በየዓመቱ በወርኃ ኅዳር ከ40,000 በላይ ተሳታፊዎች የሚካፈሉበት የአዲስ አበባው ታላቁ ሩጫን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ሩጫን ብቻ ሳይሆን ጠቃሚ መልዕክቶች ለኅብረተሰቡ በማድረስ የሚታወቀው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፣ ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ ‹‹ለጾታ እኩልነት በጋራ እንቁም›› በሚል መሪ ቃል የሚያከናውነው 5 ኪሎ ሜትር የሴቶች ሩጫ በአዲስ አበባ መገናኛ ዳያስፖራ አደባባይ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ባለፈው ረቡዕ ጥር 25 ቀን 2008 ዓ.ም. በጎልደን ቱ ሊፕ ሆቴል በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የኅብረተሰቡ ግማሽ አካል የሆኑት ሴቶች በተለያዩ መስኮች ለሚያስመዘግቡት ስኬት እውቅና በመስጠት ሁለንተናዊ ተሳትፎዋቸውን በማበረታታት ለተከታታይ 12 ዓመታት ‹‹ቅድሚያ ለሴቶች›› በሚል መሪ ቃል ውድድሮችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ለ13ኛ ጊዜ ለማከናወን ዝግጅቱን ያጠናቀቀ መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡
የካቲት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደሚካሄድ በሚጠበቀው 5 ኪሎ ሜትር የሴቶች ሩጫ ላይ ከአሥር ሺሕ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚካፈሉ፣ በውድድሩ ላይም የለንደን ኦሊምፒክ የማራቶን አሸናፊዋን ቲኪ ገላናን ጨምሮ አሰለፈች መርጊያ፣ ሰንበሬ ተፈሪና በአጠቃላይ ከ200 በላይ የክለብና በግላቸው የሚሮጡ አትሌቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡
ሩጫውን ፕላን ኢንተርናሽናል ‹‹ሴት ነኝና›› በሚል ተጨማሪ መሪ ቃል ስፖንሰር እንደሚያደርገው ተነግሯል፡፡ ድርጅቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶችን ከድህነት አረንቋ ለማውጣት በተለይ ልጃገረዶችን በማበረታታት ሥራ ላይ መሰማራቱን የፕላን ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ ዳይሬክተር ማኖም ከመርም በጋዜጣዊ መግለጫው፣ ሴቶች መማር፣ መምራት፣ መወሰንና ማደግ የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ በሴቶች የተቋቋመው እናት ባንክም ሌላው የሩጫው ስፖንሰር መሆኑ ተነግሯል፡፡
በውድድሩ ተሳታፊ መሆን የሚያስችለው ምዝገባው ከሰኞ ጥር 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በባንኩ ሁለት ቅርንጫፎች እንደሚጀመር ዝግጅት ክፍሉ አስታውቋል፡፡ የአንድ ቲሸርት ዋጋ 120 ብር ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡