Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹አገሬን ስናፍቅ ሙዚቃ መድኃኒቴ ነው›› ድምፃዊት አቢ ላቀው

‹‹አገሬን ስናፍቅ ሙዚቃ መድኃኒቴ ነው›› ድምፃዊት አቢ ላቀው

ቀን:

‹‹ደስታ›› እና ‹‹ማን አለ›› በአጭር ጊዜ ዕውቅናን ካገኙ ዘፈኖቿ መካከል ናቸው፡፡ ጎንደር ውስጥ የተወለደችው ድምፃዊት አቢ ላቀው ወደ አሜሪካ ያቀናችው በልጅነቷ ነበር፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች እንደ መዝናኛ ሙዚቃ ጀመረች፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሙዚቃ ፍቅሯ በርትቶ ሙሉ በሙሉ ወደ ሙዚቃ ገባች፡፡ አሁንም ኑሮዋን በአሜሪካ፣ ዳላስ ያደረገችው ድምፃዊቷ በቅርቡ የለቀቀችው ነጠላ ዜማ ‹‹የኔ አበሻ›› በዓመታዊው የሙዚቃ ውድድር ኮራ ዕጩ አድርጓታል፡፡ ስለአጠቃላይ የሙዚቃ ሕይወቷና ከመላው አፍሪካ የተውጣጡ ሙዚቀኞች ስለሚሳተፉበት የኮራ ውድድር ከምሕረተሥላሴ መኮንን በኢሜይል ለተላኩላት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥታለች፡፡

ሪፖርተር፡- በኮራ ውድድር ላይ በቤስት ትራዲሽናል ፊሜል አርቲስት (ምርጥ የባህል ሴት አርቲስት) ዘርፍ የታጨሽው እንዴት ነበር?

አቢ፡- ለአዲሱ ነጠላ ዜማዬ ‹‹የኔ አበሻ›› ቪዲዮ ክሊፕ የሠራሁት ባለፈው ሰኔ ሲሆን፣ በዩቲዩብ ቻናል ተለቆ ነበር፡፡ ከስድስት ወራት በኋላ የኮራ አዘጋጆች የቤስት ትራዲሽናል ፊሜል አርቲስት ኦፍ አፍሪካ ዕጩ መሆኔን አሳወቁኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ፌስቡክ ገጽሽ ላይ ስለ ውድድሩ የተገለጹ መረጃዎች አሉ፡፡ ከፌስቡክ በተጨማሪ የምረጡኝ ቅስቀሳ እያደረግሽ ያለሽበት መንገድ አለ?

አቢ፡- በአሁኑ ወቅት ሕዝቡን ስለ ውድድሩ ለማሳወቅና እንዲመርጥ ለመቀስቀስ እየተጠቀምን ያለነው እንደ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራምና ትዊተር ያሉ የማኅበረሰብ ድረገጾችን ነው፡፡ በሚዲያው በኩል የቻልነውን ሕዝብ መድረስ እንድንችል ማኔጂንግ ፓርትነሬ (አጋሬ) ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ነበር፡፡ የቅስቀሳው ዋነኛ አካል ሕዝቡ መምረጥ እንዲችል ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡ መምረጥ የሚፈልጉ “KORA 74” የሚል ጽሑፍ በ+248984000 ላይ መላክ ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ኮራ አፍሪካ ውስጥ ከሚታወቁ የሙዚቃ ውድድሮች አንዱ ነው፡፡ በዘንድሮው ውድድር ከኢትዮጵያ የታጫችሁት አንቺና ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ናችሁ፡፡ በውድድሩ መካተትሽ ምን ዓይነት ስሜት ፈጥሮብሻል?

አቢ፡- ለውድድሩ በመታጨቴ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ከኢትዮጵያ ሁለት ድምፃውያን በሁለት የተለያዩ ዘርፎች በመታጨታቸውም ደስ ብሎኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በምትወዳደሪበት ዘርፍ ኤርትራዊት ድምፃዊትን ሻም ጌሹ (‹‹ጎተና ህድሞ›› በሚል ዜማዋ) ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ አርቲስቶች አሉ፡፡ ተፎካካሪዎችሽን እንዴት አገኘሻቸው?

አቢ፡- ዛሬ ያለሁበት ቦታ እንድደርስ የረዳኝን እግዚአብሔር አመሰግናለሁ፡፡ ተወዳዳሪዎቹ በአጠቃላይ ችሎታ ያላቸው አርቲስቶች ናቸው፡፡ ጉዳዩ ማን የተሻለ ነው የሚል አይደለም፡፡ ዋናው ነገር የምናገኘው ድጋፍ ስለሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉም ይሁን ከአገራችን ውጪ ያሉ አድናቂዎቼ ድምፅ ሰጥተው እንደማሸንፍ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከውድድሩ ምን ትጠብቂያለሽ? በውድድሩ መካፈልሽ ላንቺ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሙዚቃ በአጠቃላይ ምን ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለሽ ታስቢያለሽ?

አቢ፡- እንደ ሙዚቀኛ በዚህ ውድድር መታጨት ታላቅ ዕድል ነው፡፡ ውድድሩ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ያስተዋውቃል ብዬ እጠብቃለሁ፡፡ ከተለያዩ የአፍሪካ አርቲስቶችና ፕሮዲውሰሮች ጋር በጥምረት ለመሥራትም ዕድሉን ይፈጥርኛል፡፡ ትልቁ ነገር በቀጣይ በርካታ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች በተለያየ ዘርፍ ይታጫሉ የሚለው ተስፋ ነው፡፡ በየዓመቱ በተለያየ ዘርፍ መታጨት የሚችሉ ኢትዮጵያ ውስጥና ከኢትዮጵያ ውጪም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ የእኛ መታጨት ወጣት ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች በራሳቸው መተማመን ማንኛውንም ነገር ማድረግ እንደሚችሉ እንደሚያመላክታቸው አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ራስሽን እንደ ሙዚቀኛ የምትገልጪው በምን መንገድ ነው? የምታተኩሪበት ርዕሰ ጉዳይ ወይም ማስተላለፍ የምትፈልጊው መልዕክትስ እንዴት ያለ ነው?

አቢ፡- እንደ ሙዚቀኛ የራሴን ግጥምና ዜማ ማዘጋጀት እወዳለሁ፡፡ ‹‹የኔ አበሻ›› ከእነዚህ አንዱ ነው፡፡ ራሴን ልገልጽበትና የማምንበትን መልዕክት ላስተላልፍበት ችያለሁ፡፡ በሙዚቃዬ ስለ ሰላም፣ ስለፍቅርና ጥልቅ ባህላዊ እሴቶቻችንም እንዳይዘነጉ የሚያደርጉ መልዕክቶችን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ፊልም ሠርተሽ እንደነበር ይታወሳል? ተሞክሮው ምን ይመስላል?

አቢ፡- የመጀመሪያ ፊልሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ስሠራ የሚያስገርም ተሞክሮ ነበረኝ፡፡ ፊልሙ ‹‹እየሩስ›› የተሰኘ ሲሆን፣ የተሠራው በታላቁ ባለሙያ ጌታቸው አያልቄ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ሙዚቃን ከኢትዮጵያ ውጪ መሥራት ፈታኝ ነው?

አቢ፡- አንዳንዴ ፈታኝ ቢሆንም በጣም እንድሠራ የሚያነሳሳኝ ነገርም ሆኖ አገኘዋለሁ፡፡ ፈታኝ የሚሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አዳዲስ እንዲሁም ታላላቅ ፕሮዲውሰሮችና ሙዚቀኞችን የማግኘት ዕድሉ ጠባብ ስለሆነ ነው፡፡ አነሳሽ ሆኖ የማገኘው ደግሞ ከተለያየ የዓለም ክፍል ከተውጣጡ ሙዚቀኞች ጋር አብሮ የመሥራት ዕድሉን ስለሚከፍት ነው፡፡ ይህ እንደ አርቲስት ተሞክሮዬን ያሰፋልኛል፡፡

ሪፖርተር፡- አዲስ አልበም እየሠራሽ ነው? ምን አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል?

አቢ፡- አልበሜ በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ በቅርቡ ይለቀቃል፡፡ ከተለያዩ ፕሮዲውሰሮች ጋር ነው የሠራሁት፡፡ ከአዲሱ አልበሜ ላይ የሁለተኛ ነጠላ ዜማዬን ‹‹በፍቅር እስክስታ›› ቪዲዮ ለቅቄያለሁ፡፡ ሙዚቃው የተጻፈው በእውቁ አብርሃም ወልዴ ሲሆን፣ ሙዚቃውን ያቀናበረው ፕሮዲውሰሬና ወንድሜ ሚሊዮን ላቀው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በትውልድ ቀዬሽ ጎንደር የምታካሂጃቸው የበጎ አድራጎት ሥራዎች አሉ፡፡ በዚህ ረገድ ቀጣይ ዕቅድ አለሽ?

አቢ፡- ጥቂት የበጎ አድራጎት ሥራዎችን በትውልድ አገሬና እዚህ አሜሪካ ውስጥም አካሂዳለሁ፡፡ ህልሜ በምችለው መጠን ዕርዳታ የሚሹ ሰዎችን መደገፍ ነው፡፡ ግቤ የብዙ ሰዎችን ሕይወት መለወጥ መቻል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አሜሪካ ውስጥ ከተለያዩ ድምጻውያን ጋር በመጣመር የምትሳተፊባቸው ኮንሰርቶችን ከአድናቂዎችሽ ጋር ከምትገናኝባቸው መንገዶች መካከል መጥቀስ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥስ በቂ መንገድ አለኝ ትያለሽ?

አቢ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎች ቱር ለማድረግ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ፕሮሞተሮች ጋር ድርድር ላይ ነን፡፡ እግዚአብሔር ከፈቀደ በቅርቡ ይሳካል፡፡ አገር ውስጥ ሥራዎቼን ማቅረብ ያስደስተኛል፡፡ አገር ውስጥ ካሉ አድናቂዎቼ ጋር ለመገናኘትም ቸኩያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በትርፍ ጊዜሽ ምን ያዝናናሻል?

አቢ፡- ከቤተሰቦቼና ጓደኞቼ ጋር ጊዜዬን ማሳለፍ እወዳለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በሙዚቃው መነሻዬ የምትያቸው ድምፃውያን እነማን ናቸው?

አቢ፡- ብዙ ያነሳሱኝ ሙዚቀኞች አሉ፡፡ በዓለም ላይ ያሉ የተለያዩ አገሮች ሙዚቃዎችን አዳምጣለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ዕቅድ አለሽ ወይስ በአሜሪካ እየኖርሽ ሥራሽን ትቀጥያለሽ?

አቢ፡- በእርግጠኝነት ዕቅዴ ወደ አገሬ መመለስ ነው፡፡ እንደ አገር ያለ ነገር የለም በእግዚአብሔር ፈቃድ በቅርቡ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- አገርሽን ስትናፍቂ ሙዚቃን እንደ መጽናኛ የምትጠቀሚበት መንገድ አለ?

አቢ፡- አገሬን ስናፍቅ ሙዚቃ ሁሌም መድኃኒቴ ነው፡፡ ሙዚቃ ያረጋጋኛል፡፡ ያነሳሳኛል፡፡ ከአገሬ እንዲሁም አጠቃላይ ከሕይወት ጋር ያስተሳስረኛል፡፡ ሙዚቃን የምወደው ለዚሁ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...