– የግል ኩባንያዎች ለተጎጂዎች ድጋፍ መስጠት ጀመሩ
መንግሥት በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመታደግ ተጨማሪ ድጋፍ መስጫ ጣቢያዎችን እየከፈተ መሆኑን አስታወቀ፡፡ የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሰው ወደ ዕርዳታ ሳይሆን ዕርዳታ ወደ ሰው መሄድ አለበት በሚል መርህ ተጨማሪ ጣቢያዎች እየተከፈቱ ነው፡፡
የጣቢዎቹ መከፈት ለዕርዳታ አሰጣጡ መቀላጠፍ ወሳኝ ድርሻ አለው ተብሏል፡፡ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የአንበሳውን ድርሻ በመያዝ ድጋፍ ሲያደርግ የቆየው መንግሥት ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ግን የግል ኩባንያዎች በራሳቸው ፈቃድ ድጋፍ ማድረግ ጀምረዋል፡፡
ኮሚሽነር ምትኩ እንደተናገሩት የፌዴራል መንግሥት ድርቁ ያስከተለው ችግር ሰፊ ቢሆንም፣ መንግሥት ችግሩን ለመቆጣጠር ከአቅሙ በላይ ባለመሆኑ በይፋ ጥሪ አላደረገም፡፡ ኮሚሽነሩ እንዳሉት፣ መንግሥት በአሁኑ ወቅት ከሕዝቡ ገንዘብ ለማሰባሰብ ጥሪ ባያደርግም፣ አስቸጋሪ ወቅት የሚመጣ ከሆነ ግን ሕዝባዊ ጥሪ እንደሚያደረግ በዕቅድ አስቀምጧል፡፡
ነገር ግን የግል ኩባንያዎች ከክልሎች ጋር በመነጋገር ድጋፍ ማድረግ መጀመራቸውን አቶ ምትኩ አስረድተዋል፡፡ እስካሁን በይፋ ድጋፍ ማድረግ ከጀመሩት መካከል ሼክ መሐመድ ዓሊ አል አሙዲ፣ አቶ ኑር ሁሴን (ለንደን ካፌ)፣ ራያ ቢራ እንዲሁም ቀይ መስቀል ማኅበር ይገኙበታል፡፡
ሼክ አል አሙዲ ከረዥም ጊዜ ወዳጃቸው አቶ ኑር ጋር በመሆን ሥር የሰደደ ድርቅ በተከሰተበት አፋር ክልል ውኃ በማውጣት ሥራ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በአፋር ክልል የድርቅ አደጋው በከፋባቸው አምስት ወረዳዎች ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶችን ለመቆፈር ባለፈው ሐሙስ ጥር 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ከክልሉ መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱ ታውቋል፡፡
የጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራውን የተረከበው ሆነስት ኢንጂነሪንግና ኮንስትራክሽን ኩባንያ፣ ግዙፍ የውኃ ጉድጓድ መቆፈርያ ማሽኖችን ማንቀሳቀስ መጀመሩ ታውቋል፡፡
ለዚህ ሥራ የሚያስፈልገው በጀት ባይቆረጥም ኅብረተሰቡን ከድርቅ አደጋ ለማውጣት የትኛውንም ወጪ ለማውጣት መዘጋጀታቸውን አቶ ኑር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አቶ ኑር ጨምረው እንደገለጹት ውኃ በማፍለቅ የአካባቢዎቹን ችግር ለመፍታት ሼክ አል አሙዲ መወሰናቸውን ተናግረው፣ አስፈላጊውን ወጪ ለማውጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡
ራያ ቢራ በትግራይ ክልል በማይጨው ከተማ በ1.7 ቢሊዮን ብር የተገነባ ቢራ ፋብሪካ ነው፡፡ የራያ ቢራ ፋብሪካ ቦርድ ሰብሳቢ የቀድሞው የአገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማጆር ሹም ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረተንሳይ በቅርቡ በመቐለ ከተማ በተካሄደው የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ፣ ራያ ቢራ በድርቅ ከተጎዱ ወገኖች ጎን እንደሚቆም ተናግረዋል፡፡
ቢራ ፋብሪካው በቢራ ጠመቃ ሒደት ለከብቶች መኖ የሚሆን ተረፈ ምርት ያገኛል፡፡ ይህንን ተረፈ ምርት ያለምንም ክፍያ ለአካባቢው ገበሬዎች ማከፋፈል ጀምሯል፡፡ ሌተና ጀኔራል ፃድቃን ራያ ቢራ ፋብሪካ ተረፈ ምርቱን ቢሸጥ 20 ሚሊዮን ብር ያገኝ እንደነበር በጉባዔው ወቅት ገልጸዋል፡፡
የሌተና ጄኔራሉን ሐሳብ ጠቅላላ ጉባዔው በሙሉ ድምፅ የደገፈ ሲሆን፣ ባለአክሲዮኖች ይህ የከብቶች መኖ በነፃ መከፋፈሉን የትርፍ ክፍፍል (ዲቪደንድ) እንዳገኙ እንደሚቆጥሩት በመግለጽ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል በተለያዩ ዓመታት በኢትዮጵያ በሚከሰት ድርቅ ከሚጎዱ ዜጎች ጎን በመቆም የሚታወቀው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር፣ በአሁኑ ወቅትም በድርቅ ከተጎዱ ወገኖች ጎን እንደሚቆም አስታውቋል፡፡
ቀይ መስቀል ማኅበር ለተጎጂዎች ገንዘብ ማሰባሰብ ጀምሯል፡፡ ኮሚሽነር ምትኩ ይህንን የዜጎች እንቅስቃሴ የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑን ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አቅጣጫዎች የድርቁን ተፅዕኖ ለመቆጣጠር እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ኮሚሽነር ምትኩ ጨምረው እንደገለጹት፣ መንግሥት በቅርቡ 14 ቢሊዮን ብር በጀት ያፀደቀ በመሆኑና ዕርዳታ ሰጪዎችም ድጋፍ ማድረግ በመጀመራቸው፣ መንግሥት የጀመራቸውን ፕሮጀክቶች ሳይታጠፉ እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡