Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርስብሰባ ያልፈታቸው የአዲስ አበባ ችግሮች

ስብሰባ ያልፈታቸው የአዲስ አበባ ችግሮች

ቀን:

ከተመሠረተች 125ኛ ዓመት የልደት በዓሏን አክብራ በማግሥቱ ላይ የምትገኘው መዲናችን የኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካም መዲና ነች፡፡

ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆን ነዋሪ በውስጧ አቅፋ የያዘች አዲስ አበባ የውጭ አገር ዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮች፣ የንግድ ሰዎችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች መኖሪያም ጭምር ነች፡፡

አሥራ አራት ዓመት ሙሉ በቁሟ አንቀላፍታ የቆየችና የመሠረተ ልማት እጥረት ሲንጣት የነበረች አዲስ አበባችን ከምርጫ 97 ወዲህ መሻሻሎችንና ለውጦችን አሳይታለች፡፡ ያረጁና ዕድሜ ጠገብ የነበሩ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች እየፈረሱ በዘመን አመጣሹ ኮንዶሚኒየም ቤቶች መተካት ጀምረዋል፡፡ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ፣ ከሰሜን ወደ ደቡብ የተዘረጋው የባቡር መስመር ከተማዋ ወደ ዘመናዊነት ለመሸጋገር ለምታደርገው ጥረት ማሳያዎች ናቸው፡፡

 በአንዳንድ ቦታዎች የኮብልስቶን ንጣፍ በመዘርጋቱ ከተማዋን ውብና ማራኪ እንዲሁም ለትራፊክ የተሳለጠች እንድትሆን አስችሏታል፡፡ በዋና ዋና መስመሮችና አደባባዮች ላይ የሚታዩት የማስዋብ ሥራዎች ይበል የሚያሰኙ ናቸው፡፡

የመንግሥታችን በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎችና አመራሮች ከላይ እስከ ታች በተዘረጋው የመንግሥት አወቃቀር ከተማችንን የመሠረተ ልማት ባለቤት ለማድረግ ሰባቱን ሙሉ ቀን ስብሰባ ላይ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረስኩት ዩኒቨርሲቲ አብረን ተምረን የነበረ አንድ ወዳጄ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ውስጥ ባለ አንድ ወረዳ ውስጥ የድርጅት ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊነት ሆኖ እየሠራና ሰባቱን ቀን ሙሉ ስብሰባ እንደሚውል ከነገረኝ ወዲህ ነው፡፡ ኃላፊ ቦታ ላይ ከመቀመጡ በፊት ከሳምንት ቢያንስ ሁለት ቀን እንገናኝ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን በሦስት ወራት አንዴ እንኳን ለመገናኘት ተቸግረናል፡፡

ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የእሱ ዘወትር ስብሰባ ላይ መሆን ነው፡፡ በዚህም መሠረት አብዛኛው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ያሉ አመራሮችና ኃላፊዎች ሰባቱን ቀን ሙሉ ስብሰባ ላይ ናቸው ወደ ሚል መደምደሚያ ደርሻለሁ፡፡ የእነሱ ስብሰባ የከተማዋ አንገብጋቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እልባት ለመስጠት ለምሳሌ የውኃ፣ የኔትወርክ፣ የቤትና የትራንስፖርት፣ ወዘተ ችግሮችን ለመፍታት ነው የሚል ሌላ ውሳኔ ላይ እንድረስ፡፡ የተባሉት ችግሮች ለዘመናት ፈቀቅ አለማለቃቸው እንዲያውም እየባሰባቸው መምጣታቸው፣ መንግሥትንና ሕዝቡን ያቃረኑ ጉዳዮች ሆነው ይኼው ብዙ ዓመታት አለፉ፡፡

ኢሕአዴግ የሚያካሂዳቸው ልማታዊ እንቅስቃሴዎች በጥናት ላይ የተመሠረቱ ባለመሆናቸውና እነዚህ ልማቶች በፈጠሯቸው ችግሮች የተነሳ ሕዝቡ ቅር የተሰኘ መሆኑን፣ በተለያዩ ሚዲያዎች መስማት አዲስ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይኼንን ለማለት ያስገደዱኝ ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡

የመጀመርያው ጉዳይ ለልማት ተብለው በአንዳንድ ቦታዎች የተቆፈሩ ጉድጓዶች በቶሎ አለመደፈናቸውና ለተለያዩ ግለሰቦች ሞትና የአካል ጉዳት ምክንያት መሆናቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ጊዜ በልደታ ኮንዶሚኒየም አካባቢ ሳይሞላ ከአንድ ዓመት በላይ በሆነው ጉድጓድ አንድ ዓይነ ሥውር ሴት ገብታ ለጉዳት ተዳርጋለች፡፡ ይህንን እኔ ራሴው ምስክር ነኝ፡፡ እነዚህ ጉድጓዶች ለእንደዚህ ዓይነት የአካል ጉዳት ላለባቸው ዜጐቻችን የጉዳት መንስዔ ሲሆኑ ማየት የሚያም ነው፡፡ የተቆፈሩ ጉድጓዶችና ቦዮች በቶሎ ባለመደፈናቸው የተነሳ ብዙ ዜጐቻችን ለሞትና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ከዚህ ጉዳት ባሻገርም የከተማዋን ውበትም ጥላሸት ቀብተውታል፡፡

ሌላውና ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ የአዲስ አበባችን የፅዳትና ውበት አጠባበቅ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ካሉ መንግሥታዊ ተቋማት አንዱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውበትና መናፈሻ ዘላቂ ማረፊያ ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ ነው፡፡ የዚህ ኤጀንሲ ዋና ዓላማ አዲስ አበባችንን ፅዱ፣ ውብ፣ ማራኪና ሳቢ በማድረግ የቆየ ገናናነቷን ማስጠበቅ ቢሆንም፣ እየሠራ ያለው ሥራ ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

በእርግጥ ኤጀንሲው በከተማችን ውስጥ የፅዳት ሠራተኞችን ቀጥሮ የከተማዋን ፅዳት ለማስጠበቅ የሚያደርገው ጥረት ቢኖርም፣ እንቅስቃሴው ዘላቂና በጥናት ላይ የተመሠረተ ባለመሆኑ የችግሩ አሳሳቢነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ለምሳሌ ዘወትር ቅዳሜ በየመኖሪያ ቤቱ እየመጡ ‹‹ቆሻሻ አውጡ›› የሚሉ የፅዳት ሠራተኞች አየር ጤና በተለምዶ ብረት ጫፍ ተብሎ በሚጠራው ሠፈር መምጣት ካቆሙ ሳምንታት አልፈዋል፡፡ በዚህም የተነሳ  አካባቢው የቆሻሻ መናኸሪያ ሆኗል፡፡

ሠፈራቸው ያለው ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳ አንድ ብቻ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ነዋሪዎች ቆሻሻውን በየቦታው ለመጣል ተገደዋል፡፡ በዚህም የተነሳ በተፈጠረው መጥፎ ጠረን ሕፃናትና የዕድሜ ባለፀጋዎች ለተለያዩ በሽታዎች እየተጋለጡ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግሥት መሥሪያ ቤት የታለ? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ እንገደዳለን፡፡ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች በጥናት ላይ የተመረኮዙና ዘላቂነት ባላቸው ሁኔታዎች ያልተመሠረቱ መሆናቸውን እንገነዘባለን፡፡

ይህ መሥሪያ ቤት የመላ አዲስ አበባችንን ውበት ለመጠበቅ የቆሻሻ መጣያ ቅርጫቶችን በአንዳንድ ቦታዎች ያስቀመጠ ቢሆንም፣ የቆሻሻ መጣያ ቅርጫቶች ተገቢ ሥራቸውን እየሠሩ እንዳልሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አንደኛ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ተገቢውን የቁጥጥር ሥርዓት ባለመዘርጋቱ ሲሆን፣ ሁለተኛ ደግሞ የኅብረተሰቡ ንቃተ ህሊና አነስተኛ መሆን ነው፡፡ የኅብረተሰቡ ንቃተ ህሊና አነስተኛ መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች መረዳት እንችላለን፡፡ ከአውቶቡስ ሲወርዱ የያዙትን የጉዞ ትኬት በየቦታው መጣል፣ ፌስታል፣ የሙዝ ልጣጭና ሌሎች ለከተማዋ ፀር የሆኑ ነገሮች በየቦታው ሲጣሉ ማየት እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ከተማችንም እያደረች ወደ ቆሻሻ መናኸሪያነት እየተቀየረች የመጣች ነው የሚመስለው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውበትና መናፈሻ ዘላቂ ማረፊያ ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት አስተማሪና አስገዳጅ አሠራሮች ያሉት ቢሆንም፣ ለኅብረተሰቡ ስለቆሻሻ አወጋገድ ዘዴዎች ሲያስተምርና ሲያሳውቅ ብዙም አይታይም፡፡ የአፍሪካ መዲና በሆነች ከተማ ላይ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ እየወሰደ ያለው ዕርምጃ በጣም አነስተኛ ነው፡፡  

የተለያዩ ሚዲያዎችን በመጠቀም ኅብረሰተሰቡ ቆሻሻ እንዴት ማስወገድ እንዳለበት አያስተምርም፡፡ የሚወሰዱ ሕጋዊ ዕርምጃዎችንም ይፋ አያደርግም፡፡ በዚህ የተነሳ አዲስ አበባችን ለኑሮ ምቹና ማራኪ የመሆን ዕጣ ፈንታዋ ጥያቄ ምልክት ውስጥ እየገባ መጥቷል፡፡

መፍትሔ

ስመ ገናና ከተማችንን ውበት የመጠበቅ ኃላፊነት የሁላችን ቢሆንም፣ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የአንበሳውን ድርሻ ወስዶ ተገቢውን ዕርምጃ መውሰድ  አለበት፡፡ የአዲስ አበባችንን ችግር ሊፈታ ከማይችል የዘወትር ስብሰባ ወጥቶ ዛሬውኑ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመግባት  ቁርጠኛ መሆን ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ቁርጠኛ ሆኖ ወደ ሥራና ለውጥ ሲገባ ሕዝቡ ከጎኑ ይሠለፋል፡፡ ኃላፊዎችና ተሿሚዎች ከቻይና በሚመጣላቸው ተሸከርካሪ ወንበር ላይ ተቀምጠው እየተንፈላሰሱ፣ አዲስ አበባችንን የተለያዩ ችግሮች መፍለቂያና መናኸሪያ እንድትሆን ከመፍቀድ  ወጥተው ቅድሚያ አካፋና ዶማ ይዘው ስለ አዲስ አበባ ውበት አጠባበቅና ሌሎች ችግሮች ለሕዝባቸው ትምህርት ይስጡ፡፡ ያኔ ሰፊው ሕዝብ ከነሱ ጎን ይሠለፋል፡፡ ሕዝቡም የእነሱ የኋላ ደጀን ይሆናል፡፡ ያኔ የተቀመጡበት ወንበር የበለጠ ምቾት ይሰጣቸዋል፡፡ አዲስ አበባችንም ሌላኛዋ ፓሪስ ሆና የቱሪስቶች ዓይን ማረፊያ ትሆናለች፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡  

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...