የአፍሪካ ኅብረት 26ኛው የመሪዎች መደበኛ ጉባዔ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡ በዘንድሮው ጉባዔ ትኩረት የተሰጣቸው የአኅጉሪቱን አንድነት ማጠናከር፣ መቻቻል፣ ሰብዓዊ መብትና መልካም አስተዳደር ናቸው፡፡ እነዚህ ባልተሟሉበት የአፍሪካን ዙሪያ ገብ ችግሮች መፍታት እንደማይቻል ተወስቷል፡፡ በተለይ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ትኩረትን ስቧል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባን ኪሙን የአፍሪካ መሪዎች መቻቻልን፣ ሰብዓዊ መብትንና ሁሉን አቀፍ ልማት በማስፋፋት ሰላምና ዘላቂ ዕድገት እንዲያስመዘግቡ ጠይቀዋል፡፡ በአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡ ይህም እያንዳንዱን አገር ይመለከታል፡፡
ዋና ጸሐፊው የማፑቶ ፕሮቶኮልን በማስታወስ የሴቶች መብትን፣ ዴሞክራሲን፣ ምርጫንና መልካም አስተዳደርን በሚመለከት የወጣውን የአፍሪካ ቻርተር፣ እንዲሁም የአፍሪካን ፍርድ ቤትና የሰብዓዊና የሕዝብ መብቶችን ፕሮቶኮል መሪዎች እንዲያፀድቋቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ እነዚህን መብቶች ተግባራዊ በማድረግ በአኅጉሩ ሰላምና ፀጥታን በአስተማማኝነት ማስፈን አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ በአኅጉሪቱ ውስጥ በተለያዩ ሥፍራዎች የሚነሱት ግጭቶች ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር ቁርኝት ስላላቸው፣ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ችላ ሊባል አይገባም፡፡
የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ሆነ የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት ያፀደቋቸውን የሰብዓዊ መብት ሰነዶች ለመቀበል የነበረው ፈተና ይታወቃል፡፡ ብዙ አገሮች ሰብዓዊ መብት የማያከብሩ በመሆናቸው የኅብረቱን አንድነት ለማጠናከር፣ መልካም አስተዳደር ለማስፈንና ሰብዓዊ መብት ለማክበር ፈቃደኞች አልነበሩም፡፡ ሌላው ቀርቶ የአፍሪካ ኅበረት ማቋቋሚያ ሰነድ ከዓመታት በኋላ እንዲሻሻል ተደርጎ፣ ከ54 አገሮች ውስጥ ያፀደቁት 28 ብቻ ናቸው፡፡ በሕጉ መሠረት ማሻሻያው የሚፀድቀው በሁለት-ሦስተኛ ድምፅ ነው፡፡ ይህ በራሱ የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች ምን ያህል ለራስ የመታመን ችግር እንዳለባቸው ያሳያል፡፡ ቀልድ ነው፡፡
‹‹አጀንዳ 2063›› የተባለውን አኅጉሪቱን ወደ አንድነት የሚያመጣውን መርሐ ግብር ለማሳካትና ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትራንስፎርሜሽን ለማፋጠን፣ ሕዝቡን በሰብዓዊ መብት አጠባበቅ፣ በትምህርት፣ በተመጣጠነ ምግብ፣ በጤና፣ በንፁኅ የመጠጥ ውኃ፣ በፅዳት፣ በኢነርጂና በመሳሰሉት ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በዚህ ጉባዔ ላይ ተወስቷል፡፡ ነገር ግን አኅጉሪቱ ወደ አንድነት እያመራች ነው ሲባልና መርሐ ግብሩ ሲተነተን አገሮች ለዓላማው ተፈጻሚነት ግዴታ ሊጣልባቸው ይገባል፡፡ ሰብዓዊ መብት እየተጣሰና የመልማት መብት እየተገደበ በአምባገነኖች መዳፍ ሥር በድህነት መቆራመድ በብዛት ይታያል፡፡ ብዙዎቹ አምባገነን የአፍሪካ መንግሥታት ሰብዓዊ መብት እየጣሱ ዜጎችን ለሞት፣ ለስደትና ለጉስቁልና ሲዳርጉ ይታያል፡፡
በአፍሪካ አኅጉር በምርጫ ሥልጣን መያዝ እየተለመደ ቢመጣም፣ በትክክል ተግባራዊ እየሆነ ያለው በተወሰኑ አገሮች ብቻ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የለየላቸው አምባገነኖች ጭምር ለዴሞክራሲ እጃቸውን ቢሰጡም፣ አሁንም ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ዓለም አቀፉን ደረጃ የሚያሟሉ ምርጫዎች ይካሄዳሉ፡፡ በስመ ዴሞክራሲ የይስሙላ ምርጫ በማካሄድ የፖለቲካውን ሥነ ምኅዳር የሚያጠቡ ብዙ አሉ፡፡ ‹‹አጀንዳ 2063›› የአኅጉሪቱን ሕዝብ ማዕከል እንዲያደርግ ሲፈለግ፣ መሪዎች ይህንን አጀንዳ ለማስፈጸም ቁርጠኝነት ማሳየት አለባቸው፡፡ ሰብዓዊ መብት ዋነኛው የተግባር መርህ እንዲሆን ቁርጠኝነት ከሌለ ትርፉ ግጭትና ውድመት ነው፡፡
እ.ኤ.አ. በ1948 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ያፀደቀው ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ለተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች በከፊል ምላሽ የሰጠ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት የድርጅቱ አባል አገሮች የሰብዓዊ፣ የሲቪል፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ መብቶችን እንዲያስከብሩ፣ እነዚህም መብቶች የዓለም የነፃነት፣ የፍትሕና የሰላም መሠረት እንዲሆኑ ደንግጓል፡፡ ብዙዎቹ አገሮችም በሕገ መንግሥቶቻቸው ውስጥ አስፍረዋቸዋል፡፡ ኢትዮጵያም እንዲሁ፡፡ የአፍሪካ አገሮች ከኅብረቱ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች በተጨማሪ እነዚህን መሠረታዊ መብቶች የያዘ ሰነድ በየአገሮቹ ተግባራዊ ቢያስደርግ ውጤቱ ጥሩ ይሆን ነበር፡፡ ይህ ባለመሆኑ ግን ቀልድ በዝቷል፡፡
በአፍሪካ በርካታ አገሮች ውስጥ የሚነሱ ግጭቶች ምክንያታቸው በቀጥታ ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር የተገናኘ በመሆኑ፣ ዜጎች በገዛ አገራቸው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ሲጣሱ ብጥብጥ ይከሰታል፡፡ የገዛ አገራቸውን ሀብት ሲነፈጉ ለሰላምና ለመረጋጋት እጦት በር ይከፍታል፡፡ ጥቂቶች እየበለፀጉ ብዙኃን ሲራቡ ችግር ይፈጠራል፡፡ በሀብት ክፍፍልም ሆነ በሥልጣን ክፍፍል አድልኦና መድልኦ ሲኖር እንቢታ ይኖራል፡፡ ይህ በአፍሪካ አኅጉር ውስጥ ለበርካታ አገሮች ሰላም ማጣት፣ ሕይወት መጥፋት፣ አካል መጉደልና ንብረት መውደም ትልቁ ምክንያት ነው፡፡ በሕዝብና በመንግሥታት መካከል ልዩነት እየፈጠረ ሰላም እንዲደፈርስ ያደርጋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶ/ር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ እንዳሉት፣ በአፍሪካ አኅጉር ውስጥ ለሰብዓዊ መብት በትልቁ ቁርጠኝነት ማሳየት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ እሳቸው የአፍሪካን ሕዝብና መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቱን የ‹‹አጀንዳ 2063›› ማዕከል ማድረግ በእጅጉ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡ ሕዝብን ከዴሞክራሲ፣ ከሰብዓዊ መብት፣ ከፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ከመሳሰሉት እያገለሉ አገር ለማስተዳደር መሞከር ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚደረግ ጉዞ ለብጥብጥ፣ ለድህነት፣ ለጉስቁልናና በግዳጅ ለሚከናወን ስደት በር ይከፍታል፡፡ በተጨማሪም ለአገር ህልውናም ጠንቅ ነው፡፡
በአፍሪካም ሆነ በአገር ደረጃ ሁሉም ወገን ቅድሚያ መስጠት ያለበት ለሰብዓዊ መብት መከበር ነው፡፡ ሰብዓዊ መብት እንዲከበርና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በአስተማማኝነት እንዲገነባ ከተፈለገ፣ ከጽንፈኝነትና ከአክራሪ አስተሳሰብ መላቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ጠቃሚው መፍትሔ የዴሞክራሲን ጽንሰ ሐሳቦች በሚገባ ተረድቶ ለዘላቂው የጋራ ጥቅም ራስን ማዘጋጀት ነው፡፡ ሕዝብ በአኅጉርም ሆነ በአገር ደረጃ ሰብዓዊ መብቱ ሲከበርና ተደማጭነት ሲኖረው፣ በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሲሳተፍ፣ መሪዎችን የሚቆጣጠርባቸው ዴሞክራቲክና ሲቪክ ተቋማት በነፃነት ሲንቀሳቀሱ፣ እኩልነት በተግባር ሲረጋገጥ፣ ወዘተ አንድነትም ሆነ ሰላም፣ ብልፅግናም ሆነ ህልውና አስተማማኝ ይሆናል፡፡ የአገር መሪዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ በሚካሄዱ ምርጫዎች ሥልጣን ሲይዙ፣ ሲሸነፉ ደግሞ ሥልጣን ሲለቁ፣ ከተወሰነላቸው ጊዜ ገደብ በላይ ሥልጣን ላይ ለመቆየት ሰበብ ሳይፈልጉና በአጠቃላይ ምርጫ ሳያጭበረብሩ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ በግለሰብ ደረጃም ሆነ በቡድን ሰብዓዊ መብትን ማክበር አለባቸው፡፡ ለዚህም ነው ሰብዓዊ መብት መቀለጃ አይደለም የሚባለው!