Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በመከባበር ልዩነቶቻችንን አቻችለን በጋራ ጥቅሞቻችንና ጉዳዮቻችን ላይ እየሠራን ነው››

አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፣ በአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር

አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በአውሮፓ ኅብረት፣ በቤልኑክስና በባልቲክ አገሮች የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ናቸው፡፡ ቀደም ሲል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ በመሆንም አገልግለዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተካሄደው 26ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ተገኝተው ነበር፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ በቅርቡ በኢትዮጵያ ላይ በወጣው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ፣ በኢትዮጵያና በኅብረቱ ግንኙነት ወሳኝ መገለጫዎች፣ እንዲሁም በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ነአምን አሸናፊ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት ግንኙነት መገለጫዎች ምንድናቸው? ወሳኝ የሚባሉት የግንኙነት መገለጫዎችስ ምን ምን ናቸው?

አምባሳደር ተሾመ፡- የኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት ግንኙነት 40 ዓመታት የሞሉት ግንኙነት ነው፡፡ ባለፈው ጥቅምት ወር ግንኙነት የጀመርንበትን 40ኛው ዓመት በዓል በጋራ እዚሁ አክብረናል፡፡ የግንኙነቱ ማዕከል ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን እንደማንኛውም የአፍሪካ፣ የካሪቢያንና የፓስፊክ አገር አውሮፓ ኅብረት እንዳለው ግንኙነቱ ሁሉ፣ በኮቶኑ ስምምነት መሠረት ነው የኢትዮጵያና የኅብረቱ ግንኙነት የሚገዛው፡፡ ከእኛ ጋር ባለው ግንኙነት በዋናነት አንደኛው ኢትዮጵያ በውስጧ በምትሠራው የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ሥራ ላይ ኅብረቱ እንደ አጋር የሚያደርገው ድጋፍ አለ፡፡ ይኼ በዋናነት በአውሮፓ የልማት ፈንድ አማካይነት የሚደገፍ ነው፡፡ ከዚያ ውጪም ሃያ ስምንቱ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች በተለያዩ መንገዶች የሚያደርጉት የልማት ድጋፍ አለ፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ የድህነት ቅነሳ ፕሮግራምና የልማት ፕሮግራም አለ፡፡ በአጠቃላይም ኢትዮጵያ የተረጋጋች፣ የበለፀገችና ዴሞክራሲያዊት አገር ለመሆን በምታደርገው ጥረት ውስጥ ኅብረቱና አባል አገሮች የሚጫወቱት ሚና አለ፡፡ በዚያው ማዕቀፍ ውስጥ እንደዚሁ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገነባው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ በኮቶኑ ስምምነት አንቀጽ 8 መሠረት የጋራ የፖለቲካ ውይይት አለ፡፡ ስለዚህ አንዱ የግንኙነቱ መገለጫ ኢትዮጵያ በውስጥ በምታደርገው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ኅብረቱ እንደ አጋር በሚጫወተው ሚና ላይ ነው የሚመሠረተው፡፡

ሁለተኛው ገጽታ ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነቷ በተለይም ደግሞ በአፍሪካ ቀንድና በአፍሪካ በምትጫወተው የሰላም ማስከበርና ሌሎች እንቅስቃሴዎች አካባቢው የተረጋጋ እንዲሆን የምትጫወተው ሚና አለ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ እኛ ለብሔራዊ ጥቅም ብለን የምናደርጋቸው የሰላም ማስከበር ሥራዎች በአካባቢው የተፈጠሩ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት የምናደርገው ጥረት እንዳለ ሁሉ፣ ኅብረቱም በዚሁ ጉዳይ ላይ የራሱ ፍላጎት አለው፣ የራሱ ጥቅም አለው፡፡ ስለዚህ የጋራ ጥቅሞቻችን የሚዋሀዱበት አንዱ በአፍሪካ ቀንድ የማታዩትን አለመረጋጋቶችንና ግጭቶችን በማስወገድ ረገድና በዲፕሎማሲው መስክ፣ ችግሮችን በድርድር በመፍታት ረገድ፣ ኢትዮጵያ በኢጋድ ሊቀመንበርነቷም በራሷም ስም የምትጫወተው ሚና አለ፡፡ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ግንኙነታችን የሚገለጽበት አንደኛው ምሰሶ ነው፡፡ ሦስተኛው ዓለም አቀፍ ጉዳዮችን መውሰድ ይቻላል፡፡ በዋናነት በሁለት ዋና ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ አንዱ ሽብርን በመዋጋት ረገድና በፀረ ሽብር ትግል ከኅብረቱ ጋር በጋራ እንሠራለን፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ለዓለም ሥጋት የሆኑ እንደ አየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ደግሞ ሌሎች መገለጫ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የምትሠራቸው ሥራዎች አሉ፡፡ በዚህም ችግር ኢትዮጵያ ለብሔራዊ ጥቅሟ በምታደርገው እንቅስቃሴ ላይ የአውሮፓ ኅብረትም ከአፍሪካ ጋር ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ የሆነ አቋም አለው፡፡

ኢትዮጵያ ደግሞ ባለፉት ዓመታት የአፍሪካ ቃል አቀባይ ሆና በሚደረጉ የአየር ንብረት ለውጥ ዓለም አቀፍ ድርድሮች ላይ ግንባር ቀደም ሚና እየጫወተችና በመጫወት ላይ ያለች አገር ስለሆነች፣ በዚህም ዙሪያ ላይ በጋራ እንሠራለን፡፡ ስለዚህ የግንኙነቶች መገለጫዎች ወይም ዋና ምሰሶዎች ምንድናቸው ለሚለው ጥያቄ በውስጥ በምናደርገው የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ የፖለቲካዊ ልማት ሥራ ላይ፣ እንደዚሁም ደግሞ በአካባቢውና በአፍሪካ በምናጫውተው የሰላም ማስከበርና የማረጋጋት ሥራ፣ በአጠቃላይ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት በምንጫወተው ሚናና ሦስተኛው ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ በምታጫውተው ሚና ላይ የሚገለጽ ግንኙነት ነው ያለን፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያና የኅብረቱ ግንኙነት 40 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በአጠቃላይ የሁለቱ ግንኙነት የዕድገት ሒደት ምን ይመስላል? ሒደቱ ከየት ተነስቶ የት ደረሰ? አሁን ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል?

አምባሳደር ተሾመ፡- አሁን ግንኙነቱ ወደላቀ አጋርነት ተሸጋግሯል፡፡ ለዚህም መገለጫዎችን ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ ከአፍሪካ ውጪ የመጀመሪያውን የውጭ ጉብኝት ያደረጉት ወደ አውሮፓ ኅብረት ነበር፡፡ ይህ ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡ ምክንያቱም አውሮፓ ኅብረት ከላይ በልማት ሥራ ላይ ስናወራ ከአውሮፓ የሚገኝ ድጋፍ ነበር፡፡ ከዚያ በተጨማሪ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሌሎች ማኅበራዊ ዘርፎች ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በልማታችን አጋር በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንሠራለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ በተለይ የውጭ ንግዱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በሚደርስበት ጊዜ 40 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ምርት የሚሄደው ወደ አውሮፓ ነው፡፡ ስለዚህ ከንግድ አኳያ ትልቅ ሸሪካችን ነው፡፡ ከኢንቨስትመንትም አኳያ የምንፈልገውን ያህል ባይሆንም፣ በዚያው ልክ የሚገለጽ ትልቁ የኢንቨስትመንትና የቱሪስት አመንጪ ኅብረቱ ነው፡፡ ስለዚህ ከኅብረቱ ጋር ያለን ግንኙነት በዚህ መንገድ ስለሚመዘን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የመጀመሪያ ጉብኝት ያደረጉት ወደ አውሮፓ ኅብረት ነበር፡፡ የግንኙነቶቹ አንዱ መገለጫ በመሪዎች ደረጃ የሚደረጉ ጉብኝቶች ናቸው፡፡ ሁለተኛው የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ግንኙነት ኮሚሽን የውጭ ግንኙነትና የደኅንነት ኃላፊ ባለፈው ጥቅምት ወር በኢትዮጵያ ይፋ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በዚህ ጉብኝት ወቅት ተጨባጭ የሆኑ ግንኙነቶቻችንን ወደ ከፍታ ሊያሸጋግሩ የሚችሉ የጋራ መግባባቶች ተፈጥረዋል፡፡ ለዚህ ጉብኝት ምላሽ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በቅርቡ ለሁለት ቀናት በኅብረቱ ጉብኝት አድርገዋል፡፡ በጉብኝቶቹ ወቅት የተስማማነው አንደኛ ቀደም ሲል በኮቶኑ ስምምነት በአንቀጽ 8 መሠረት በኢትዮጵያና በአውሮፓ ኅብረት መካከል ይካሄድ የነበረው ንግግር ከእኛ አመራርና  በአዲስ አበባ ነዋሪ በሆኑ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች አምባሳደሮችና በኅብረቱ ወኪል አምባሳደር እየተመራ ነበር፡፡ ይህ ግንኙነት ከፍ ያለ ደረጃ መድረስ አለበት ተብሎ የኢትዮጵያና የኅብረቱን ግንኙነት ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር ተስማምተናል፡፡

ስለዚህ ይህ ግንኙነት ከአሁን በኋላ የሚደረገው በሚኒስትሮች ደረጃ ነው፡፡ ወደ ሚኒስትሮች ደረጃ ይህን ግንኙነት ከፍ ለማድረግ ስናስብ በሁለቱም በኩልና በሃያ ስምንቱም አባል አገሮች በኩል ፍላጎት ነበር፡፡ ሁሉም አባል አገሮች በዚህ ጉዳይ ላይ ተወያይተው የአውሮፓ የውጭ ግንኙነት ጽሕፈት ቤትም የቀረበውን ውሳኔ ተቀብሎ አፅድቋል፡፡ ስምምነቱን በቅርቡ እንፈራረማለን፡፡ ይህን ሲያደርጉ ኢትዮጵያ ቅድም እንዳልኩት ከአውሮፓ ኅብረትና ከአባል አገሮች ጋር ባላት ግንኙነት፣ እንደዚሁም በአካባቢው በምትጫወተው ሚና የአውሮፓ ኅብረት አጋር ነች የሚለው ላይ ሙሉ መተማመን ስለተደረሰ ነው፡፡ ሁለተኛው ይህ ስምምነት ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ከደቡብ አፍሪካ ጋር ቀደም ሲል ከነበረው ስትራቴጂካዊ አጋርነት ግንኙነት ውጪ ከአንጎላና ከናይጄሪያ ጋር ብቻ ነበር፡፡ የሁለቱ በዋናነት ከነዳጅም ከኢኮኖሚም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አሁን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ስምምነት ላይ ሲደረስ ኢትዮጵያ ሦስተኛ አገር ነች፡፡ ይህ ቅድም እንዳልኩት የኢትዮጵያና የኅብረቱ አጋርነት ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ለመድረሱ አንዱ መገለጫ ነው፡፡ በዚህ ላይ ከዚህ በፊት በኮቶኑ ስምምነት በአንቀጽ 8 መሠረት ስናደርግ የነበረው ውይይት በአብዛኛው ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብት፣ የፕሬስ ነፃነት፣ እንዲሁም የፖለቲካ ምኅዳር በሚባሉ አጀንዳዎች ብቻ ላይ የታጠረ ነበር፡፡ አምባሳደሮቹ በአብዛኛው የሚያነሱት ይህንን ነው፡፡ እኛም በአጠቃላይ ፖሊሲያችንን ስንገልጽ ነው የነበረው፡፡ አሁን ግን ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ምክንያቱም በኮቶኑ ስምምነት አንቀጽ 8 የተገለጸ በመሆኑ ይህንን እናነሳለን፡፡ ይህን ስናነሳ ገንቢ በሆነ መንገድ እናቀርባለን፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ደረጃ ለኅብረቱና ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ሌሎች ቅድም ያነሳኋቸው በርካታ ጉዳዮች ላይም ተጨማሪ ውይይት ይደረጋል፡፡

ሁለተኛው ግንኙነቱ የላቀ ደጃ ለመድረሱ ሌላው ማሳያ ደግሞ የሠራተኞች ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ ስደት አሁን ለአውሮፓ ትልቅ አጀንዳ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከ750,000 በላይ የሆኑ ስደተኞችን የምታስተናግድ አገር ነች፡፡ ይህ ምናልባት የክፍት በር ፖሊሲ ስላለን በአብዛኛው ወደ አውሮፓ ሊሻገር የሚችልና አሁን ያለውን የስደተኞችን ፍሰት ከፍ ሊያደርግ ይችል የነበረውን እዚህ ለመግታት ኢትዮጵያ በመቻሏ ምክንያት፣ የአውሮፓ ኅብረት በዚህ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት አለው፡፡ ወደፊትም በተቻለ መጠን በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲቀጥል ፍላጎት ያሳያሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህንና እነዚህን በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ተፈራርመናል፡፡ ይህ ስምምነት የጋራ የስደትና የዝውውር አጀንዳ (Migration and Mobility Agenda) በአፍሪካ ደረጃ በሁለተኛነት የፈረመች አገር ኢትዮጵያ ነች፡፡ በዚህም ውጤታማ የሆነ በተጨባጭ ሊታዩና ውጤት ሊያመጡ በሚችል ጉዳዮች ላይ እየተባበርን ነው ያለነው፡፡ ሦስተኛው በፀረ ሽብር ትግል ላይ እያደረግን ያለውን ጥረት ለማገዝ በሚያስችል መንገድ የእነሱ የፀረ ሽብር ትግል አስተባበሪ በቅርቡ ኢትዮጵያ ይመጣሉ፡፡ በስደተኞች  ጉዳይ ላይ የሚነጋገር ቡድንም ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ያጋጠማትን የድርቅ አደጋ ከመከላከል አኳያ የአውሮፓ ኅብረት ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ ምንም እንኳን የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም ዕርዳታ እየሰጡ ናቸው፡፡

ሌላው ኢትዮጵያ በአንድ በኩል የድርቁን አደጋ ለመቋቋም፣ በሌላ በኩል ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራች ነውና ድርቁንም በመቋቋም ረገድ ዕቅዱንም በተጠናከረ ሁኔታ ለመፈጸም እንድትችል ተጨማሪ ዕርዳታ እንዲያደርጉ ጠይቀናል፡፡ በኅብረቱ የግማሽ ዓመት ግምገማ (Mid term Review) የሚባል አለ፡፡ የአምስት ዓመት ፕሮግራም አለን፡፡ ስለዚህ ሁሉም አገሮች የሁለት ዓመት ተኩል አፈጻጸማቸው ይታይና ጥሩ የተንቀሳቀሱ አገሮች ካሉ ተጨማሪ ገንዘብ እንዲያገኙ የሚደረግበት አሠራር አለ፡፡ ከዚህ አንፃር ነው ተጨማሪ ድጋፍ የጠየቅነው፡፡ ኢትዮጵያ ከ11ኛው የአውሮፓ የልማት ፈንድ ትልቁ የልማት ድርሻ ያላት አገር ነች፡፡ ይህ ደግሞ በሥራ ውጤታችን የተገኘ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በግንኙነቱ ተጨባጭ ደረጃ ተጨማሪ ዕርዳታ እንዲገኝ ከተፈለገ ደግሞ፣ የአውሮፓ ኅብረት የግል ዘርፍም እንዲሳተፍ ማድረግ አለብን በሚል ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የአውሮፓ የግል ዘርፍ የሚሳተፍበት የኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት የቢዝነስ ፎረም ብራሰልስ ውስጥ በመጋቢት ወይም በሰኔ ወር ለማድረግ ተስማምተናል፡፡ እነዚህ ግንኙነቱ ወደ ላቀ ደረጃ ለመድረሱ ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በሁለት ወገኖች መካከል እርስዎ የገለጹት ዓይነት የተጠናከረ ግንኙነት ሲኖር፣ አንዱ መገለጫ ግንኙነቱን ወደ ኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት ትስስር ማሳደግ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያና የኅብረቱ የንግድ፣ የኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ምን ይመስላል? በርካታ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት የንግድ ግንኙነቱ ተጠቃሚነት ወደ አውሮፓ ያጋደለ ነውና ይህንንስ ለማስተካከል መንግሥት ምን እየሠራ ነው?

አምባሳደር ተሾመ፡- አንደኛው ዞሮ ዞሮ የኢኮኖሚ ግንኙነቱ እንዲጠናከር ለማድረግ በእኛ በኩል በሁለት ነገሮች ላይ ተግተን መሥራት አለብን፡፡ አንዱ ንግድን የተመለከተ ነው፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ትልቅ ገበያ ነው፡፡ ግማሽ ቢሊዮን ሕዝብ ያለበት ነው፡፡ ቁጥሩ ብቻ ሳይሆን የመግዛት አቅም ያለው ነው፡፡ ወደ ገበያው ገብተናል፡፡ ነገር ግን በቂ አይደለም፡፡ በአውሮፓ ገበያ ተመጣጣኝ የሆነ ምርትና ሸቀጥ እያቀረብን አይደለም፡፡ ከዚህ በላይ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ገበያው በጣም ሰፊ ነው፡፡ ጥራት ያለው ምርት ማቅረብ አለብን፡፡ በገበያው ተፈላጊ የሆኑ ምርቶች ጥሬ ምርቶችን ብቻ ሳይሆን አቀነባብረን መላክ የምንችል ከሆነ በጣም ሰፊ ገበያ ነው፡፡ ሁለተኛው አሁን ባለን የንግድ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ከታዳጊ አገሮች ተርታ ውስጥ ስለምትመደብ፣ ከጦር መሣሪያ ውጪ ማንኛውንም ዓይነት ኢትዮጵያ ውስጥ የተመረተ ያለ ቀረጥ የአውሮፓ ገበያ ውስጥ ይገባል፡፡ ይህ ለእኛ ትልቅ ጥቅም ነው፡፡ ግን ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ አልሆንም፡፡ ስለዚህ በእኛ በኩል ሊሠሩ የሚገባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ምርቶቻችንን በ28ቱም የኅብረቱ አገሮች የበለጠ የማስተዋወቅ ሥራ መሥራት አለብን፡፡ ይህንን ሚሲዮኖቻችን ይሠራሉ፡፡ ከቱሪዝም እንደዚሁ ተጠቃሚ ለመሆን እየሠራን ነው፡፡ በቴክኖሎጂ ሽግግር በተለይ ከኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ በትምህርት ተቋማት አማካይነት ከብዙ የኅብረቱ አባል አገሮች ጋር ሰፊ የሆነ የትምህርት ትብብር ከዩኒቨርሲቲዎቻችን ጋር መሥርተናል፡፡ ይህን አጠናክረን መቀጠል መቻል አለብን፡፡ በአብዛኛው ደግሞ ንግዳችንን ለማስፋፋትና የበለጠ ጥራት ያለው ምርት በመላክ ረገድ አገር ቤት የሚሠራው ሥራ ወሳኝ ነው፡፡ ስለዚህ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶቻችንንና ሸቀጦቻችንን የበለጠ ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ በዚህ በኩል እንደሚታወቀው በሁለተኛ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አሉ፡፡ ሌላው ትልቁ ከአውሮፓ ኅብረት የምንፈልገው ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ጥራት ያለው ኢንቨስትመንት እንዲመጣ እንፈልጋለን፡፡ እስካሁን የመጣው በቂ አይደለም፡፡ ኅብረቱ ውስጥ ያሉ ትልልቅ የግል ኢንቨስተሮች እንዲመጡ እንፈልጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ባለው የሰብዓዊ መብት አያያዝና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ዙሪያ ኅብረቱ የሚገልጻቸው የራሱ የሆኑ አቋሞች አሉት፡፡ ከዚህ አንፃር በሰብዓዊ መብት አያያዝና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጉዳዮች ላይ የኅብረቱና የኢትዮጵያ ግንኙነት ምን ይመስላል?

አምባሳደር ተሾመ፡- በነገራችን ላይ ኅብረቱ ስንል አንድ ወጥ አካል እንዳልሆነ ማወቅ አለብን፡፡ በኅብረቱ ውስጥ የተለያዩ ተቋማት አሉ፡፡ አንዱ የአውሮፓ ኅብረት ካውንስል የሚባለው ነው፡፡ 28 አባል አገሮች በጋራ የሚሳተፉበት ካውንስል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የአውሮፓ ፓርላማ ነው፡፡ በጋራ ሕግ የማውጣት፣ ውሳኔ ለመወሰንም፣ በጀት ለማፅደቅም ሥልጣን ያለው ተቋም ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ኮሚሽኑ ነው፡፡ አራተኛው በኮሚሽኑ ሥር የውጭ ግንኙነትን የሚመራው የአውሮፓ የውጭ አገልግሎት አለ፡፡ ስለዚህ በተቋሟት ደረጃ በምናይበት ጊዜ ከአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ጋር ያለን ግንኙነት በዚህ ረገድ የራሱ ተግዳሮት ያለበት ነው፡፡ ዋናው ነገር መታየት ያለበት የሰብዓዊ መብት፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ የዴሞክራሲ ባህል እንዲያብብ፣ እንደዚሁም ደግሞ ከፕሬስ ነፃነትና ከፖለቲካ ምኅዳር ጋር በተነሱ ጉዳዮች ላይ የሚያቀርቧቸው ትችቶች አሉ፡፡ ትችቶቹን አንዳንዶቹን በገንቢነት የምንወስዳቸው፣ እንዲሁም የእኛንም ፖሊሲ፣ አተያይና አቋም የምንገልጽባቸው ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ልዩነት የምናይባቸው መስኮች አሉ፡፡ አንዱ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ባለን ግንኙነት ልዩነት የሚንፀባረቅበት መስክ ይህ ነው፡፡ ልዩነቱ ለምንድነው በዚህ ልክ የሚገለጸው ለሚለው፣ ከአውሮፓ ፓርላማ ጋር ያለን ግንኙነት አንደኛ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ ጤነኛ አይደለም፡፡ ፓርላማው ከአገሮች ጋር ያለውን ግንኙነትና የኮሚሽኑን ወይም የኅብረቱን የውጭ ግንኙነት የሚመራ ተቋም አይደለም፡፡ የፖለቲካ ተቋም ነው፡፡ አጀንዳ ይይዛል፣ ውይይት ያደርጋል፣ ውሳኔ ያሳልፋል፡፡ በዚህ ልክ በ1997 ዓ.ም. የአውሮፓ ኅብረት ከላከው የምርጫ ታዛቢ ቡድን ጋር የተፈጠረው ችግር እስካሁን ድረስ መፍትሔ ያላገኘ ነው፡፡ ያ ማለት ግን 750 የፓርላማ አባላት ተመሳሳይ አቋም አላቸው ማለት አይደለም፡፡ አንዱ ከዚያ የሚመነጭ ልዩነትና ተግዳሮት ያልኩት በዚህ ልክ የሚገለጽ ነው፡፡

ሁለተኛው ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉት የሰብዓዊ መብት አያያዝና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ እንዲሁም የፕሬስ  ነፃነትና የፖለቲካ ምኅዳር ብለው ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ማንጠልጠያ የሚያደርጉት ከግለሰቦች ጋር በማገናኘት ነው፡፡ በዚህ ላይ ልዩነት አለን፡፡ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አንደኛው መገለጫ የሕግ የበላይነት ነው፡፡ ስለዚህ ሕግ ጥሰው፣ በሕግ በተቀመጠው አሠራርና አግባብ መሠረት ፍርድ ቤት አቅርቦ ሕጉ ያስወሰነባቸው ሰዎች ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና መሪዎች ሲሆኑ፣ እነዚህ ሰዎች ከሕግ በላይ እንደሆኑ አድርጎ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ታስራለች የሚል ወቀሳ ይነሳብናል፡፡ ይህ ተገቢ አይደለም ብለን በተደጋጋሚ ለመግለጽ ሞክረናል፡፡ ይህ ልክ የማይሆንበት ኢትዮጵያ ውስጥ የሕገ መንግሥታችን አንዱና ትልቁ ቁም ነገር ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል ነው የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ሕግ የጣሰ ሰው ይጠየቃል፡፡ አውሮፓ ውስጥም ይጠየቃል፡፡ አውሮፓ ኅብረት አባል አገር ውስጥ የወጣ ሕግ ወይም በኅብረቱ ሕግ የሆነ ነገርን የማይወድ ሰው ሕጉን አይጥስም፡፡ ሕጉን ያከብራል፡፡ ሕጉ እንዲቀየር ግን በአግባቡ ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ እየተሞከረና እየሆነ አይደለም፡፡ ሕጉን የማይወዱ ሰዎች አለመውደዳቸውን የሚገልጹት ሕጉን በመጣስ ነው፡፡ ይህ አውሮፓ ውስጥ አይደረግም፡፡ ይህን ለምን አደረጋችሁ ብለው ግን ይወቅሱናል፡፡ በዚህ ላይ ልዩነት አለን፡፡

ሁለተኛውና መሠረታዊው ጉዳይ እኛ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ የዜጎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበር የማድረግ፣ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታና የነፃ ፕሬስ ጉዳይ ኅብረቱ ስለጠየቀን የምናደርገው ነገር አይደለም፡፡ በሕገ መንግሥታችን ውስጥ እነዚህ መብቶች ሙሉ በሙሉ ተከብረዋል፡፡ ኢትዮጵያ አምናና ሕዝቦቿ በራሳቸው ያመጧቸው የትግል ድል ውጤቶች ናቸው፡፡ አምነን ነው በሕገ መንግሥታችን ውስጥ ያስገባናቸው፡፡ ማንም ተፅዕኖ ስላደረገብን አይደለም፡፡ ነገር ግን እነዚህን መብቶች ተግባራዊ በምናደርግበት ጊዜ የሚያጋጥሙ ችግሮች አሉ፡፡ ይህን ችግር ክደን አናውቅም፡፡ ከማስፈጸም አቅም ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙን ችግሮች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ቅድም እንዳልኩት ሕጉን ጥሰው ምናልባት ከውጭ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ አካላት አሉ በማለት ከሕጉ በላይ ለመንቀሳቀስ የሚፈልጉ ሲኖሩ ግጭት ይነሳል፡፡ አንዱ ችግር ይህ ነው፡፡ ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በራሳቸው ደረጃ መለካት ይፈልጋሉ፡፡ አውሮፓ አሁን በደረሰበት ደረጃ መለካት ይፈልጋሉ፡፡ ይኼ አንዱ የልዩነት ምንጭ ነው፡፡ እኛ ገና ታዳጊ ዴሞክራሲ ነው የያዝነው፡፡ ያለቀለት አይደለም፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የትም ያለቀ አይደለም፡፡ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎች በብዙ አገሮች ይነሳሉ፡፡ ሆን ተብሎ የሚደረግ ነገር የለም፡፡ ግልጽ የሆነ ፖሊሲና ሕገ መንግሥት አለን፡፡ እነዚህን እንዲያስፈጽሙ ያቋቋምናቸው ተቋማት አሉ፣ አሠራሮች አሉ፣ አደረጃጀቶች አሉ፡፡ እነዚህን ግን ገና ለጋ ናቸው አልጠነከሩም፡፡

ነፃ ፕሬስ ኢትዮጵያ ውስጥ ገና ጅምር ላይ ያለ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማት ገና በጅምርና በሒደት ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ሒደት ነው፡፡ ዋና ዋና በሆኑ ጉዳዮችና ለዚህ መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን እየመለስን ነው ያለነው፡፡ በዚህ ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮች አሉ፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ከአውሮፓ ኅብረት፣ ከፓርላማውም ሆነ ከሌሎች አካላት የምንጠብቀው ገንቢ በሆነ መንገድ የአቅም ግንባታና የልምድ ልውውጥ እንድናደርግ ካልሆነ በስተቀር፣ በተፅዕኖ የሚገነባ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የለም፡፡ በአጠቃላይ ግን የኅብረቱና የኢትዮጵያ መገለጫው ይህ አይደለም፡፡ ይህ አንዱ የግንኙነቱ መገለጫ ነው፡፡ ዋናው መገለጫ ግን ከላይ የገለጽኳቸው ሌሎች ለሁለቱም ወገኖች ጠቃሚ በሆኑ መስኮች የምንሠራቸው ሥራዎችና በዚያ ላይ ያለው ግንኙነት ነው፡፡ ይህ አንዱ ትችትም ወቀሳም የሚያቀርቡለት መስክ ሆኖ፣ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በመከባበር ልዩነታችንን አቻችለን በጋራ ጥቅሞቻችንና ጉዳዮቻችን ላይ እየሠራን ነው ያለነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ጋር በተያያዘ በቅርቡ የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ያቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ (ሞሽን) ነበር፡፡ በዚህ ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ በቅርቡ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የተከሰተውን አለመረጋጋት አስመልክቶ መንግሥትን የሚተቹ በርካታ አንቀጾች የተካተቱበት ሲሆን፣ ረቂቁ የውሳኔ ሐሳብ በመንግሥት የተወሰደውን ዕርምጃ እንደሚያወግዝ፣ እንዲሁም ጥፋተኛ የተባሉትን ግለሰቦች ለፍርድ እንዲያቀርብ ይጠይቃል፡፡ በዚህ በረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ዙሪያ የመንግሥት አቋም ምንድነው?

አምባሳደር ተሾመ፡- በመንግሥት ደረጃ ምላሽ አልሰጠንም፡፡ አስፈላጊ ከሆነ ተመካክረን ምላሽ እንሰጣለን፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን በእኔ ደረጃ በውሳኔ ሐሳቡ ላይ ያለኝን አመለካከት መግለጽ እችላለሁ፡፡ እንደተባለው አጀንዳ እንዲያዝና ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ እንዲቀርብ የተደረገበት አግባብ፣ በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎችና በአማራ አንድ አካባቢ በተፈጠረ ችግር ላይ ነው፡፡ ይህን ደግሞ ማድረግ ይችላሉ፡፡ በማንም ላይ ሥጋት አለን ሲሉና አጀንዳ ሊያዝ ይገባል ብለው ሲያስቡ አጀንዳ ይይዛል፡፡ በእኛ ጉዳይ አጀንዳ ሲያዝም ውሳኔ ሲተላለፍም የመጀመርያ አይደለም፡፡ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወቅትም አድርገዋል፡፡ ስለዚህ እንደ አሠራር አዲስ ነገር አይደለም፡፡ አጀንዳ ሊቀርብ የሚችልበት የራሱ የሆነ አሠራር አለው፡፡ አንዱ አንድ የፓርላማ ኮሚቴ በዚህ ጉዳይ ላይ አጀንዳ ይቅረብ ካለ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ሁለተኛው አንድ የፖለቲካ ቡድን እንዲቀርብ ከፈለገ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም 40 የፓርላማ አባላት አጀንዳ እንዲያዝና ውሳኔ እንዲተላለፍ ብለው ከጠየቁ ሊቀርብ ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ የምንጠረጥረው የሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ ቡድን ነው፡፡ ይህ ደግሞ አዲስ አይደለም፡፡ ከላይ እንደገለጹኩት ከምርጫ 97 በኋላ ባለው የፓርላማ ግንኙነት ውስጥ ያኔ ምርጫውን ለመታዘብ የታዛቢ ቡድኑ መሪ ሆነው የመጡት የፓርላማው አባል አሁንም የፓርላማው አባል ስለሆኑ፣ ኢትዮጵያ ላይ ሁልጊዜ አጀንዳ እንዲቀርብ ብዙ ግፊት ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ ከዚህ ለይተን የምንመለከተው አይደለም፡፡ ችግሩ አጀንዳ መቅረቡ ወይም ውሳኔ መተላለፉ አይደለም፡፡ የውሳኔው ይዘት ነው፡፡ የተነሳው አሁን በተፈጠረው ሁኔታ ነው ከተባለ በእሱ ላይ የተጣራ መረጃ ይዞ ችግሩን ለመፍታት አጋዥ በሚሆን መንገድ የተላለፈ ውሳኔ ነው ወይ የሚል ጥያቄ ብታነሳ ከዚህ ጋር አይዛመድም፡፡ በሁኔታው ላይ ያነሷቸው የተወሰኑ ነገሮች አሉ፡፡ ስለዚህ አንደኛ ከመረጃው ጀምሮ በአብዛኛው ተቃዋሚዎችና ማኅበራዊ ድረ ገጾች ሲያነሷቸው የነበሩ መረጃዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም መንግሥት እስካሁን ድረስ በዚህ ጉዳይ ላይ አጣርቶ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር፣ ችግሩ የተከሰተበትን ሁኔታ፣ የችግሩን መንስዔ፣ እንዲሁም ለዚህ ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን እስካሁን ድረስ አጣርቶ አላቀረበም፡፡ ነገር ግን ተጣርተውና ተሟልተው የተገኙ መረጃዎችን እንዳሉ አድርጎ የሚያቀርባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ስለዚህ በመረጃ ደረጃ ብዙ ስህተቶች አሉ፡፡ ይህ ደግሞ ትክክለኛ ወዳልሆነ ድምዳሜና ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል፡፡

ስለዚህ አነሳሱ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው ስለሆነ ትክክለኛ ወዳልሆነ ድምዳሜና ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል፡፡ ትክክለኛ መረጃ ይዞ በጥናት ላይ የተመሠረተ ሥራ ሠርቶ ገንቢ በሆነ መንገድ ለመቅረብ ቢሞክሩ ከዚህ የተሻለ ሥራ ሊሠሩ ይችሉ ነበር፡፡ አጋዥና ችግሩን ለመፍታት ደጋፊ በሆነ መንገድ መቅረብ ይችሉ ነበር፡፡ ስለዚህ የመረጃ መፋለስ አለው፡፡ ጉዳዩን ሳያጣሩ ይህን ያህል ሰው ሞቷል፣ የፀጥታ ኃይሉ ከሚገባው በላይ ኃይል ተጠቅሟል የሚለውን ያጣራው ማን ነው? በመንግሥት በኩል የፀጥታ ኃይሉም አመፁ ላይ የተሳተፉ ሰዎችም ድርጊት ተጣርቶ፣ እውነትም ከሚፈለገው በላይ ኃይል ተጠቅሟል ወይስ የፀጥታ ኃይሉ በወቅቱ የገጠመውን ፈተና ለመፍታት የወሰደው ዕርምጃ በቂ ነው በቂ አይደለም የሚለው ገና አልተጣራም፡፡ የሞቱ ሰዎች ቁጥር እንኳን በመንግሥት ደረጃ ሳይገለጽ ነው አቋም የያዙት፡፡ በአንድ በኩል ይጣራ ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንደተጣራ አድርገው ያንን መረጃ ይዘው በስሞታ ላይ የተመሠረተ ሐሳብ ነው በረቂቅ የውሳኔ ሐሳቡ ውስጥ ያለው፡፡ ሦስተኛው ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ አለ የሚባል ችግር በሙሉ ለቅመው ነው ያመጡት፡፡ አንዱ ገንቢ የማያደርገው ይህ ነው፡፡ አሁን ከተፈጠረው ችግር ጋር ያልተያያዘ መሆኑንና ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው አጀንዳ የሚያደርገው ይኼ ነው፡፡ በአጠቃላይ ፓርላማው ያደረገውን ውይይት በገንቢነት አንመለከተውም፡፡ ፓርላማው 750 አባላት አሉት፡፡ የኢትዮጵያ ሚሽን በቀረበበት ወቅት ለውይይት የተገኙት 41 አባላት ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥም 12  ሰዎች ብቻ ናቸው የተሳተፉት፡፡ ስለዚህ የአብዛኛው የፓርላማ አባላት ውሳኔ አይደለም፡፡ ውሳኔው ግን ዞሮ ዞሮ የወጣው በአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ስም ነው፡፡ በእኔ ግምገማ ውሳኔው በኢትዮጵያና በኅብረቱ ግንኙነት ላይ የሚያመጣው ጉዳት የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቡ በፓርላማው ይፋ ከተደረገ በኋላ በጉዳዩ ላይ ከፓርላማው አባላትና ከኅብረቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተገናኝቶ የመወያየትና የማስረዳት ዕድል ነበረዎት?

አምባሳደር ተሾመ፡- ውሳኔው ከተላለፈ በኋላ በውሳኔው ውስጥ ያሉትን ችግሮች በማሳየት ረገድ መረጃዎች እየሰጠን ነው፡፡ በነገራችን ላይ ውሳኔው ከመተላለፉ በፊትም የውሳኔ ሐሳቡ ያለበትን ስህተት የሚገልጽ ከ100 በላይ የሚሆኑ የፓርላማ አባላት መረጃ እንዲያገኙ አድርግናል፡፡ ነባራዊና ተጨባጭ ሁኔታውንና መንግሥት እያደረገ ያለው ነገር ይኼ ነው የሚል መረጃ ሰጥተናል፡፡ ከውሳኔው በኋላ ደግሞ በውሳኔው የተሳተፉትንም፣ እንደዚሁም ደግሞ በተለያዩ ኮሚቴ የሚሠሩ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ውሳኔው ምን ችግር እንዳለበትና አካሄዱ ገንቢ እንዳልሆነ ለማሳየት ፕሮግራም ይዘን እየሠራን ነው፡፡ ከዚህ ጋር አንዱ ችግር ግን የፓርላማው መቀመጫ ስትራስበርግ ስለሆነ አባላቱ ወደዚያ ይሄዳሉ፡፡ ብራሰልስ የኮሚቴ ሥራ አላቸው፡፡ ከዚያ ደግሞ ወደ ምርጫ ክልላቸው ይሄዳሉ፡፡ ስለዚህ በተባለው ቀጠሮና በምትፈልገው ልክ የማግኘት ጉዳይ የራሱ ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ብዙዎቹን ለማግኘት እንሞክራለን፡፡ ሁለተኛው ፓርላማው ውስጥ ባሉ ወዳጆች አማካይነት የኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት ወዳጅነት እንዲመሠረት ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ሚኒስትራችን በቅርቡ ጉብኝት ባደረጉበት ጊዜ ከሦስት የተለያዩ የፓርቲ ግን የተለያዩ ኃላፊነት ካላቸው የፓርላማ አባላት ጋር ተገናኝተዋል፡፡ በፓርላማው ዙሪያ ያለው ግንኙነት ገንቢ በሆነ መንገድና በመርህ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን እንዲሠሩ፣ ኢትዮጵያ በውስጥም በውጭም እየሠራች ያለችውን የስደተኞችን ጉዳይና የፀረ ሽብር ትግሉን በተመለከተ ከኅብረቱ ተቋማት ጋር እየሠራች ያለችውን ሚኒስትሩ ገልጸውላቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከላይ እንደገለጹት ከኢትዮጵያና ከኅብረቱ ስትራቴጂካዊ የሥራ አካባቢዎች አንዱ የፀረ ሽብር ዘመቻን በጋራ ማከናወን የተመለከተ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጃቸው ተቋማት አመራሮች በኅብረቱ ፓርላማ ፊት እየቀረቡ በአገሪቱ ስላሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ለፓርላማው ያስረዳሉ፡፡ ይህ ከያዛችሁት ስትራቴጂካዊ አጋርነት ጋር አይጣረስም? ይህ እንዴት ይታያል?

አምባሳደር ተሾመ፡- እንግዲህ የአውሮፓ ፓርላማ የሚሠራበት ሕግ አለው፡፡ አንዱ እንዳልከው በአንድ በኩል ይህን የመሰለ ስትራቴጂክ አጋርነት ያለው ሥራ እየሠራ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት በሽብር ተግባር ላይ ተሳትፎ አድርገዋል የሚላቸውን ድርጅቶች የሚመሩ ግለሰቦች አውሮፓ ፓርላማ ድረስ ይዞ ሲመጣ ምንድነው የሚባለው አይጣረስም ወይ የሚል ጥያቄ ቢነሳ አይገርመኝም፡፡ ዞሮ ዞሮ በዚህ ጉዳይ ላይም ተነጋግረናል፡፡ ከፓርላማው ጋር ሳይሆን ከፓርላማው አባላት ጋር ተነጋግረናል፡፡ እንደዚህ ዓይነት በሕገ መንግሥት የተመረጠ መንግሥትን በኃይል እጥላለሁ ብሎ ያውም ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ማዕቀብ የጣለበት አገር ላይ ሆኖ ኢትዮጵያን የሚወጋ የድርጅት መሪ አውሮፓ ኅብረት ድረስ ጋብዘው ይህን እንዴት እንደሚያደርጉ፣ ይኼ ደግሞ ኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት ከያዙት ስትራቴጂካዊ አጋርነት ጋር እንዴት ይሄዳል የሚል ብቻ ሳይሆን፣ ከዴሞክራሲ ሥርዓት መርህ አኳያ ጋርም የማይሄድ ነገር ነው፡፡ ችግሩ አንድ የፓርላማ አባል በፓርላማው ሕግ የተሰጠው መብት አለው፡፡ ያንን መብት ያላግባብ የሚጠቀም አለ፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገር እንዲቆም የሚጠይቁ የፓርላማ አባላትም አሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን አሠራሩ ስለሚፈቅድ ይህን መከልከል አልቻልንም የሚል ምላሽ ነው የሚሰጡን፡፡ ይህ ማለት ግን ይህን እንደግፋለን ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ የውጭ ግንኙነት ያወጣው መግለጫ እዚህ ባለው ልዑክ አማካይነት እንደዚህ ዓይነት ተግባር በመርህ ደረጃ አንደግፍም፣ አሠራሩን አንደግፍም፣ ተግባሩን አንደግፍም፡፡ ከዚህ በላይ ግን እንደዚህ ዓይነት ነገር የሚሆነው በግለሰብ የፓርላማው አባላት ግብዣ ካልሆነ በስተቀር፣ በኅብረቱ ተቋማት ግብዣ እንዳልሆነ መግለጫ አውጥቷል፡፡ ይህ ለእኛ በጣም በቂ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምርጫ 97ን ተከትሎ የኢትዮጵያና የኅብረቱ ግንኙነት የመሻከር አዝማሚያ ማሳየቱ ይታወሳል፡፡ በተለይ ደግሞ ከሰብዓዊ መብት አያያዝና ከዴሞክራሲ ጋር በተያያዘ፡፡ ለሁለቱ ወገኖች ግንኙነት መሻከር መንስዔው ደግሞ ምርጫውን ተከትሎ የኅብረቱ የምርጫ ታዛቢ ቡድን ያወጣው ሪፖርት ነበር፡፡ ታዛቢ ቡድኑን ይመሩት የነበሩት ደግሞ ፖርቹጋላዊቷ የኅብረቱ ፓርላማ አባል አና ጐሜዝ ናቸው፡፡ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥትና አና ጐሜዝ እሰጥ አገባ ውስጥ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር አና ጐሜዝ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ በመሥራት የኢትዮጵያ መንግሥትን በጣም በልጠውታል የሚል አስተያየት ይሰነዘራል፡፡ እርስዎ እዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አምባሳደር ተሾመ፡- ከምርጫ 97 በኋላ ግንኙነቱ በተወሰነ መልኩ ሻክሮ ነበር፡፡ ያኔም ቢሆን ከሁሉም ተቋማት ጋር አይደለም፡፡ የፓርላማ ታዛቢ ቡድኑ ያደረገው ነገር ለታዛቢ ቡድኑ ከተሰጠው ሥልጣን በላይና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ከፈጸመው ስምምነት ውጪ ነበር፡፡ በተለይ የምርጫ ታዛቢው ቡድን መሪ የወሰዱት አቋምና የፈጸሙት ተግባር ከዚህ ውጪ ስለሆነ ይህን በመቃወም ተቃውሞአችንን ገልጸናል፡፡ ሪፖርቱም እንዳይቀርብ አድርገናል፡፡ የታዛቢ ቡድኑ መሪ በግል እንደተጎዱና ማንነታቸው እንደተነካ አድርገው ስለቆጠሩ በአደባባይ ኢሕአዴግ የሚባል ድርጅት እስከሚወድቅ ድረስ ከተቃዋሚዎች ጋር እታገላለሁ ብለው ገልጸዋል፡፡ ከእሳቸው ጋር ለምሳሌ እኔ ለስድስት ዓመታት ለፓርላማ ጥምር ጉባዔ በሄድኩበት ጊዜ ሁሉ በመድረክ በጣም ፍትጊያና ፍጥጫ ነበረን፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን የሚለወጡ ከሆነ ለማየት ብለን በተወሰነ ደረጃ ተቀራርበን ለመሥራት ሞክረን ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2013 የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓስፊክ-አውሮፓ ፓርላማ ስብሰባ አዲስ አበባ አስተናግዳ እንዲገቡ ተፈቅዶላቸው መጥተው ነበር፡፡ ነገር ግን እሳቸው ባዩት ነገር የያዙትን አቋም ለመለወጥ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ከእሳቸው ጋር ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ተነጋግሮ በአንድ በኩል የተለወጠ ነገር አለ፡፡ ስለዚህ ይህን ዕውቅና ሰጥቶ በሌላ በኩል አሁንም እዚህ አካባቢ ላይ ልዩነት አለንና በልዩነቱ ላይ በቀጣይነት እንወያይ የሚል አቋም የለም፡፡ በተገኘው መድረክ ሁሉ ኢትዮጵያን የማውገዝና በኢትዮጵያ ሕዝብ የተመረጠ መንግሥትንና ድርጅትን የመኮነን ሥራ ነው እየተሠራ ያለው፡፡ ይህ ኢ-ዴሞክራሲያዊና ለኢትዮጵያ ሕዝብም ክብር የማይሰጥ ነው፡፡ እሳቸው የሚሠሩትን ያህል የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ለመሥራት ፍላጎቱ የለንም፡፡ ምክንያቱም ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ ምናልባት እሳቸው ተቃዋሚውን ለማስደሰት የሚሠሩት ሥራ ስለሆነ፣ እኛ በዚያ ልክ መልስ እየሰጠን ጊዜያችንን ማባከን አንፈልግም፡፡ የእኛ አትኩሮት የፓርላማና የኅብረቱ ተቋማት ናቸው፡፡ ስለዚህ ከእነሱ ጋር በቂ መረጃ እየሰጠን እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አገሪቱ በአሁኑ ወቅት የድርቅ አደጋ አጋጥሟታል፡፡ ይህንንም አደጋ ለመቋቋም የተለያዩ አገሮችና ተቋማት የዕርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉ መንግሥት ጠይቋል፡፡ ከዚህ አንፃር ከአውሮፓ ኅብረት የተሰጠው ምላሽ ምን ይመስላል? በተገኘው ምላሽስ መንግሥት ረክቷል?

አምባሳደር ተሾመ፡- እውነቱን ለመናገር ከውጭ ድርቁን በተመለከተ ድጋፍ እንዲገኝ ላቀረብነው ጥያቄ በተሰጠው ምላሽ አልረካንም፡፡ ለኅብረቱም ይህን ገልጸናል፡፡ ለተሰጠን ዕርዳታ አመስግነናል፡፡ ከውጭ ለችግሩ ይፈለጋል ብሎ መንግሥት በየጊዜ የገለጸው መጠን አለ፡፡ አሁን ወደ 1.4 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ይህን ያውቃሉ፡፡ ከችግሩ አንፃር የሰጡት በቂ እንዳልሆነ ሚኒስትራችን ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት አስረግጠው ነው የተናገሩት፡፡ መንግሥት አንድም ሕይወት እንዳይሞት እየደረገ ነው ያለው፣ ይህን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ይህ ማለት ግን በተወሰነ ደረጃ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ የያዝነው ዕቅድ እንዲታጠፍ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ወደዚያ ከመድረሳችን በፊት ሁለቱንም አቻችለን ለመሄድ ነው ሐሳባችን፡፡ ምክንያቱም ሁለተኛ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘላቂ ችግርን በመፍታትና ዘላቂ ልማትን በማምጣት ረገድ የሚጫወተው ሚና አለ፡፡ በአሥር ዓመታት ውስጥ እንደርስበታለን ብለን ያስቀመጥነው ግብ አለ፡፡ ስለዚህ ይህ ግብ እንዳይደናቀፍ በተቻለ መጠን በድርቁ አደጋ ላይ መንግሥት ድጋፍ ቢያገኝ ምርጫችን ነው፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ ፕሮጀክቶች እስከ መዝጋት እንሄዳለን የሚል ነገር አለ፡፡ ይህ እንዳይሆን ግን በድርቁ አደጋ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ፣ እንስሳት እንዳይሞቱ የሚያስፈልገው ዕቅድ በተሟላ መንገድ እንዲካሄድ፣ እንዲሁም ለዚያ ያስቀመጠውን መዋዕለ ንዋይ ወደዚህ ሳያዞር እንዲሄድ የማድረግ ሰፊ ሥራ እየሠራን ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በሐሳብ ደረጃ እስካሁን ድረስ የተሰጠው ገንዘብ በቂ አይደለም፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ሒጂራ ባንክ የ143 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዘገበ

በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ...

አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የሁለትዮሽ የምንዛሪ ገበያ እንዳይኖር ሊመክሩ ነው

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ያለውን...

ቡና ባንክ ዓመታዊ ትርፉን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር ቻለ

ቡና ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውን ለመጀመርያ...