Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበአገሪቱ የዘረመል ሀብቶች ላይ ምዝበራ እንደሚፈጸም ጥርጣሬ ተፈጠረ

በአገሪቱ የዘረመል ሀብቶች ላይ ምዝበራ እንደሚፈጸም ጥርጣሬ ተፈጠረ

ቀን:

– ተቋሙ ስለጉዳዩ የማውቀው ነገር የለም ብሏል

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተለያዩ አገሮች የባለቤትነት መብት የኢትዮጵያ ብቻ የሆኑ የዘረመል ሀብቶች እየተመዘበሩ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ለዚህም በአዲስ አበባ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት (International Livestock Research Institution) በጥራጥሬና በሥጋት እየተመለከተው መሆኑን ገልጿል፡፡ ለዚህም ልዩ ኮሚቴ በማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን እንዲሰጥ ላቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፣ ስለጉዳዩ ምንም የሚያውቀው እንደሌለው ገልጿል፡፡

- Advertisement -

ሚኒስትሩ አቶ ዓብይ አህመድ ረቡዕ ጥር 18  ቀን 2008 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሳይንስና መገናኛ ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፣ በኢንስቲትዩቱ ላይ ‹‹የመጨረሻ ድምዳሜ›› ላይ ባይደረስም፣ እያከናወነ ያለውን ድርጊት ለመመርመር ልዩ ኮሜቴ ተቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን  አስረድተዋል፡፡

‹‹የአገራችንን የተለያዩ የዘረመል ሀብቶች ባለቤትነት ለማረጋገጥ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያካሄድን ነው፡፡ እነዚህ ሀብቶች በተለያዩ መንገዶች እንዴት ማስጠበቅ እንዳለበን በኮሚቴ ደረጃ በተዋቀረ እንቅስቃሴ ምን ማድረግ እንዳለብንም እያየን ነው፤›› ሲሉ ከቋሚ ኮሜቴው አባላት የኢትዮጵያ የዘረመል ሀብቶችን ባለቤትነት ስለማስጠበቅ ለተነሳላቸው ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል፡፡ የአገሪቱ የዘረመል ሀብቶች እንዴት በውጭ አገሮችና ድርጅቶች እንደሚመዘበሩ በሰጡት ማብራርያ፣ ‹‹እዚሁ በመዲናችን አዲስ አበባ ሲኤምሲ አካባቢ ኢልሪ የሚባል ትልቅ ዓለም አቀፍ የምርምር ተቋም አለ፤›› ሲሉ ሚኒስቴሩ ማብራርያቸውን ይጀምራሉ፡፡

‹‹ይህንን ድርጅት ሄዳችሁ ብትመለከቱ ብዙ ጉድ ታያላችሁ፡፡ ለምሳሌ ኢሊሪ ያለው ጂን ባንክ (የዘረመል ባንክ) በዓለም ከአንድ እስከ አሥር ያሉትን ደረጃ ይይዛል፡፡ በጣም ትልቅ የዘረመል ባንክ ቢኖረውም እኛ ግን አናውቀውም፡፡ በዚህ ባንክ ውስጥ እያንዳንዱ የዘረመል ዓይነት ይጠናል፡፡ ከተጠና በኋላም ብራዚል ‘የኔ ጠንካራ ቡና’ ትላለች ስትፈልግ ከኢትዮጵያ ወስዳ፡፡ ጀርመንም ሲፈልግ እንደዚሁ ይላል፤›› በማለት የኢትዮጵያ የዘረመል ሀብቶች እንዴት ከአገር እንደሚወጡ አቶ ዓብይ ጠቁመዋል፡፡

‹‹የአገሪቱ የዘረመል ሀብት በእውቀት አይመራም፡፡ እነሱ ሲፈልጉ ለኢትዮጵያውያን የዶክትሬት ዲግሪ የሚያስገኝላቸውን ስኮላርሺፕ እንሰጣለን እያሉ፣ አሥር ብርና ሃያ ብር እየሰጡ ከባዱን ሥራ ያሠሯቸዋል፡፡ ከዚያም እውቀቱን ከኛው ሰዎች በመውሰድ ይጠቀማሉ፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በተጨማሪም ወደ ኢንስቲትዩቱ የሚመጡ የውጭ ዜጎች እንዴት እንደሚገቡና እንደሚወጡ ስለማይታወቅ፣ የአገራችን ሀብቶች ለማስጠበቅ የራሳችንን አቅምና ዕውቀት በማጠናከር ልንሠራ ይገባል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡  

ኢንስቲትዩቱ ዓለም አቀፍ በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ሊቆጣጠረው ስለማይችል ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥናት እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡ ለመንግሥት በቀጥታ ስለሚያከናውናቸው ተግባራት ሪፖርት እንደማያደርግ፣ በአግባቡ ሥራውን የማያከናውን ከሆነ ደግሞ የአገርን ሀብት ላልተገባ ነገር ያውላል የሚል ሥጋት ሚኒስቴሩ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ለመንግሥትም ልዩ ኮሚቴ ማቋቋም ማስፈለጉን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ይህ ልዩ ኮሚቴም በሒደት አቅሙን እያጠናከረ በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በመንቀሳቀስ ያሉትን የዘረመል ዓይነቶች በማጥናት፣ በመመዝገብና እንዴት ማስጠበቅ እንደሚቻል ጥናት ሊያቀርብ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ድርጊቱን ይበልጥ ለማወቅ ደግሞ ምርመራ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ጂሚ ስሚዝ ለሪፖርተር በላኩት የኢሜል ምላሽ፣ ‹‹አለ ስለተባው ጉዳይ ፈጽሞ አናውቅም፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ከዋና ዳይሬክተሩ የኢሜል ምላሽ በፊት ቀደም ብለው የአስተዳደር ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት ጋኤል አማሬ በጻፉት ደብዳቤ፣ ኢንስቲትዩቱ የዘረመል ባንኩን አቋቁሞ የሚያከናወናቸውን የጥናትና ምርምር ተግባራትም ሆነ የምርምር ውጤቶችን ወደተለያዩ አገሮች የሚያሰራጨው፣ በዓለም አቀፍ ሕጎች መሠረት መሆኑንና ኢትዮጵያም በተመሳሳይ የዚሁ ዓለም አቀፍ ስምምነት ፈራሚ በመሆኗ የተለየ ነገር ኢንስቲትዩቱ እያደረገ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ሪፖርቱን ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት፣ መሥሪያ ቤታቸው ያከናወናቸውን ተግባራት፣ ስኬትና ተግዳሮቶች አብራርተዋል፡፡ በአጠቃላይ የሳይንስ ሥራ በኢትዮጵያ የልማት ጉዳይ ስላበረከተው አስተዋጽኦም ያልተጠበቀ መልስ ሰጥተዋል፡፡

በተለይ አገሪቱ ሳይንስን ለኢኮኖሚው ዕድገትና ትውልድን በዕውቀትና በቴክኖሎጂ ለመቅረፅ መጠቀም የቻለችው ‹‹ዜሮ ሊባል በሚችል ደረጃ ነው›› ሲሉ መልሰዋል፡፡

ነገር ግን ሳይንስን በአግባቡ መጠቀመ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑና ጥሩ ውጤት ያስገኙም መኖራቸውን ሚኒስትሩ በዝርዝር ከገለጹ በኋላ፣ ሳይንስን በአግባቡ የበለጠ ለመጠቀም በሁለት ዓመት ውስጥ ሚኒስቴሩ የራሱን ሳተላይት ቻናል ያቋቁማል ብለዋል፡፡ ሳይንስ ነክ የሆኑ ፕሮግራሞችን ብቻ የሚያስተላልፍ የ24 ሰዓት ቴሌቪዥን እንደሚከፍትም አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...