Sunday, October 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኩባንያዎች መልካም አስተዳደርና የኢትዮጵያ ኮርፖሬት ገቨርነንስ ኢንስቲትዩት ማነቆ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የንግዱ ኅብረተሰብ በሥነ ምግባር የታነፀ አሠራር መተግበር ግድ እየሆነ ስለመምጣቱ በተለያዩ መንገዶች ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በኮርፖሬት ገቨርናንስ የማይመራ የንግድ ተቋም ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል ከማይችልበት ደረጃ ላይ የሚጥለው መሆኑን ባለፈው ሐሙስ ጥር 26 ቀን 2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኮርፖሬት ገቨርናንስ ኢንስቲትዩት ባካሄው ጠቅላላ ጉባዔው ላይ ተገልጿል፡፡

የኮርፖሬት ገቨርናንስ ትግበራ የተለያዩ ድርጅቶች እንደሚከተሉት የሥራ አመራር ዘይቤና የእያንዳንዱ ድርጅት የባለቤትነት ሁኔታ በሚያስከትለው ውጤት የተነሳ የተለያየ ገጽታ ሊኖረው ቢችልም፣ የኮርፖሬት ገቨርናንስን መተግበር ግድ ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ፍትሐዊነት የመሳሰሉት መርሆዎች መሠረታዊና በሁሉም የኮርፖሬት ገቨርናንስ አደረጃጀቶች ውስጥ ሊታዩና ሊተገበሩ እንደሚገባ በጠቅላላ ጉባዔው ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኤልያስ ገነቲ ይገልጻሉ፡፡

በርካታ የንግድ ድርጅቶች የመንግሥትንም ሆነ በፈቃደኛነት የተቀበሉአቸውን ደንቦችና ሥርዓቶች በመከተል ኮርፖሬት ገቨርናንስን ተፈጻሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን መገንዘባቸውን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ቁጥራቸው ጥቂት የሆኑ ደግሞ በኮርፖሬት ገቨርናንስ የማይመሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ ስለዚህ የንግድ ኅብረተሰቡ አባላት የሥራ አካሄዳቸውና አፈጻጸማቸውን አስተካክለው ራሳቸውም፣ መንግሥትም ሆነ ኅብረተሰቡ በጋራ ተጠቃሚ የሚሆኑበትንና በቀጣይም ተገማች የሆነ አሠራር እንዲከተሉና የኮርፖሬት ገቨርናንስ መርሆዎችን መፈፀም ግድ እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡

ኮርፖሬት ገቨርናንስ ለአንድ አገር ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው፣ ለንግድ ድርጅቶች አለኝታ፣ በንግድ ድርጅቶችና ማምረቻዎች እንዲሁም በአገር፣ በኅብረተሰብና በዜጐቹ መካከል ያለውንና የሚኖረውን መተማመን በእጅጉ የሚጨምር ፅንሰ ሐሳብ እንደሆነም በዕለቱ የቀረበውም ጥናታዊ ጽሑፍ አመላክቷል፡፡

የኮርፖሬት ገቨርናንስ ክንውኖች አንድ የንግድ ድርጅት ሌሎች ድርጅቶች የደረሱበትን ደረጃ ገምግሞ የተሻለ አፈጻጸም ካላቸው እየተማረና ልምድ እየቀሰመ በተገቢው ዲሲፕሊን ሥራውን እያከናወነ እንዲራመድ ዕድል የሚሰጥ ጭምር መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ለገበያዎች፣ ለባለአክሲዮኖችና ለሌሎች ባለሀብቶች በወቅቱና በተሟላ ደረጃ በማቅረብ የድርጅቱን ባለቤቶችና የሌሎችን ባለድርሻ አካላት ጥቅም ማስከበር የሚችል በመሆኑ ጭምር፣ ሁሉም ተቋማት ሊተገብሩት ይገባል የሚለው አመለካከት የተንፀባረቀበትም መድረክ ነበር፡፡

በሌላ በኩል በንግድ ድርጅቶች የኮርፖሬት ገቨርናንስ ክፍተት ካለ የደንበኞች ቁጥር መቀነስ፣ ድርጅቱም በባለሀብቶችም ሆነ በሕዝቡ ዘንድ ድርጅቱ ያለው ተቀባይነትና እምነት በእጅጉ እየቀነሰ የሚሄድበት አዘቅት ውስጥ ሊገባ የሚችል መሆኑን በመግለጽ ኮርፖሬት ገቨርናንስን ያለመተግበር አደጋ ያለው መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ በአገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የድርጅቱ ተወዳዳሪነት ስለሚቀንስ፣ ለህልውናውም ሆነ ለአገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የሚዳከም ስለመሆኑ የኮርፖሬት ገቨርናንስ አስፈላጊነት በተመለከተ በዕለቱ የቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍም ሆነ በንግድ ምክር ቤቱና በኢንስቲትዩቱ የሥራ ኃላፊዎች በተለያየ መንገድ ተገልጿል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ውብሸት ኃይሉም የኮርፖሬት ገቨርናንስ አስፈላጊነት እጅግ አስፈላጊ ስለመሆኑ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ዓለም በቴክኖሎጂ እየታገዘና ባልታሰበ የዕድገት ፍጥገት እየቀጠለ ባለበት ሁኔታና ይዘት ምክንያት የንግድና ኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በአገሮች ታጥረው የሚከናወኑ አይደሉም፤›› በማለትም እንቅስቃሴያቸው ዓለም አቀፋዊ ገጽታ እየተላበሰ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ይህም በመሆኑ በአገሮችና በሚያመርቷቸው ምርቶችና አገልግሎቶች መካከል በገበያ ውስጥ ተወዳድሮ ለማሸነፍ የሚደረገው ውድድር ከምንጊዜም በላይ እየተጋጋለ መጥቶ በውድድሩ አሸናፊ ሆኖ መውጣት የሞት ሽረት ትግል እየሆነ ስለመጣ የኮርፖሬት ገቨርናንስ ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳ እየሆነ ነው፡፡

እንደ ኢንጂነር ውብሸት ገለጻ፣ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባትና የኢትዮጵያ የንግድ ድርጅቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸውን የመልካም አስተዳደር መርሆዎች ተቀብለው ተግባራዊ ማድረግ ካልቻሉ፣ ከዓለም ገበያ ውድድር ውጭ ይሆናሉ፡፡

ይህንን ጉዳይ ታሳቢ በማድረግ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ከውድድር እንዳይወጡና ተዳክመው እንዳይቀሩ ለማድረግ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት የኢትዮጵያ ኩባንያዎችን ኮርፖሬት ገቨርናንስን እንዲተገብሩ የኢትዮጵያ ኮርፖሬት ገቨርናንስ ኢንስቲትዩት መቋቋሙን ይገልጻሉ፡፡ እንዲህ ያሉ አስጊ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት የተቋቋመው ይህ ኢንስቲትዩት፣ ከንግዱ ኅብረተሰብ የተወከሉ የቦርድ አባላትን በመምረጥ ወደ ሥራ ከገባም ሁለት ዓመታት አልፈውታል፡፡

የተቋቋመበትን ዓላማ ለማሳካት ኩባንያዎች በኮርፖሬት ገቨርናንስ መርህ እንዲሠሩ ለማድረግም ንግድ ምክር ቤቱ ከስዊዲን ተራድኦ ድርጅት (ሲዳ) ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ኢንስቲትዩቱ ወደ ሥራ ቢገባም የታሰበውን ዓላማ ማሳካት አልቻለም፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዓላማ ወቅታዊ ስለመሆኑ በጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተገኙት የመንግሥት ተወካዮች ጭምር የመሰከሩለት ቢሆንም፣ ኢንስቲትዩቱ ይዞ የተነሳውን ዓላማ ለማሳካትና እንደታሰበው ሊራመድ ያልቻለበት ዋነኛ ምክንያት ከተቋሙ ዕውቅና ካለማግኘት ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል፡፡

የተቋሙ ፕሬዚዳንት እንደገለጹትም ተቋሙ በሚፈለገው ደረጃ ያልተራመደበት ዋነኛ ምክንያት፣ ተቋሙ ራሱን ችሎ ለመንቀሳቀስ የሚያስችለው የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ከመንግሥት ያለማግኘቱ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኤልያስም እንደ ኢትዮጵያ ኮርፖሬት ገቨርናንስ ያሉ ተቋማት ፍቃድ የሚሰጥ መንግሥታዊ አካል ባለመኖሩ ተቋሙ ሕጋዊ ሰውነት ሳያገኝ እስካሁን ቆይቷል፡፡  

ችግሩ የኢትዮጵያ ኮርፖሬት ገቨርናንስ ኢንስቲትዩት ብቻ ያለመሆኑን ያስታወሱት አቶ ኤልያስ፣ ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም በተመሳሳይ ፍቃድ ያለማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኮርፖሬት ገቨርናንስ ኢንስቲትዩት ሲጠነሰስ ጀምሮ የራሱ ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ እንዲንቀሳቀስ ታስቦ ነበር ያሉት አቶ ኤልያስ፣ በዚሁ መሠረት ተቋሙ ሕጋዊ ዕውቅና ተሰጥቶት ራሱን ማስተዳደር እንዲችል በቅድሚያ ለኢንስቲትዩቱ የመተዳደሪያ ደንብ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚሁ መተዳደሪያ መሠረት ሕጋዊ ዕውቅና ለማስገኘት የተደረገው ጥረት ግን አለመሳካቱንና እንዲህ ያሉ ተቋማት ለመመዝገብ ግልጽ ሥልጣን የተሰጠው አካል ባለመኖሩ፣ በተቋሙ የሥራ ሒደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ተቋሙን ለማስመዝገብና ፍቃድ ለማግኘት ብዙ ሙከራዎች ቢደረጉም፣ ለጊዜው ሊሳካ ባለመቻሉም የኢንስቲትዩቱ የፋይናንስና አስተዳደር ሥራዎች ብቻ ሳይሆኑ በሦስተኛ ወገኖች ዘንድ ኢንስቲትዩቱ የሚወከለው በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በኩል እንዲሆን አድርጐታል፡፡ በቅርቡም የሕጋዊ ዕውቅና ጉዳይ እልባት አግኝቶ ኢንስቲትዩቱ ኃላፊነቱን ሙሉ በሙሉ ይረከባል የሚል ግምት የሌላቸው መሆኑን የጠቀሱት አቶ ኤልያስ፣ የኢንስቲትዩቱን ሥራ ለማስቀጠል በሌላ መንገድ ለመጓዝ መወሰኑንም ተናግረዋል፡፡

ስለዚህ ምክር ቤቱ ቀደም ሲል በራሱ ጥላ ሥር አቋቁሞት ነገር ግን ከንግዱ ኅብረተሰብ መካከል በተመረጡ አባላት በተመሠረተ ካውንስል እንደሚመራው የግልግል ተቋም ሁሉ፣ ይህም ኢንስቲትዩት የራሱ ቦርድ፣ ፕሬዚዳንትና አባላት ኖረውት በሙያና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ከራሱ ቦርድ አመራር እየተቀበለ በምክር ቤቱ ሥር ሆኖ ሥራውን እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም ከዚህ ውጪ አማራጭ እንደሌለም በማስገንዘብ የንግድ ኩባንያዎች በኮርፖሬት ገቨርናንስ የሚመሩትን አሠራር ለማስፋፋት ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ አስገንዝበዋል፡፡

በዕለቱ በውጭ ኦዲተር የቀረበው የኦዲት ሪፖርት ላይ እንደቀረበውም ኢንስቲትዩቱ በ2007 በጀት ዓመት በተለይ ከስዊዲን ተራድኦ ድርጅት ካገኘው በጀት ውስጥ 65 በመቶ ያህሉን አልጠቀምበትም፡፡

ይህንን ያህል በጀት ጥቅም ላይ ሳይውል የቀረበት ዋናው ምክንያት የዕውቅናው ጉዳይ ቢሆንም፣ ኢንስቲትዩቱ በያዘው ዕቅድ መሠረት ሊሠሩ የሚችሉ በተለይ ዋና ሥራ አስኪያጅ ያለመገኘቱ መሆኑን የኢንጂነር ውብሸት ገለጻ ያስረዳል፡፡ በዚህ ዘርፍ ብቁ የሆነ ሥራ አስኪያጅ ያለመገኘቱም ሁለቱን ሥራ አስኪያጅ አሰናብቶ ለሦስተኛ ጊዜ የቅጥር ማስታወቁያ መውጣቱን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ የሚፈለገው የሥራ መሪ ቢገኝና ይሠራሉ የተባሉት ሥራዎች ቢሠሩ በጀቱን በአግባቡ መጠቀም ይቻል ነበር ብለዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ የታሰበውን ያህል ያለመሥራቱ ከመንግሥት ፍቃድ አለማግኘቱ ተደጋግሞ የተገለጸ ቢሆንም፣ የንግድ ሚኒስቴር ተወካይ ጉዳዩን መንግሥት እየተመለከተው በመሆኑ ችግሩ ሊቀረፍ ይችላል ብለዋል፡፡    

ዕውቅና መነፈጉ ያስከተለበት ክፍተት ቢኖርም ባለፉት ሁለት ዓመታት ለኮርፖሬት ገቨርናንስ ስርፀት የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ እንደነበሩ ከዓመታዊ ሪፖርቱ መገንዘብ ተችሏል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት ተወዳዳሪና ውጤታማ የገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓትን ለመገንባት ከፍተኛ ግብዓት እንደተገኘ እምነት አለኝ የሚሉት አቶ ኤልያስ፣ የንግዱ ኅብረተሰብ የራሱንም ሆነ የመላውን ኅብረተሰብ የኑሮ ደረጃ ለማሳደግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ይህ ሳይሆን ሲቀር መንግሥት ክፍተቱን ለመቀነስ ወይም ለማስወገድ ሲል የተለያዩ የሥነ ምግባር ሕጐችንና ደንቦችን እየቀረፀ በንግድ ኅብረተሰቡ ላይ ተፈጻሚ ማድረጉ የማይቀር በመሆኑ፣ ኩባንያዎች የኮርፖሬት ገቨርናንስን መተግበር አለባቸው ተብሏል፡፡ ኮርፖሬት ገቨርናንስ በፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የሥነ ምግባር ደንብ በመቅረፅ የሚከናወን በመሆኑ፣ የኩባንያዎች ፍቃደኝነት ወሳኝ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ 

በጠቅላላ ጉባዔው ላይ የተገኙት ተወያዮችም ኮርፖሬት ገቨርናንስ ካልተተገበረ የውጭ ኩባንያዎች ከአገር ውስጥ ኩባንያዎች ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስቸግራቸው ይሆናል፡፡

በተለይ በቀጣዩ አምስት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ልትሆን ስለምትችል፣ ኩባንያዎች ከወዲሁ ይህንን ጽንሰ ሐሳብ ለመተግበር ይዘጋጁ ተብሏል፡፡

በዚሁ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ኢንስቲትዩቱን ለቀጣዩ የሥራ ዘመን በፕሬዚዳንትነትና በቦርድ አባልነት የሚያገለግሉ አመራሮችን ምርጫ ተካሂዷል፡፡

በዚሁ ምርጫ የዋት ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ውብሸት ኃይሉ በድጋሚ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡ ከኢንጂነር ውብሸት ሌላ የኢትዮጵያ ሌዘር ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አምባሳደር ብሩክ ደበበ፣ የዋሪት ሙሉጥላ ኢንተርናሽናል ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ትህትና ለገሰ፣ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አየለ አሰፋም በድጋሚ የቦርድ አባላት ሆነው እንዲያገለግሉ ተመርጠዋል፡፡

በቀድሞ ቦርድ ውስጥ ሲያገለግሉ የቆዩት የሞላ ዘገየና ቤተሰቡ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሞላ ዘገየና የደቡብ ግሎባል ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሃባ ምትክ አዳዲስ የቦርድ አባላት ተመርጠዋል፡፡ ሁለቱን የቦርድ አባላት ተክተው እንዲሠሩ የተመረጡት የዳሸን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ ዓለሙና የቱሪስት ንግድ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ጉያ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች