Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አባላት የተራበው የሐዋሳ ንግድ ምክር ቤትና አከራካሪው ምርጫ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ከሚደረግባቸውና በማደግ ላይ ካሉ የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል የደቡብ ክልል ርዕሰ ከተማዋ ሐዋሳ አንድዋ ነች፡፡ የከተማዋ አስተዳደር መረጃ እንደሚያመለክተው በሐዋሳ ከ14,700 በላይ ፍቃድ ያላቸው ነጋዴዎች አሉ፡፡ በዕድገት ላይ የምትገኘው የሐዋሳ ከተማ የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አሁንም እያደገ ሲሆን፣ ወደፊትም ይህ ዕድገት ይቀጥላል ተብሎ ይታመናል፡፡

ከተማዋ በተለያዩ ንግድና ኢንቨስትመንቶች ላይ የሚሳተፉ የንግዱ ኅብረተሰብ አባላት ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ቢሆንም፣ የንግድ ኅብረተሰቡን የሚወክለው የከተማዋ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሥር በአባልነት የተመዘገቡት ግን አንድ አሥረኛ እንኳን አይሞሉም፡፡

ከሐዋሳ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተገኘው መረጃም ይህንኑ የሚያመለክት ነው፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ ቀደም ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ደግሞ፣ ከሁለትና ሦስት ዓመታት በፊት በንግድ ምክር ቤቱ በአባልነት ታቅፈው ከነበሩ ነጋዴዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ለቀዋል፡፡ ከ1200 በላይ አባላት የነበሩት የሐዋሳ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ውስጥ በአሁኑ ወቅት በአባልነት የተመዘገቡት 456 ብቻ መሆናቸው ባለፈው ቅዳሜ ንግድ ምክር ቤቱ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ላይ ተገልጿል፡፡ ከዚህ ውስጥ 270ዎቹ ብቻ በትክክል የአባልነታቸውን የሚከፍሉ መሆናቸውንም ከቀረበው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ ቀድሞ ከ1200 በላይ አባላት አልነበሩትም የሚል መከራከሪያም የሚያነሱ አሉ፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ንግድ ምክር ቤቱ ያሉት አባላት በከተማ ውስጥ ከሚገኙ የንግድ ኅብረተሰብ አባላት ውስጥ ከ14,200 በላይ የሚሆኑትን ያላሳተፈ መሆኑን ያሳየ ሆኗል፡፡

አባልነት በፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ቢሆንም የሐዋሳ ንግድ ምክር ቤት አባላቱን ከመጨመር ይልቅ እየቀነሰ መምጣቱ ለምን? የሚል ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ አባላትን ለማበራከት የሠራው ሥራ ዝቅተኛ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡  

አዲሱ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ሚልኪያስ አንዴቦ፣ የአባላት ቁጥር አነስተኛ ስለመሆኑ ይስማማሉ፡፡ ነገር ግን ከዚህ ቀደም ንግድ ምክር ቤቱ 1200 አባላት አሉት ተብሎ የቀረበውን ሲፈተሽ፣ በትክክል የተገኙትና የተመዘገቡት 456 ብቻ ናቸው ብለዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ ቀድሞም ቢሆን በሺሕ የሚቆጠር አባላት አልነበሩትም፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ አሁን ግን አባላትን ለማሳደግ አዲሱ ቦርድ ይሠራል ብለዋል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ ባለፈው ቅዳሜ ጥር 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ አዲስ የአመራር አባላትን የመረጠው ከ200 በታች በሆኑ አባላቱ ነው፡፡ ምርጫው ግን አንዳንድ ክፍተቶች እንዳሉበት ያነጋገርናቸው የጠቅላላ ጉባዔው ተሳታፊዎችና የምክር ቤቱ አባላት ይገልጻሉ፡፡

የምርጫ ሒደቱ ክፍተት ነበረበት የሚል አስተያየት እንዲሰጥበት ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ ባሰናዳውና በዕለቱ እንዲፀድቅ በቀረበው የንግድ ምክር ቤቱ አሠራርና  የምርጫ ደንብ መሠረት መካሄድ ያለመቻሉ አንዱ ነው፡፡  

በተሰናባቹ ቦርድ የተዘጋጀው የምርጫ ማስፈጸሚያ ደንብ በዕለቱ ተግባራዊ ባለመሆኑ፣ ምርጫው ዲሞክራሲያዊ እንዳይሆን አድርጐታል ተብሏል፡፡ በተሰናዳው ደንብ መሠረት ምርጫው በካርድ ድምፅ ሊሰጥ ሲገባው፣ እጅ በማንሳት እንዲካሄድ መደረጉም አግባብ አልነበረም ሲሉ የምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል፡፡

ይህ አሠራር የምርጫውን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው ብለው የሚከራከሩት እነዚህ ወገኖች፣ የምርጫው ውጤትም በቡድን የተሠራ ሥራ መኖሩን ያመላክታል ይላሉ፡፡

በዕለቱ መፅደቅ ነበረበት የተባለው ደንብ ቢያከራክርም፣ ምርጫው ተደርጐ አሥራ አንድ አባላት ያሉት ቦርድ ተመርጧል፡፡ ከተመረጡት 11 አባላት ውስጥ ዘጠኙ አዲስ ሲሆኑ፣ ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ሦስት አባላት ደግሞ በቀድሞ ቦርድ ውስጥ የነበሩ ናቸው ተብሏል፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለጻ የምርጫ ሒደቱ ክፍተት ነበረበት፡፡ በተለይ የንግድ ምክር ቤቱ የመተዳደሪያ ደንብ ተጥሷል የሚል እምነት አላቸው፡፡

በንግድ ምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንበ ውስጥ አንድ የቦርድ አባል ከሁለት ምርጫ ዘመን በላይ መሥራት እንደሌለበት የሚያመለክት ቢሆንም፣ በቅዳሜው ምርጫ ግን  ፕሬዚዳንት በመሆን የተመረጡት ግለሰብ ለሦስተኛ የሥራ ዘመን እንዲመረጡ ዕድል የሰጠ ሆኗል ተብሏል፡፡ ይህ የመተዳደሪያ ደንቡን የጣሰ መሆኑ ቢገለጽም ሊታረም አለመቻሉንም ገልጸዋል፡፡ አሁን የታየው ችግር ደግሞ ቀድሞም ሲንከባለል የመጣ ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የምርጫው ሒደት ትክክል ስለመሆኑ የሚገልጹት ወገኖች ደግሞ፣ አለ የተባለው የምርጫ ደንብ በጠቅላላ ጉባዔው የፀደቀ አይደለም ይላሉ፡፡ ደንቡ ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ቀርቦ በጠቅላላ ጉባዔ ያልፀደቀና በምርጫው ዕለት ለጠቅላላ ጉባዔ የቀረበ በመሆኑ፣ በቅዳሜው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ደንቡን ተፈጻሚ ማድረግ እንዳልተቻለም ተገልጿል፡፡ በዕለቱ የተገኙት የጠቅላላ ጉባዔ አባላትም ምርጫው ከዚህ ደንብ ውጭ እንዲካሄድ በመወሰናቸው የተደረገ እንጂ፣ ደንቡ አያስፈልግም ከሚል በመነሳት እንዳልሆነ የንግድ ምክር ቤቱ አመራሮች ገልጸዋል፡፡

ተሰናባቹ ቦርድ ይህንን ደንብ እንዲወጣ ያስፈለገው በተደጋጋሚ ወደ አመራር የሚመጡ ሰዎችን ለመገደብና አዳዲስ አመራሮችን ለማምጣት ይረዳል በሚል ጭምር ነበር፡፡ ደንቡ አንድ ተመራጭ ከሁለት የምርጫ ዘመን በላይ እንዳይመረጥ የሚገድብ ነበር፡፡ አገር አቀፉ የንግድ ምክር ቤትም በሁሉም ንግድ ምክር ቤቶች ተመሳሳይ ሰዎች እየወጡ በመሆኑ ይህንን ለማስቀረት አንድ ተመራጭ ከሁለት የሥራ ዘመን በላይ እንዳይሠራ የሚገድብ መመርያ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡

አቶ ሚልኪያስ እንደገለጹት፣ ደንቡን እርሳቸው ሲመሩ በቆዩት ቦርድ የረቀቀና በቅዳሜው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንዲፀድቅ የቀረበ ነበር፡፡ ደንቡ እንዲፀድቅም ፍላጐት ነበረን ያሉት አቶ ሚልኪያስ፣ ‹‹ጠቅላላው ጉባዔ ግን ደንቡን አሁን ልናፀድቅ አንችልም በቀጣይ ጉባዔ ይፅደቅ በማለቱ እንዲቀር ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡ ሆኖም ምርጫው በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት የምርጫ ደንብ መሠረት ይካሄድ ተብሎ በዚሁ መሠረት መከናወኑንም አቶ ሚልኪያስ ገልጸዋል፡፡

ለሦስተኛ ጊዜ የተመረጡ አመራሮች አሉ ስለተባለውም አስተያየት፣ ይኸው ደንብ በጠቅላላ ጉባዔ ካለመፅደቁ ጋር በተያያዘ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ንግድ ምክር ቤቱ መረጃ ለሦስተኛ ጊዜ ተመርጠዋል የተባሉት ደግሞ፣ ቀድሞ በቦርድ አባልነት ከዚያም በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩትና በቅዳሜው ምርጫ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት አቶ ሚልኪያስ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በቅዳሜው ጠቅላላ ጉባዔ አቶ ሚልኪያስ በከፍተኛ ድምፅ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡

  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች