Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የማኑፋክቸሪንግ ወጪ ንግድ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ለውጥ አለማምጣቱ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተጠናቀቀው ግማሽ ዓመት በማኑፋክቸሪንግ ወጪ ንግድ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በ15 በመቶ ለማሳደግ ቢታቀድም፣ አፈጻጸሙ ዜሮ መሆኑ ተጠቆመ፡፡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ በ0.3 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱ ታውቋል፡፡

ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን ወጪ ንግድ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በ15 በመቶ ለማሳደግ ያቀደው፣ የፋብሪካዎች የማምረት አቅም 75 በመቶ ይደርሳል በሚል ነበር፡፡ ነገር ግን የፋብሪካዎች የማምረት አቅም ከ58 በመቶ መብለጥ ባለመቻሉ የሥራ አፈጻጸሙ ደካማ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ አነስተኛ በመሆኑ መንግሥት  ከሌሎች የፋይናንስ ምንጮች የውጭ ምንዛሪ በማቅረብ የገበያውን ፍላጎት ለማሟላት እየሞከረ ነው ተብሏል፡፡ ነገር ግን ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ወደ ኢንቨስትመንት የገቡ ኢንቨስተሮች የውጭ ምንዛሪ እጥረት በዚሁ ከቀጠለ አስቸጋሪ ሁኔታ ስለሚፈጥርባቸው ሥጋት እንደገባቸው ተናግረዋል፡፡

ጥር 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸሙን በተመለከተ ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ተዋናዮች ጋር በመከረበት ስብሰባ እንደተገለጸው፣ ለዕቅድ አፈጻጸሙ ደካማ መሆን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ፣ የጥሬ ዕቃዎች አቅርቦት እጥረት፣ የውጭ ምንዛሪ ችግርና የተመረቱ ምርቶች የጥራት ደረጃ ዝቅ ያለ መሆንና የገበያ ዕጦት ተጠቃሽ ምክንያቶች ሆነው ቀርበዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የዕቅድና የበጀት ጥናት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ ህሉፍ ለውይይት መነሻ ባቀረቡት ጽሑፍ፣ ፋብሪካዎች የማምረት አቅማቸውን ሙሉ በሙሉ እንዳይጠቀሙ ካደረጓቸው ምክንያቶች መካከል የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ 28 በመቶ፣ የገበያ ማጣት 27 በመቶ፣ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር 22 በመቶ፣ የሥራ ማስኬጃ በጀት እጥረት ስምንት በመቶ ድርሻ እንዳላቸው ተጠቅሷል፡፡

የማኑፋክቸሪነግ ዘርፍ መዳከም ያሳሰባቸው ባለሀብቶች መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ መሠረታዊ ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

የሉና ኤክስፖርት ስላውተር ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋ ልደት ሐጎስ የአገሪቱ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በ15 በመቶ ያድጋል ተብሎ በ0.3 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱ አደገኛ አዝማሚያ መሆኑን በመጥቀስ፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይኼንን አካሄድ ለማስተካከል ሊወሰድ ያሰበው ዕርምጃ እንዳለ ጠይቀዋል፡፡

ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ አስቸጋሪ ስለሚሆን ሚኒስቴሩ ከብሔራዊ ባንክ ጋር ሆኖ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት መመርመር እንዳለበት አቶ ተስፋ ልደት ገልጸው፣ በእሳቸው በኩል ግን ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት ዘርፉን ለማስፋፋት ከመጣር ይልቅ፣ ለመቆጣጠር የሚሠሩ በመሆኑ ጉዳዩ በጥልቀት ሊጤን እንደሚገባው  ተናግረዋል፡፡

መንግሥት በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በአማካይ በ21.9 በመቶ እንደሚያደርግ ታቅዷል፡፡ በዚህ መሠረት በ2012 ዓ.ም. ከዘርፉ 3.6 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል፡፡

በዚህ ግዙፍ ዕቅድ መነሻ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ወጪ ንግድ በተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ 806 ሚሊዮን ዶላር፣ በስድስት ወራት ደግሞ 288.1 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል፡፡ ነገር ግን በስድስት ወራት ውስጥ የተገኘው 190.9 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ መንግሥት ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሚጠብቃቸው የሚመረቱ ምርቶች በሙሉ ወደ ውጭ ተልከው የውጭ ምንዛሪ እንዲያመጡ ቢሆንም፣ ባለፉት ስድስት ወራት ይህ አስተሳሰብ ፈተና እንደገጠመው ታይቷል፡፡

አቶ መንግሥቱ ህሉፍ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃን ጠቅሰው እንዳሉት፣ ኩባንያዎች 93 በመቶ ገቢያቸውን ከአገር ውስጥ ሽያጭ በማግኘታቸው ሰባት በመቶ ብቻ የሚሆነውን ገቢ ከውጭ ገበያ አግኝተዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው መንግሥት ይኼንን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ለማስቀረት ዘላቂ መፍትሔ ተደርጎ የተቀመጠው ፋብሪካዎችን ኢንዱስትሪ ፓርክና ክላስተሮች ውስጥ በማሰባሰብ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ ኢንዱስትሪዎች የተለየ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር እንዲያገኙ፣ ከአሥር ሜጋ ዋት በላይ ኤሌክትሪክ የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች የራሳቸው ሰብስቴሽን እንዲኖራቸው አቅጣጫ መሰጠቱ ተገልጿል፡፡

‹‹የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግም በዋናነት የፋብሪካ ውጤቶች በብዛትና በጥራት ወደ ውጭ መላክ አስፈላጊ ነው፤›› በማለት የተናገሩት አቶ አህመድ፣ ‹‹በኃይል መቆራረጡ ምክንያት የፋብሪካ ምርቶች ጥራት የሚፈለገው ደረጃ ላይ ባለመድረሱ ምርቶቹ ለአገር ውስጥ ገበያ ሊቀርቡ ችለዋል፤›› ብለዋል፡፡

እነዚህ ችግሮች ለመፍታት መንግሥት ማነቆዎቹን ለይቶ እየሠራ መሆኑን አቶ አህመድ ጨምረው ገልጸዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች