‹‹ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ሁሉ እንደ አገር የሚቆጠር የመንግሥት ሥርዓት በመገንባት በየትኛውም መሥፈርት የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ ነች፡፡ እንደ አገር ለመቆጠር ታሪካዊ መሠረትም ሆነ ፍላጎቷ ያስችላታል፡፡ ነገር ግን በቅርበት ለሚያያት ኢትዮጵያ እንደ አገር እያነሳች ትሄዳለች፡፡ ስለኢትዮጵያ አስተዳደር ቀጣይነት፣ ቅቡልነትና ሥርዓት የሚቀርቡ አፅንኦቶች ሁሉ በእኩል መጠን ተቃራኒ ምላሽ ይሰጥባቸዋል፡፡››
እነዚህ ቃላት የዓለም የሰላም ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚና በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም በሱዳን ዙሪያ በሚጽፏቸው ጽሑፎች ዕውቅ የሆኑት እንግሊዛዊ አሌክስ ዲዋል ናቸው፡፡ ዲዋል በኢትዮጵያ ጉዳይም ለረዥም ጊዜያት ምርምር ያደረጉ ናቸው፡፡ በቅርቡ በሒልተን ሆቴል በተመረቀውና “The Real Politics of the Horn of Africa: Money, War and the Business of Power” የሚል ርዕስ በሰጡት አዲሱ መጽሐፋቸውም በአንዱ ምዕራፍ ስለኢትዮጵያ አንስተዋል፡፡
ዲዋል በትክክልም እንደገለጹት ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ፅንፍ የያዙ ተዋንያን ዋነኛ መገለጫዎቹ ናቸው፡፡ ለአብነት ሙስናን ብንወስድ በችግሩ ስፋት፣ ምንጭና መፍትሔዎች ላይ በፖለቲካ ኃይሎች ዘንድ ስምምነት የለም፡፡ ዓለም አቀፉ በሙስና ላይ የሚሠራው መንግሥታዊ ያልሆነው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል በቅርቡ ያወጣው የሙስና ዕይታ ጠቋሚ (Corruption Perception Index) ከ168 አገሮች የኢትዮጵያ ደረጃ 103 እንደሆነ ያሳያል፡፡ የአብዛኛው ሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎት ለማሟላት ሌት ተቀን እንደሚሠራ በኩራት ለሚገልጸው የኢትዮጵያ መንግሥት ይህ ደረጃ በየትኛውም መሥፈርት በጥሩ ሁኔታ አይወሰድም፡፡ በ2004 ዓ.ም. የዓለም ባንክ በሙስና ላይ ያወጣው ሪፖርትም በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የሚፈጸመው ሙስና ከፍተኛ ባይሆንም፣ በሕዝቡ ዘንድ ያለው እምነት ግን ከባድ ሙስና ይፈጸማል የሚል እንደሆነ አመልክቶ ነበር፡፡ ይህ መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እያደረግኩ ነው ከሚለው በተቃራኒ የሕዝብ እምነት እየተሸረሸረ ስለመሆኑ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡
በሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ ጽሑፎች ይበልጥ ተብራርቶ የተቀመጠውና በሥራ ላይ ያለው የልማታዊ መንግሥት የዕድገት ሞዴል ልማትን በማፋጠን ሥልጣን ያላግባብ የሚጠቀሙና ሙስና የሚፈጽሙ ግለሰቦችን መታገያ ሥልት ይነድፋል፡፡ ለአቶ መለስ በጣም ቅርብ ከነበሩ ምሁራን መካከል የሚካተቱት ዲዋል የአቶ መለስ ሞዴል ስለገጠመው ተግዳሮት ሲገልጹ፣ ‹‹የአቶ መለስ ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት ሞዴል በመጨረሻ የግላቸው እንጂ የቡድን እምነት አልሆነም፡፡ ውጤቱ ጽንሰ ሐሳቡን መረዳት አስቸጋሪ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን እሱን ለመፈጸም ዝግጁ የሆነ ድርጅታዊ አወቃቀርም አልተፈጠረም፡፡ በዚህ የተነሳ መንግሥታዊ ጉዳዮች በየቀኑ ይዘነጉ ነበር፡፡ የመለስ ተግዳሮት ተግባራዊነቱ ነበር፤›› ብለዋል፡፡
እንደ ዲዋል ገለጻ፣ አቶ መለስና የቅርብ ጓደኞቻቸው ጽንሰ ሐሳቡ ላይ የሙጥኝ ቢሉም የተቀረው ኢትዮጵያዊ ድጋፉን የቸረው አልነበረም፡፡ ሞዴሉ የበላይነት ሊይዝ እንዳልቻለ አቶ መለስ ተረድተው እንደነበርም ዲዋል አመልክተዋል፡፡ አቶ መለስ ከመሞታቸው ከሦስት ወራት በፊት ለኢሕአዴግ ፖሊት ቢሮ ጻፉት ብለው የጠቀሱት ማስታወሻ ላይ፣ የፓርቲው አመራር ድክመት ፕሮጀክቱን አደጋ ላይ እንደጣለው መግለጻቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ለአፈጻጸሙ የሚረዳ ስትራቴጂካዊ የአመራር ብቃት ካልፈጠርን ትክክለኛ ፖሊሲ ብንቀርፅም የትም ልንደርስ አንችልም፡፡ ትክክለኛ ፖሊሲዎች ቢኖሩንም እነሱን ለመፈጸም የሚያስፈልገውን ስትራቴጂካዊ አመራር ከማግኘት አኳያ በብዙ ርቀት ላይ እንገኛለን፤›› በማለት አቶ መለስ መጻፋቸውን ዲዋል ጠቅሰዋል፡፡
ዲዋል የኢሕአዴግ አመራር አባላት በአጠቃላይ የተቀናጣ ኑሮ ከመግፋት ተቆጥበው የፓርቲውንና የአገሪቱን ፍላጎቶች ለማሟላት በመጣር ሕይወታቸውን የሰጡ ቢሆንም የሙስናው ሰደድ ወደ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ እየተስፋፋ መምጣቱ አሳሳቢ እንደሆነ ግን ሳይገለጹ አላለፉም፡፡ ‹‹ለኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ተግዳሮት የሆነው በኢሕአዴግ የፖለቲካ አመራር፣ በደኅንነት ተቋማት ኃላፊዎችና በመከላከያ አመራሮች መካከል ያለው ውድድር ባህርይ ነው፡፡ የአገር ሀብት የሚከፋፈለው በእነዚህ ልሂቃን ሲሆን አባላቱ ይህንን ሀብት ለግል ጥቅማቸው፣ ለቡድናዊ የፖለቲካ ፍጆታና አንዳንዴም ለሁለቱም ይጠቀማሉ፤›› ብለዋል፡፡
እንደ ዲዋል ሁሉ ሙስና የአገሪቱን ጤንነት እያወከ እንደሆነ የሚያምኑ ዜጎች በርካቶች ናቸው፡፡ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ጥቂት ታማኝና ቁርጠኛ የሕዝብ አገልጋዮች ሙሰኛና አቅም በሌላቸው በርካቶች ተውጠዋል የሚል ቅሬታ ሲያቀርቡ መስማትም አዲስ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይም እምነት የሌላቸው በርካቶች ሲሆኑ፣ ሙሰኞችና አጥፊዎችን ተጠያቂ ስለማድረጉ ጥርጣሬዎች ይደመጣሉ፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት ግልጽነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን የባለሥልጣናቱን ሀብት በመመዝገብና ለሙስና ተጋላጭ ናቸው ብሎ በለያቸው እንደ የመንግሥት ግዢ ሥርዓት፣ ገቢዎች፣ ጉምሩክና የገንዘብ አስተዳደር በመሳሰሉ አካባቢዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ ይገልጻል፡፡
ይህ በመንግሥትና በሕዝቡ መካከል ያለው እምነት የተቀናጀ እንዳልሆነ አመላካች ነው፡፡ ይሁንና ይህንንም የሚቃወመው መንግሥት በመሠረታዊ እሴቶች ላይ ብሔራዊ መግባባት እየዳበረ እንደሆነ ይከራከራል፡፡ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ‹‹በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ መሠረታዊ መርሆዎች፣ በፀረ ድህነት ትግልና ፈጣን ልማት ለማረጋገጥ ባለው ራዕይ አፈጻጸም ላይ፣ ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ፣ ብዝኃነትን በማክበር፣ የህዳሴው ጉዞ ጅምር ውጤቶች፣ እየተቀየረ በመጣው የአገሪቱ ገጽታ፣ በትምህርት፣ በጤናና መሠረተ ልማት በተመዘገቡ ውጤቶች ላይ ብሔራዊ መግባባት ተፈጥሯል፤›› ይላል፡፡ ዕቅዱ በተጨማሪም ሙስናን ጨምሮ በዴሞክራሲና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የሚነሱ ወሳኝ ጉዳዮች የሚቀረፉበትን ዝርዝር ሒደት ያብራራል፡፡
የኢሕአዴግ ሌላ ፕሮፓጋንዳ ወይስ እውነተኛ ቃል?
የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በ2007 ዓ.ም. ከተጠናቀቀ በኋላ በቅርቡ በፓርላማ በፀደቀው ቀጣይ ክፍል አማካይነት ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች፡፡ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2025 መካከለኛ ገቢ ያላት አገር የመሆን ራዕይ ሰንቃ እየተንቀሳቀሰች ሲሆን፣ በሒደቱ ሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶች የሚከበሩባት፣ የሕግ የበላይነት የሚረጋገጥባት፣ መልካም አስተዳደር የሚሰፍንባት፣ የዜጎች ነፃነትና ደኅንነት የሚከበርባት፣ በሥነ ምግባር የታነፀና ከሙስና ነፃ የሆነ ማኅበረሰብ የሚፈጠርባት ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ታስባለች፡፡ ስለዚህ ይህ ዕውን እንዲሆን ቢያንስ አንድ ተጨማሪ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እንደሚኖር መገመት ይቻላል፡፡
የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ግን ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስለ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ያሰፈራቸው ሃተታዎች ናቸው፡፡ እንዳለፈው ዕቅድ ሁሉ ይኼኛውም ስለ ዴሞክራሲ መሠረታዊ ሐሳቦች ያወሳል፡፡ ነገር ግን የዴሞክራሲ ርዕሰ ጉዳዮች በአብዛኛው ከመልካም አስተዳደር አንፃር ተቃኝተው ቀርበዋል፡፡ በዕቅዱ መሠረት መልካም አስተዳደርን በአገሪቱ ለማስፈን ዕርምጃዎች ይወሰዳሉ፣ ግልጽና ተጠያቂ የሆነ የመንግሥት አሠራር ለመፍጠርና ለማጠናከር፣ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞችን አቅም ለማጎልበትና የዜጎችን ተሳትፎ ለማጠናከርም ታቅዷል፡፡
ሰነዱ እነዚህ ሥራዎችን በስኬት ለመወጣት የሚያስችል ሥራ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አማካይነት መከናወኑንም ያስታውሳል፡፡ በዋነኛነት ከአቅም ግንባታ፣ ልማታዊ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ አስተሳሰብ ከመፍጠርና ዜጎችን ተሳታፊ ከማድረግ አኳያ መሠረቱ መጣሉንም ያትታል፡፡ እነዚህ አበረታች ውጤቶች ሁለተኛውን ዕቅድ በተሻለ አውድ እንዲፈጸም እንደሚያደርጉትም ተስፋ ተደርጓል፡፡
ከትኩረት አቅጣጫ አንፃር ሁለተኛው ዕቅድም አዲስ ነገር ይዞ አልመጣም፡፡ ሁለተኛው ዕቅድ በዋነኛነት ታሳቢ ያደረገው በከተሞች አካባቢ የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካል ኢኮኖሚ የበላይነት መያዙን ነው፡፡ ስለዚህ ዕቅዱ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት የኪራይ ሰብሳቢ አመለካከትን ከሥር መሠረቱ ለማድረቅ እንደሚሠራ ያስቀምጣል፡፡ በሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መሪነት ይህን ቁልፍ ችግር ለመፍታት ርብርብ እንደሚደረግም ያመለክታል፡፡
ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ካካተታቸው ግቦች መካከል ዋነኛዎቹ ልማታዊና ብቁ የፖለቲካ አመራርና ቢሮክራሲ መፍጠር፣ ሕዝቡ አቅሙ እንዲጎለብትና የልማቱ ባለቤት እንዲሆን ማስቻል፣ መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ የፍትሕ ሥርዓቱ ውጤታማና ከሙስና እንዲሁም ከአድልኦ እንዲነፃ ማድረግና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ማጠናከር ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ዕቅዱ የትራንስፎርሜሽን ሒደቱ ወሳኝ አደጋዎች ናቸው ብሎ ያስቀመጣቸው ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚፈጸም ለዜጎች ቃል ይገባል፡፡ የአመራሩና የቢሮክራሲው አቅም የሚገነባው ብቃትን መሠረት ያደረገ ምደባና ምልመላ በማድረግ እንደሚሆንም ያመለክታል፡፡
የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በአገሪቱ ያለውን ብዝኃነት እንዲያንፀባርቁና የሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲወክሉ እንደሚደረግም ይገልጻል፡፡ በተለይ ለሴቶችና ለወጣቶች ቅድሚያ በመስጠት እንዲሠሩ ማድረግም ሌላኛው ዕቅድ ነው፡፡ የዜጎች ቻርተር ተግባራዊ እንዲሆን በማድረግ በመንግሥት አሠራር ላይ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ማረጋገጥም ሌላኛው ግብ ነው፡፡ የሕዝብ እርካታና ተዓማኒነት የሚያስገኙ ሥራዎችን መሥራትም ትኩረት ከተደረገባቸው ዕቅዶች አንዱ ነው፡፡
ሁለተኛው ዕቅድ በሕዝብ ተሳትፎና በመልካም አስተዳደር ላይ እንደሚሽከረከር ግልጽ ነው፡፡ የትራንስፎርሜሽን ሒደቱን ዘላቂ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመንግሥት የሚደረገው ጥረት ሕዝብን መሠረትና ማዕከል ካላደረገ ሊሳካ አይችልም የሚል ግምትም ወስዷል፡፡ ሕዝቡ ስለ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ኋላቀርና ፀረ ልማት አስተሳሰቦች ያለው አመለካከት ከመንግሥት መሠረታዊ ፖሊሲዎች አንፃር ከተቃኘ፣ የሕዝቡ ፍላጎት በመንግሥት ኃላፊዎች ፍላጎት ላይ የበላይነቱን እንደሚይዝም ታሳቢ አድርጓል፡፡
እንደ መጀመሪያው ዕቅድ ሁሉ የሕዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ መሬት አስተዳደር፣ ጉምሩክና ታክስ አስተዳደር፣ የመንግሥት የፋይናንስና ግዥ አስተዳደርና የገበያ ውድድር ሥርዓት ላይ ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችሉ አሠራሮች ተግባራዊ እንደሚሆኑም ያመለክታል፡፡ በዚህም ጉዳይ ላይ ቁልፉ ጉዳይ የሕዝብ ንቅናቄ፣ እንዲሁም በመንግሥት ውሳኔ አሰጣጥ ሒደት ላይ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የዴሞክራሲ ሥርዓቱንና የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማት የሆኑት እንደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በየተዋረዱ የሚገኙ ምክር ቤቶች፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምና ዋናው ኦዲተር ያሉ ተቋማት ሚና ከመጀመሪያው ዕቅድ የተሻለና የጎላ ለማድረግም መታቀዱን ማየት ይቻላል፡፡ በተለይም የዴሞክራሲ ባህል እንዲገነባ ለማድረግ ቁልፍ ሚና እንደተሰጣቸው ዕቅዱ ይገልጻል፡፡
በመርህ ደረጃ የዴሞክራሲ መሠረታዊ መገለጫዎችን ማካተት ለኢሕአዴግ መራሹ የመንግሥት ዕቅድ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ የመንግሥትና የገዢው ፓርቲ ሰነዶች እንደሚገልጹት፣ የመንግሥት የልማት ዕቅዶች ከዴሞክራሲያዊ አጀንዳዎች ተለይተው አይፈጸሙም፡፡ የኢሕአዴግ የፖሊሲ አፍላቂ የነበሩት ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ፣ ዴሞክራሲን ለማሳካት የሚፈለው ዋጋ ዕድገትን መቀነስ ከሆነ እሱ ይመረጣል ብለው ነበር፡፡
የሕገ መንግሥቱ ንባብም የሚያመለክተው ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ገሸሽ ያደረገ የአመራር ዘይቤ መተርጎም እንደማይቻል ነው፡፡ ከዚህ በመነሳትም ሲቪል ማኅበራት፣ መንግሥት፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሕዝቡና ልሂቃኑ በመሰላቸው መንገድ በነፃነት ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት የመንቀሳቀስ መብት አላቸው ማለት ሞኝነት አይሆንም፡፡ በተጨማሪም እነዚህ አካላት በመንግሥት ፖሊሲዎች ላይ ግብዓት እንዲሰጡና አማራጭ እንዲያቀርቡ ማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ካደጉ አገሮች ልምድ መረዳት ይቻላል፡፡
እንደ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ከሰጠው ጥበቃ በተቃራኒ የዴሞክራሲያዊ ሒደቱ በተግባር የታጀበ አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ ዴሞክራሲን ከልማት አንፃር አጥብቦ ያያል ተብሎም ይተቻል፡፡
ከዚህ በተቃራኒ ዴሞክራሲን ለማዳበር ቁልፍ ሚና እንዳላቸው የሚታሰቡትን ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኞችንና ጋዜጠኞችን በማዋከብና በማሰርም ይከሰሳል፡፡
ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር እንደ ማስፈጸሚያነት
ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር ፀድቆ ባለፉት ሦስት ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ መርሐ ግብሩን እንዲያዘጋጅ የተቋቋመው ጽሕፈት ቤት ደግሞ ባለፉት አምስት ዓመታት ሥራ ላይ ቆይቷል፡፡ መርሐ ግብሩ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተቀናጀ መልኩ ተግባራዊ እንዲሆኑና የፍትሕ ሥርዓቱ እንዲጠናከር ለማድረግ የተዘጋጀ ነው፡፡ ጽሕፈት ቤቱ በመርሐ ግብሩ አማካይነት የመንግሥት ተቋማቱን ከማስተባበር ባሻገር በምርምርና በግንዛቤ መፍጠር ረገድ ቁልፍ ሚና እንዲጫወቱ የተቋቋመ ነው፡፡
እርግጥ በሁለተኛው ዕቅድ የፍትሕ ሥርዓቱን ከሙስናና አድልኦ ነፃ እንዲሆን ማድረግ እንደ አንድ ትልቅ ግብ ይዞታል፡፡ ለዚህ እንደ ማስፈጸሚያ ሥልት ከተጠቀሱት መካከል የተረጋገጠና ተዓማኒ ማስረጃ እንዲቀርብ ማስቻል፣ ሕጎች ሲረቀቁና ሲሻሻሉ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን ማረጋገጥ፣ የዳኝነት አካሉና ፍርድ ቤቶች ነፃነታቸው እንዲረጋገጥ ማድረግ፣ ግልጽና ተጠያቂ የመንግሥት ሥርዓት መፍጠር፣ የዘርፉን የሰው ኃይል አቅም በዕውቀት፣ ክህሎትና በመሠረተ ልማት ማሳደግ፣ በሕገ መንግሥቱና በፍትሕ ሥርዓቱ ዙሪያ የሕዝቡን ንቃተ ህሊና ማሳደግ ይገኛሉ፡፡
የድርጊት መርሐ ግብር ጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ይበቃል ግዛው ከ300 በላይ የመንግሥት ተቋማት ለጽሕፈት ቤቱ ሪፖርት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ ካለፉት ሦስት ዓመታት በመነሳት በድርጊት መርሐ ግብሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው ተቋማት የትኞቹን ሥራዎች በምን ያህል መጠን ሠሩ የሚለው በጽሕፈት ቤቱ መገምገሙንም አመልክተዋል፡፡ ‹‹በመጀመሪያው የድርጊት መርሐ ግብር አበረታች ሥራ ሠርተናል፡፡ ዕቅዶቹ እንደ መጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሁሉ የተለጠጡ ነበሩ፤›› ብለዋል፡፡
የመጀመሪያው የድርጊት መርሐ ግብር እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ ዘልቋል፡፡ ‹‹ቁልፉ ነገር ግን ሰብዓዊ መብትን የማስከበር ጉዳይ በየትኛውም አገር የጊዜ ገደብ አስቀምጠህ እዚህ ጋ አጠናቅቄያለሁ የምትለው አይደለም፤›› ያሉት አቶ ይበቃል፣ ሰብዓዊ መብትን የማስከበር ጥረት ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ በተለይ ሕገ መንግሥቱ በ1987 ዓ.ም. ከፀደቀ በኋላ ተጠናክሮ የቀጠለ ሥራ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ መርሐ ግብሩ ለዚህ ጥረት ጉልበት የሚሰጥና አንድ ተጨማሪ መሣሪያ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡
ለሰብዓዊ መብት መከበር ትልቁ መሠረት የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ይበቃል፣ ሰብዓዊ መብትን ተግባራዊ የማድረግ ‹‹ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት አለ፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ማለት ግን በጉዳዩ ላይ መሠረታዊ ክፍተት የለም ማለት እንዳልሆነ አስምረዋል፡፡ ከአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ተጨባጭ ሁኔታ፣ ያለው የዴሞክራሲ ሥርዓት ገና በመሆኑና የሰብዓዊ መብት ባህል በሚፈለገው ደረጃ ያልዳበረ ከመሆኑ አንፃር በሕገ መንግሥቱ ጥበቃ ያገኙ መብቶች ላይፈጸሙ እንደሚችሉ ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
ነገር ግን በርካታ ዜጎች ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሰብዓዊ መብትን የሚያከብር አይደለም ሲሉ ይተቻሉ፡፡ በአገር ውስጥ የሚገኙና የውጭ አስተያየት ሰጪዎች በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ሥር እንዲሰድና ሰብዓዊ መብት እንዲከበር የሚያስችሉ ተጨባጭ ዕርምጃዎች በመንግሥት አልተወሰዱም ሲሉም ቅሬታቸውን ያሰማሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብን ገዢው ፓርቲን በሚጠቅም መልኩ ብቻ ጥቅም ላይ ይውላል ሲሉም ይከሳሉ፡፡ አቶ ይበቃል እነዚህ ትችቶች ከዕውነታው ፈቀቅ ያሉና የተጋነኑ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
አቶ ይበቃል መንግሥት ግዴታዎቹን በሚወጣበት ወቅት የሚፈጽማቸው ስህተቶች ካሉ ዋናው መገለጫቸው የመልካም አስተዳደር ዕጦት እንደሆነም ተከራክረዋል፡፡ ‹‹ሰብዓዊ መብትና መልካም አስተዳደርን ልትነጣጥላቸው አትችልም፡፡ ከዚህ አንፃር የድርጊት መርሐ ግብሩ መልካም አስተዳደርን የማስፈኛ ተጨማሪ መሣሪያ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተጠበቁ ዋና ዋና መብቶች በተገቢው መንገድ ከተጠበቁ መልካም አስተዳደር ሰፈነ ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡
እንደ ድርጊት መርሐ ግብር ጽሕፈት ቤቱ ያሉ ሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ የመንግሥት ተቋማትና ነፃና ገለልተኛ ናቸው ተብለው በሕገ መንግሥቱ የተቋቋሙ እንደ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና እንባ ጠባቂ ተቋም ያሉ ተቋማት ግንዛቤ መፍጠር ላይ ቢያተኩሩም፣ ግንዛቤ በራሱ መብቶቹን ለማስከበር ወሳኝ ነገር አይደለም የሚል ወቀሳ ይቀርባል፡፡ ግንዛቤው ያላቸው በእምነት ማጣት ወደ ፍትሕ አካላት አለመሄዳቸው እንደ አብነት ይጠቀሳል፡፡ አቶ ይበቃል ግን ግንዛቤ ብቻውን ለውጥ እንደማያመጣ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹እንደ መርሐ ግብሩ ግንዛቤ ላይ ብቻ አናተኩርም፡፡ ጠያቂ ማኅበረሰብ መፍጠር አለብን፡፡ መብቶቻችንን የመጠየቅና ተግባራዊ የማድረግ ባህል እንዲዳብርም መሥራት አለብን፡፡ በዚሁ ልክ ደግሞ ምላሽ ሰጪ ቢሮክራሲ መፍጠር አለብን፤›› ብለዋል፡፡ ምላሽ ሰጪ የሆነ ሊታመን የሚችል ሥርዓት፣ ተጠያቂ የሆነ ሥርዓት፣ ስህተት ሲሠራ የሚጠየቅ ሥርዓት ከሌለ ትልቅ ችግር ነው ያሉት አቶ ይበቃል፣ ‹‹በአጠቃላይ ተዓማኒ የሆነ ቢሮክራሲ አለ ብለን እናምናለን፡፡ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ጥርጣሬ ያለው የኅብረተሰብ ክፍልም ካለ ጥርጣሬውን የሚያስተው ሥርዓት መፍጠር ያስፈልጋል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡
ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብት ቅድሚያ መሰጠቱ
በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ሁሌም ስሟ በክፉ የሚነሳው ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ቢያንስ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ላይ ያላት አፈጻጸም መሠረታዊ ለውጦች እያሳየ እንደሆነ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ እነዚህ መብቶች ላይ የሚደረገው ትኩረት በሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶች ላይ ይበልጥ ጫና መፍጠሩም ይነገራል፡፡
አሌክስ ዲዋል ኢትዮጵያ በኢሕአዴግ አመራር ለማደጓ የተሠሩት መንገዶች፣ ድልድዮች፣ ግድቦች፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎቶች፣ ትምህርት ቤቶችና የጤና ማዕከላት ምስክር እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ዕድገት ለሁለት አሥርት ከቀጠለ የኢትዮጵያ ትራንስፎርሜሽን እንደሚሳካና የኢትዮጵያ ገጽታም በጣም እንደሚለወጥ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት አገሪቱ ባለፉት አሥር ዓመታት የኢኮኖሚ ዕድገቱን በ11 በመቶ እንዲቀጥል በማድረጉ እንደ ዲዋል ሁሉ ሙገሳ የሚያጎርፉለት ብዙዎች ናቸው፡፡ አንዳንዴ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የዕድገት መጠኑ ላይ ልዩነታቸውን ቢያሳዩም፣ ዕድገቱ በአጠቃላይ ከአፍሪካ ተቀዳሚ ከሆኑ አገሮች መካከል ኢትዮጵያን አንዷ እንደሚያደርግ ግን ይመሰክራሉ፡፡
እነዚህ አበረታች ውጤቶች የሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ ጥበቃን ለማስቻል የተሻለ መሠረት ይጥላሉ በሚል የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያመላክት ሲሆን፣ ተቺዎች ግን በልማት ስም የመብት ጥበቃዎች ላይ ይበልጥ ጫና ተፈጥሯል ይላሉ፡፡
በተግባር መንግሥት የበለጠ ትኩረትና ቅድሚያ የሚሰጠው ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብት ቢሆንም፣ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ግን ሁሉም መብቶች በእኩልነት ተግባራዊ መሆን እንዳለባቸው ያስቀምጣል፡፡
ሰብዓዊ መብቶች የማይነጣጠሉና የተሳሰሩ መሆናቸውን ያስታወሱት አቶ ይበቃል፣ በተመሳሳይ ለአንዱ መብት ቅድሚያ መስጠት የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡ ‹‹መንግሥት የአንደኛው መብት መፈጸም ለሌላኛው መብት መፈጸም ቅድመ ሁኔታ ነው በሚል እሳቤ አይሠራም፡፡ የአንዱ መብት ቅድሚያ መፈጸም ለሌላኛው መብት አፈጻጸም ሊያግዝ ግን ይችላል፤›› ያሉት አቶ ይበቃል፣ ይኼ ግን የግድ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች መከበር መቅደም አለበት የሚለውን እንደማያሳይ አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ለምሳሌ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶቹ ሙሉ በሙሉ የተከበሩለት አገር ከመንግሥት ጎን ተሠልፎ ለልማቱ ለመንቀሳቀስ ቁርጠኛ ይሆናል፣ አቅሙ ይዳብራል፣ ሰላም ይሰፍናል፡፡ መንግሥት የዜጎቹን በሕይወት የመኖር መብት በአግባቡ የሚያስከብር ከሆነ፣ ኢሰብዓዊ አያያዝ የማይኖር ከሆነ፣ የመደራጀት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት፣ በምርጫ የመሳተፍ መብቶች የተከበሩለት አገር ሰላማዊ የመሆን ዕድሉ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ሰላማዊ አገር ለልማት የሚያስፈልገውን ዋነኛ መሠረት ጥሏል ማለት ነው፤›› በማለት አንዱ ለአንዱ እኩል ድጋፍና መሠረት ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል፡፡ ይሁንና ሁሉም መብቶች በእኩልነት ይከበራሉ የሚለውን ለዜጎችና ለተለያዩ አካላት ማሳመን፣ የሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ቁልፍ ተግዳሮት ሆኖ እንደሚቀጥል ይገመታል፡፡