– በንግድ ቤቶች ጨረታ ከፍተኛው ዋጋ ሆኗል
የአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ በኮንዶሚኒየም ሕንፃዎች ሥር ላሉ የንግድ ቤቶች ባወጣው ጨረታ፣ ለአንድ ካሬ ሜትር 101 ሺሕ ብር ዋጋ መሰጠቱ ተሰማ፡፡
ኤጀንሲው በቅርቡ ባወጣው የ2,399 የንግድ ቤቶች ጨረታ ለሽያጭ ከቀረቡት ውስጥ፣ ለአንድ ካሬ ሜትር 101 ሺሕ ብር ዋጋ የተሰጠው በልደታ ክፍለ ከተማ ከቀረቡ 39 የንግድ ቤቶች ውስጥ ለአንዱ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በልደታ መልሶ ማልማት ኮንዶሚኒየም ሕንፃ ሥር ላለው ንግድ ቤት የተሰጠው ይህ ዋጋ፣ ኤጀንሲው እስከ ዛሬ ባካሄደው ጨረታዎች ላይ ያልተመዘገበ ከፍተኛው መሆኑን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከዚህ ቀደም በተካሄደ ተመሳሳይ ጨረታ በዚሁ ልደታ መልሶ ማልማት ኮንዶሚኒየም ሕንፃ ሥር ለነበረ አንድ ንግድ ቤት ለአንድ ካሬ ሜትር 56,164 ብር የተሰጠው ዋጋ ከፍተኛ ተብሎ ነበር፡፡
በአሁኑ ዙር ጨረታ ግን በአንድ ካሬ 101 ሺሕ ብር መሰጠቱ የንግድ ቤቶች የመሸጫ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እንዳሳደገው አሳይቷል፡፡ በካሬ ሜትር 101 ሺሕ ብር ዋጋ ከቀረበበት ንግድ ቤት በተጨማሪ፣ በዚሁ ልደታ ለጨረታ የቀረቡ ሌሎች ንግድ ቤቶች በካሬ ሜትር 72 ሺሕ፣ 64 ሺሕ እና 40 ሺሕ ብር ዋጋ እንደተሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይኼም የልደታ መልሶ ማልማት ቦታ ከፍተኛ ዋጋ እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡ ለአንድ ካሬ ሜትር የተሰጠው 101 ሺሕ ብር ንግድ ቤቶቹ 50 ካሬ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን፣ የሽያጭ ዋጋው ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
ጥር 5 እና 6 ቀን 2008 ዓ.ም. በአራት ቦታዎች በተካሄዱት ጨረታዎች 2,390 የንግድ ቤቶች እንደሚቀርቡ የተገለጸ ሲሆን፣ ጥቂት ንግድ ቤቶች ግን ጨረታ እንዳልተካሄደባቸው ታውቋል፡፡ በሰሞኑ ጨረታ ንግድ ቤቶቹን ለመግዛት የሰነድ ግዥ ፈጽመው የነበሩት ተጫራቾች ከ21 ሺሕ በላይ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አስተዳደሩ በዚህኛው ዙር የንግድ ቤቶች ሽያጭ ጨረታ ለአንድ ካሬ ሜትር ያስቀመጠው መነሻ ዋጋ 8,405 ብር ነው፡፡ ለንግድ ቤቶቹ እየቀረበ ያለው ከፍተኛ የመጫረቻ ዋጋ እየጨመረ በመምጣቱ አስተዳደሩም የጨረታ መነሻ ዋጋውን ከፍ እያደረገ ሄዷል፡፡ ከዚህ ቀደም የተካሄዱት ሁለት ጨረታዎች ለአንድ ካሬ ሜትር የመነሻ ዋጋቸው 6,606 እና 6,742 ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡
በአራት ቦታዎች ተከፋፍለው የተከፈቱት የተጫራቾች ሰነዶች እንደሚያመለክቱት፣ በአብዛኛው ለአንድ ካሬ ሜትር የቀረቡት ዋጋዎች ከ15 እስከ 20 ሺሕ ብር ነው፡፡
ሰሞኑን ለጨረታ ከቀረቡት የንግድ ቤቶች ውስጥ 659 በአቃቂ ቃሊቲ፣ 20 በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ 20 በኮልፌ ቀራኒዮ፣ 39 በልደታ፣ 45 በአራዳ፣ 1,250 በየካ፣ 366 ደግሞ በቦሌ ክፍላ ከተሞች ውስጥ በተገነቡ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ሕንፃ ሥር ያሉ የንግድ ቤቶች ናቸው፡፡
አስተዳደሩ ለሽያጭ ያቀረባቸው የንግድ ቤቶች ከ33 ካሬ ሜትር እስከ 69 ካሬ ሜትር ስፋት አላቸው፡፡ አሁን ለጨረታ ከቀረቡት ቤቶች ዋጋ አሰጣጥ አንፃር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንግድ ቤቶች ሽያጭ ጨረታ ከዚህ ቀደም ካገኘው ገቢ በላይ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የጨረታው ውጤትም በቅርቡ ይገለጻል ተብሏል፡፡ የጨረታ ሰነዱ እንደሚያስረዳው አሸናፊዎች ያሸነፉበትን ዋጋ ግማሹን በቅድሚያ፣ ቀሪውን ደግሞ በአምስት ዓመት ይከፍላሉ፡፡
ከዚህ ቀደም በአንድ ጊዜ ይህንን ያህል የንግድ ቤቶች ለጨረታ ባይቀርቡም፣ ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት በተካሄደ የንግድ ቤቶች ጨረታ 489 የንግድ ቤቶች ቀርበው እንደነበር ይታወሳል፡፡