Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአሜሪካ ኩባንያዎች ኢንቨስትመንት ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱ ተጠቆመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደ ጥናት መሠረት የአሜሪካ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የኢንቨስትመንትና የንግድ መስኮች፣ ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ማድረጋቸው ተገለጸ፡፡

የኧርነስት ኤንድ ያንግ ማኔጂንግ ፓርትነር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ይህን ያስታወቁት ለአሥረኛ ጊዜ የአፍሪካ ኮርፖሬት ምክር ቤት የተባለ መቀመጫውን አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው ድርጅት፣ በአዲስ አበባ እያካሄደው ባለው የአሜሪካና አፍሪካ የንግድ መድረክ ስብሰባ ወቅት ነው፡፡

የአሜሪካና የአፍሪካ የንግድ መድረክ ከጥር 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ሲሆን፣ መድረኩን በይፋ የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ናቸው፡፡ በመክፈቻ ንግግራቸው የአሜሪካ ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን በአኅጉሪቱ እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከአሜሪካ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የኢንቨስትመንት ምኅዳሩን የተመቻቸ ለማድረግ ቃል የገቡ ሲሆን፣ በተለይም የቴሌኮም አገልግሎቱን እንደምታሻሽል ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የአሜሪካ ባለሀብቶች ከማዕድናት ዘርፍ በተጨማሪ በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ፣ በግብርናና በግብርና ማቀነባበሪያ፣ በታዳሽ ኃይል፣ በመንገድና በባቡር መስመር ዝርጋታዎች ቢሳተፉ የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ለተሰብሳቢዎቹ አስረድተዋል፡፡

የአፍሪካ ኮርፖሬት ምክር ቤት እንዲህ ዓይነት ስብሰባ በሁለት ዓመት አንዴ የሚያካሂድ ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም አኅጉሪቱን ከአሜሪካ ኢንቨስተሮች ጋር በማገናኘት ቢዝነስና ኢንቨስትመንት እንዲጠናከር የሚያደርግ ድርጅት ነው፡፡

ይህ ስብሰባ ኢትዮጵያ ውስጥ መካሄዱ ትልቁ አንድምታ አለው ያሉት አቶ ዘመዴነህ፣ ‹‹አሜሪካኖች ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ትኩረት እንደተሰጠው የሚያሳይ ነው፤›› በማለት፣ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ቀደም ሲል ይታወቅበት ከነበረበት የደኅንነትና አካባቢውን የማረጋጋት ሥራ ባሻገር ወደ ኢንቨስትመንትና ኢኮኖሚ መስክ መሸጋገሩን የሚያሳይ እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሠረት ባለፉት ዓመታት ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የኢንቨስትመንት መጠን ከፍተኛ እንደሆነ አስታውሰው፣ የአገሪቱ ትልልቅ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል የኮርቤቲ ጂኦተርማል ፕሮጀክት፣ ከጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ የሚዘረጋው የነዳጅ መስመር ማስተላለፊያ መስመር፣ የጄኔራል ኤሌክትሪክ አነስተኛ ፋብሪካ ለመሥራት መፈለግ፣ እንዲሁም በ250 ሚሊዮን ዶላር የሚካሄደው የኮካ ኮላ ማስፋፊያ ፕሮጀክት የአገሪቱና የአሜሪካ ግንኙነት እየተጠናከረ ለመምጣቱ ማሳያ ነው በማለት አብራርተዋል፡፡

አሁን ከመጡትና መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ ከጀመሩት ኩባንያዎች በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ለመግባት በዝግጅት ላይ ያሉ ድርጅቶች እንዳሉ የገለጹት አቶ ዘመዴነህ፣ ‹‹ምንም እንኳን በአሁኑ ጊዜ ስማቸውን መግለጽ ባልችልም በመጪው ዓመት ከመንፈቅ ውስጥ ግን የሚፈረሙ ስምምነቶች ይኖራሉ፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በዚህ ለአራት ቀናት በአዲስ አበባ የሚካሄደው የንግድና ኢንቨስትመንት መድረክ ላይ ከ1,200 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡ በስብሰባ መድረኩ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሊንዳ ቶማስ ግሪን ፊልድን ጨምሮ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ፣ እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሥራ አስፈጻሚዎችና ኃላፊዎች እንደሚገኙ ታውቋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች