናኘት ሞከርን፡፡ ነገር ግን ያኔም የሚከተሉት ሥልት ከእነሱ ውጪ የነበረውን መከፋፈል ላይ ያለመ ነበር፡፡ ሌላው ኢሕአዴግ ያኔም ቢሆን አሁን የወሰደው ግምት የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ ደርግን ስላስወገድንለት አመሥጋኝ ነው የሚለው ነው፡፡ በቃ ደርግን የሚያህል አምባገነንና ጨፍጫፊ ነገር አስወገደልን ብሎ ያመሠግናል፣ ስለዚህ በቃ አለቀ ምንም ሊያደርግ ይችላል የሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ እንዳልሆነና ከዚያም አልፎ የኢትዮጵያ ሕዝብ እኛንም አዳምጡን፣ እሺ ደርግ ተወግዷል ወደፊት ለሚሆነው ነገር መነጋገር ስላለብን እኛንም ስሙን አዳምጡን የሚል መሆኑን ጨርሶ ከግምት ውስጥ አላስገቡም፡፡ ስለዚህ ዝም ብሎ መጋጨት ሆነ፡፡ የመጀመሪያው ስለምርጫ ሕዝብ ይወስን የሚባለው ቅድመ ምርጫ ምርጫ (Snap Election) በሚባለው ነው፡፡ ከ1984 ዓ.ም. ምርጫ በፊት ማን ምርጫውን ያስተዳድር የሚለውን መልስ ለመስጠት የአካባቢ አስተዳዳሪዎች ይሰየሙ? ለሚለው ጥያቄ የየቀበሌው ሕዝብ ይጠራና በእጅ ማንን ትመርጣላችሁ እየተባለ እንዲካሄድ ተወሰነ፡፡ በዚያ ምርጫ አዲስ አበባ ላይ 20 በመቶ ድምፅ ብቻ ነው ያገኙት፡፡ በኦሮሚያ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ነው የተሸነፉት፡፡

አንዱ ሌላው ትልቁ ድክመት ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለዚህ አገር መልካም ያስባል የሚል አመለካከት አለመያዛቸው ነው፡፡ አገራችን በእውነቱ ብትለማ፣ ብትሻሻል የሚጠላ ኢትዮጵያዊ አለ? ሕዝቦች እኩል ቢሆኑ የሚጠላ ነፍስ ያለው ፍጡር አለ? ማንም የሚያነሳው ይህ በአግባቡ ይስተዳደር የሚል ጥያቄ ነው እንጂ፣ ከዚያ አልፎ ለዚህች አገር ዝም ብሎ ክፋት የሚያስብ ወገን በዚያ ረድፍ እነርሱ ደግሞ ለዚህች አገር መልካም የሚያስቡ ወገን አድርገው ራሳቸውን መፈረጃቸው ሌላው ችግር ነው፡፡ ከእነሱ እጅ ውጪ ትንሽ ነገር ቢወጣ ሥልጣናቸው ትንሽ ቢከለስ ይህች አገር አደጋ ላይ ትወድቃለች የሚባለው ከፍርኃት የተነሳ ሐሳብ ነው የችግሮቹ ምንጮች፡፡ ኢሕአዴግ እዚህች አገር ላይ ማኅበራዊ ሙከራ ሲሠራ ነው የነበረው፡፡ ሙከራው ግን የተደረገው የተሻለውን ውጤት አግኝቶ ተግባር ላይ ለማዋል ሳይሆን፣ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ አስተሳሰብ ለማምታታት ነው፡፡ ምርጫውን ከፈቱ፣ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ ያካሂዳሉ፣ ወዘተ የሚባለው በልማት ስም የሚመጣውን ድጋፍ በዘላቂነት ለማቆየት የሚጠቀሙበት ድራማ እንጂ፣ በእውነቱ መድበለ ፓርቲ ሥርዓት እዚህ አገር ዕውን እንዲሆን ያለመ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ድርጅቶች አቋቁመው መልካም ነገር ለዚህ አገር ያስባሉ የሚለውን ታሳቢ ተቀብሎ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስተካከል ፈቃደኛ ያልሆነ ቡድን ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ሥልጣን የያዘው፡፡ ስለዚህ ይኼ ነው ችግሩ፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት 25 ዓመታት ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲስተካከል አለመፈለጉን በሰፊው አብራርተዋል፡፡ የገዥው ፓርቲ ድርሻና የሚጫወተው ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ፣ እርስዎ ደግሞ በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ላይ በተለይ የተቃውሞ ጎራውን በመምራት ከፍተኛ ሚና እንደመጫወትዎ መጠን፣ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል ገዢው ፓርቲን ለመፎካከር፣ ሕዝቡን ለማደራጀትና ኅብረት ከመፍጠር አንፃር ያለው ችግርስ ምንድነው?

ፕሮፌሰር በየነ፡- ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ ያለው ችግር አንደኛ እኛ ኢትዮጵያውያን ዝም ብለን የምናልማትን ኢትዮጵያ ሳይሆን ጠለቅ አድርገን ውስጡ ገብተን በምናይበት ጊዜ የጥያቄዎቹ መብዛት፣ እንዲሁም ፓርቲዎቹ በእነዚያ ጥያቄዎች ዙሪያ የተሰባሰቡ መሆናቸው፣ አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ደግሞ ርዕዮተ ዓለማዊ ሳይሆኑ የብሶት ፓርቲዎች ናቸው፡፡ የጊዜው ችግር የፈጠራቸው፡፡ ፓርቲዎቹ በአብዛኛው የድሮዎቹ እንደ ኢሕአፓና መኢሶን የሚባሉት ትንሽ የርዕዮተ ዓለም መስመር ተከተለው ድሮ የተቋቋሙ ናቸው፡፡ እነርሱ ደግሞ በታሪካዊ ሒደት በደርግ ጊዜ የደረሰባቸውና የሆኑት ይታወቃል፡፡ እዚህ አገር መሬት ረግጠው ለመንቀሳቀስ የማይችሉበት ሁኔታን ደርግ ፈጠረ፡፡ ኢሕአዴግ ደግሞ ያንኑ በር ጨርሶ ዘጋው፡፡ በርዕዮተ ዓለማዊ ፖለቲካ ዓላማን ለማራመድ ከሚፈልጉት አንፃር ማለት ነው፡፡ ከዚያ ወዲህ ተቋቋሙ የሚባሉት ፓርቲዎች በአብዛኛው የብሶት ፓርቲዎች ናቸው፡፡ የወሰደውን ያህል ጊዜ ወስደን ታግለን ይህችን አገር በዚህ ዓይነት የእምነት መተክል ላይ እንድትተዳደር እናደርጋለን የሚሉ ዓይነት ብዙ ፓርቲዎች የሉም፡፡ ስለዚህ በብሔር ብሔረሰብ መሠረት ያደረጉ፣ መብታችን በብቃት አልተከበረም፣ በቂ ዕውቅና አላገኘንም የሚል ነው አጀንዳው፡፡ በጣም ርቆ የማይሄድ ማለት ነው፡፡ ሌሎቹም ደግሞ የሚሰባሰቡ አሉ፡፡ የኢትዮጵያዊነት ፓርቲዎች ምናምን የሚሉ፡፡ እነርሱ ደግሞ ኢትዮጵያ ልትበታተን ነው ይላሉ፡፡ ምን ሆና ነው የምትበታተነው? የኢትዮጵያ ሕዝብ እኮ ድሮም የሚኖረው ስለፈለገ ነው፡፡ አልፈልግም ያለውማ ተገንጥሎ ሄደ፡፡ ይኼ አይደለም የኅብረቱ ማዕከል መሆን ያለበት ለመገናኘትም አብሮ ለመሆንም ማዕከል መሆን ያለበት አንድ መርህ ነው፡፡

እኔ በግሌ ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ ከኢሕአዴግ ሌላ አማራጭ አለን የሚሉትን እንቅስቃሴዎች ለማስተባበር ብዙ ጊዜዬንና ጉልበቴን ነው የተጠቀምኩት፡፡ አሁን መለስ ብለን ስናይ መቼም አንዱ ጋ ያደርሳል በሚል ነበር ስንለፋ የነበረው፡፡ አሁን ግን ስናይ እርሱም እየራቀ ነው፡፡ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ፡፡ የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማሰባሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ ከማን ጋር ተገናኝተህ፣  ምን ዓይነት የፖለቲካ መስመር ከያዘው ጋር ነው ቁጭ ብለህ አንድ ኅብረት እንፍጠር ብለህ የምትደራደረው? ይህንን ደጋግሜ አይቼዋለሁ፣ አስቸጋሪ ነው፡፡ ለመደራደርም ለመሰባሰብም አስቸጋሪ ነው፡፡ ኢትዮጵያችን እንዲህ ሆነች በሚል ይህንን የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን ፈጠርን የሚሉት ሁሉ በስሜታዊነት ነው፡፡ እንዲህ ሲሆን ደግሞ ሌላውን ሥጋት ውስጥ ይከተዋል፡፡ እስካሁን ድረስ ከተሰባሰቡት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ለእኔ ጥሩ ምሳሌ አማራጭ ኃይሎች ነው፡፡ ስብስቡ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሙያ ማኅበራት የነበሩበት ነው፡፡ ያንን ሁሉ አሰባስበን ወደፊት ለመሄድ ተነሳን፡፡ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን አግኝቶ ነበር፡፡ ከኢሕአዴግ ውጪ ያሉት ኃይሎች አሁን ተሰባሰቡ ብሎ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕውቅና የሰጠው ነበር፡፡

ስለዚህ ችግሩ ምንድነው? እንዳልኩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተቋቋሙበት መሠረቱ በጣም በርካታ ስለሆነ፣ አሰባስቦ በአንድ ዓይነት አጀንዳ ማምጣት አቅቶን ነው የቆየው፡፡ መጀመሪያ ታክቲካዊ ጥያቄዎችን መመለስ ተገቢ ነው፡፡ ታክቲካዊ ጥያቄዎች ማለት ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ፣ የሰብዓዊ መብት ጥያቄ፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄና የሕግ የበላይነት ናቸው፡፡ በአንዲት ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ፈቃደኛ የሆኑት ፓርቲዎች ሁሉ ይህንን እንደ ቅድመ ሁናቴ ይዘው ዝርዝር አጀንዳቸውን ቢተውት ጥሩ ይመስለኛል፡፡ መሬት የግል ይሁን፣ ፌዴራሊዝሙ እንዲህ ይሁን የሚባሉ ዝርዝር ጉዳዮችን ትቶ መጀመሪያ መሠረታዊ የሆነው ነጥብ ላይ ለምንድነው የማንተባበረው ሲባል፣ አይ የእኔ መብት እዚህ ጋ አልተከበረም እየተባለ ወደ ዝርዝሩ ይገባል፡፡ ወደ ዝርዝሩ ይገባና እኛ ሳናውቅ አኩርፎ ትቶ ይወጣል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ታክቲካዊና ስትራቴጂካዊ ፖለቲካዊ አጀንዳን ለይቶ ለማስተናገድ፣ ወይም በዚያ አካባቢ ለመደራደር ብቃት ማነስ ይታያል፡፡ የትም አገር እንደሚታየው ዝም ብለህ መጨረሻ ላይ እደርስበታለሁ የምትለውን ግብ ይዘህ ከማንም ጋር መደራደር አትችልም፡፡ በጣም አስቸኳይ የሆኑት ችግሮች ምንድን ናቸው የሚለው ላይ መጀመሪያ መስማማት አለብን፡፡

በዚህ አገር በነፃነት ተደራጅቶ ነፃ ምርጫ ስለሚካሄድበት ሁኔታ መደራደር ነው፡፡ የፈለገውን የፖለቲካ መስመር ሊያቀነቅን ይችላል፡፡ ግን ይህንን ለማምጣት አንድ ላይ ሆነን ባለው ሥርዓት ላይ ጫና እንፍጠር ስንል አንድ ላይ መቆም አልተቻለም፡፡ ምሳሌ ልስጥህ፡፡ ለአንዳንዶች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ወርቃማ ጊዜ እየተባለ በሚጠራው የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወቅት ቅንጅት ኅብረትን አቅም ለማሳጣት የተፈጠረ ቡድን ነው፡፡ ከኅብረቱ ውስጥ የወጡ ሁለት ፓርቲዎች ሌሎች ለጊዜው የይድረስ የይድረስ የተዘጋጁ ሁለት ፓርቲዎችን በማካተት አራት ፓርቲዎች ስለሆኑ ቅንጅት ተብለናል በማለት አርቲፊሻል ነገር የተፈጠረበት ሁኔታ አንዱ ምሳሌ ነው፡፡ ይህም ጊዜው ሲደርስ የምንፅፈውና በዝርዝር የምናስቀምጠው ይሆናል፡፡ ለዚህም ኃላፊ የሆኑ ሰዎች አሁንም ከእኔ በላይ ማንም የለም የሚል ነገር ሲናገሩና መጽሐፍ ሲጽፉ አያለሁ፡፡ ይህ ትዝብት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መድረክ ምርጫ 2007 በተቃረበበት ሰሞን ተደጋጋሚ መግለጫዎችን በማውጣትና በተለያዩ መንገዶች ደጋፊዎችንና መራጩን ሕዝብ ለማግኘት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ነበር፡፡ የምርጫውን መጠናቀቅ ተከትሎ ግን በመድረክ ብቻ ሳይሆን በአብዛኛዎቸ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያን ያህል የጎላ ሥራ ሲሠራ አይስተዋልም፡፡ መድረክ በአሁን ወቅት ምን እየሠራ ነው?

ፕሮፌሰር በየነ፡- መድረክ እንግዲህ ትልቅ ጉዳት ደርሶበት ነው ከምርጫው የወጣው፡፡ ጉዳት ስልህ በቁሳቁስ፣ በሰው ኃይል እንዲሁም ከሁሉም በላይ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት በገዢው ፓርቲ ደርሶበታል፡፡ እኛም የመድረክ መሪዎች ከፍተኛ የሆነ ሸክም የተሰማን ጊዜ ነው፡፡ መቼም ይህ አገር እኮ ‹የተናገሩት ከሚጠፉ የወለዱት ይጥፋ› የሚል ሕዝብ ያለበት አገር ነው፡፡ እኛ ሕዝባችንን ማሸነፍ ይቻላል ብለን ነው ስንቀሰቅስ የነበረው፡፡ እናንተ ብቻ ጠንክራችሁ ተደራጁ ተዘጋጁ እንጂ ማሸነፍና በቂ መቀመጫ ማግኘት ይቻላል ብለን ነው የቀሰቀስነው፡፡ እንግዲህ ያንን ከውጤቱ ጋር አገናኘው፡፡ ምን ይዤ ነው ሕዝቡ ጋ የምሄደው? ዋሾው በየነ ብሎ እንዲጠራኝ ነው? አንድ የፖለቲካ መሪ ሊከሰት የሚችለውን ነገር ማንበብ አለበት፡፡ አለዚያ መሪ አይደለም፡፡ ያሉትን ነገሮች መተንበይ አለበት፡፡ ያሉትን ታሳቢዎች በሙሉ ቀምረህ ውጤቱ ይኼ ሊሆን ይችላል ብለህ መተንበይ መቻል አለብህ፡፡ የኢሕአዴግ ፀባይ እኛን መተንበይ የማንችል መሪዎች አድርጎ ነው ያስቀመጠን፡፡ እኔ በዚህ ምርጫ መቸም ሒሴን መዋጥ ይኖርብኛል፡፡ ይህ መቶ በመቶ የማሸነፍ ውጤት ይመጣል የሚል ነገር ኢሕአዴጎች ራሳቸው መቼም ጤነኞች ናቸው ነው የምለው እብዶች አይደሉም፡፡ ያለፈው 99.6 በመቶ ነው ያሉት፡፡ አሁን ደግሞ ከዚያ በላይ አልፈው ይደግሙታል የሚል በፖለቲካ ለመተንበይ የማይቻል ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም 99.6 በመቶ አሸነፍን ባሉበት ጊዜ ብዙ ወቀሳና ትችት ከኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ደርሶባቸው ነበር፡፡ እና ይህ ሲሆን መቼም እነዚህ ሰዎች ያለፈው ትንሽ ሳያሳፍራቸው አይቀርም ከሚል ትንሽ ይከፍታሉ የሚል ትንበያ ነው የነበረኝ፡፡ ያን ሁሉ እንደሌለ አደረጉት፡፡ በዚህም ምክንያት መድረክ ክፉኛ ተጎድቶ ነው የወጣው፡፡ ያለችንን ሀብት አሟጠን ተጠቅመናል፡፡ ይህን ሁሉ ስናደርግ ዋናው ግባችን የነበረው ከእኛ ቀረ እንዳንል ነው፡፡

ቢያንስ እኛ በቂ ጥረት ስላላደረግንና ስላልቀሰቀስን ነው እዚህ እዚህ አካባቢ የተፍረከረከው፣ ወይም ሽንፈት ያጋጠመን እንዳንል ጉልበታችንንና ሀብታችንን አሟጠን ነው የተጠቀምነው፡፡ ስለዚህ ያን ሁሉ አድርገን በእኔ እምነት በተወዳደርንበት ቢያንስ ሦስቱ ዋነኛ ክልሎች [ደቡብ፣ ትግራይና ኦሮሚያ] ከእኛ ቀረ የምንለው ነገር አልነበረም፡፡ ቢያንስ በቂ መቀመጫዎች ለማግኘት የሚያስችለን ነበር፡፡ ያን ሁሉ ዜሮ ሲያደርጉ ሕዝባችንን ግዴለም ታሸንፋለህ ብለን የነገርነውን አንዲት መቀመጫ እንኳን ማሳየት ሲያቅተን ለምንድነው የሚያምነኝ? ሕዝቡ የሚጠይቀን እኮ ለምንድነው የምታስቸግሩን? አሁን የምታካሂዱት ምርጫ ካለፈው በምን ይለያል ብላችሁ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ነው፡፡ አሁን ምን እየሠራችሁ ነው ላልከው፣ በመሠረቱ ቀውስን የመቆጣጠር (Crisis Management) ላይ ነው እየሠራን ያለነው፡፡ አገሪቱ ውስጥ የተፈጠሩ አለመረጋጋቶችን የመከታተል ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ያ ማለት በየገጠሩ በየአካባቢው ያለንን አደረጃጀታችንን በሙሉ አጥፈን ቤታችሁ ግቡ ያልንበት ጊዜ አይደለም፡፡ ሕዝቡ አሁንም በየቤቱ ባንዲራ ሰቅሎ ይህ ጽሕፈት ቤት ነው እያለ እኮ እየተፋለመ ነው፡፡ አርሶ አደሩ እስካሁን ድረስ ኢሕአዴግ ማሸነፉን አምኖ አልተቀበለም፡፡ ምንድን ነው የሚለን አሁንም አዲስ ነገር የለም እንዴ? እነዚህ ሰዎች እንዲሁ ሊቀጥሉ ነው እንዴ? ማን የሰጠውን ድምፅ ነው አሸንፈናል የሚሉት? የሚል ነው፡፡ ሕዝቡ እስካሁን አያምንም የሚቀየር ነው የሚመስለው፡፡ የእኛ ፓርቲ በስፋት በተወዳደርንባቸው ስፍራዎች አርሶ አደሩ በእርግጠኝነት እንዳልተሸነፈ ነው የሚያውቀው፡፡

ሪፖርተር፡- ከምርጫው በኋላ ባለው ጊዜ አባላት ባለው አሠራር እየሠሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ እርሱ እንደተጠበቀ ሆኖ ከደጋፊዎቻችሁ ጋር እንዴት ነው እያተገናኛችሁ ያላችሁት?

ፕሮፌሰር በየነ፡- ሕዝቡን በስፋት ለማግኘትና ስሜቱን ለማዳመጥ የምናደርገውን ጥረት ሙሉ በሙሉ መንግሥት ዘግቶታል፡፡ አሁን እየተነገረን ያለው ነገር ያልሆነ ነገር ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ስብሰባ ስለሚካሄድ፣ በምታልፉበት ቦታ ትምህርት ቤቶች ስላሉ፣ ግንባታ የሚካሄድበት ስለሆነ፣ ከዚያም በላይ ደግሞ በጊዜው ባለው መንፈስ ምክንያት ደግሞ መፍቀድ ወይም ዕውቅና መስጠት አንችልም ይሉሃል፡፡ እኛ ፍቀዱ አላልንም፡፡ በዚህ ቀን ሠልፍ ልንወጣ ነውና ዕወቁት ነው ያልነው፡፡ ልናውቅ አንችልም ይሉሃል፡፡ ድሮውንም ትልቅ ችግር ውስጥ ባለንበት ወቅት እኛ አሳውቀናል ብለን ወጥተን ሌላ ችግር እንዲደርስ አንፈልግም፡፡ ይህ የሕግ የበላይነት የማያውቅ ሥርዓት እንግዲህ ሁላችንንም ሰብስባችሁ እሰሩን ብንል ለአንድ ሰሞን ዜና ሊሆን ይችላል፡፡ ግን እኛ ደግሞ እንዲሁ ተነሳስተን የምናደርገውን ትንሿንም ጥረት እንዲያጠፏት አንፈልግም፡፡ ከዚህ ሁሉ በመነሳት የተቆጠብንባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ለመሰብሰብ ጠይቀናል፣ ለመሠለፍ ጠይቀናል፡፡ ለዚህ ሁሉ የሚሰጠው ምላሽ አናውቅም የሚል ነው፣ ዕውቅና አንሰጥም ነው፡፡ እንግዲህ ዕውቅና ያልተሰጠውን ነገር ደግሞ ብናደርግ እንደለመደው ወጥቶ መተኮስ ሊጀመር ነው፡፡

ለዚህ ዓይነቱ ነገር ደጋፊያችንንና ሕዝባችንን ማጋለጡ ተገቢ አሠራር አይሆንም ብለን ነው ቆጠብ ብለን ያለነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር የትም ቦታ እንሰበሰብ፣ እንሠለፍ ብለን ብንጠይቅ ይህ ሥርዓት አይፈቅድም፡፡ ስለዚህ መድረክ ከሕዝቡ ጋር መገናኘት ማለት ትልቅ የሚፈራው ነገር ሆኖበታል፡፡ ይህን እንዴት እናድርግ? ይህ መንግሥት የሚፈልገው ግጭት ነው፡፡ ሕጉ የሚለው አሳውቁ ነውና አሳውቀን እንወጣለን ስንል መጋጨት፣ ስብሰባ ልንቀመጥ ነው ስንል መጋጨት፡፡ ቀደም ብሎ የተፈጠረውን ግጭት መፍትሔ መስጠት ባልተቻለበት ሁኔታ በችግር ላይ ችግር እየጨመሩ መሄድ ለዚህ አገር ጤነኛ የፖለቲካ ድባብ አይሆንም፡፡ ያም ያሳስበናል ማለት ነው፡፡ ሁሉም ነገር ከቁጥጥር ውጪ የወጣበት ሁኔታ ቢፈጠር እዚህች አገር ላይ ምንድነው ሊከሰት የሚችለው የሚለው ደግሞ ያስስበናል፡፡ በዚህም ምክንያት ሰብሰብ የማለት ጉዳይ እንጂ ዕቅዶቹ ጠፍተውን አይደለም፡፡ ምን ማድረግ እንዳለብን እናውቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- የሕግ ባለሙያዎችና የፖለቲሳ ሳይንስ ጠበብቶች የሚያስቀምጡት ‹‹ሻዶው መንግሥት›› (Shadow Government) የሚባል ጽንሰ ሐሳብ አለ፡፡ ይህ ምንድነው ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመንግሥት መዋቅር ሥር እንዳሉ መሥሪያ ቤቶችና ኃላፊዎች ሁሉ ራሳቸውን በማዘጋጀት፣ አመራሮቻቸውን የማብቃት ሥራ ይሠራሉ፡፡ ከዚህ አንፃር በመድረክ በኩል ነገሮችን በቅርብ እየተከታተለና ስህተቶችን እየነቀሰ የሚያወጣ ሥርዓት ከመዘርጋት አንፃር የሚደረግ ጥረት አለ?

ፕሮፌሰር በየነ፡- ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ይህ ሁሉ ቅንጦት ነው፡፡ አሁን አንተ የምትነግረኝ የቅንጦት ፖለቲካ ነው፡፡ እኛ የምንናገረው እኮ ስለመሠረታዊ አሠራሮች ነው፡፡ ልክ ዝንጀሮዋ ‹‹መጀመሪያ የመቀመጫዬን›› እንዳለችው፡፡ ምን ላይ ተቀምጠህ የት ላይ ቆመህ ነው ይህንን የምታስበው? እያንዳንዱ ትንንሽ መሰባሰብ በትልቁ ጥርጣሬ በሚታይበት፣ መንግሥት በምላስ ብቻ የተናገረን ሰው እንኳን የቁም እስረኛ አድርጐ ከዚህ ብትወጣ እንገልሃለን የሚልና ከሕግ በላይ የሆነ ፀባይ በሚያሳይበት አገር፣ እንዲያው ዝም ብለን ሁሉንም ነገር አንሞክርም፡፡ አንድን ሥርዓትንም ሆነ የሰው ልጅን የሚገዛው እኮ ሕግ ነው፡፡ ሕግ አለ ብለን ነው እኮ መጥተን የምንሄደው፡፡ ይህ መንግሥት ግን ይህን እምነት እየጣሰ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ያህል የዋህ ሆነን እንዲያው የመቀመጫችንን እንኳን ሳናረጋግጥ ወደዚህ ዓይነት ነገር ውስጥ ለመግባት ዱለታ ነው የሚሆነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር በሚያግባቧችሁ የጋራ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ንግግር እንደጀመራችሁ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ሲገለጽ ነበር፡፡ የሁለቱ ፓርቲዎች ውይይት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ፕሮፌሰር በየነ፡- አብረን በሚያግባቡን ጉዳዮችና አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ላይ አቅማችንን አስተባብረን እንንቀሳቀስ የሚሉ ደብዳቤዎች ተለዋውጠናል፡፡ በተለዋወጥናቸው ደብዳቤዎች መስማማት ነው እንጂ፣ አከራካሪ ወይም ያልተስማማንበት መንፈስ የለም፡፡ ከዚህም በመነሳት በጋራ ከመድረክም ወገን ከሰማያዊም ወገን ሁኔታዎችን የሚከታተሉ ሰዎች መድበን የጋራ ኮሚቴ አቋቁመናል፡፡ ያ ኮሚቴ ለምሳሌ ይህንን ሰላማዊ ሠልፍ አብሮ እንዲያቅድ ነው ተልዕኮ የተሰጠው፡፡ አሁንም ከፊታችን የምናስባቸውን ቀጣይ ዕቅዶችና እንቅስቃሴዎች ይህ መንግሥት ዕድሉን ከሰጠን አብረን ነው የምናቅደው፡፡ እናም ሌሎችንም እነደዚሁ ሕዝባዊ የሆኑ ጉዳዮችን አብሮ ለማስተጋባትና አንዱ አቅም ባነሰው ጊዜ ሌላኛው እየደገፈው የሕዝብን ጥያቄ አጉልቶ ለማውጣት፣ ያለውንም ሥርዓት ወደ ውይይት መድረክ እንዲመጣ ለመጋበዝ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን አብረን እናቅዳለን፣ ተግባራዊም እናደርጋለን፡፡ ይኼ ነው መቋጫው ሌላ ብዙ ዝርዝር ነገር የለውም፡፡ በአቋም ጉዳይ በዓላማ ጉዳይ እዚያ ውስጥ አልገባንም፡፡ በተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ አብረን ለመሥራት አዎ ተስማምተናል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ አስከፊ የሆነ ድርቅ ተከስቷል፡፡ መድረክ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ሠርቷል? ምን እያደረገ ነው? የፓርቲው አመራር አባላትስ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በመገኘት የአቅማችሁን አስተዋጽኦ የማድረግና ከሕዝቡ ጎን መቆማቸውን አሳይተዋል?

ፕሮፌሰር በየነ፡- ጉዳዩን እየተከታተልን ነው፡፡ በጣም ሰፋ ባለ ሁኔታ ሕዝቡ መሀል በመገኘት ይህንን የድርቁን መጠንም ሆነ ሁኔታ ገምግማችኋል ወይ ለምትለው፣ በእርግጠኝነት ለማስቀመጥ አመራሩ ከዚህ ተነስቶ ሄዶ እዚያ ተገኝቶ ነገሮችን የሚገመግምበት አቅም የለንም፡፡ ድርቅ የተከሰተባቸው አካባቢዎች ደግሞ ቆላ ቀመስ የሆኑ ራቅ ራቅ ያሉ አካባቢዎች ናቸው፡፡ ይህ ሲሆን ግን በየአካባቢው አባላት አሉን፡፡ ከእነሱ ዘወትር ሪፖርት እናገኛለን፡፡ መኪና አስነስተን ሄደን ደርሰን የደረስንበትን ሁሉ በመታዘብ ልንሰጥ የሚገባውን የሞራል ድጋፍ አድርገናል አልልም፡፡ ለዚህ አልታደልንም፡፡ ይህም አላስፈላጊ ሆኖ አግኝተነው ሆኖ ሳይሆን ሁኔታዎች የፈጠሩብን ነው፡፡ ነገር ግን ከየአካባቢው ካሉ አባሎቻችን ሁልጊዜ ሪፖርት ይደርሰናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹መንግሥት ለአገር ውስጥ የኅትመት ኢንዱስትሪ ገበያ ከመፍጠር ጀምሮ ሥራ የመስጠት ኃላፊነት አለበት›› አቶ ዘውዱ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የኅትመት መሣሪያ በጉተምበርግ ከተፈበረከ ከ400 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ በ1863 ዓ.ም. በምፅዋ የተጀመረው የኅትመት ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ ቢሆንም፣ ዕድገቱ ውስን መሆኑ ይነገራል፡፡ ከኢትዮጵያ በኋላ የኅትመት...

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...

‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ባለን አቅም ሁሉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ለመዳሰስ ሞክረናል›› የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› በመባል የሚታወቀውን በኢትዮጵያ ታሪክ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመ ሐሳብ አመንጪ የጥናት ተቋም (ቲንክ ታንክ) ከመሠረቱት አንዱ መሆናቸውን...