Thursday, February 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 80 ሚሊዮን ዶላር ያወጣበት የአቪዬሽን አካዳሚ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ተጠናቀቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ80 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ላለፉት አምስት ዓመት ሲያካሂድ የቆየውን የአቪዬሽን አካዳሚ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አጠናቀቀ፡፡

ከአየር መንገዱ ፈጣን ዕድገት ጋር ተያይዞ እያደገ የመጣውን የሰው ኃይል ፍላጐት ለማሟላት፣ አየር መንገዱ የተጠቀሰውን ገንዘብ ወጪ በማድረግ ሰፊ የማስፋፊያ ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ የተለያዩ ሕንፃዎች ግንባታ በማካተት በርካታ የመማሪያ ክፍሎች፣ የተማሪዎች መኝታ ክፍሎች፣ ቤተ መጻሕፍት፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል፣ የጥገና ማዕከላት፣ የበረራ አስተናጋጆች ማሠልጠኛ ካፊቴሪያዎች የያዘ ነው፡፡

የአቪዬሽን አካዳሚው የአብራሪዎች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት፣ የአውሮፕላን ጥገና ቴክኒሺያኖች፣ የበረራ አስተናጋጆችና የማርኬቲንግ ባለሙያዎች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤቶች አሉት፡፡ በማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ከሕንፃዎች ግንባታ በተጨማሪ የአብራሪዎች ማሠልጠኛ ዘመናዊ ምሥለ በረራዎች፣ የበረራ አስተናጋጆች ማሠልጠኛ የመዋኛ ገንዳና የአደጋ ጊዜ መውጫ ልምምድ የሚካሄድባቸው የአውሮፕላን ሞዴሎች ተገዝተው ተገጥመዋል፡፡ ከእነዚህም በተጨማሪ የተለያዩ በኮምፒዩተር የሚታገዙ የማሠልጠኛ መሣሪያዎችና ማሽኞች ተሟልተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቪዬሽን አካዳሚ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል አሰፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አካዳሚው ቀደም ሲል በዓመት 200 ተማሪዎች ተቀብሎ የማስተማር አቅም የነበረው ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በዓመት 1,500 ተማሪዎች የመቀበል አቅም ገንብቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2025 በዓመት 4,000 የአቪዬሽን ባለሙያዎች የማሠልጠን አቅም እንደሚኖረው አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡

‹‹በአፍሪካ ትልቁንና ዘመናዊ የአቪዬሽን ትምህርት ቤት ገንብተናል፤›› ያሉት አቶ ሳሙኤል፣ ከአየር መንገዱ ፍላጎት አልፎ ለሌሎች አየር መንገዶች የሚሠሩ ብቃት ያላቸው የአቪዬሽን ባለሙያዎች ማሠልጠን እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

‹‹ከዚህ በኋላ ከሌሎች አገሮች የሚመጡ ተማሪዎችን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ የአቪዬሽን አካዳሚውን አትራፊ ማድረግ ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡

የአቪዬሽን አካዳሚው ከተመሠረተ 60 ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን፣ 11,000 ባለሙያዎች አስመርቋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 2,000 የሚሆኑት ከ40 አገሮች (አፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅ) የመጡ ሠልጣኞች ይገኙበታል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአቪዬሽን አካዳሚው ማስፋፊያ ካወጣው 80 ሚሊዮን ዶላር፣ 50 ሚሊዮን ዶላር ያህሉ ከፈረንሣይ ልማት ባንክ በብድር የተገኘ ነው፡፡

የአቪዬሽን አካዳሚው ማስፋፊያ ፕሮጀክት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በተገኙበት ጥር 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ይመረቃል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቪዬሽን አካዳሚ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን፣ በዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት፣ በዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር፣ በአሜሪካ አቪዬሽን አስተዳደር፣ በአውሮፓ አቪዬሽን ደኅንነት ኤጀንሲና በአፍሪካ አየር መንገዶች ማኅበር ዕውቅና ተሰጥቶታል፡፡      

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች