Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዝንቅየአቡነ ጴጥሮስን ሐውልት የሚጠብቀው አደባባይ

የአቡነ ጴጥሮስን ሐውልት የሚጠብቀው አደባባይ

ቀን:

ከሦስት ዓመት በፊት ከነባር ስፍራው ተነሥቶ የነበረው የሰማዕቱ ቅዱስ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት በዕለተ ሰንበት (ጥር 29 ቀን 2008 ዓ.ም.) ከቆየበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በክብር ወጥቶ ሊተከል ነው፡፡ በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት መስመር ዝርጋታ በመሬት ውስጥ ለማከናወን ሲባል ነበር፣ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ሚያዝያ 24 ቀን 2005 ዓ.ም. የተነሳው፡፡ የሐውልቱን መሠረት ግንባታ ያካሄደው አሰር ኮንስትራክሽን  ሲሆን፣ ሐውልቱ በሚቆምበት በኩል የሚያልፈውን መስመር እንቅስቃሴ ያገናዘበ ዲዛይን በቀላል ባቡር ሥራ ተቋራጭ መሠራቱ ታውቋል፡፡ ከሰማንያ ዓመት በፊት በ1875 ዓ.ም. የተወለዱትና ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም.  ሰማዕት የሆኑት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፣ የኢጣሊያ ፋሺስት በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ጦርነትን ባነሳ ጊዜ ከጦሩ ባለመለየት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ተከትለው ወደ ሰሜን ጦር ግንባር ዘምተዋል፡፡ ፋሺስቱ በማይጨው የመርዝ ጦርነት ከማድረጉ የተነሣ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሲበታተንም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የተመለሱት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሔደው ለአገርና ለነፃነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን ለሰላሌ አርበኞች በመስበክም ይታወቃሉ፡፡ ፎቶው ሐሙስ ጥር 26 ቀን 2008 ዓ.ም. የመሠረት ግንባታውን የተቋራጭ ኩባንያው ባልደረቦች እያጠናቀቁ ሳለ የተነሳ ነው፡፡ (ፎቶ በሔኖክ ያሬድ)

****-*

ቅጠሪኝ በበጋ

- Advertisement -

ከወንዝ ወዲያ ማዶ

      ያለሽው ለግላጋ፣

ክረምቱ አለፍ ሲል

      ነይልኝ በበጋ፡፡

ወደ አንቺ ለመምጣት ልቤ ቢከጅልም፣

አይንሽን ለማየት እጅጉን ብጓጓም፤

የሰው ልጅ ነኝና ፍርሃት አደረብኝ፣

እንደ ዛፍ፣ እንደ ግንድ አባይ እንዳይወስደኝ፡፡

በምትፈካው ፀሐይ፤ በአደይ አበባ፣

መስኩ በሚያምርበት፤ መስከረም ሲጠባ፤

እኔና አንቺ ብቻ ከምናውቃት ስፍራ፣

ከተቋደስንባት የፍቅርን አዝመራ፤

እዚያች ግራሯጋ፣

ቅጠሪኝ በበጋ፡፡

  • በረከት ተስፋማርያም (የንግሥት) “በዚያች ቅፅበት” (2005)

 

*********

‹‹ሠርግ እና ሞት …››

ቅዳሜ ዕለት ሥራ ስለነበረኝ ቢሮ ለመድረስ ሃያ ሁለት ማዞርያ አካባቢ ለሩጫ ቀረብ እርምጃ ላይ ነኝ፡፡ በየጠዋቱ እግር አውጥቶ ወደ አስፋልቱ ጠጋ ይል የሚመስለኝ፤ አሁን አሁን የሰፈሬ ሰው ሁሉ ‹‹አጓጉል ህንፃ›› ብሎ የሰየመው ሕንፃ ያለበትና ነፃ- እርምጃ ከልክል ስፍራ ስደርስ ግን አይቼ የማላውቀውን ትእይንት አየሁና ቆምኩ፡፡

አደባባይነቱ ተቀባይነት ባላገኘውና እግረኛውም መኪናውም እንዳሻው በሚራኮትበት አደባባይ ዙሪያ በፍጥነት በሚንቀሳቀሱ ስድስት ብስክሌቶች ላይ እግሮችና እጆቻቸውን ሊገለፅ በማይችል አኳሃን አንጨፍርረው የሙሽራና ሚዜ መኪና ያጀቡ ስድስት ወጣቶችን አየሁ፡፡

የሚያደርጉትን ሁሉ በአስፈሪ ፍጥነትና በሚያስገርም ኅብረት ሲያደርጉት ላየ በነፍስ ወከፍ ስድስት እግርና ስድስት እጅ የታደላቸው ይመስላሉ፡፡

ጎማቸውን መሽከርከሩን ሳያቆም አንዴ የቀኝ አንዴ የግራ፤ መልሰው የቀኝ መልሰው የግራ እግርና እጃቸውን በቄንጥ እያወናጨፉ ሲሄዱ የአካባቢው ሰው በመደመም ያያል፡፡

ለሥራ መቸኮሌ ቢነዘንዘኝም፣ በልጆቹ የመንገድ ላይ ትርኢት መንገዴ ተዘግቶ ለሥራ መዘግየቴ ቢከነክነኝም፣ ለአፍታ አጠገቤ ቆሞ በነበረው የሙሽሮቹ መኪና መስታወት ወደ ውስጥ አየሁ፡፡

ሙሽሪትን አየኋት፡፡ ወጣት፣ ሜክ አፕ-አመጤ ያልሆነ ቁንጅና ባለቤት ናት፡፡ በሠርጓ ድምቀት የተደሰተች ትመስላለች፡፡

ሙሽራውን አየሁት፡፡ ምራቁን ም…ጥ…ጥ አድርጎ የዋጠ ነው፡፡ እንዳየሁት የመጣብኝ ፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፍ ላይ ያለው ዝነኛው ገፀ ባህሪ ጉዱ ካሳ ያላት ነገር ናት፡፡

‹‹ከዕድሜ ገፋ ብሎ ምራቅ መዋጥ አንድ ነገር ነው፡፡ ከዕድሜ ገፋ ብሎ ምራቅ መሰብሰብ አለመቻል ግን ሌላ ነገር ነው፡፡››

የሙሽራው ሚዜዎች ደህና መሃረብ ሸጎጥ እንዳደረጉለት ተስፋ አድርጌ ወደ ባለብስክሌቶቹ ደናሾች ተመለስኩ፡፡ አስደማሚ ትእይንታቸውን ቀጥለዋል፡፡ እኔ ግን ከመደመሙ ይልቅ ሰቀቀኑ ገደለኝ፡፡ ምክንያቱም ጎማቸውም እነሱም እኩል ይሽከረከራሉ፡፡ ምክንያቱም ያጀቧቸው መኪኖችም በፍጥነት ይሽከረከራሉ፡፡ ምክንያቱም ከሠርጉ ጋር ግንኙነት የሌላቸው መኪኖችም በስፍራው በፍጥነት መሽከርከራቸውን አላቆሙም፡፡

 

‹‹እንዴት ቢያንስ ዕድሜ ብዙ ያሳየው ሙሽራ እንኳን የዚህን ነገር ሰቀቀናምነት መተንበይ አቃተው›› ብዬ አሰብኩ፡፡

የመርዶ ተንባይ መሆኔ የገባኝ አሳቤን እንኳን በቅጡ ሳልጨርስ፤ ከስድስቱ አንዱ ልጅ ስልቱን ስቶ፣ ብስክሌቱን መቆጣጠር አቅቶት ሲከነበል ሳይ ነው፡፡

ተደምሞ ሲያይ የነበረው ሰው ሁሉ ክው አለ፡፡

ከጥቂት የመደናገር ደቂቃዎች በኋላ፤ እንዴት እንዴት እንደሆነ ባልገባኝ ሁኔታ ከኋላው የነበረው መኪና ‹‹ገጨው›› ተብሎ ሲሠጋለት ከጎማ ጥርስ ለጥቂት ማምለጡን አየን፡፡

‹‹ሠርግና ሞት አንድ ነው›› የሚባል የቆየ አባባል አለ፡፡ ነገር እናሳምር ባዮቹ ቄንጠኛ ሙሽሮች ግን ይህንን አባባል ‹‹ሠርግና ሞት አንድ ቀን ነው›› በሚል ከመተካት ለጥቂት ተረፉ፡፡

  • ሕይወት እምሻው በፌስቡክ ገጽዋ እንደከተበችው

****-*

የአንበሳው ዘፈን

አንዲት ከሴት አያቷ ጋር የምትኖር ልጃገረድ ነበረች፡፡ ታዲያ አንድ ቀን የመንደሯ ወጣቶች ወደ ሌላ መንደር ለመጫወት ሲሄዱ የእርሷ አያት “እህሉን ፈጭተሸ ከጋገርሽ በኋላ ነው የምትሄጂው፤” አሏት፡፡

ሌሎች ወጣቶች ሲሄዱ እርሷ ለአያቷ ሁሉንም ሥራ ሠራችላቸው፡፡ ማብሰሉን ስትጨርስም አያቷ “አሁን ምግብ ብዪ፤ ካለበለዚያ መንገድ ላይ ይርብሻል፤” አሏት፡፡

እናም በላች ነገር ግን ሁሉም ጥለዋት ሄደዋል፡፡ ከዚያም ብቻዋን ወደ መንደሩ እየሄደች ሳለ መንገዷ ላይ አንድ አንበሳ አገኘች፡፡ አንበሳውም እንዳይበላት የሚከተለውን ዘፈን ዘፈነችለት፡፡

“አንበሳ ሆይ፣ ስትበላኝ ኋላዬን ብቻ ብላ ፊት ለፊቴን ለኦላንግ ልጆች ተውላቸው የኦላንግ ልጆች ከበሮ እየመቱ ነው አጉታ ንዲማሩም ከእርሱ አንዱ ነው ከበሮ መምታት ስለማይችል ወደ ጨዋታው አልሄደም ዛሬ በአንበሳው ይበላል” አንበሳውም “አዎን አንቺን በኋላ እበላሻለሁ፤” አላት፡፡ ከዚያም አንበሳው እየተከታተላት እርሷ እየዘፈነችለት ከመንደሩ አጠገብ ደረሱ፡፡

ፍቅረኛዋም ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ድምጿን ስለሰማ ተዘጋጅቶ በመምጣት አንበሳውን በጦር ወጋው፡፡

አንበሳውም ሲወድቅ እንዲህ አለ “እባክህ እንደገና ውጋኝ?” ፍቅረኛዋም “ለምን? ፍቅረኛዬን በልተሃት ቢሆን ኖሮ እንደገና ትበላት ነበር?” አለው፡፡

የልጅቷ ዘፈን ትርጉም “ከኋላዬ ብላኝ ከፊቴ ሳይሆን ፍቅረኛዬ ፊቴን አይቶ ይለየኝ ዘንድ” ማለት ነው፡፡

  • በአላሚ አክውር የተተረከ የአኙዋህ ተረት

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...