የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በማኑፋክቸሪግ ዘርፍ ለመሰማራትና በአጠቃላይ በዘርፉ ዙሪያ ያሉ መረጃዎችን ለማግኘት ያስችላል ያለውን አዲስ ድረ ገጽ ሥራ ላይ አዋለ፡፡
ከንግድ ምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ ድረ ገጹ ከሚሰጠው መረጃ ባሻገር በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለተሰማሩና መሰማራት ለሚፈልጉ የምክር አገልግሎት ለመስጠት ባለሙያ ቀጥሯል፡፡ በየትኛውም የማኑፋክቸሪንግ ኢንቨስትመንት ዙሪያ የምክር አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት በመደረጉ፣ አገልግሎቱን ማግኘት የሚሹ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ከንግድ ምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ ያየህ ይራድ አባተ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተለይ ድረ ገጹ በማኑፋክቸሪነግ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ማንኛውንም ዓይነት መረጃዎችን የሚይዝ ይሆናል፡፡
ድረ ገጹ ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎችን ለማሳካት ወደ ሥራ የሚገባ ሲሆን፣ የመጀመርያው ዓላማ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲገቡ ለማበረታታትና ለመርዳት ያስችላል የሚል እምነት በመያዙ ነው፡፡
እንዲህ ዓይነቱ መረጃዎችን በተደራጀ ሁኔታ በቀላሉ እንዲገኝ ማድረጉ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ የሚሹ የውጭ ኢንቨስተሮች በቂ መረጃ እንዲኖራቸው ለማድረግ እገዛ ማድረጉ ደግሞ እንደሁለተኛ ግብ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ በድረ ገጹ ይካተታሉ ተብለው ከሚጠበቁ መረጃዎች ውስጥ አንዱ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን የሚመለከት ሕጎችና መመርያዎች በዋናነት ተቀምጠዋል፡፡ እነዚህ ሕጎችና መመርያዎች የሚለዋወጡ ከሆነም ይህንኑ እየተከታተሉ መረጃዎቹ ይቀመጣሉ ተብሏል፡፡
ከዚህም ሌላ በዘርፉ ለመሰማራት የሚፈልግ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኩባንያ የትኛው የመንግሥት መሥሪያ ቤት መሄድ እንደሚገባውና ፍቃድ ለማግኘትና ሌሎች አገልግሎቶችን ቢሻ እንዴት ማግኘት እንደሚቻል ዝርዝር መረጃም ይሰጣል፡፡
የየአንዳንዱን ተቋም ኃላፊነትና የሥራ አድራሻም በማቅረብ ድረ ገጹ የተሟላ መረጃ እንዲኖር በማስቻል ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡ የድረ ገጹ ሌላው መገለጫ ነው የተባለው ደግሞ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ኩባንያዎችን ምርት ማስተዋወቅና የኢትዮጵያን ምርቶች የሚገዙ አገሮች ግዥውን ለመፈጸም የሚጠየቁትን መስፈርቶች የሚመለከት በቂ መረጃ የያዘ መሆኑ ነው፡፡
የኢትዮጵያን የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች የሚቀበሉ አገሮች እነማን እንደሆኑ መረጃ የሚሰጠው ይህ ድረ ገጽ፣ የትኞቹ አገሮች የኢትዮጵያን ምርት ከቀረጥ ነፃ እንደሚቀበሉ፣ የትኞቹ ከኮታ ውጪ ምርቱን የሚያስገቡ እንደሆኑ በዝርዝር የሚታይበት በመሆኑ፣ ወደ ዘርፉ የሚገቡ ባለሀብቶች በቂ መረጃ እንዲያገኙ ይረዳል ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያን ምርቶች ለመግዛት የሚፈልጉ አገሮች ምርቱን ለማስገባት የሚጠይቋቸውን መስፈርቶች በዝርዝር ለማወቅ ከተፈለገም ከድረ ገጹ መረጃ ማግኘት ይቻላል፡፡ በድረ ገጹ ሌላው ይስጠዋል የተባለው አገልግሎት ደግሞ ለማኑፋክቸሪነግ ዘርፍ የሚያስፈለጉ ጥሬ ዕቃዎችን የሚያቀርቡና የሚገዙ ኩባንያዎችን ሊገናኙበት የሚያስችል ሁኔታ ያመቻቸ መሆኑን ነው፡፡ ማንኛውም ኩባንያ የሚፈለገውን ምርት ለመግዛት ጥያቄ የሚያቀርብበት፣ የሚሸጡትም ምርታቸውን ለሽያጭ የሚያቀርቡበት የራሱ የሆነ ቦታ ይኖረዋል፡፡ የገዥና ሽያጭ አድራሻዎችም ይጠቀሱበታል፡፡ የኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ምርቶች የገዥዎች አድራሻዎችም በድረ ገጹ ይቀመጣል፡፡
በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን ስኬት ካላስመዘገቡና ዝቅተኛ አፈጻጸም ከታየባቸው ዘርፎች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መሆኑ በይፋ ተነግሯል፡፡
ከዕቅዱ አንፃር ሲታይ አምስት በመቶ እንኳን መድረስ አልቻለም የተባለው ይህ ዘርፍ፣ አንዱ ችግር የመረጃ እጦት በመሆኑ ይህ ድረ ገጽ ክፍተቱን ሊሞላ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡