በከተሞች እየታዩ ያሉ የጤና ችግሮችን በተቀናጀ መንገድ መፍታት ይቻል ዘንድ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤትና ኅብረተሰብ ጤና ላይ የሚሠራው ጄኤስ አይ (JSI) የጋራ ትብብር የከተማ ጤና አማካሪ ቡድን ረቡዕ ጥር 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ተቋቋመ፡፡ አማካሪ ቡድኑ በተመሠረተበት ዕለት በዘውዲቱ ሆስፒታል የሚገኘው የኢትዮጵያ የከተማ ጤና ልማት ማዕከልም በይፋ ተከፍቷል፡፡ ባለፉት ጥቂት አሠርታት በኢትዮጵያ የታየው የከተሞች መስፋፋትና ከተሜነት በተለያየ መልኩ ያስከተላቸው የጤና ሥጋቶች በመኖራቸው ይህ አማካሪ ቡድን የከተማ የጤና ሥጋቶችን በመለየት፣ ጥናት በማድረግና ውይይት በማካሄድ የፖሊሲና ስትራቴጂ ግብዓት እንደሚያቀርብ በኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት መምህርና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ሚርጊሳ ካባ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በአገሪቱ የከተሞች መስፋፋት ከመሠረተ ልማት መስፋፋት ጋር አብሮ እየተራመደ ባለመሆኑ የተለያዩ የጤና ሥጋቶችን እያስከተለ መሆኑ በተለያዩ ጥናቶች ተመልክቷል፡፡ ከእነዚህ ያልተሟሉ መሠረተ ልማቶች የውኃና የንፅህና አገልግሎት አቅርቦት፣ የምግብ ዋስትና የጤናና የማኅበራዊ አገልግሎት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ የዚህ አሉታዊ ተፅዕኖውም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኙ የከተማ ኗሪዎች ላይ የሚበረታ ሲሆን፣ እንደ ቲቢ ላሉና ለሌሎች ውኃ ወለድ በሽታዎች መባባስ ምክንያት ነው፡፡ የከተማ ጤና ጉዳይ ዘርፈ ብዙ በመሆኑም ብሔራዊ የከተማ ጤና አማካሪ ቡድኑ እንደ ከተማና ቤቶች ልማት ሚኒስቴር፣ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት፣ የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣንና ትምህርት ሚኒስቴርን የመሰሉ ተቋማት ተወክለውበታል፡፡ በሌላ በኩል የሚመለከተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ፣ የከተማ ጤና የሚመለከታቸው ተቋማት፣ በጤና ላይ የሚሠሩ በጐ አድራጐት ተቋማት፣ ለጋሾች፣ በከተማ ጤና ጉዳዮች የካበተ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች እንዲሁም መገናኛ ብዙኃን የቡድኑ አባል እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡ ቡድኑ የፖሊሲና ስትራቴጂ ሐሳቦችን ከማቅረብ በተጨማሪ በተለያዩ የከተማ ጤና ጉዳዮች ላይ የተሠሩ ጥናቶችን እንዲሁም ሌሎች መረጃዎችን በየጊዜው ለባለድርሻ አካላትና ለመገናኛ ብዙኃን እንዲደርስ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡ የአገሪቱን የከተማ ጤና ፕሮግራም ዳግም በማጤን ክፍተቶችን መለየትና የመፍትሔ ሐሳብ መጠቆም፣ የከተማ የጤና ፕሮግራም በማውጣት ረገድ ያሉ ጉድለቶችን መለየት፣ ከከተማ ጤና ጋር በተያያዘ የተሠሩ ሥራዎችን መሠነድና የከተማ ጤና ላይ የሚሠሩ ጥናትና ምርምሮች ደረጃቸው የጠበቁ እንዲሆኑ ማድረግም ከአማካሪ ቡድኑ የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው፡፡