Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአክሰስ ሪል ስቴት መሥራች የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ሳይለይ መታሰራቸውን ጠበቃቸው ተቃወሙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጥር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለው በእስር ላይ የሚገኙት የአክሰስ ሪል ስቴት መሥራች አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ፣ የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ሳይለይ መታሰራቸው ከሕግ አግባብ ውጪ መሆኑን ጠበቃቸው ጥር 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ለፍርድ ቤት ገለጹ፡፡

የአቶ ኤርሚያስ የሕግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ሞላ ዘገዬ የደንበኛቸው መታሰር አግባብ እንዳልሆነ የገለጹት፣ አቶ ኤርሚያስን በቁጥጥር ሥር አውሎ እየመረመራቸው የሚገኘው የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) መርማሪ ቡድን፣ ለሦስተኛ ጊዜ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት ባቀረባቸው ቀን ነው፡፡ ጠበቃው ለፍርድ ቤቱ እንደተናገሩት፣ አቶ ኤርሚያስ የተጠረጠሩበት ድርጊት ወንጀል ወይም ፍትሐ ብሔር መሆኑ አልተለየም፡፡ ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩበት ድርጊት ሳይለይ፣ እሳቸውን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ተገቢና ሕግን የተከተለ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

አቶ ኤርሚያስ በተጠረጠሩበት ድርጊት ማስረጃ ቀርቦባቸዋል ቢባል እንኳን ዋስትና የሚያስከለክላቸው ሊሆን እንደማይችል የተናገሩት ጠበቃው፣ ያላቸው ማንኛውም ዓይነት ሀብት ዕግድ ስለተጣለበት የሚያሸሹትም ሆነ የሚሸሽጉት ነገር ስለሌለ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ቀደም ብሎ በተሰጠው የምርመራ ጊዜ የሠራውን በጽሑፍ ለፍርድ ቤቱ ካቀረበ በኋላ፣ ምርመራውን እንዳላጠናቀቀ ገልጾ ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ እንዲሰጠው ሲጠይቅም ጠበቃው ተቃውመዋል፡፡

የመርማሪ ቡድኑን ጥያቄ የተቃወሙት ጠበቃ ሞላ ዘገዬ እንደገለጹት፣ ፖሊስ መጀመሪያውኑ ግለሰቡን በቁጥጥር ሥር ከማዋሉ በፊት የሚያስፈልገውን ማስረጃ የመሰብሰብ ኃላፊነት እንደነበረበት ጠቁመው፣ ከዚያም በኋላ በተሰጠው የምርመራ ጊዜ ማጠናቀቅ ሲችል ለሦስተኛ ጊዜ መጠየቁ ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

አቶ ኤርሚያስ በአክሰስ ሪል ስቴትና በቤት ገዢዎች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ለመፍታት መንግሥት ዋስትና ሰጥቷቸው ወደ አገር ውስጥ መመለሳቸውን ያስረዱት ጠበቃው፣ የተሰጣቸው ዋስትና ሳይወርድ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ማዋሉ፣ እሳቸው የነበረውን ችግር ለመፍታት ጫፍ ላይ ያደረሱትን ጥረት ከማክሸፉም በተጨማሪ፣ የመንግሥትን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ ሊያስገባ የሚችል ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፖሊስ አቶ ኤርሚያስ በዋስ ቢፈቱ ማስረጃና ምስክር ያሸሹብኛል የሚል ሥጋት ካለው፣ ለመረጃና ደኅንነት ከአገር እንዳይወጡ ማገጃ ማጻፍ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡

የጠበቃ ሞላን ክርክር ተከትሎ መከራከሪያ ነጥቡን ያቀረበው መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ አቶ ኤርሚያስን ፍርድ ቤት እያቀረበ ጊዜ ቀጠሮ የሚጠይቀው የተጠረጠሩበትን ወንጀል ለማጣራት ነው፡፡ መንግሥት ደብዳቤ የጻፈላቸው ማለትም ቀደም ብሎ የተጠረጠሩበትና ለዓቃቤ ሕግ ተሰጥቶ የነበረው የደረቅ ቼክ ወንጀል ለጊዜው የታገደ ስለመሆኑ እንጂ ሌላ አለመሆኑን ገልጿል፡፡ በቀጣዩ የሚያደርገውን ምርመራ የሚያግድ አለመሆኑንም አክሏል፡፡ እውነታውን ለማውጣት እንጂ ግለሰቡን የማሰር ፍላጐት ኖሮት እንዳልሆነም ገልጿል፡፡

የተጠረጠሩት 1.4 ቢሊዮን ብር አላግባብ ወጪ አድርገዋል በሚል በመሆኑና ገንዘቡን ሲያወጡ እንዴት እንዳወጡት ስለማይታወቅ የማጣራት ሥራ እየሠራ መሆኑን መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡ አቶ ኤርሚያስ ጂቡቲን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ድርጅቶችን መክፈታቸውንና ምርመራ ማድረግ እንደሚቀረው ገልጾ፣ ይኼንን ሁሉ ድርጊት የሚፈጽሙት በራሳቸው ኃይል ከቦርድ ፈቃድ ውጪ ገንዘብ ወጪ በማድረግ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ቤት ገዢዎችም ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ክፍያ የፈጸሙ ቢሆንም፣ አንዳቸውም ቤት እንዳላገኙ አስረድቶ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ባለፉት የምርመራ ጊዜያት ምርመራውን ሊያጠናቅቅ ያልቻለው፣ አቶ ኤርሚያስ ምንም የፈጸሙት የወንጀል ድርጊት ባለመኖሩ መሆኑን የገለጹት አቶ ሞላ፣ አቶ ኤርማያስ በመንግሥት ፈቃጅነት ወደ አገር ሲገቡ በቤት ገዢዎች ላይ ተፈጥሮ የነበረውን አለመረጋጋትና ችግር ለመፍታት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ አሁንም የተፈጠረው ችግር ሊፈታ የሚችለው አክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር፣ ቤት ገዢዎችና አቶ ኤርሚያስ በአዲስ መንፈስ ተረጋግተውና ተግባብተው መሥራት ከቻሉ ብቻ መሆኑን የተናገሩት ጠበቃው፣ ለዜጐች መፍትሔ ከመስጠት አንፃር መንግሥት ጉዳዩን በፅሞና እንዲከታተለውም ጠይቀዋል፡፡

እስካሁን አቶ ኤርሚያስ ስለሚጠየቁበትም ሆነ ፈጽመዋል ስለተባለው ጉዳይ መርማሪ ቡድኑ ያለው ነገር እንደሌለ የተናገሩት ጠበቃው፣ በአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ላይ ችግር ተፈጥሯል ቢባል እንኳን ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉት አቶ ኤርሚያስ ብቻ ሳይሆኑ፣ አክሲዮን ማኅበሩና የአክሲዮኑ ባለድርሻዎች ጭምር ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ የተሰበሰበው ገንዘብ የት እንደደረሰ በማጣራት ላይ መሆኑን መግለጹን እንደሚስማሙበት የገለጹት ጠበቃው፣ መጀመሪያ አቶ ኤርሚያስ 1.4 ቢሊዮን ብር መሰብሰባቸውን ብቻ መናገር ሳይሆን አክሲዮን ማኅበሩ ያለው ሀብት ምን ያህል እንደሆነ፣ ሕጋዊ ወጪዎቹ ምን ያህል እንደሆኑ ማጣራትና ማወቅ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ ኤርሚያስን ለእስር ያበቃቸውን ምክንያት የሚያውቀው መንግሥት ብቻ መሆኑን የገለጹት አቶ ሞላ፣ አቶ ኤርሚያስ ለመንግሥት የገቡትን ቃል አለማጠፋቸውን፣ ነገር ግን የቤት ገዢዎች ተወካይ ኮሚቴ፣ ቦርዱና ሌሎች አካሎች የመፍትሔ ሐሳብ ከማቅረብ ይልቅ የሆነ ያልሆነውን በማድረግ የተጀመረው ዓላማ ግቡን እንዳይመታ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ ኤርሚያስ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ጊዜ ጀምሮ ሊያገኟቸው ወይም ፖሊስ ሊያገናኛቸው እንዳልቻለም ጠበቃው አመልክተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ሁለቱ ተከራካሪ ወገኖች ያደረጉትን ክርክር ካዳመጠ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ እንደገለጸው፣ አቶ ኤርሚያስ ከሕግ ባለሙያ ጋር የመገናኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት ያላቸው በመሆኑ መገናኘት አለባቸው፡፡ የተጠረጠሩበት ጉዳይ ወንጀል ይሁን ፍትሐ ብሔር አልተለየም ስለተባለው ክርክር፣ ሥልጣኑ የዓቃቤ ሕግና የፍትሕ ሚኒስቴር እንጂ የጊዜ ቀጠሮውን እያየው ያለው ችሎት አይደለም፡፡ ክሱ ሊቋረጥ ይገባል የሚለውን የጠበቆች ክርክር በሚመለከት፣ ክስ የማቋረጥ ሥልጣን የፍትሕ ሚኒስቴር መሆኑን አስረድቷል፡፡ አቶ ኤርሚያስ የተጠረጠሩት በ1.4 ቢሊዮን ብር በመሆኑ ይኼንን ያህል ገንዘብ እያላቸው ምስክር አያባብሉምና ሰነድ አያሸሹም ሊል እንደማይችል ገልጾ፣ መርማሪ ቡድኑ ከጠየቀው የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ውስጥ አሥር ቀናት በመፍቀድ የዋስትና ጥያቄያቸውን አልፎታል፡፡

አቶ ኤርሚያስ አመልጋ አክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበርን ከ600 በላይ ከሆኑ ባለድርሻዎች ጋር መሥርተው፣ በውጭና በአገር ውስጥ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቤት ሠርተው ለማስረከብ ከ2,500 በላይ ግለሰቦች ጋር ውል ፈጽመው ነበር፡፡ በቃላቸው መሠረት ለቤት ገዢዎቹ ቤቱን ሠርተው ማስረከብ ባለመቻላቸው በተፈጠረ ውዝግብ በድንገት በ2005 ዓ.ም. ከአገር ወጥተው ነበር፡፡ ለቤት ገዢዎች ችግርና ብሶት ምላሽ ለመስጠት ከቤት ገዢዎች የተውጣጣ ኮሚቴ ከመቋቋሙም በተጨማሪ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የተካተቱበት አብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየመከረ እያለ አቶ ኤርሚያስ የችግሩ መፍትሔ አካል ለመሆን ባቀረቡት ሐሳብ መሠረት፣ ፍትሕ ሚኒስቴር በጊዜያዊነት ክሱ እንዲቋረጥ በማድረጉ የካቲት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውንና ሥራ መጀመራቸው ይታወሳል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች