Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከዋናው ልምምድ ባሻገር

ከዋናው ልምምድ ባሻገር

ቀን:

ዋና ከረዥም ዘመናት በፊት የተጀመረ ስፖርት ቢሆንም፣ ብዙ ሳይለመድ ቆይቷል፡፡ ቀስ በቀስ እየተለመደ ሲመጣ ግን እንደ አንድ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በብዙዎች ይዘወተር ጀመረ፡፡ የኋላ ኋላም እ.ኤ.አ. በ1830ዎቹ አካባቢ ከመወዳደሪያ ስፖርቶች መካከል ሆነ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላም ከኦሊምፒክ ስፖርቶች አንዱ ለመሆን በቃ፡፡ ይኽም ይበልጥ እንዲታወቅ ዕድል ፈጠረለት፡፡ ካለው በርካታ የጤና ጥቅሞች አንፃር እንዲሁም በመዝናኛነት በብዙዎች ይዘወተርም ጀመረ፡፡

በአገር ውስጥ ይህን ያህል ተለምዷል ባይባልም በባህር ዳር፣ በሐዋሳ፣ በደብረ ዘይትና በሌሎችም ሐይቆች ባሉባቸው ከተማዎች ነዋሪዎች  ዋናን ያዘወትራሉ፡፡  

በውኃ ላይ ለመንሳፈፍ በራስ መተማመንና አካልን ዘና አድርጎ መልቀቅ ግድ ይላል፡፡ ዕውነታውን ተቀብሎ በተግባር ላይ ለማዋል ግን የቀናት ልምምድ ይጠይቃል፡፡ ዋና ጀማሪዎች ከገንዳ ሲገቡ በመኖርና ባለመኖር መካከል እንዳሉ  እንደሚሰማቸው ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን አስበው ልምዱ ባላቸው አሠልጣኞች መሠልጠንን የሚመርጡ እንዳሉ ሁሉ፣ በባለሙያ ከመሠልጠን ይልቅ ሌላ ዋና የሚችል ሰው እንዲያሠለጥናቸው የሚያደርጉም አሉ፡፡

 በዚህና በሌሎች የመስጠም አደጋ ደርሶባቸው ሕይወታቸው የሚያልፍ ወይም  ጉዳት የሚደርስባቸው ጥቂት አይደሉም፡፡ ይህ ሁኔታ ለነፍስ አንድን ሠራተኞች ሌላ ጫና ነው፡፡ ወደ መዋኛ ገንዳ የሚመጡ ደንበኞችን ለሰዓታት በንቃት መከታተል የሕይወት አንድን ሠራተኞቹ ግዴታ ነው፡፡ በግድ የለሽነት የሚዋኙ ሰዎች መብዛትም ሥራቸው በሥጋት የተሞላ እንዲሆን አድርጓል፡፡

ውኃ ዋናን ከመዝናኛነት ባለፈ አስቦት አያውቅም፡፡ ተወልዶ ያደገው  ባህርዳር ከተማ ሲሆን፣ ዋና የጀመረው ደግሞ በጣና ሐይቅና በዓባይ ወንዝ ላይ ነበር፡፡ የዳበረ የዋና ክህሎት ስለነበረውም በስፖርቱ ለማደግ ብዙ አልተቸገረም፡፡ ቅልጥፍናውን የተመለከቱ አንድ የዋና አሠልጣኝ አብሯቸው እንዲሠራ ጠየቁት፡፡ ሳያቅማማም እሺታውን ገለጸላቸው፡፡

 የተለያዩ የዋና ቴክኒኮችን ሲያስተምሩትም ውኃ ዋና ከመዝናኛነት ባለፈ እንጀራው እንደሚሆን ገባው፡፡ በ1976 ዓ.ም. ላይም ለመጀመርያ ጊዜ በአካባቢው ከሚገኙ ዋናተኞች ጋር ተወዳደረ፡፡ ጀማሪው እስከዳር አቻምየለህ፣ ውድድሩን አንደኛ ሆኖ አጠናቀቀ፡፡ አጋጣሚው በራሱ እንዲተማመን ከማድረጉም ባሻገር የበለጠ እንዲሠራ ሞራል ሆነው፡፡ ይኸም ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ እንዲበቃ መሠረት ሆኖታል፡፡ ባህርዳር በሚገኘው ፓፒረስና በግዮን ሆቴል የሕይወት አድን ሠራተኛ ሆኖ አገልግሏል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በቦሌ ሮክ ሆቴል በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም የብሔራዊ የውኃ ዋና ቡድን አሠልጣኝ እንደሆነ ይናገራል፡፡

 የልብ ችግር፣ የሚጥል በሽታ ላለባቸው እንዲሁም የስኳርና የግፊት ታማሚዎች ዋና አጥብቆ አይመከርም፡፡ በሌላ በኩልም ምግብ እንደተመገቡ መዋኘት ለከፋ አደጋ ስለሚያጋልጥ ምግብ በልቶ መዋኘት ይከለከላል፡፡ ይሁን እንጂ ባለማወቅ ወይም በሌላ ማሳሰቢያዎቹን የሚተላለፉና ለከፋ አደጋ የሚጋለጡ አሉ፡፡ እስከዳር በዚህ ረገድ በርካታ ገጠመኞች አስተናግዷል፡፡ አንደኛውንም እንዲህ ያስታውሳል፡፡

ከዓመታት በፊት ይሠራበት በነበረው ሆቴል ውስጥ ነው፡፡ በሆቴሉ የቀናት ወርክ ሾፕ የተዘጋጀ ሲሆን፣ የወርክሾፑ አዘጋጅ፣ ለተሳታፊዎቹ አልጋ የያዘው እዚያው ሆቴሉ ውስጥ ነበር፡፡ ከወርክሾፑ መልስም አብዛኛዎቹ ተሳታፊዎች የዋና ትጥቃቸውን በመያዝ ወደ መዋኛ ገንዳው ሄዱ፡፡ ትጥቃቸው ግን ለዋና የተመቸ አልነበረም፡፡ ብዙዎቹ የለበሱት ለዋና የማይመከር ሰፋ ያለ ቁምጣ ነበር፡፡

 እስከዳርም ልብሳቸው ለዋና ያልተመቸ መሆኑን ቀይረው እንዲመለሱ ነገራቸው፡፡ ከአንደኛው በስተቀር ሁሉም ተስማምተው ልብስ ለመቀየር ተመለሱ፡፡ ልብሱን ለመቀየር ፈቃደኛ ያልነበረው ግለሰብም ለመዋኘት ወደ ገንዳው ተጠጋ፡፡ እስከዳርም እንዳይገባ አስጠነቀቀው፡፡ ከገንዳው ጎን ቆሞ ያደፍጥ ጀመረ፡፡ ነገሩ ያልገባው እስከዳር በዓይኑ ይከታተለውም ያዘ፡፡ በመካከል ሌሎቹን ዋናተኞች ለመመልከት ዘወር ብሎ ሲመለስ ግን ግለሰቡ ከነበረበት ቦታ አጣው፡፡

ምናልባት ወደ መልበሻ ክፍል ሄዶ ይሆናል በሚል መልበሻ ቤቶቹ ውስጥ ፈለገው፡፡ ሊያገኘው ግን አልቻለም፡፡ ገንዳው አካባቢ የነበሩ ሰዎችን ቢጠይቅም ልብ እንዳላሉ  ነገሩት፡፡ በሁኔታው ግራ ተጋብቶ የገንዳውን የውስጠኛ ክፍል በአትኩሮት ይመለከት ገባ፡፡ ወለሉ ላይ የተኛ ሰውም ተመለከተ፡፡ ወዲያው ገንዳው ውስጥ በመጥለቅ ራሱን ስቶ የተኛውን ግለሰብ ጎትቶ አወጣው፡፡ የደረሰበት ጉዳት ከፍተኛ ስለነበር ዕርዳታ ቢያደርግለትም በቶሎ ሊነቃ አልቻለም፡፡ ሆስፒታል ገብቶ በሕክምና ሲረዳ ሰንብቶ በሦስተኛው ቀን ነቃ፡፡

‹‹በዋና ላይ ያለ አንድ ሰው ሕይወቱን ቅድሚያ ራሱ ሊጠብቅ ይገባል፤›› የሚለው እስከዳር፣ ብዙዎች ዋና ተለማማጆች የሕይወት አድን ሠራተኞች ይረዱናል፣ ሰው ይደርስልናል በሚል በድፍረት ገንዳ ውስጥ እንደሚገቡና ለአደጋ እንደሚጋለጡ  ይናገራል፡፡ ጥቂት የማይባሉ የጤና ችግር ያለባቸውም፣ ለማሳሰቢያ ቦታ ሳይሰጡ ገንዳው ውስጥ በመግባት ለአደጋ ይጋለጣሉ፡፡ ሕመማቸውን ደብቀው የሚገቡና ድንገት የሚሰምጡም አሉ፡፡ ‹‹የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች በሚዋኙበት ጊዜ ራሳቸውን ስተው ይወድቃሉ፡፡ አጋጣሚውን ከሌላው የከፋ የሚያደርገው በዚህ መልኩ የሚሰምጡ   ምንም ዓይነት ምልክት ስለማያሳዩ ሰው ሳይደርስላቸው ለሞት የሚዳረጉበት አጋጣሚ ሰፊ መሆኑ ነው፤›› ይላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አሳዛኝ ገጠመኝ አስተናግዷል፡፡

ከዓመታት በፊት ነው፡፡ አንድ የሚጥል በሽታ ያለበትና መድኃኒት በመከታተል ላይ ያለ ወጣት፣ ከጓደኞቹ ጋር ለመዋኘት እስከዳር ወደሚሠራበት ሆቴል ይሄዳል፡፡ መድኃኒቱን ሳይወስድ ከመምጣቱ ባሻገር፣ ገንዳው አካባቢ የተለጠፈው ማሳሰቢያ ቢኖርም፣ ገንዳው ውስጥ ገብቶ ብዙም ሳይቆይ ራሱን ስቶ በጀርባው ወደቀ፡፡ ወዲያውም ሕይወቱ አለፈ፡፡

በሌላ በኩል ምግብ ተመግቦ መዋኘት ክልክል ቢሆንም ማሳሰቢያውን ከምንም ባለመቁጠር ለመዋኘት በሚያደርጉት ጥረት የሚታመሙና ሕይወታቸው የሚያልፍም ያጋጥማሉ፡፡ ይህ በብዛት በመዋኛ ገንዳው አካባቢ የሚለጠፉ ማሳሰቢያዎችን ካለማንበብ አንፃር የሚፈጠር እንደሆነ ይናገራል፡፡ ‹‹ብዙዎቹ ማሳሰቢያው ምን መሆኑን አያውቁም፡፡ ለማንበብም ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ጠይቆ ለመረዳትም መጠየቅ ያለበት ዋና የማይችል ብቻ አይደለም፡፡ ልምዱ ያለው ሰውም ቢሆን ስለ ገንዳው ጥልቀት ሊጠይቅ ይገባል፡፡ ነገር ግን የመጠየቅ ልምዱ ባለመኖሩ ተወርውረው የሚገቡና ከወለሉ ጋር ተጋጭተው ጉዳት የሚደርስባቸው አሉ፤›› ሲል ማንኛውም ዋናተኛ ወደ ዋና ገንዳ ከመግባቱ አስቀድሞ ማሳሰቢያዎችን በማንበብ ወይም ባለሙያዎችን ጠይቆ በመረዳት ራሱን መጠበቅ እንደሚገባው ይመክራል፡፡

ውኃ ዋና ቀላል ነው በሚል አሠልጣኝ ሳይቀጥሩ ልጆቻቸው ገንዳ ውስጥ እንዲገቡ የሚያደፋፍሩ ወላጆች መኖር፣ ሕፃናት ላይ አደጋ እንዲፈጠር ምክንያት ሲሆን ይታያል፡፡ በሌላ በኩልም ዋና የሚችል ማንኛውም ሰው ማሠልጠን ይችላል በሚል እሳቤ እንዲያሠለጥናቸው በማድረግም አደጋ የሚገጥማቸው አሉ፡፡ ‹‹ዋና መቻል ብቻ አሠልጣኝ ለመሆን ብቁ አያደርግም፡፡ ለአሠልጣኞች ራሱን የቻለ ትምህርት አለ፡፡ ሰው ለማዳን የተለያዩ ቴክኒኮችን መጠቀም ግድ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን ሳይረዱ ዋና የሚችል ሰው ማሠልጠን እንደሚችል የሚያስቡ ብዙ ናቸው፤›› ሲሉ ቅሬታ የሚያሰሙ አሉ፡፡

ባህርዳር ከተማ ተወልዶ ያደገው ደሳለኝ ባየ፣ ውኃ ዋና የጀመረው በጣና ሐይቅ ሲሆን፣ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት በመማርም ሙያውን አዳብሮታል፡፡ በሕይወት አድን ሙያ መሥራት ከጀመረ ዘጠኝ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በኢተርኮንቲኔንታል ሆቴል ያገለገለ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት በሞናርክና በሐርመኒ ሆቴል በጅምና በዋና አሠልጣኝነት፣ እንዲሁም በሕይወት አድን ሙያ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡

ስፖርት ሳይንስ መማሩ ዋናን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለደንበኞቹ እንዲያስረዳ  ረድቶታል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ጀማሪዎች፣ አሠልጣኝ ቀጥረው ለመሠልጠን ፍላጎት እንደሌላቸው ሆኖም ተገቢውን የዋና ክህሎት ለማዳበር የአሠልጣኞች ዕርዳታ እንደሚያስፈልግ ይናገራል፡፡ ክፍሎት የሌላቸው ዋና ገንዳ ውስጥ የገቡትን ለመታደግም ከነልብሱ ገንዳ ውስጥ ገብቶ ሕይወት ለማትረፍ ሞክራል፡፡

ተመሳሳይ አጋጣሚዎች ሰዎች ዳግመኛ ውኃ እንይጠጉ ምክንያታዊ ያልሆነ ሥጋት ሲፈጥርባቸው ይስተዋላል፡፡ በዚህም ብዙዎች ከዋና ራሳቸውን ያርቃሉ፡፡ ደሳለኝ ግን መሰል ሥጋቶች እንዳይፈጠሩ ችግሩ የተከሰተው ከልምምድ ማነስ እንደሆነ፣ ይህም የተለያዩ ቴክኒኮችን በመጠቀም የሚቀረፍ መሆኑን ለማስረዳት ይሞክራል፡፡ በዚህም ደጋግመው እንዲሞክሩና ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ብዙዎችን መርዳት ተችሏል፡፡

ሕይወት ለማዳን የሚያደርጉት ሩጫ የራሳቸውን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥልበት አጋጣሚም አለ፡፡ የ41 ዓመቱ ሳምሶን አሰፋ ዋና የጀመረው የአምስት ዓመት ልጅ ሳለ ነበር፡፡ ጥሩ የዋና ችሎታ ስለነበረው በብሔራዊ የዋና ቡድን ተሰላፊ ነበር፡፡ በ1997 ዓ.ም. የሕይወት አድን ሥልጠና በመውሰድ በአንድ ባለ ሦስት ኮከብ ሆቴል ውስጥ በሙያው ማገልገል ከጀመረ ቆይቷል፡፡

በርካታ ሥልጠናዎችን አግኝቷል፡፡ ይህም ሥራውን ይበልጥ አቅልሎለታል፡፡ ‹‹ዋና የማይችሉ ሰዎችን ሁኔታቸውን በማየት መለየትና ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ይቻላል፤›› በማለት በተለያዩ ጊዜያት የወሰዳቸው ሥልጠናዎች በሰዎች ላይ የሚደርሱትን አደጋዎች አስቀድሞ ለመከላከል እንዲችል እንደረዳው ይናገራል፡፡

በዚህ የሚደርሱ አደጋዎችን መቀነስ ቢሞከርም ከአቅም በላይ በሆኑ አጋጣሚዎች አደጋዎች ይከሰታሉ፡፡ በአንድ ወቅትም በፍጥነት ደርሶ ሕይወት የማትረፉን ኃላፊነት ሲወጣ የራሱ ሕይወት አደጋ ውስጥ የገባበት አጋጣሚ ተፈጥሮ እንደነበርም ያስታውሳል፡፡

ሴትዮዋ ዋና ብትችልም ጥልቀት ያለው ቦታ ላይ ስትደርስ እሰጥም ይሆናል በሚል ሥጋት ትርበተበታለች፡፡ በመሆኑም የምትዋኘው ጥልቀት በሌላቸው ቦታዎች ጥግ ጥግ ላይ ነበር፡፡ ነገር ግን በአጋጣሚ ሳይታወቃት ጥልቅ ከሆነው ቦታ ላይ ደረሰች፡፡ ተደናግጣም ሚዛኗን ሳተች፡፡ እጅና እግሮቿ ሥራቸውን አቆሙ፡፡ ሁኔታውን ከርቀት የተመለከተው ሳምሶን ሕይወት የማዳኑን ሥራ ቅድሚያ በመስጠት ልብሱን ሳያወልቅ ዘሎ ከገንዳው ገባ፡፡

የለበሰችው ታይት ያሟልጨው ስለነበር በቀላሉ ሊይዛት አልቻለም፡፡ እንደምንም አድርጎ ቢይዛትም ትንፋሽ ያጥረው ጀመረ፡፡ ሴትዮዋ ነፍሷን ለማዳን ስትፍጨረጨር የለበሰውን ባለኮፍያ ሹራብ ከአገጩ ሥር አስገብታው ኖሯል፡፡ ውኃ ያዘለው ሹራቡ ፊቱ ላይ በመጠምጠሙ አየር ማስገባት ማስወጣት ተሳነው፡፡ በመሆኑም ለአፍታ እሷን ትቶ ራሱን ለማዳን ተገደደ፡፡ ሹራቡን ከፊቱ አላቅቆ አየር ከሳበ በኋላ ሴትዮዋን ተሸክሞ ያወጣበትን አጋጣሚ አይረሳውም፡፡

‹‹ሥራዬን በጣም እወደዋለሁ፤›› የሚለው ሳምሶን፣ በተለያዩ አካባቢዎች ለመዝናናት ሲሄድ አዕምሮው እንደማያርፍ ምናልባት አደጋ ሊደርስ ይችላል በሚል የሚዋኙ ሰዎችን በዓይነ ቁራኛ እንደሚጠባበቅ ይናገራል፡፡

በብዛት በሕይወት አድን ሥራ የተሰማሩት ወንዶች ቢሆኑም፣ አንዳንድ ሴቶችም አሉ፡፡ ሳምራዊት ደመቀ ትባላለች፡፡ ተወልዳ ያደገችው ኮምቦልቻ ከተማ ሲሆን፣ ዋና የጀመረችው በልጅነቷ ነበር፡፡ በተለያዩ ብሔራዊና ዓለም አቀፍ ውድድሮች የመሳተፍ ዕድሉን አግኝታለች፡፡ በ2007 ዓ.ም. ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በሕግ ተመርቃለች፡፡

ሥራ በማፈላለግ ጊዜ አልፈጀችም፡፡ ተመርቃ ብዙም ሳትቆይ ነበር በሐርሞኒ ሆቴል በሕይወት አድን ሙያ የተቀጠረችው፡፡ በቆይታዋ አደጋ ባያጋጥማትም፣ አንዳንድ ለዋና የሚያስፈልገውን መስፈርት ሳያሟሉ ‹‹እንዋኛለን›› በማለት ሰጣ ገባ ውስጥ የሚገቡ ሰዎች መኖራቸውን ትናገራለች፡፡ ‹‹ገንዳ ውስጥ ለመግባት በቅድሚያ ሻወር መውሰድ ግድ ነው፡፡ ነገር ግን አንታጠብም የሚሉ፣ ሳይታጠቡ ታጥበናል ብለው ዋሽቶ ለማለፍ የሚሞክሩ ኮፍያ የሚያደርጉ ብዙ ናቸው፤›› ትላለች፡፡

በመዋኛ ገንዳ ውስጥ በሚያጋጥማችው የመስጠም አደጋ ሕይወታቸውን ያጡ ጥቂት አይደሉም፡፡ ብዙ ጊዜም በቦታው የነበሩ የሕይወት አድን ሠራተኞች ላይ ክስ ሲመሠረትና ሲታሰሩ ይስተዋላል፡፡ ይህም የብዙዎቹ ሕይወት አድን ሠራተኞች ገጠመኝ ነው፡፡ አንድ የሕይወት አድን ሠራተኛ በገንዳ ውስጥ ለሚደርሱ አደጋዎች ኃላፊነት መውሰድ የሚገባው አደጋው የተከሰተው በራሱ ስህተት ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በተቋሙ ችግር ወይም በግለሰቡ ችግር የሚደርሱ አደጋዎች አሉ፡፡ ለዚህም ሁሉም የሕግ  ኃላፊነት ሊከፋፈል ይገባል፡፡ ነገር ግን ባለው የአሠራር ችግር ተጠያቂ እየተደረገ ያለው የሕይወት አድን ሠራተኛው ብቻ ነው፡፡ ችግሩን መቅረፍ የሚቻለውም የውኃ ዋና ፌዴሬሽን ኃላፊነቱን ወስዶ ሲሠራ ብቻ እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራችው የሕይወት አድን ሠራተኞች ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳ ጥያቄው ተገቢ ቢሆንም፣ ካለው የአሠራር ክፍተት አንፃር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የውኃ ዋና ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ጉዳዩን በቅርበት ለመከታተልና ለመቆጣጠር አሠራሩ እንደማይፈቅድለት የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳዊት ትርፉ ይናገራሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት የመዋኛ ገንዳዎቹ የሚገኙት በሆቴሎች ሥር በመሆኑ፣ ሆቴሎችን የሚቆጣጠረውና ፈቃድ የሚሰጠው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው፡፡  ፌዴሬሽኑ ከዋና ጋር በተያያዘ ያለውን ሁኔታ ለመቆጣጠርና ክትትል የማድረግ ሥልጣኑ የለውም፡፡  ይህም ችሎታ የሌላቸው የሕይወት አድን ሠራተኞች እንዲቀጠሩ፣ አደጋዎች እንዲፈጠሩ፣ በተቋሞቹ ችግር በሚፈጠሩ አደጋዎች የሕይወት አድን ሠራተኞች ኃላፊነት እንዲወስዱና ለመሳሰሉት ችግሮች መፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ ይሁን እንጂ ክፍተቱን ተቀናጅቶ በመሥራት ለመሙላት ጥረት እየተደረገ መሆኑንና በቅርቡ መፍትሔ ላይ እንደሚደረስ አቶ ዳዊት ገልጸዋል፡፡

  

 

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...