በልዑል ዘሩ
የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአንድ ባንዲራ፤ በአንድ ሉዓላዊ ግዛትና በአንድ መንግሥታዊ ሥርዓት የኖሩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የታሪክ ዝዋዥዌው ቀላል ባይሆንም የአሁኗ ኤርትራ በቱርክ፣ በግብፅ፣ በጣሊያንና በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ከመያዟ በፊት የኢትዮጵያ ‹‹ባህረ ነጋሽ›› ግዛት እንደነበረች በቀደሙ የታሪክ ድርሳናት ተደጋግሞ የተገለጸ ነው፡፡
የኤርትራና የኢትዮጵያ የሁለት አገሮች ፍላጎት ተባብሶና ጎልቶ የወጣው ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ በረዥሙ ዓመት የሰሜን ኢትዮጵያ ታሪክ ባዕዳን አገሮች የባህር ወደብን ለመያዘ የነበራቸው ፍላጎት ትልቁን ድርሻ ተጫውቷል፡፡ በተለይ በኤርትራ ምድር የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ከሌላው የአገራችን ሕዝብ የተለየ ሥነ ልቦና ታሪክና ማንነት ያለው በማስመሰል የመነጠል ሥራ ሠርተዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖትና ብሔር ያላቸውን ውህደት በማናጠብ የኢትዮጵያ የየዘመናቱ ገዥዎች የቀኝ ግዛት ቀንበር ጭሰኝነት የአገሪቱ አካል ሆኖ እንዲኖር ሲሰበክ ኖሯል፡፡
በዚህም መነሻ የጀበሃና የሻዕቢያ ዓይነቶቹ ለኤርትራ ነፃነት የታገሉ ኃይሎች፣ በንጉሡም ሆነ በደርግ ሥርዓቶች የኢትዮጵያ መንግሥታት በያዙት ግትር አቋምና ኢሕአዴግ የሸዓቢያን ፍላጎት በገቢር ለመፈጸም በመተባበሩ የሁለት አገሮች ውልደት ተፈጽሟል፡፡ እነሆ ከዚያም ወዲህ አጭር ቢመስልም 25 ዓመታት አልፈዋል፡፡ የኤርትራ ሕዝብ ብዙ መስዋዕትነት የከፈለበትንም ሆነ በጥላቻ ዛር ልቡና አዕምሮው እንዲቆስል የተደረገበትን ከኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ‹‹ነፃ እናወጣላን›› የፖለቲካ ጨዋታ ግን ፍሬ አፍርቶ አላየውም፡፡ እንዲያውም በሻዕቢያ ከቀድሞዎቹ ገዥዎችም በባሰ ሁኔታ መፈናፈኛ አሳጥቶ፣ ሕዝቡ ሲመኘው የኖረው ዴሞክራሲም ሆነ መልካም አስተዳደር አሰናክሎ በጎበዝ አለቃ የሚመራ መናኛ አድርጎታል፡፡ በዚሁ መዘዝ የኤርትራ ወጣቶች እስራትና እንግልት ዕጣ ፈንታቸው ሆኗል፡፡
አንዳንዶች የኤርትራ ሕዝብ ለዘመናት አብሮት ከኖረው ወገኑ ሲነጠል አገዛዞችንና ሕዝብን እንኳን እንዳይለይ ተደርጎ ነው፡፡ ሻዕቢያና ቀጣሪዎቹ ባዕዳን አገሮች በክፋት ፀንሰው የተገላገሉት ‹‹ነፃነት›› አልሰምር ያለውም ለዚህ ነው፡፡ ሕዝቡ ከጎረቤት አገሮች ጋር ተስማምቶና ተረዳድቶ ለመኖር በሚገኝም፣ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ተጠቅሞና የሥራ ተነሳሽነት ባህሉን ተግባሩ ዕድል ቢኖረው በሩን የዘገባት ራሱ ሻዕቢያ መራሹ የአገሪቱ ሥርዓት ነው፡፡
አሁን የኤርትራ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊም ሆነ ሰብዓዊ መብቱ የማይተገበር፣ የመንቀሳቀስ ነፃነቱ ያልተከበረና ከድህነት ያልወጣ ብቻ ሳይሆን የቁም እስረኛም ሆኗል፡፡ ለነገሩ ራሱ የኤርትራ መንግሥት ታጋች ኢሳያስም እስረኛ የሆነበት ሁኔታ የተፈጠረ መስሏል፡፡
አሜሪካዊው የምሥራቅ አፍሪካ ተመራማሪ ዳን ኮኔል በአንድ ወቅት የኢሳያስ አድናቂ ነበር፡፡ ይኼ የቦስተን የጋዜጠኝነት መምህርና ተመራማሪ ግን ዛሬ በሚያሳዝን ደረጃ ላይ ወድቀው በማየቱ ማዘኑን ይገልጻል፡፡
ሥርዓተ አልባ፣ የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነትና የሕግ የበላይነት አልባውን የኢሳያስ የፖለቲካ ሥርዓት ‹‹መውጫ የሌለው የወፍ ጎጆ›› ሲል ሰይሞታል፡፡ ሰውዬው እንኳን በዜጎች የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ ጉዳይ ወይም የአገር ልማት አጀንዳ ይቅርና ጎረቤት አገሮችን በመውረር ውሳኔ (ባድመና ሃኒሽን ልብ ይሏል) ላይ እንኳን በግልጽነት የሚወሰኑ እንዳልሆኑና ፈጽሞ የለየላቸው አምባገነን መሆናቸውን ይገልጻል፡፡
በኤርትራ ያለው አገዛዝ ‹‹ደርግ ሄዶ ደርግ መጣ›› እስከመባል የደረሰው በሥርዓቱ ተቃዋሚዎች፣ በነፃ ጋዜጠኞችና በሲቪክ ማኅበራት መሪዎች ላይ በሚወስደው የግፍ ዕርምጃ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም በ ‹‹ነፃነት›› ታጌዮቹና በሥርዓቱ ቱባ ባለሥልጣናት ላይ ሳይቀር በሚወስደው የግፍ ግድያ፣ እስርና እንግልት ነው፡፡ ኤርትራ ውስጥ እነ ‹‹አዲ ነፍሲት››፣ አዳርሰር (ሳዋ)፣ ዓዲ ቀይህ፣ ዳህላክ ከቢር (ዳህላክ ደሴቶች)፣ ኢራኢሮ (በአስመራና በምፅዋ መካከል) ጋልዓሎ (በቀይ ባህር ዳርቻ)፣ ሐዲሽ መአሰክር (ሱዳን ጠረፍ አቅራቢያ) የሚባሉት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ የግፍና የሰቆቃ ሥፍራዎች በሥርዓቱ ቁንጮ የቅርብ ክትትል የሚታወቁ መቅጫዎች ሲሆኑ፣ በየመንደሩ ያሉ ማሰሪያዎች ከትምህርትና ከጤና ተቋማቱ የበዛ ቁጥር እንዳላትው ይነገራል፡፡
የኤርትራ ሕዝብ ታስሯል የሚባልበት ዋነኛው መገለጫ የማሰሪያው መብዛት ብቻ አይደለም፡፡ ያለ ርትዕና ፍትሕ በግፍ የሚታሰረውም የበዛ ስለሆነ ነው፡፡ ሰሞኑን እ.ኤ.እ. የ2015 አጠቃላይ ሪፖርት ይፋ ያደረገው ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ጥበቃ ኮሚቴ (CPJ) አማኑኤል ክንፈ ሚካኤል የተባለን የኤርትራ ጋዜጠኛ ለሐሳብ ነፃነት ከፍተኛ ዋጋ የከፈለ ሲል ዕውቅና ሰጥቶታል፡፡ ሌሎች 35 የሚደርሱ የኤርትራ ጋዜጠኞችም ካለፉት 15 ዓመታት ወዲህ በየእስር ቤቱ ታጉረውና ደብዛቸው ጠፍቶ እንደቀሩ አትቷል፡፡
የኤርትራ ወጣቶች በብሔራዊ ወታደራዊ ግዴታ ዘመቻ ስም ገና በለጋ ዕድሜያቸው ወታደራዊ ሥልጠና ይወስዳሉ፡፡ ‹‹ሳዋ›› በተባለው የሥልጠና ማዕከል ለወራት በሚሰጠው ወታደራዊ ሥልጠና ሥርዓቱ በሥጋትና በውሸት የፈጠራቸው ጠላት ጎረቤቶች (በዋናነት ኢትዮጵያ) አንድ ቀን ከሚፈጸምብን ወረራ ራሳችንን ለመከላከል ብቸኛው መፍትሔ ሰልጥኖ፣ ተደራጅቶና ታጥቆ መቀመጥ ነው የሚል የፖለቲካ ትምህርት ይሰጣቸዋል፡፡ ስለሆነም ባለው አቅም አምርቶ ራሱንና አገሩን ሊቀይር የሚችለው ትኩስ ኃይል ሁሉ ሲቪል የለበሰ ወታደር ሆኖ ይቀመጣል፡፡
በነገራችን ላይ ወደ ኢትዮጵያ በብዛት እየተሰደዱ ካሉት የኤርትራ ወጣቶች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወታደራዊ ሥልጠና የወሰዱ ናቸው፡፡ ዋነኛ ጠላታቸው ኢትዮጵያ ነች ሲባሉ ኖረው በዚህ አገር ያለውን የሕዝቡን አቀባበል ሲመለከቱ እስከ መገረም የሚደርሱትም ለዚህ ነው፡፡ የኤርትራ ገዢ መደብ ሹማምንት የአገራቸውን ዜጋ እስረኛ ያደረጉበት ዋነኛው ተግባር ኢፍትሐዊነትና ሙስና ነው፡፡ የታገለው በወታደራዊም ሆነ በሲቪል የመንግሥት ኃላፊነት ላይ የሚገኘው ባለሥልጣን የፈለገውን ሕገወጥ ተግባር ይፈጽማል፡፡ የሥርዓቱ ባህሪ ጥገኝነት እንደመሆኑ ከመንደር ኮንትሮባንድ ድንበር ተሻግሮ እስከሚሄድ ንግድ ድረስ እየተደራጀ የፈቀደውን ይፈጽማል፡፡ ብዙኃኑ ዜጋ ግን ከተፈቀደለት የዱቄት፣ ማጣፈጫና ስኳር ሬሽን እንኳን ፈቀቅ ሳይል፣ መብራትና ውኃ ዓመት ሙሉ በፈረቃ (ያም ቢሆን በከተሞች ነው) እያገኘ እንዲኖር የተፈረደበት ነው፡፡
ከሁሉ በላይ ሕዝቡ በግዳጅ የነፃ የጉልበት ሥራ እንዲሠራ የሚገደድ፣ በአገራዊ ተሳትፎ ስም ወታደርነትን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ሥራዎችን በትዕዛዝ የሚተገበር፣ ያለ ይለፍ ወረቀት በኤርትራ ምድር መንቀሳቀስ የማይችል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህን ሀቅ በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚዎችና አንዳንድ ምሁራን ማጋለጣቸው አይዘነጋም፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት የአልጄዚራ ታዋቂ ጋዜጠኛ ጄን ዳተን ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ቃለ ምልልስ ለማድረግ ስትሄድ በኤርትራ የታዘበችውን ሁሉ መዘገቧም አይዘነጋም፡፡ የአገሪቱን ትንሽነትና ሕይወት አልባ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ ከምፅዋ እስከ አስመራ ባለው መንገድ ብቻ እንኳን ያለውን የፍተሻ ኬላ ብዛት፣ በየጊዜው ከአገሪቱ ወደ ጎረቤት አገሮች የሚወጡ ወጣቶች የስደት ዋነኛ መንስዔ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ግዳጅ ስለመሆኑ፣ የዜጎች የግዴታ ሥራ፣ አገሪቱ አሁንም በጦርነት መንፈስ ውስጥ ያለች ስለመሆኗ፣ ወዘተ ብዙ ብዙ ጉድ አውጥታለች ጄን ዳተን፡፡ እነዚህ እውነቶች የኤርትራ ሕዝብ በእስር ላይ መሆን ጥሩ ማረጋገጫ ናቸው፡፡
አንዳንድ የዚህ ጽሑፍ አንባቢያን ታዲያ የኤርትራ ሕዝብ በፀረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ መታሰሩን ቢያምኑም፣ ከእስር የሚፈታው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሲቀራረብ ነው እንዴት አልክ ሊሉ ይችላሉ፡፡ እንዲያውም እውነተኛ ነፃነቱን የሚያገኘው ሻዕቢያን ታግሎ ሲያሸንፍና ነፃነቱን ሲቀዳጅ ብቻ ነው ብለው ሊከራከሩኝ ይችላሉ፡፡
በእኔ በኩል የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝብ መቀራረብ፣ መታረቅ፣ ቁርሾና ጥላቻን ማስወገድ ብቻ ሳይሆን ለጋራ ተጠቃሚነት መነሳት እንደ መፍትሔ ያስቀመጡኩበትን እውነታ ልፈትሽ፡፡ ከላይ እንደተገለጸው በታሪክ አጋጣሚ አንድ የነበሩትን እነዚህ የሁለት አገር ሕዝቦች ለመለያየትና ለማቃቃር ከውጭ ወራሪ ባዕዳን አንስቶ በጉያቸው እስከተፈጠሩ ‹‹ፖለቲከኞች›› ድረስ ከፍተኛ ሴራ ተጎንጉኗል፡፡ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተፈጸሙ ጦርነቶች የሚጠየቁ ሥርዓቶችና የሽምቅ ተዋጊዎች ቢሆኑም፣ በሕዝብ እንደተፈጸመ ውጊያ ተቆጥሮም ብዙ ፕሮፓጋንዳ ተነዝቷል፡፡
ይህን የተዛባ አስተሳሰብ ቀርፎ መቀራረብ ካልተቻለ አሁንም መተማመን አይቻልም፡፡ መተማመን ከሌለ ደግሞ ሻዕቢያን ለመሰሉ የግፍ አገዛዞች ዕድሜ መርዘም አስተዋጽኦ ከማድረግ ውጪ አማራጭ የለም፡፡ አንዳንዶች እውነተኛውን የሕዝብ ለሕዝብና የፖለቲካ ኃይሎች መቀራረብ ‹‹አንድ አገር የመፍጠር ምኞት›› ወይም በግድ እንዋሀድ የማለት ጉጉት አድርገው ሊወስዱት ይችላሉ፡፡ ያ ግን በተለይ በአጭር ጊዜ ያውም ከምልዓተ ሕዝቡ ፍላጎት ውጪ የማይሞከር መሆኑን ማንም ሰው የሚገነዘበው ነው፡፡
የኤርትራ መንግሥት የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ እንደ ምድር መንግሥት ከሥልጣን መውረዱ አይቀርም፡፡ ሲወርድ ደግሞ የፈጠረው የዴሞክራሲ ባህልም ሆነ ሥርዓት (System) በጅምር ደረጃ እንኳን ስለሌለ ዕጣ ፈንታው ክፉኛ መንኮታኮት ነው፡፡ ‹‹ሻዕቢያ መውደቅ በኤርትራ መበታተን የሚጣፋ ነው፤›› የሚሉ የፖለቲካ መላምቶች በአንዳንዶች የሚሰነዘሩትም ለዚህ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ዛሬ በእስር ቤት ላለው የኤርትራ ሕዝብም ሆነ ለጎረቤት አገሮች መጥፎ ክስተት ነው፡፡
ከዚያ በፊት ግን የሻዕቢያ ተስፋ ቆራጭነት የሚታይበት እንቅስቃሴ አሁንም ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› ከምትለው እንስሳ የተለየ አይደለም፡፡ ሻዕቢያ በሶማሊያ በዳሂር አዌይስ ይመራ የነበረውንና ኋላ ላይ ስሙን ከእስላማዊ ምክር ቤት ወደ አልሸባብነት የቀየረው የአልቃይዳ የምሥራቅ አፍሪካ ክንድ ለመሆን የበቃ ዓለም አቀፍ አሸባሪ ሲደግፍ ኖሯል፡፡ ይኼም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና አኅጉራዊ ተቋማት ጭምር ተረጋግጦ ማዕቀብ ሊጣልበት ችሏል፡፡
ይኼ ሳያንሰው በቅርቡ የባህረ ሰላጤው አገሮች በየመን ላይ የሚያካሂዱትን ጦርነት በመደገፍ 400 ተዋጊ ወታደሮችን ወደ የመን አዝምቷል፡፡ ከዚያም አልፎ የምፅዋንና የአሰብን ወደብ ሙሉ በሙሉ የባህረ ሰላጤው አገሮች ባህር ኃይሎች ተዋጊ ሠራዊት እንዲጠቀምበት ለበርካታ ዓመታት በኮንትራት መስጠቱ ይነገራል፡፡ ይህን በማድረጉ ከሚያገኘው ቀላል የማይባል ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ በላይ ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚረዱ የወሃቢያ አራማጅና የግብረ ሽብር ኃይሎች የመረጃና መረማመጃ ዕድል ከመፍጠር አይቦዝንም፡፡ ይኼም ቢሆን ዞሮ ዞሮ ከትውልድ ተሻጋሪነት አንፃር ሲታይ የኢትዮጵያና የኤርትራን ሕዝብ ለመነጠል ከማሴር የሚመነጭ ነው፡፡
በዚህ ሀቅ ላይ በመመሥረት ነው በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ የሚኖሩ አገር ወዳድ ዜጎች፣ ምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎችና ፖለቲከኞች ቆም ብለው ማሰብ ግድ የሚላቸው፡፡ መንግሥትም ሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች (መሪዎችም) ኃላፊዎችና ጠፊዎች ናቸው፡፡ አገርና ሕዝብ ግን ቋሚ (ተተኪ) እና ዘለዓለማዊ ናቸው፡፡ ስለሆነም የኤርትራ ሕዝብን ከተደቀነበት የእስር ፍርድና ስቃይ ለመታደግ ብቻ ሳይሆን፣ ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ሰላምና ደኅንነት ሲባል የሕዝብ ለሕዝብ መቀራረብና ጠንካራ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለማምጣት መሥራት ያስፈልጋል፡፡
በእርግጥ አሁን ባለንበት ወቅት ኢትዮጵያውያን ኤርትራ ምድር ለመግባት ባይችሉም፣ በይፋዊ መንገድ ከኤርትራውያን ወገኖቻቸው ጋር ተቀራርበው የሚኖሩበት ዕድል ባይፈጠርም፣ ብዛት ያላቸው የኤርትራ ወጣቶች ግን አዲስ አበባ ድረስ እንደልባቸው እየከተሙ ነው፡፡ በትግራይ የተለያዩ ከተሞች፣ እንደ ደሴና ወልዲያ ባሉት አካባቢዎችም ከአነስተኛ ሥራ ጀምሮ መሰማራት ጀምረዋል፡፡ በተለይ በኢንተርኔት ካፌና በሞባይል ንግድ (ይኼ ነገር በቀላሉ ወደ ውጭ ስልክ ለማስደወል በይፋ የተፈቀደላቸው ሥራ እየመሰለ መሆኑን ልብ ይሏል) በስፋት ተሰማርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ይኖሩ የነበሩ ኤርትራውያን በአደራና በውክልና የሰጡትን ንብረት ከማስመለስ አልፈው የተከዱትና የተነጠቁትንም በፍርድ ቤት ተከራክረው ማስመለስ እየቻሉ ነው፡፡ በዚህ በኩል መተማመኑና እንደ አገር በተቆርቋሪነት ሠርተው ለመሥራት ከቻሉ መንግሥት የሚያደርገው ድጋፍ መቀጠል ያለበት ነው፡፡ ክህደት፣ ሸፍጥና ‹‹የላሟ አፍ አዲስ አበባ ጡቷ አስመራ›› ሥሌት ከመጣ መልሶ የሚያጋጭና ሕዝብን ቅር የሚያሰኝ ነው፡፡ ዛሬ ከ18 ዓመታት በኋላ ኤርትራውያን ጋራዦች፣ የተሽከርካሪ ማኅበራት፣ ሆቴሎች፣ የሲሚንቶና ብረታ ብረት መጋዘኖች … በኢትዮጵያውያን ስም ደግሞ እየተከፈቱ ሲሠሩ መቃኘት ያለበት ከዚህ አንፃር ነው፡፡
በአጠቃላይ የሁለቱ አገሮች መንግሥታት ተጣልተዋል፡፡ ያሉትም በእልህና በጥላቻ ውስጥ ነው፡፡ እውነት ለመናገር ሕዝቡንም አቃቅረውታል፡፡ አንዱ የሌላውን ጠላት እየደገፈ አገሮቹን ብቻ ሳይሆን ቀጣናውንም የሚረብሽ ተግባር እንዳይፈጸም ያሠጋል፡፡ አሁን የሁለቱ አገሮች የፊት ለፊት ጦርነት ሥጋት የለም፡፡ ውስጥ ለውስጥ አንዱ አንዱን ለማዳከም ግን አይተኙም፡፡ ይኼ ደግሞ የትም የማያደርስ ውድቀትን የሚጋብዝ ተግባር ነው፡፡
ይልቁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኤርትራ ሕዝብ ጋር የሚቀራረብበት፣ የሚተማመንበትና የሚደጋገፍበት አሠራር ይጀመር፡፡ አንዱ ሌላው እስኪፈርስ መጠበቁን ትቶ በዚህ ትውልድ የመቀራረብ ፖሊሲ ብልጭታ ይታይ፡፡ ሻዕቢያ ኢትዮጵያ ግቡ እንደፈለጋችሁ እያለ እኔ እንኳን ባልኖር ኤርትራ የሌላ (የመካከለኛው ምሥራቅ አክራሪ ኃይሎች) አድርጊያት አልፋለሁ እያለ የጋራ ተጠቃሚነት የለም፡፡ ስለሆነም በሁሉም ወገኖች ሊታሰብበት የሚገባ ወቅታዊ ጉዳይ ነው ማለት እሻለሁ፡፡ በእልህና በጥላቻ አረንቋ ውስጥ ያለው ግንኙነት የመፍትሔ ያለህ እያለ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡