Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየእግዚአብሔርን ለቄሳር የመስጠት ልማድና አደጋው

የእግዚአብሔርን ለቄሳር የመስጠት ልማድና አደጋው

ቀን:

ጥር 29 ቀን 2008 ዓ.ም. የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ወደ ቀደመ ሥፍራ መመለሱን ሳስብ የአቡኑ ታሪክ፣ ሰብዕናና አገር ወዳድነት ትውስ አለኝ፡፡ ጊዜውን የኖርኩት መሰለኝ፡፡ 80 ዓመታት ሊሞላው ጥቂት ወራት ቀርቶታል፡፡ ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም. አቡኑ በሰማዕትነት ያለፉባት ያቺ ቀን፡፡ የሰማዕቱ ድርሳን እንደሚናገረው የኢጣሊያ ፋሽስት በ1928 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ጦርነትን ባነሳ ጊዜ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ከጦር ሥፍራ ለመለየት ስላልሆነላቸው፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ተከትለው ወደ ሰሜን ጦር ግንባር ዘምተዋል፡፡ ፋሽስቱ በማይጨው የመርዝ ጦርነት ከማድረጉ የተነሳ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሲበታተንም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የተመለሱት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደው ለአገርና ለነፃነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን ለአርበኞች በመስበክም ይታወቃሉ፡፡ አርበኞች አዲስ አበባን በሁለት አቅጣጫዎች ከሰሜናዊ ምዕራብና በደቡባዊ ምሥራቅ አቅጣጫ ለመቆጣጠር ውጊያ በከፈቱበት ጊዜ የተማረኩት አቡነ ጴጥሮስ፣ ለፋሽስት እንዲገዙ የኢጣሊያ መንግሥት ገዢነትንም አምነው አሜን ብለው እንዲቀበሉ ግፊት ቢያደርጉባቸውም እምቢኝ ለአገሬና ለሃይማኖቴ ብለው ለሰማዕትነት ያበቃቸውን የሞት ጽዋ ተቀብለዋል፡፡

አቡነ ጴጥሮስን ታሪክና ትውልድ ሲዘክራቸው ለዘለዓለም የሚኖረውን ሥራ ሠርተው አልፈዋል፡፡ ሐውልትም፣ ውዳሴም፣ ቅድስናም ተገብቶአቸዋል፡፡ የአቡኑን ታሪክ በጥሞና ላሰበ የሃይማኖት አባቶች ከመንግሥትና ከአገር ጋር ሊኖራቸው የሚገባውን የግንኙነት ባህርይ ይረዳበታል፡፡ የሃይማኖት አባቶች የአገር ጉዳይ በሆኑ ኩነቶች ላይ ጠንካራና የነቃ ተሳትፎ ሊኖራቸው እንደሚገባ ነው፡፡ ለአገር ነፃነት ኅብረተሰብን መስበክም ሆነ በጦር አውድማ ጀግና ሆኖ መስዋዕት መሆን ትልቅ አርዓያነት ነው፡፡ አገር ከሌለ ሃይማኖት የለምና፡፡ ይህ ማለት የሃይማኖት አባቶች በፖለቲካ ሥራ ይጠመዱ፣ መንፈሳዊና ዘለዓለማዊ የሆነን ተግባራቸውን በምድራዊ ሥራ ይተኩ ማለት አይደለም፡፡ መጽሐፉ እንደሚለው የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር፣ የቄሳርንም ለቄሳር መስጠት ተገቢ ነው፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቅዳሴ የሚመሩትን፣ ቅኔ የሚያስተምሩትንና የሚፀልዩትን ዋና ሥራ ሳይተው ብሔራዊ በሆኑ አገራዊ የነፃነት ትግሎች ተሳትፈዋል፡፡ ያለአግባብ በመንግሥት ሥራ አልገቡም፤ አገራዊ የሆኑ ብሔራዊ የነፃነት ትግል ጥያቄዎችንም ወደ ጎን አላደረጉም፡፡

ይህ ለዘመናዊው የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት (Secularism) ዓቢይ ማሳያ ነው፡፡ በጊዜው የነበረው ሕገ መንግሥት የመንግሥትና የሃይማኖትን መለያየት የሚደነግግ ባይሆንም አቡኑ ‹‹የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር›› በሚለው ቀዳሚ መርህ ልዩነቱን ያስጠበቀ ታሪክ ባለቤት ሆኑ፡፡ በዚህ ሰሞን በማኅበራዊ ድረ ገጾች በስፋት ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጋር ተያይዞ የምናየው ድርጊት ግን ሁሉም የሃይማኖት አባቶች ወይም ቤተ እምነቶች የሃይማኖትና የመንግሥትን መለያየት ሕገ መንግሥታዊነት ማወቃቸውን የሚያጠራጥር ነው፡፡ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ለመንፈሳዊ ኮሌጆች ማኅበረ ቅዱሳንን በተመለከተ ደብዳቤ ሲጽፉ በግልባጭ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር፣ ለፍትሕ ሚኒስቴር፣ ለፖሊስ ወዘተ. ግልባጭ ማድረጋቸው ለጸሐፊው ያስታወሰው ይህንኑ የሕገ መንግሥታዊ መርህ ግንዛቤ ክፍተትን ነው፡፡ የአቡኑ ደብዳቤ ከመንፈሳዊነትና ከቤተ ክርስቲያን አስተዳደር አንፃር ያለበት ክፍተት በማኅበራዊ ሜዲያ ብዙ እየተባለለት ስለሆነና ይህ የጋዜጣው ዓምድ ሕግ ነክ ጉዳዮች የሚስተናገዱበት በመሆኑ ደብዳቤው ከመሠረታዊ የሕገ መንግሥት ድንጋጌ ጋር ያለውን ስምሙነት ላይ ምልከታ በማድረግ ላይ ብቻ ይወሰናል፡፡

የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት

የፓትርያርኩን ደብዳቤ ሕገ መንግሥታዊነት ለመፈተሽ የሕግ መሠረት የሚሆኑን ድንጋጌዎች የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 11 እና አንቀጽ 27 ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ድንጋጌ ስለ መንግሥትና ሃይማኖት መለያየት የሚደነግግ ሲሆን፣ ሁለተኛው የእምነት ነፃነትን ይደነግጋል፡፡ በአንቀጽ 11 ሦስት መሠረታዊ መርሆች ተቀምጠዋል፡፡ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፣ መንግሥታዊ ሃይማኖት አይኖርምና ለተነሳንበት ጉዳይ አግባብነት ያለው ‹‹መንግሥት በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ አይገባም፡፡ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤›› የሚሉ፡፡ የሃይማኖትና የመንግሥት መለያየት ከተቋማቱ ልዩነትና እያንዳንዳቸው ከሚሠሩት ሥራ መለያየት ጋር ይያያዛል፡፡ መንግሥት ጳጳሳትን ለቤተ ክርስቲያን አይሾምም፤ የሚሠሩትንም አያቅድም፡፡ ሥራቸውንም አይመራም፤ በበላይነት አይከታተልም፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ፕሬዚዳንቱን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ ሚኒስትሮችን ወይም ሌሎች የመንግሥት ኃላፊዎችን አትሾምም፤ ሥራቸውንም አትመራም፡፡ መንግሥት ከፈጣሪ/አምላክ ጋር በተያያዘ እምነቱን የመወሰን ድርሻም፣ ሥልጣንም የለውም፡፡ የሕገ መንግሥቱ ማብራሪያም ይህንኑ ነው በአጽንኦት የሚገልጸው፡፡

‹‹መንግሥት የሃይማኖት ነፃነት ከማስከበር በስተቀር የሃይማኖት ተቋማትና ሃይማኖታዊ ድርጅቶችን አያደራጅም፤ አያግዝም፡፡ መንግሥት የሃይማኖት ስብከት የሚካሄድበትን ትምህርት ቤት አይከፍትም፤ ለሃይማኖት ትምህርት ቤቶችም ዕውቅና አይሰጥም፡፡ በመንግሥት ሥራ ላይ እስካለ ድረስ ማንም የሕዝብ ተመራጭ ወይም የመንግሥት ባለሥልጣን ለየትኛውም ሃይማኖት መወገን አይኖርበትም፡፡››

ሁለተኛው ድንጋጌ የሃይማኖት ነፃነትን ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና የሚሰጥ ሲሆን፣ ማንኛውም ሰው አለማመንን ጨምሮ የመረጠውን ሃይማኖት የመያዝ፣ የመቀበል ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን ያካትታል፡፡ ድንጋጌው የእምነት ነፃነት በዝርዝር ከመደንገግ ባለፈ ሊኖርበት የሚችለውንም ገደብ አስቀምጧል፡፡ ሃይማኖትን የመግለጽ መብት ሊገደብ የሚችለው የሕዝብን ደኅንነት፣ ሰላምን፣ ጤናን፣ ትምህርትን፣ የሕዝብን የሞራል ሁኔታ፣ የሌሎች ዜግነትን መሠረታዊ መብቶች ነፃነቶችና መንግሥት ከሃይማኖት ነፃ መሆኑን ለማረጋገጥ በሚወጡ ሕጎች ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የእምነት አገላለጽን ለመገደብ የሚያስችሉ ምክንያቶች ካልተከሰቱ መንግሥት በእምነት ነፃነት ላይ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት ወይም ገደብ ሊፈጽም አይችልም፡፡ የመንግሥትና የሃይማኖት መለያያት መርህ የአገራችን ሕገ መንግሥታዊ ማዕዘን ከሆኑ ድንጋጌዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ለመሆኑ ይህ መርህ በተግባር ይከበራል? ላለመከበር ምክንያት የሚሆነውስ ማን ነው? ያለመከበሩ አንድምታስ ምንድን ነው? የተነሳንበትን ደብዳቤ መሠረት አድርገን እነዚህ ጭብጦች በአጭሩ እንመልከት፡፡

ሕገ መንግሥታዊ መርሁ እንዳይሸራረፍ

ከላይ የተመለከትናቸው መሠረታዊ የሕገ መንግሥት መርሆች በተለያዩ ምክንያቶች ሊጣሱ ይችላሉ፡፡ በአብዛኛው የተለመደውና ብዙ የሰብዓዊ መብት ምሁራን የሚስማሙበት ለመርሆቹ መጣስ መንግሥት ምክንያት እንደሚሆን ነው፡፡ መንግሥት በሃይማኖት ነፃነትን ለመገደብ የሚሆኑ ምክንያቶችን አስፍቶ ወይም ለጥጦ በመተርጎም የሃይማኖትና የመንግሥት መለያየትን መርህ ሊጥስ እንደሚችል መታሰቡ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ ማብራሪያም ይህንን ተግባራዊ ምልከታ የተከተለ ይመስላል፡፡ ማብራሪያው የዜጎች የእምነት ነፃነት እንዲረጋገጥ መንግሥት በሃይማኖታዊ ጉዳይ እጁን ማስገባት እንደሌለበትና በሃይማኖት ጉዳይ እጁን ካስገባ ግን ከፊሎቹን ዜጎች በተለየ ዓይን ተመለከተ ማለት እንደሆነ መግለጹ በዚህ መነሻነት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር አንዳንድ የመንግሥት ሹሞች በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ በመግባት በአስተዳደሩ፣ በሥርዓቱ፣ በአመራሩ ወዘተ. የሚፈተፍቱ ከሆነ ሕገ መንግሥቱ ያልፈቀደላቸውን ሥራ እየሠሩና የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት (Secularism) መርህን እየጣሱ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

ሌላው መርሁ ሊጣስ የሚችለው መንግሥትን የሚወክሉ ሠራተኞች፣ ሹሞች ወይም ባለሥልጣናት በሕቡዕ ወይም በግልጽ አንድን እምነት የሚጠቅም ወይም የሌላውን የእምነት ተከታይ የሚጎዳ ሥራ ሲሠሩ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ባለሥልጣናት በግላቸው የፈለጉትን እምነት መከተላቸውን ባይከለክልም እምነታቸውና አስተሳሰባቸው ግን የተሾሙበትን የመንግሥት ኃላፊነት ላይ ተፅዕኖ እንዲያደርግባቸው አይፈቅድም፡፡ የመንግሥት ሥልጣኑ በእጁ ስላለ ብቻ እሱ የሚከተለውን እምነት ወይም ሃይማኖት የማይገባውን የመንግሥት ልዩ ጥቅም /ነፃ ግብር፣ ቦታ፣ ፈቃድ ወዘተ./ የሚሰጥ ከሆነ ሕገ መንግሥታዊነትና የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት ውኃ በላው ማለት ነው፡፡

የመንግሥትና ሃይማኖት መለያየት ሕገ መንግሥታዊ መርህ የሚጣስበት ወይም የሚሸረሽርበት ሌላው ምክንያት በሃይማኖት ተቋማቱ ወይም በቤተ እምነቱ መሪዎች ወይም አባቶች ድርጊት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ምክንያት ለተነሳንበት ዓቢይ ዓላማ መሠረት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በተግባር መንግሥት የሃይማኖትን ነፃነት ገደበ፣ ከሃይማኖት ጋር ያለውን ልዩነት አልጠበቀም የሚል ትችት ይቀርባል እንጂ አንዳንድ ጊዜ መንግሥትን የሚገፉት ቤተ እምነቶቹ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አሁን በተነሳንበት ጉዳይ ፓትርያርኩ የቤተ እምነታቸውን የውስጥ አስተዳደር ጉዳይ በደብዳቤ ለመንግሥት አካላት እንዲያውቁት ማድረጋቸው የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየትን የሚጥስ ወይም የሚሸረሽር ድርጊት ነው፡፡ ጉዳዩ ሃይማኖታዊ እንደመሆኑ ሊያልቅ የሚገባው በሃይማኖት ተቋማቱና በመሪዎቻቸው ብቻ ነው፡፡ አንድ ደብዳቤ የሃይማኖት ጉዳይ ይዘት ኖሮት ግልባጭ መደረግ ያለበት በአስተዳደር ሒደቱ ሊሳተፍ ለሚችል፣ ውሳኔ ሊሰጥ ለሚችል፣ የጉዳዩ ባለቤት ለሆነ ወይም ከተወሰኑ ጊዜ በኋላ ጉዳዩን በይግባኝ ሊመለከት ለሚችል አካል ነው፡፡ እንኳን ሕገ መንግሥታዊ ፍቺአቸው በግልጽ ለታወጀላቸው በሃይማኖትና መንግሥት መካከል፣ በሦስቱ የመንግሥት አካላት (ሕግ አውጭ፣ አስፈጻሚና ተርጓሚ) መካከል እንኳን እንዲህ ዓይነት ነገር ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ በፍርድ ቤት የተያዘን የመንግሥት ጉዳይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በደብዳቤ የሚያሳውቅ ዳኛ ሕገ መንግሥቱን የሚጥሰውን ያህል፤ ቤተ እምነቶችም ለመንግሥት መንፈሳዊ ጉዳያቸውን ባሳወቁ መጠን መርሁን ይጥሱታል፡፡ ይህ ጉዳይ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ቢሆን ሕገ መንግሥቱም፣ የመንግሥት ባህሉም ይፈቅድ ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የመንግሥት ሃይማኖት፣ አፄውም የበላይ ጠባቂ በመሆናቸው መንፈሳዊ ወይም የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ጉዳይ በግልባጭ እንዲያውቁ ቢደረግ ተገቢም፤ ሕጋዊም ሊሆን በቻለ ነበር፡፡ በአሁኑ ሕገ መንግሥት ግን ቤተ እምነቶች ሃይማኖታዊ ደብዳቤዎችን ለመንግሥት ግልባጭ ማድረጋቸው መርሁ እንዲጣስ መግፍኤ ምክንያት እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ የእግዚአብሔርን ለቄሳር መስጠት እምነቱም፣ ሕገ መንግሥቱም አይፈቅድም፡፡ መንግሥትም ቤተ እምነቶቹ ተመሳሳይ ደብዳቤዎች ለመንግሥት መላካቻው ሕገ መንግሥታዊ አለመሆኑን በመግለጽ እንዲቆም ካልጠየቀ ሕገ መንግሥቱ መሸርሸሩ አይቀርም፡፡ ዝምታዉም መንግሥት እንደተቀበላቸው፤ ልማዱም (Precedence) እንዲቀጥል የመፍቀድ ያህል ነው፡፡ በዕለት ተዕለት ኑሮአችን እንደምናስተውለው የእንዲህ ዓይነት ደብዳቤዎች ፋይዳ ባለጉዳዩን ማስፈራራት፣ ማስጨነቅና መንግሥትን በጉዳዩ እንዳለበት የሚያስወስድ መረዳት እንዲኖረው ማድረግ ስለሆነ ውጤቱ የከፋ ነው፡፡

ከሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው በሃይማኖት ጉዳይ መንግሥት ጣልቃ መግባቱ ሕጋዊ የሚሆነው ወይም የእምነት ነፃነትን መገደቡ ተገቢ የሚሆነው ለመገደብ ምክንያቶች መኖራቸው ሲረጋገጥ ነው፡፡ በደብዳቤው የተገለጸው ጉዳይ በቤተ እምነቱ መፍትሔ ማግኘት አቅቶት ለሕዝብ ደኅንነት ሥጋት ከሆነ፣ አመጽና የኃይል ተግባር ከታከለበት ጉዳዩ ከሃይማኖት ወደ መንግሥት፣ ከአማኝ ጉዳይ ወደ ዜጋ ጉዳይ ሊቀየር ይችላል፡፡ የዶግማ ወይም የሥርዓት ወይም የአስተዳደር ጉዳይ በአንድ ቤተ እምነት ተከታዮችም ሆነ በተለያዩ እምነት ተከታዮች መካከል ቢነሳ የሃይማኖት ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ በተነሳንበት ጉዳይ በኦርቶዶክስ አቡን እና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል የተነሳው የአስተዳደር ጉዳይ የሃይማኖት ጉዳይ እንደመሆኑ መንግሥትን አይመለከተውም፡፡ መንግሥት እንደሚመለከተው አድርጎ እያንዳንዱን የደብዳቤ ልውውጥ ለመንግሥት ማሳወቅ፣ የእግዚአብሔርን ለቄሳር መስጠት፣ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንዲገባ መፈተን ነው፡፡ በሁለት የተለያዩ አማኞች መካከል ዶግማን/ቀኖናን መሠረት አድርጎ ውይይት ቢደረግም እንዲሁ የመንግሥት ጉዳይ አይደለም፡፡ ሁለቱ ወገኖች ጉዳያቸውን ሰላማዊ ባልሆነ መልኩ እልባት መስጠት ሳይችሉ ቀርተው አንዱ ሌላው ላይ እምነቱን ወይም ሥርዓቱን ወይም አቋሙን ለመጫን ሲጠቀም መንግሥት ጉዳዩ ይመለከተዋል፡፡ ጉዳዩ የኃይል ተግባር ወይም ትንኮሳ ካለው ወይም ድርጊቱ በአማኞች መካከልም ቢሆን የወንጀል ተግባር ካለው ምንም እንኳን የዶግማና የቀኖና ጉዳይን ቢመለከት የማስተካከል ዕርምጃው የመንግሥት ይሆናል፡፡

አንድምታውና መፍትሔው

ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸውን ደብዳቤዎች ለመንግሥት አካላት መላክ የራሱ አንድምታዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንዲገባ መግፋት ነው፡፡ መንግሥት ደብዳቤውን ተቀብሎ ዝምታን ቢመርጥ እንኳን ዝምታው ጣልቃ ገብነቱን የመፍቀድ ያህል ስለሚቆጠር ተምሳሌቱ አደጋ አለው፡፡ ሁለተኛው የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት በሕግ ከተቀመጠው በላይ በባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ሲያገኝ ነው ልማዱ የሚዳብረው፡፡ Secularism የአንድ ጀምበር ውጤት ሳይሆን በሒደት የሚመጣ በመሆኑ ደብዳቤ መላላኩ ካልቆመ ይህንን ባህል ይጎዳዋል፡፡ ነገ ሌላው ቤተ እምነት ተመሳሳይ ጉዳይ ሲያጋጥመው የሃይማኖት ምስጢሩንና ገመናውን ለመንግሥት ሊልክና የሁለቱ የልዩነት መስመር ሊጠብ ነው፡፡ ሦስተኛውና ዋናው አንዳንድ የቤተ እምነት መሪዎች ወይም አባቶች መንግሥትን እንደማስፈራሪያነት በመጠቀም አማኞች በመንፈሳዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ዝምታን እንዲመርጡ የእምነት ነፃነት እንደሌለ እንዲያስቡ ይሆናሉ፡፡ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ያሉ የሙስና አሠራሮችን፣ ሕገወጥ ልማዶችንና እምነቱ የማይፈቅዳቸውን ነገሮች ማጋለጥ፣ እንዲስተካከል መረባረብ ሕልም ይሆናል፡፡

ከዚህ አንፃር ጸሐፊው የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት ከሕጉ ባለፈ በተግባር እንዲከበር መንግሥት ሰፊ ድርሻ እንዳለበት ያምናል፡፡ የመጀመሪያው የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 11 መሠረት አድርጎ የመንግሥትና የሃይማኖት ትብብር የሚያደርጉባቸውን ዓቢይ የፖሊሲ ነጥቦች መለየት፣ ልዩነታቸውን የተመለከተውን መርህ የትርጉሙን ይዘት በግልጽና በዝርዝር ማስቀመጥ፣ ከአንቀጽ 27 ገደቦች ጋር በጣምራ የትርጉሙን ይዘትና ወሰኑን ማስቀመጥ ይገባል፡፡

ሁለተኛው ቤተ እምነቶቹን በጋራ ወይም በነጠላ በSecularism መርህ፣ ጥቅም፣ ተግዳሮትና ተግባራዊ አፈጻጸም ላይ ሥልጠና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ልማዱ የሚፈጠረው ባለድርሻ አካላት ተመሳሳይ መግባባት ሲኖራቸው ነው፡፡ መንግሥት ግዴታውን አውቆ በሃይማኖት ጣልቃ አልገባም ቢል እንኳን የቤተ እምነቶቹ መሪዎች መርሁን ካላወቁት በየዕለቱ የሃይማኖት ጉዳያቸውን መንግሥት እንዲወስንላቸው ደብዳቤ ሲጽፉ መኖራቸው ነው፡፡ ካወቁ፣ የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው ይጨርሳሉ፣ መንግሥት አስፈላጊ ሲሆን ብቻ በአግባቡ ከመንግሥት ጋር ይገናኛሉ፡፡

ሦስተኛ መፍትሔ መንግሥት ዕውቀቱም ኑሮአቸው መንፈሳዊ ደብዳቤን ለማይመለከተው መንግሥት መጻፍ የሚያዘወትሩትን ተገቢ እንዳልሆነ አቋሙን ገልጾ ሊገስጻቸው ይገባል፡፡ ይህን በማድረጉ ለሌላው ቤተ እምነትም ትምህርት ይሆናል፤ ለመብት ጠያቂ አማኝም መንግሥትን እንደማስፈራሪያ የመጠቀም ያልተገባ ባህል የሕግ መሠረት አለመኖሩን ያስረዳል፡፡ የመንግሥትና የሃይማኖት መለያ በሕገ መንግሥቱ ዋስትና ማግኘቱ ለመንግሥትም ለቤተ እምነቶችም ታላቅ ጥቅም አለው፡፡ ተግባራዊነቱ ግን ሒደት ስለሆነ  ብዙ ሥራ የሚፈልግ ነው፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

          

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...