Tuesday, May 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው አሁንም ነጥብ እየጣለ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያፋጥናሉ ተብለው በቀዳሚነት ከተቀመጡ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ውስጥ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ አንዱ ነው፡፡ ይህ ዘርፍ ከየትኛውም የኢንዱስትሪ ዘርፎች የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ በማጐልበት፣ ከፍተኛ የሰው ኃይል በመያዝና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦዎቹ ብዙ ተስፋ የተጣለበትም ሆኖ ቆይቷል፡፡

የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ከሌሎች በተለየ ተስፋ የተጣለበት ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ዘርፉ መቼም የማይነጥፍ ገበያ ያለው በመሆኑና ኢትዮጵያም ለዚህ ኢንዱስትሪ ምቹ መሆንዋ ነው፡፡

በአጭር ጊዜ ብዙ የሚገኝበትና የሚጠቅም መሆኑን በልበ ሙሉነት ሲዘመርለት ቆይቷል፡፡ ይህንኑ ተስፋ በመያዝም አገሪቱ በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ዕቅድ በማስላት አገሪቱ ከዘርፉ ልታገኝ የምትችለውን ጥቅም መተንበይ ተችሎም ነበር፡፡ ዘርፉ የበለጠ እንዲጐለብትና የሚያስገኘውን ከፍተኛ አገራዊ ጠቀሜታ ታሳቢ በማድረግ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በራሳቸው ጥያቄ እንደ አይካ አዲስ ያሉ ግዙፍ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ አድርገዋል፡፡ እንዲህ ያሉ መልካም ዕድሎችን በማየት የዘርፉ ተስፋ እንዲገዝፍ ተደርጓል፡፡ በተለይ ከመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ከዘርፉ እንደሚገኝ ታስቦ የነበረውን የውጭ ምንዛሪና ሊፈጥር የሚችለውን የሥራ ዕድል ብቻ መመልከት ይበቃል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ዘርፍ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመንም ሆነ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመጀመሪያው ስድስት ወራት ክንውኑ የታለመለትን ግብ እየመታ ያለመሆኑ ነው፡፡

በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን በአምስት ዓመታት ውስጥ ይገኛል ተብሎ ከታሰበው ግማሽ ያህሉን እንኳን ማግኘት አልቻለም፡፡

በዕቅዱ ዘመን መጨረሻ (2007 ዓ.ም.) ብቻ አንድ ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ እንደሚገኝ ታቅዶ ሊገኝ የቻለው 400 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑ ተስፈኛው ዘርፍ ዕቅዱና ክንውኑ ሳይገጣጠሙለት አልፏል፡፡

ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን አንድ ብሎ ከተጀመረበት በዚህ የበጀት ዓመት የስድስት ወራት ክንውኑ ሲፈተሽም ዘርፉ አሁንም ነጥብ እየጣለ መጓዙን አመላክቷል፡፡

የግማሽ ዓመቱ ውጤት

የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪውን የ2008 ዓመት የስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም በተመለከተ የተደረገ ግምገማና የባለድርሻ አካላት ውይይት ላይ ይፋ እንደተደረገውም፣ በስድስት ወራት ያስገኛል ተብሎ የተያዘለትን የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት አለመቻሉ ነው፡፡ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በኩል የቀረበ ጽሑፍ እንዳሳየው፣ በስድስት ወራት ከጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ይገኛል ከተባለው የውጭ ምንዛሪ ማሳካት የተቻለው 69.6 በመቶውን ብቻ ነው፡፡

በግማሽ በጀት ዓመቱ ከድርና ማግ፣ ከብትን ጨርቅ፣ ከስፌት ውጤቶችና ከባህላዊ አልባሳት የወጪ ንግድ በጠቅላላው ይገኛል ተብሎ የታቀደው 60.07 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ነገር ግን ከበጀት ዓመቱ መጀመሪያ አዳዲስ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ታክለውበትም የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 41.8 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡

በተለይ የግማሽ ዓመቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከቀዳሚው ዓመት ተገኝቶ ከነበረው ጋር በንጽጽር ሲቀመጥ፣ ዕድገቱ የ5.7 በመቶ ብቻ መሆኑ ዘርፉ አሁንም ዕቅዱንና ክንውኑን ያለማጣጣሙን አሳይቷል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ ያገኘናቸው አስተያየት ሰጪዎች እንደገለጹት፣ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ አዳዲስ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ ገብተው የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ በ5.7 በመቶ ብቻ ፈቀቅ ማለቱ እንዲሁም በዕቅድ የተቀመጠውን ያህል ያለማስገኘቱ እንዳስገረማቸው ገልጸዋል፡፡

ከአራቱ የምርት ዓይነቶች አንዱ የሆነው በተያዘለት ውጥን መሠረት የውጭ ምንዛሪ ያላስገኘው እንዲሁም ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ያዘቀዘቀው የብትን ጨርቅ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ነው፡፡

በዕለቱ ይፋ የሆነው መረጃ እንደሚያሳየው፣ የብትን ጨርቅ በግማሽ በጀት ዓመት 8.57 ሚሊዮን ዶላር ይገኝበታል ተብሎ የታቀደ ቢሆንም፣ በተግባር የተገኘበት ግን 2.97 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ ይህም የዕቅዱን 50 በመቶ እንኳን ሳይደርስ 34.7 በመቶ ላይ ተንጠልጥሎ ቀርቷል፡፡

ከድርና ማግም 10.42 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል ተብሎ የተገኘው ግን 6.12 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ ይህም አፈጻጸሙ 58.7 በመቶ ነው፡፡ ከዘርፉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይገኝበታል የተባለው የስፌት ውጤቶችም ቢሆን በተመሳሳይ የዕቅዱን ያህል ያልሰመረለት ሆኗል፡፡ ከስፌት ውጤቶች በግማሽ በጀት ዓመቱ 40.35 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስገኝ ታልሞ፣ ያስገኘው ግን 30.92 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑ አጠቃላይ የጨርቃ ጨርቅ የወጪ ንግዱ አፈጻጸም አነስተኛ እንዲሆን አድርጐታል፡፡

እንደ ኢንስቲትዩቱ መረጃ፣ በግማሽ በጀት ዓመቱ ከዕቅዱ በላይ የውጭ ምንዛሪ አስገኝቷል የተባለው የባህል አልባሳት የወጪ ንግድ ነው፡፡ በግማሽ በጀት ዓመቱ ከባህል አልባሳት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ከዕቅዱ ጋር ሲመሳከር የ247.9 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ከሦስቱ ምርቶች ጋር ሲነጻጸር ገቢው ዝቅተኛ የሆነው የባህል አልባሳት በግማሽ በጀት ዓመቱ ያስገኛል ተብሎ የነበረው 730 ሺሕ ዶላር ብቻ ነው፡፡ የባህል አልባሳት ከዕቅዱ አንፃር በከፍተኛ ደረጃ ዕድገት አሳይቷል ቢባልም፣ ያስገኘው የውጭ ምንዛሪ 1.81 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ ይህም ሆኖ የባህል አልባሳት የወጪ ንግድ ገቢ ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ገቢው ጋር ሲነጻጸር ግን 21 በመቶ ቅናሽ የታየበት በመሆኑ፣ ይህም ንዑስ ዘርፍም ተሳክቶለታል ሊባል አይችልም፡፡ በቀደመው ግማሽ በጀት ዓመት ያስገኘው የውጭ ምንዛሪ 2.29 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በአጠቃላይ በግማሽ በጀት ዓመቱ ከተገኘው 41.82 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 21.8 ሚሊዮን ዶላር ወይም ግማሽ ያህል የተገኘው ከአይካ አዲስ ያስገኘው የውጭ ምንዛሪ መሆኑ ደግሞ፣ ዘርፉ በአንድ ወይም በተወሰኑ ኩባንያዎች ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ አመላክቷል፡፡

የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች መውጣትና መውረድ

የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው የውጭ ምንዛሪ ገቢ በተፈለገው ደረጃ ሊጐለብት ያልቻለበት በርካታ ምክንያቶች ይቀርባሉ፡፡ በሐሙሱ ውይይት መድረኩ ላይም እንደ ችግር የተነሱ ነጥቦች ነበሩ፡፡ በተለይ አንዳንድ ትላልቅ ፋብሪካዎች በታሰበው ደረጃ ሊጓዙ አለመቻላቸው እንዲያውም ከዚህ ቀደም ሲልኩ ከነበረው ምርት በታች መላካቸው ለገቢው ማሽቆልቆል አንድ ምክንያት ሆኖ ቀርቧል፡፡

ኢንስቲትዩቱ አኃዛዊ መረጃም በግልጽ እንዳስቀመጠው ወደ 11 የሚሆኑ ፋብሪካዎች ከቀደመው ዓመት ያነሰ ምርት ለውጭ ገበያ አቅርበዋል፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አግኝተውት ከነበረው የውጭ ምንዛሪ ከ100 ሺሕ ዶላር በላይ ያሽቆለቆለ ሆኗል፡፡ አንዳንዶቹ ፋብሪካዎችም ምርት ይጀምራሉ ተብሎ ሲጠበቅ ባለመጀመራቸው ከዘርፉ ሊገኝ የሚገባውን ያህል እንዳይገኝ አድርጓል፡፡

በ2008 ግማሽ በጀት ዓመት ያገኙት የውጭ ምንዛሪ ከቀደመው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር፣ ከ100 ሺሕ ዶላር በላይ ቅናሽ አሳይተዋል ተብለው ከተዘረዘሩት አሥራ አንድ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ውስጥ ኮምቦልቻ፣ ኤምኤንኤስ እና ከቢረ ኢንተርፕራይዝ የተባሉ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ይገኙበታል፡፡ ባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ አልመዳና ቢኤም ኢትዮጵያ ጋርመንትም ከቀደመው ያነሰ ገቢ ያስመዘገቡ ናቸው፡፡ በተለይ ኤንጅልስ ኮንተን ኤንድ ቴክስታይል የተባለው ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ አንድም የውጭ ምንዛሪ ሳያስገኝ ቀርቷል፡፡ አምና በተመሳሳይ ወቅት 159 ሺሕ ዶላር አስገኝቶ የነበረው አልመዳም፣ የግማሽ ዓመቱ አፈጻጸም በሰባት ሺሕ ዶላር ላይ እንደቆመ የቀረበው መረጃ አሳይቷል፡፡ በአንፃሩ ከመቶ ሺሕ ዶላር በላይ ጭማሪ አሳይተዋል የተባሉ 13 ድርጅቶች የተጠቀሱ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ አልመህዲ ኢንዱስትሪ፣ ኮንሰፕት ኢንተርናሽናልና ጄይጄይ ሚልስ የተባሉ ኩባንያዎች ይገኙባቸዋል፡፡

አሁንም እንደ ችግር የተነሳው የጥጥ እጥረት

በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ የወጪ ንግድ በሚፈለገው ደረጃ ያለመጓዝ የሚቀርበው ሌላኛው ችግር የጥጥ አቅርቦት ነው፡፡ ለማምረት የታሰበውን ያህል ሊመረት አልቻለም፡፡ የጥጥ አቅርቦትን በተመለከተ ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነጻጸር የአገራችን የጥጥ ዋጋ ከፍተኛ ነው፡፡ በጥራትም ረገድ ሊሻሻል እንደሚገባ በተደጋጋሚ የተገለጸ ቢሆንም፣ አሁንም ለውጥ ሊታይበት አልቻለም፡፡ ዘርፉን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ከማድረግ አኳያ ግን በዘላቂነት የጥጥ ልማቱ የሚመራበት የ15 ዓመት ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑን የኢንስትቲዩቱ ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ፣ የግብይት ሒደቱን ከማሳለጥ አኳያ ተቋም የማደራጀት ሥራ መከናወኑንና በተመሳሳይ ዘላቂያዊ የግብይት ፖሊሲ እስኪዘጋጅ ድረስ ጊዜያዊ መመርያ ስለመዘጋጀቱ ጠቅሰዋል፡፡

በጥጥ አቅርቦት ዙሪያ ለተፈጠረው ክፍተት እንደ ችግር የተጠቀሰው ለየት ያለው ጉዳይ፣ ለጥጥ ልማት ተብሎ የተሰጠን ብድር ለታለመለት ዓላማ አለማዋል የሚለው የኢንስቲትዩቱ መረጃ ነው፡፡ በዕለቱ ለውይይት በቀረበው ጽሑፍም ላይ ጥጥ ለማልማት ብድር ከወሰዱ አልሚዎች በዚህ ምርት ዘመን በጥጥ ምርት የተሳተፉት 40 በመቶ የማይበልጡ መሆኑን ጠቅሶ፣ 200 ለሚሆኑ አልሚዎች ከ88 ሺሕ ሔክታር መሬት በላይ ጥጥ እንዲያለሙ 4.2 ቢሊዮን ብር ብድር የተፈቀደ ሲሆን፣ ወደ ሦስት ቢሊዮን ብር የሚሆነው ተሠራጭቷል፡፡ አብዛኞቹ ግን ለተባለው ዓላማ እንዳላዋሉት ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡

ከ100 ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት ለጥጥ ልማት ወስደው ከሦስት እስከ አሥር ዓመት ወደ ልማት አለመግባታቸው፣ ጥጥ አምራቾች ከባንክ ብድር እንዲያገኙ ድጋፍ ስለመደረጉም አስታውሷል፡፡

የፀጥታ ችግርም ለጥጥ ልማት ዕድገት ሌላው ሰበብ ሆኖ ቀርቧል፡፡ መንግሥትም የፀጥታ ችግሮችን ከመፍታት አኳያ በጥጥ እርሻዎች ላይ የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮች እንዲፈቱ ከክልል መንግሥታት ጋር እየተሠራ መሆኑ፣ ፀረ ተባይ ኬሚካሎችን ለጥጥ ልማቱ ለሚያስገቡ የውጭ ምንዛሪ እንዲያገኙ ድጋፍ ስለመደረጉ ተብራርቷል፡፡

ለውጭ የታሰበው ለአገር ውስጥ ገበያ

እንደ ጨርቃ ጨርቅ ኢንስቲትዩት መረጃ ከዘርፉ ሊገኝ ይገባል የተባለው የውጭ ምንዛሪ ማነስ አንዳንድ ፋብሪካዎች ለወጪ ንግድ ያቀርባሉ የተባሉት ምርት በአገር ውስጥ መሸጣቸው ነው፡፡

የኢንስቲትዩቱ አንድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ እንደገለጹት፣ ትልቁ ፈተና ይህ ነው፡፡ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የነበረባቸውን ምርት ለአገር ውስጥ ገበያ በማዋል የሚፈጽሙት ተግባር የወጪ ንግድ ዕቅዱ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ግን መንግሥት እየሠራ ስለመሆኑ ግን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ አሁንም አዳዲስ ኩባንያዎች እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ ነውም የሚል መረጃ ቀርቧል፡፡

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመትም እስከ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚገመት ኢንቨስትመንት ካፒታል ግምት ያላቸው ፕሮጀክቶች ተጠናቀው በከፊል ወደ ማምረት የተሸጋገሩ ሲሆን፣ ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው ተብሏል፡፡

በኢንቨስትመንት ሒደት ላሉ ፕሮጀክቶች የማሽነሪና ቴክኖሎጂ መረጣ፣ የማሽነሪ ሌይአውት፣ የአዋጭነት ጥናት ግምገማና የማማከር ድጋፎች የተሰጡ ሲሆን፣ ሌሎች ባለሀብቶችም ወደ ዘርፉ እንዲገቡ የማማከር ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡

የዘርፉ ተግዳሮቶች

የዘርፉ አፈጻጸም የተጠበቀውን ያህል ያለመሆን የተለያዩ ምክንያቶች ቀርበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺም፣ እንደ ኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ያሉ ምክንያቶችን ጠቅሰዋል፡፡ ምርት ይጀምራሉ ተብለው ሲጠበቁ ያልጀመሩ መኖራቸውንም አመልክተዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ግን መንግሥት ጥረት እያደረገ ስለመሆኑም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡  

በዕለቱ በቀረበው የኢንስቲትዩታቸው መረጃ ላይ ለኤክስፖርት አፈጻጸም ማነስ አስተዋጽኦ ያደረጉ ችግሮችና ችግሮችን ለማስወገድ እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች ወደ አገር ውስጥ ገበያ ማዘንበል፣ የፋብሪካዎች የማኔጅመንት ቴክኒክ አቅም ውስንነት፣ በኢንቨስትመንት ሒደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች በወቅቱና በሚጠበቀው አቅም ወደ ማምረት አለመሸጋገር፣ ወደ ማምረት የገቡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችም ወደ ሙሉ የማምረት አቅም መድረስ አለመቻላቸው በዝርዝር ቀርቧል፡፡ በተለይ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያሉ ፋብሪካዎች፣ ካኖሪያ አፍሪካ ቴክስታይል፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ማጋጠሙ ለምርታማነት እንቅፋት ነበር ተብሏል፡፡

በዚህ መነሻነትም ቀጣይ ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮች የዘርፉን ፋብሪካዎች ምርትና ምርታማነት እንዲሁም ጥራት ላይ የተመሠረተ ምርት በማምረት በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማስቻል ነውም ተብሏል፡፡

ለፋብሪካ ግንባታ የመሬት አቅርቦት ችግር ለኢንቨስትመንት የሚውል መሬቶችን በተመለከተ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ከሚገነቡ ማምረቻዎች ከ15 እስከ 20 ከመቶ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲሆን አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ ከአዲስ አበባ አስተዳደርና ከክልሎች ጋር በቅንጅት እየተሠራ ስለመሆኑ የኢንስቲትዩቱ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

በዕለቱ በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታደሰ ኃይሌም በተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ መንግሥት ዘርፉን ይደግፋልም ብለዋል፡፡ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካዎች ወደ አገር ውስጥ ገበያ ማዘንበል ከሚመለከታቸው ከዘርፉ ማኅበር፣ ፋብሪካዎችና የመንግሥት አካላት ጋር በመሆን ኤክስፖርቱ እንዲሳካ የማድረግ፣ በጥጥ ግብይት ላይ የተከሰተውን ክፍተት በቀጣይ እጥረት እንዳይከሰት ከውጭ ማስገባት የመንግሥት ዕቅድ ሆኖ ተቀምጧል፡፡ የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረትና ፍልሰት ችግር እየሆነ በመምጣቱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን በመሥራት ዘርፉ አሁንም ተስፋ ያለው ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ በኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ተዋንያኖች አሁንም ያሉብን ችግሮች ሊቀረፉልን ይገባል የሚለውን ድምፅ እያስተጋቡ ነው፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ከጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ 2.5 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ይገኛል ተብሎ መታቀዱ ይታወቃል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች