Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ጋብርኤል ሙጋቤ መንበራቸውን ለቻድ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቤ ጥር 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባው ጉባኤ አስረክበዋል

ትኩስ ፅሁፎች

የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ የመሪዎች ሊቀመንበር ሆነው እ.ኤ.አ. በ2015 (በ2007/2008 ዓ.ም.) ያገለገሉት የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ጋብርኤል ሙጋቤ መንበራቸውን ለቻድ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቤ ጥር 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባው ጉባኤ አስረክበዋል፡፡ ሙጋቤ የሥልጣን ምልክት መዶሻውን ካስረከቡ በኋላ ‹‹አጠገብዎ የምገኝ በመሆኑ በፈለጉኝ ሰዓት ሊደውሉልኝ ይችላሉ›› ብለዋቸዋል፡፡  

*******************

‹‹እየኖራችሁ አንብቡ እያነበባችሁ ኑሩ!››

ማስታወሻ አንዴ ብቻ አንበውት የመጻሕፍት መደርደሪያ የተባለ “የመጻሕፍት መቃብር” ውስጥ ለዘላለም ቀብረው የሚያስቀምጡት አይደለም፤ ሁሌም ደግመው ደጋግመው የሚያነቡት እንጂ። ምክንያቱም ዘወትር ቢያነቡት ዘወትር አዲስ ነውና። በእኔ አመለካከት ይህ መጽሐፍ የሕይወት ታሪክ ዐብይ ሥራ (ማስተርፒስ) ነው። ስብሐት በዚህ መጽሐፍ ብዙ ያወጋናል። እያንዳንዱ ቃልና ዓረፍተ ነገር ፍጹም ነው–አንዳች የሚጣል የለውም። እስቲ ስብሐት ስለ ንባብ ምን ይላል? –ከሚያነቡ ከእያንዳቸው አስር ሰዎች፣ ሁለቱ የደራሲ ነፍስ አላቸው –ሳያነቡ መጻፍ ራስን ማታለል ነው –እንደ ሰው በዚህ ቀን በዚህ ሰዓት እንገናኛለን አንልም እንጂ ከመጻሕፍት ጋር ቀጠሮ አለን –መጻሕፍት የታተሙት ሁሉም የሰው ዘር እንዲያነባቸው ነው፡፡

በመሀል ደግሞ ዘነበና ስብሐት ሲጨዋወቱ ዘነበ እንዲህ ጠየቀ፦
“አንባብያንን ለማበራከት ምን መደረግ አለበት?”
“ለምንድነው ማበራከት የሚያስፈልገው?” ስብሐት ተቆጣ።
“ደራሲው ጎበዝ ከሆነ እራሱ ነው አንባቢዎችን የሚፈጥረው። ደግሞም ዋናው ማንበብ አይደለም፤ መኖር ነው”
እየኖራችሁ አንብቡ፤ እያነበባችሁ ኑሩ!

***********

ቭላድሚር ፑቲን አንጄላ ሜርክልን በውሻ አላስፈራራሁም አሉ

በወቅቱ በሥልጣን ላይ ሁለት ዓመት እንኳ ያልደፈኑት የጀርመኗ መራሔ መንግሥት አንጄላ ሜርክል እ.ኤ.አ. 2007 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቭላድሚር ፑቲን ጋር የተገናኙት በሩሲያው መሪ የበጋ ቤት ነበር፡፡ ፑቲን ከአንጄላ ሜርክል ጋር ውይይት ከሚያደርጉበት ክፍል የተገኙት ትልቅና አስፈሪ ጥቁር ውሻቸውን ይዘው ነበር፡፡ አጋጣሚው ከፍተኛ የውሻ ፍርሃት ላለባቸው ሜርክል አስደንጋጭ ነበር፡፡

በወቅቱ ፑቲን ይህን ያደረጉት ሆን ብለው የጀርመኗን መሪ ለማስደንገጥና ለማሳጣት እንደሆነ ታምኖ ነበር፡፡ መሪዎቹ ንግግር ከሚያደርጉበት ክፍል ውስጥ ትንጎራደድ በነበረችው ውሻ ምክንያት ሜርክል ሙሉ የውይይት ጊዜውን በፍርሃት ሊያሳልፉ የግድ ሆኖ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ሜርክል በውይይቱ ወቅት የተነሷቸው ፎቶግራፎች በሙሉ ምቾት ማጣትና ፍርሃታቸውን የሚያሳዩ ነበሩ፡፡ ይህ ሁኔታ ከተፈጠረ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ፑቲን ከጀርመኑ ቢልድ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነገሩ ሆን ብለው ሜርክልን ለማስፈራራት ያደረጉት አለመሆኑን ‹‹ጥሩ ነገር ላደርግላት ፈልጌ ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን ውሻ እንደምትፈራ እንደማትወድም ስረዳ ይቅርታ ጠይቄያለሁ›› በማለት መናገራቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡

*******************

አሻንጉሊቶችን እንደ አማልክት

የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ የሚያናውጣት ታይላንድ ነዋሪዎች ለችግሮቻቸው እንደ መፍትሔ የወሰዱት በሕፃናት አምሳያ ለተሠሩ አሻንጉሊቶች ጸሎታቸውን ማሰማት ነው፡፡ በሕፃናት መጠን የሚዘጋጁት አሻንጉሊቶቹ ‹‹ሉክ ቴፕ›› ወይም ‹‹ቻይልድ ኤንጅል›› በመባል የሚታወቁ ሲሆን፣ ጥሩ ዕድል እንደሚያመጡ ይታመንባቸዋል፡፡ አሻንጉሊቶቹ በሱቆች እንዲሁም በድረ ገጽ መገበያያ የሚገኙ ሲሆን፣ ነዋሪዎቹ ከሸመቱ በኋላ አሻንጉሊቶቹ ውስጥ አንዳች ጥሩ መንፈስ እንዲገባባቸው ይለማመናሉ፡፡

ታይላንድ ውስጥ መሰል አሻንጉሊቶች መሸጫ ሱቅ ያላቸው የ49 ዓመቷ ማናናያ ቦንሜ ‹‹ኢኮኖሚው ክፉኛ ወድቋል፤ ሁሉም ሰው የሚፅናናበት አንዳች ነገር ይሻል፤›› በማለት ነበር ለሮይተርስ ስሜታቸውን የገለጹት፡፡ ከዚህ ቀደም እሳቸውም በሕፃን አሻንጉሊት ዕርዳታ የሎተሪ ዕጣ እንደወጣላቸው ተናግረዋል፡፡

የአገሪቱ የአዕምሮ ጤና ክፍል ዋና ኃላፊ፣ ነዋሪዎቹ የአዕምሮ ችግር እንደሌለባቸውና ለዓመታት በታይላንዳውያን ሲታመንባቸው የኖሩ አማልክት በውጥረቱ ወቅት የብዙዎች መሸሸጊያ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

በርካታ የአገሪቱ ነዋሪዎች አሻንጉሊቶቹ ሕይወታቸውን እንደለወጡት ሲናገሩ፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፕራዩት ቻንአያ፣ አቅም የሌላቸው ሰዎች አሻንጉሊቶቹን እንዳይገዙ አሳስበዋል፡፡ ከ40 ዶላር እስከ 800 ዶላር የሚያወጡት አሻንጉሊቶች ለአንዳንድ የአገሪቱ ነዋሪዎች ጥሩ ንግድም ሆነዋል፡፡

በሌላ በኩል ታይ ኤርዌይስ አሻንጉሊት ይዘው አውሮፕላን የሚሳፈሩ ሰዎችን እንደሚያስከፍልና ለአሻንጉሊቶቻቸውም ምግብ እንደሚያቀርብ አሳውቋል፡፡ የታይላንድ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በበኩሉ፣ አሻንጉሊቶቹ ለአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ሊውሉ ስለሚችሉ አየር መንገዱን ትኬት መሸጥ እንደሚያስቆም ተመልክቷል፡፡ 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች