ከአምስት ዓመት በፊት ጋና አክራ ውስጥ ነው፡፡ አብዛኞቹ የአገሪቱ ሴቶች ፊት ወዛማ ስለሆነ ብጉር እንደሚያጠቃቸው ያስተዋለችው ዮርዳኖስ ግኡሽ ግርማ፣ ከጋና ወደ ኢትዮጵያ ትመጣና የሞሪንጋ ዱቄት ይዛ ትመለሳለች፡፡ ዱቄቱን እንዲጠቆሙ የሰጠቻቸው ሴቶች ቆዳ ሲስተካከልና ደስተኛ ሲሆኑ ስትመለከት፣ ኸርባሊስት የመሆን ሐሳብ ብልጭ ይልላታል፡፡ ከተፈጥሯዊ ንጥረ ነገሮች የሚዘጋጁ መዋቢያዎች ለመሥራት እዛው አክራ ውስጥ ኮስሞቲክ ፕሮዳክሽን ተማረች፡፡ ተፈጥሯዊ የውበት መጠበቂያዎችን ቤት ውስጥ ማምረትም ጀመረች፡፡
በመነሻዋ ምርቶቿን በቦርሳ አንግባ በጋና አክራ፣ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረች ትሸጥ ነበር፡፡ ሰዎች በምርቶቿ አምነው እንዲገዙ ማድረግ ቀላል አልነበረም፡፡ ቀስ በቀስ ምርቶቿ ዕውቅና አገኙና ኢትዮጵያን ስኪን ቢውቲ ሰክሬት የተባለ መደብር ከፈተች፡፡ የመደብሩን የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ከከፈተች ዘጠኝ ወር ገደማ ሊሆን ነው፡፡
ቸርችል ጐዳና በሚገኘው መደብር ኸርባል ሳሙና (ከሞሪንጋና ኒም የተሠራ)፣ የወተት ሳሙና፣ የማር ሳሙና፣ የቡና ሳሙና፣ የጥቁር አዝሙድ ሳሙና (ለተለያዩ የቆዳ ችግሮች የሚሆን)፣ የሎሚ ሎሽን፣ ከቅቤ የተሠራ የፀጉር ቅባት፣ ከቡናና ስኳር ውህድ የተዘጋጀ ስክራብ፣ የተልባ ሻምፖና ኮንዲሽነር፣ ከበቆሎ ዱቄት የተሠራ ባዝ ቦምብ (ሰውነትን ለማፍታታት)፣ ፕራይቬት ዋሽ (ከማህፀን አካባቢ አላስፈላጊ ባክቴሪያ ለማጥፋት) እና ሺሃ በተር (ጋና ውስጥ ብቻ ከሚበቅል ዛፍ የሚገኝ ቅቤ) ይገኛሉ፡፡
በዓለም ላይ ኸርብ ማለትም ከቅጠላቸው፣ ከፍሬአቸው ወይም ከሥራቸው መድኃኒት አልያም መዋቢያ የሚያዘጋጁባቸው አትክልቶችን የመጠቀም ጥበብ ዘመናትን አስቆጥሯል፡፡ ከሰው ልጅ ሥልጣኔ ጋር ከሚተሳሰሩ ግኝቶች አንዱም ነው፡፡ ጥንታዊት ግብጽ፣ ቻይናና ህንድ በዚህ ጥበብ ስማቸው ከሚነሱ አገሮች መካከል ናቸው፡፡ ለተለያዩ በሽታዎች መድኃኒትነት ከመዋል ባሻገር ለመዋብ የሚጠቅሙት ኸርባሎች (ፅዕዋት)፣ በተለይም በማሽን የተዘጋጁ የውበት መጠበቂያዎች ሳይስፋፉ በፊት ይዘወተሩ ነበር፡፡ ለዘመን አመጣሹ መዋቢያ መሠረትም ናቸው፡፡ ከከተሜነት መስፋፋት ጋር በተያያዘ ከተፈጥሯዊ መዋቢያዎች ውጪ ያሉ አማራጮችን የሚጠቀሙ ቢኖሩም አሁንም ከፅዕዋት በባህላዊ መንገድ ከሚቀመሙ መዋቢያዎች የሚገለገሉ አሉ፡፡
አፍሪካ ላይ ያተኮሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ሺሀ በተር፣ ኮኮናት ኦይልና ኒም በርካታ ተጠቃሚ ያላቸው ተፈጥሯዊ ግብአቶች ናቸው፡፡ መዋቢያዎቹን የሚሸጡ አፍሪካውያን ባለሙያዎች ትርፋማ እንደሆኑም ተመልክቷል፡፡ የዓለም የጤና ድርጅትም የቆዳ መዋቢያዎችን በስፋት ከሚጠቀሙ አኅጉሮች አፍሪካን ይጠቅሳል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥም ተፈጥሯዊ መዋቢያዎችን መጠቀም የዓመታት ታሪክ አለው፡፡ ቅቤ፣ እንሶስላ፣ ሐሪቲ፣ ሐደስ፣ ማር፣ አቡካዶ፣ እርድ የዕንቁላል አስኳልና ሎሚ ከብዙዎቹ ግብአቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እሬት፣ እንስላል፣ ጡንጅት፣ ፌጦ፣ ጦስኝ፣ ደማከሴና ዝንጅብል ደግሞ በመድኃኒትነታቸው የተመረጡ ናቸው፡፡ መዋቢያዎቹን በቤታቸው እያሰናዱ የሚጠቀሙ ብዙዎች ሲሆኑ፣ ለተጠቃሚ በሚመች መንገድ አዘጋጅተው ለገበያ የሚያቀርቡም እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡
አስተያየታቸውን የሰጡን ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፣ ተፈጥሯዊ መዋቢያዎች ካላቸው ጠቀሜታ አንጻር ሸማቹ ብዙ ነው ብሎ ለመደምደም ያስቸግራል፡፡ አንዳንዶች እንደ ምክንያት የሚጠቀሱት፣ የግንዛቤ ውስንነትን ሲሆን፣ ምርቶቹ እንደ ልብ አለመገኘታቸውንም የሚያነሱ አሉ፡፡ በሌላ በኩል አምራቾች ስለመዋቢያዎቹ በቂ መረጃ ከሚሰጥ መግለጫ (ሌብል) ጋር ምርቶቻቸውን ለገበያ አለማቅረባቸው ፈላጊያቸው ጥቂቶች እንዲሆኑ አድርጓል የሚል አስተያየት የሰጡን ነበሩ፡፡
ዮርዳኖስ ‹‹ለምግብነት የሚውሉና ሰዎች ፍሪጅ ውስጥ ያሉ ነገሮችን ሁሉ ወደ መዋቢያነት እንለውጣቸዋለን፤›› ትላለች፡፡ አንድ ምርት ስታዘጋጅ ተፈጥሯዊ ግብአቶችን በማዋሀድ ስለጥቅማቸውና የአገልግሎት ዘመናቸው ጥናት እንደምታደርግም ትናገራለች፡፡ ብዙ ጊዜ ምርቶቿን የምትሞክረው በራሷ ላይ ነው፡፡ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ በማቆየት ውጤታማነታቸውን ትፈትሻለች፡፡ ከቆዳ ውበት ጋር የተያያዘ ችግር ያለባቸው ሰዎች ሲገጥሟት፣ ቀድሞ ካዘጋጀቻቸው ምርቶች የተለየ በመሥራት መፍትሔ ለመስጠት ትሞክራለች፡፡
በፋብሪካ የሚሠሩ ኮስሞቲክሶች የሚይዟቸው ኬሚካሎች ያላቸውን አሉታዊ ጐን ከግምት በማስገባት፣ ተፈጥሯዊ መዋቢያዎች መጠቀም የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ትገልጻለች፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጥሯዊ መዋቢያዎች ዘመናት ቢያስቆጥሩም፣ አንዳንዶቹ ሁልጊዜ ለመጠቀም ስለማይመቹ የሚገለገሉባቸው ሰዎች ውስን ይሆናሉ፡፡ ለምሳሌ ቅቤ ከፍተኛ ጥቅም ቢኖረውም ሽታውን የማይወዱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ስለዚህም ንጥረ ነገሩ እንዳለ ሆኖ ጥሩ መዓዛ እንዲኖረው ተደርጐ ይዘጋጃል፡፡
ከተፈጥሯዊ መዋቢያዎች በበለጠ በፋብሪካ የሚዘጋጁት የተሻለ ገበያ ሲያገኙ ይስተዋላል፡፡ ለዚህም፣ ዮርዳኖስ ተፈጥሯዊ መዋቢያዎች በቀላሉ ገበያ ላይ አለመገኘታቸው ተግዳሮት እንደሆነ ታምናለች፡፡ አቅርቦቱ ቢሰፋ የተጠቃሚዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ትገልጻለች፡፡ በሌላ በኩል አገርኛ ተፈጥሯዊ መዋቢያዎችን የሚያዘጋጁ ሰዎች፣ ስለምርቶቹ ለማወቅ ሲፈለግ በቀላሉ መገኘታቸው እንዲሁም በምርቶቻቸው ተጠያቂነት ያላቸው መሆኑ ገዥዎችን ያበረታታል ትላለች፡፡
‹‹ተፈጥሯዊ መዋቢያዎችን መጠቀም አልተለመደም፡፡ መዋቢያዎቹ በሰው ጉልበት ስለሚሠሩ የሚጠየቅባቸው ገንዘብ ከፍ ማለቱም ገዥዎችን ያሸሻል፤›› ትላለች፡፡ ሰዎች የተለያዩ የውጭ ብራንዶችን የሚያዘወትሩበትና ብራንዶች የአቅም መለኪያ ወይም የማንነት መገለጫ አድርገው የሚወስዱበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ተፈጥሯዊ መዋቢያዎችን አቅርቦ ገበያውን መስበር ፈታኝ ቢሆንም፣ የምርቶቹን ጥቅም በማሳወቅና ዓይን ሳቢ በሆነ መልኩ በማቅረብ ለውጥ እንደሚመጣ ታምናለች፡፡ ‹‹አገራዊ ዕውቀቱ ቤት ውስጥ መቅረት የለበትም፤›› በማለት መዋቢያዎቹ ለዘመኑ በሚመች መልኩ መቅረብ እንዳለባቸው ትናገራለች፡፡
ሌላው ተፈጥሯዊ መዋቢያዎች አምራች ፒካ ኸርባል ትሪትመንት ከተመሠረተ ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ለቆዳና ለጸጉር ውበት ከሚውሉ ምርቶች በተጨማሪ የፀሐይ አለርጂክ፣ ሽፍታ፣ ፎሮፎርና ፈንገስን የመሰሉ ችግሮችን የሚከላከሉ ምርቶች ያቀርባሉ፡፡ ምርቶቹን የምታዘጋጀው ሳምራዊት ካህሳይ በዋነኛነት ኒም እንደምትጠቀም ትናገራለች፡፡ በልጅነቷ የኒም ዛፍ በመኖሪያዋ ግቢ ስለነበር እሷና ቤተሰቦቿ ለተለያዩ መዋቢያዎች መሥሪያ ይጠቀሙት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ ከአስመራ አምጥተው የተከሉትን የኒም ዛፍ በመጠቀም ለፊት፣ ለሰውነትና ለጸጉር እንክብካቤ የሚሆኑ ሳሙናዎችን ይሠራሉ፡፡ ለተፈጥሯዊ መዋቢያዎች ያላትን ፍቅር እንደ ሙያ መስክ ከወሰደች በኋላ፣ ኒምን ከእህል ዘሮች ጋር በማዋሀድ መሥራት ጀመረች፡፡
እሷ እንደምትለው፣ መሰል የአገር ውስጥ ምርቶችን መጠቀም አልተለመደም፡፡ ብዙዎች በምርቶቿ ላይ ያለውን የአማርኛ መግለጫ ሲመለከቱ ‹‹የአገር ውስጥ ምርት አልጠቀምም፤›› የሚል መልስ ይሰጣሉ፡፡ ግንዛቤው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ቢመጣም፣ አሁንም በጐ አመለካከት መዳበር እንዳለበት ትናገራለች፡፡ ምርቶቿን አዲስ አበባ በሚገኙ ፋርማሲዎችና ኮስሞቲክስ መሸጫዎች በየክፍለ ሀገሩም ታከፋፍላለች፡፡
አገር ውስጥ የሚዘጋጁ ተፈጥሯዊ መዋቢያዎች ለገበያ የሚቀርቡባቸው ዕቃዎችና ንጥረ ነገር የሚሰፍርባቸው ወረቀቶች (ሌብል) የሸማቾችን ዓይን እንደማይስቡ ከሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ጋር ብትስማማም፣ ‹‹ዋናው የዕቃው ውበት ሳይሆን የምርቶቹ ጥቅም ነው፤›› ትላለች፡፡ ብዙዎች ከአገርኛ መዋቢያዎች በበለጠ በውጭ ምርቶች የሚያተኩሩት መዋቢያዎቹ ፈጣን ለውጥ ስለሚያሳዩ እንደሆነ ትገልጻለች፡፡ መዋቢያዎቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠቃሚው የሚፈልገውን ውጤት ቢያመጡም፣ በውስጣቸው የሚገኙ ኬሚካሎች ጉዳት አስጊ እንደሆነ ታስረዳለች፡፡
ዘርፉ እንዲያድግ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ከመለወጥ ጐን ለጐን በተፈጥሯዊ መዋቢያዎች ዝግጅት ዝንባሌ ያላቸው ግለሰቦች አገር ውስጥ ትምህርት የሚያገኙበት መንገድ መፈጠር እንዳለበት ትናገራለች፡፡ በዘርፉ ዓመታትን ያስቆጠሩ ባለሙያዎች ዕውቀታቸውን የሚያካፍሉባቸው ተቋሞች ቢከፈቱ መልካም ነው ስትልም ታሳስባለች፡፡
ተፈጥሯዊ መዋቢያዎችን ለማስተዋወቅ በሚል በቅርቡ የተዘጋጀ ኤክስፖ ነበር፡፡ የኤክስፖው አዘጋጅ ድርጅት ግሬአትሮ ፕሮሞሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መርጀን አህመድ፣ አስተያየታቸውን የሰጡን አምራቾችን ሐሳብ በከፊል ይጋራል፡፡ በዘረፉ ያሉትን ችግሮች ለማቃለል ኤክስፖውን ማዘጋጀት እንዳስፈለገ ጠቅሶ፣ አገርኛ መዋቢያዎችን የመጠቀም ፍላጐት ያላቸው ሰዎች ጥቂት ከመሆናቸው በላይ የአምራቾቹ አቀራረብ ገበያ ተኮር የማይሆንበት ጊዜ አለ ይላል፡፡ በተፈጥሯዊ መዋቢያዎች አምራቾችና ኅብረተሰቡ መካከል ጠንካራ የገበያ ትስስር መፈጠር እንዳለበትም ያስረዳል፡፡ ከአስተሻሸግ ጀምሮ ገበያ ላይ ሲቀርቡ በማስተዋወቅና ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ መሠራት እንዳለበትም ያክላል፡፡
የ45 ዓመቷ የቤት እመቤት ወ/ሮ ኤደን በላይ፣ ተፈጥሯዊ መዋቢያዎችን እየገዙ ከሚጠቀሙ መካከል ናቸው፡፡ ፊታቸው ላይ የነበረባቸውን ማድያትና ግንባራቸው ላይ የነበረባቸውን ጥቁር ምልክት ለማጥፋት ነበር የጀመሩት፡፡ ከተለያዩ የተፈጥሮ ግብአቶች የተሠሩ ሳሙናዎችና ቅባቶች መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ቆዳቸው ላይ ለውጥ እንዳስተዋሉ ይናገራሉ፡፡ ከቅቤ የተሠራ ቅባትና ትሪትመንትም ጸጉራቸውን ይቀባሉ፡፡
እሳቸው እንደሚናገሩት፣ ተፈጥሯዊ መዋቢያዎች ተአማኒ ናቸው፡፡ እንደተመረቱ በገበያ ስለሚውሉም በቆይታ ብዛት ከሚበላሹ ምርቶች በተሻለ ይጠቅማሉ፡፡ የንጥረ ነገሮቹንና አምራቾቹ ሕጋዊ ፈቃድ እንዳላቸው አረጋግጦ መጠቀምን ይመርጣሉ፡፡
የ23 ዓመቷ ሰናይት ጥጋቡ በበኩሏ፣ ከተለያዩ አገሮች የሚመጡ መዋቢያዎችን ትገለገላለች፡፡ ኦርጋንዛ ሻምፖና ኮንዲሽነር፣ ቪክቶሪያ ሴክሬት ሎሽንና ላይፍቦይ ሳሙና ታዘወትራለች፡፡ እነዚህን ምርቶች ለማግኘት ስለሚቀላት እንደምትመርጣቸው ትናገራለች፡፡ እንደ ነጭ ሽንኩርት ካሉ ግብአቶች የሚዘጋጁ ተፈጥሯዊ መዋቢያዎች እንዳሉ ብታውቅም፣ ትኩረት አትሰጣቸውም፡፡ በሰዎች ጥቆማ ህንድ አገር የተሠራ የእርድ ሳሙና ለፊቷ መጠቀም ብትጀምርም፣ ከዛ ውጪ ያሉትን የተፈጥሮ መዋቢያዎች ሞክራ አታውቅም፡፡
አንዳንዶች ተፈጥሯዊ መዋቢያዎችን ቤታቸው አዘጋጅተው ይጠቀማሉ፡፡ የ26 ዓመቷ ሰዓዳ ጀማል፣ ከተለያዩ ድረ ገጾች መረጃ እየሰበሰበች በቤቷ መዋቢያ ታዘጋጃለች፡፡ ዕንቁላል፣ አቮካዶ፣ ስኳርና ሎሚ ከምትገለገልባቸው ጥቂቱ ናቸው፡፡ የጀመረችው ብጉር ለማጥፋት ሲሆን፣ ንጥረ ነገሮቹ ከሚፈለገው መጠን በላይ ሆነው ጉዳት እንዳያደርሱ አቀማመማቸውን ከድረ ገጽ ታነባለች፡፡ መዋቢያዎቹን ዕለት በዕለት ባለመጠቀሟ ለውጥ እንዳላሳዩ ትናገራለች፡፡ አሁን በፋብሪካ የተመረተ ክሬም መጠቀም ጀምራለች፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ሐሳብ የሰጠን ዶ/ር ይሄይስ አበበ የባህል ወይም የተፈጥሮ የሚባሉ ንጥረ ነገሮች ቆየት ያለ ታሪክ እንዳላቸውና ከትውልድ ትውልድ፣ ከአገር አገር እየተሸጋገሩ እንደመጡ ይናገራል፡፡ ምንጮቹም እንስሳት፣ ዕፅዋት፣ ድንጋይ፣ አፈር፣ ውኃ፣ የፀሐይ ብርሃንና እሳት የመሳሰሉ ማዕድኖች ናቸው፡፡ ‹‹በዓይነቱ፣ በጥራቱ፣ በይዘቱና በፈዋሽነቱ ከጥንት ጀምሮ እስካለንበት ዘመን ድረስ ራሱን እያሻሻለ የሚገኝ የሕክምና ጥበብ ነው፤›› በማለት ፍቱንነታቸውን ይገልጻል፡፡ ለዘመናዊው ሕክምና መነሻ እንደሆኑና የዓለም የጤና ድርጅት በሁሉም አገሮች (በተለይ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች) ሥርዓተ ጤና ውስጥ ሳይንሳዊ እገዛ እየተሰጠው በተግባር እንዲውል እንደሚያበረታታም ያክላል፡፡
ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ የተፈጥሮ መዋቢያዎች እንደ ሌሎች የኮስሞቲክስ ዓይነቶች ጥንቃቄ ይሻሉ፡፡ የሚዋሀዱት ንጥረ ነገሮች መጠን፣ አገልግሎት ላይ የሚውሉበት ጊዜና የተጠቃሚዎች የቆዳ ዓይነት ከግምት መግባት እንዳለባቸውም ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ ቁጥጥር ባለሥልጣን ተፈጥሯዊ መዋቢያዎችን እያዘጋጁ ለመሸጥ ከመሥሪያ ቤቱ ፈቃድ የሚጠይቁ ግለሰቦች የሚስተናገዱበት መመርያ እንዳለው የመሥሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ በኃይሉ ንጉሤ ይናገራል፡፡ ምርቶቹ ከሚዘጋጁበት ቦታ ጀምሮ፣ የባለሙያዎቹ ብቃትና አቀራረብ ይመዘናል፡፡ ብቁ መሆናቸው ተረጋግጦ ፈቃድ ከተሰጠ በኋላም፣ በድንገተኛ ፍተሻ ከምርቶቹ ናሙና ተወስዶ በቤተ ሙከራ ይመረመራሉ፡፡ ከደረጃ በታች የሆኑት ባደረሱት ጉዳት መጠን ከገበያ ማገድ፣ የጊዜ ገደብ ሰጥቶ ችግሩን መፈተሽ ወይም ወደ ሕግ የማቅረብ ዕርምጃ ይወሰድባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ተጠቃሚዎች ቅሬታ ሲኖራቸው ጥቆማ የሚያደርሱበት የስልክ መስመር ያለ ሲሆን፣ በጥቆማዎቹ መሠረት ክትትል እንደሚያደርጉም ይገልጻል፡፡