Saturday, June 10, 2023

‹‹ከኢትዮጵያ ጋር አብረን ከምንሠራቸው መካከል የፀጥታና የደኅንነት ጉዳይ አንዱ ነው››

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ዶ/ር ሳአድ አሊ ሽሬ፣ የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር

ዶ/ር ሳአድ አሊ ሽሬ የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ናቸው፡፡ ዶ/ር ሽሬ ይህን ኃላፊነት በቅርቡ ከሞሐመድ ዮኒስ ተረክበዋል፡፡ ዶ/ር ሽሬ በሙያቸው አግሪካልቸራል ኢኮኖሚስት ሲሆኑ፣ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከመሸጋገራቸው በፊት በኢኮኖሚክ ፕላኒንግ ሚኒስቴር አገልግለዋል፡፡ ዶ/ር ሽሬ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ የተካሄደውን 26ኛውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የታደሙ ሲሆን፣ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮችን ዲፕሎማቶችና ሚኒስትሮች አግኝተው ተወያይተዋል፡፡ ዶ/ር ሽሬ ከነበራቸው የተጣበበ ጊዜ ላይ በመውሰድ አስራት ሥዩም በአገራቸው ጉዳይ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የጉብኝትዎ ዋና ዓላማ ምንድነው?

ዶ/ር ሳአድ አሊ ሽሬ፡- በዋነኛነት የመጣነው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔን ለመሳተፍ የሚመጡ ልዑካንን አዲስ አበባ ላይ ማግኘት ነው፡፡ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና የልዑካን ቡድን መሪዎችን ለማግኘት ተስፋ አድርገናል፡፡ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የሶማሊላንድ ማኅበረሰብንም ማግኘት እንፈልጋለን፡፡ ከኢትዮጵያዊያን አቻዎቻችን ጋር የምንነጋገርባቸው በርካታ ጉዳዮች ስላሉ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ለመገናኘትም ፍላጎቱ አለን፡፡ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ጋር እንደምንገናኝ ተስፋ አለን፡፡ ከፀጥታና ከደኅንነት፣ ከኢኮኖሚ ልማትና ከአጠቃላይ ክልላዊ ጉዳዮች አንፃር ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ በጣም አስፈላጊ አገር ነች፡፡ በበርበራ ኮሪደር በኩል ከኢትዮጵያ ወደ ሶማሊላንድ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር የመዘርጋት ፕሮጀክት አለ፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል ለረጅም ጊዜ የቆየ የንግድና ትራንዚት ስምምነትም አለ፡፡ ትምህርት፣ ሥልጠናና መሰል ጉዳዮችን ያካተተ የባህል ትብብርና ትስስር ጉዳዮች ላይም እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- እንደተረዳሁት ከአፍሪካ አገሮች ልዑካን ጋር የሚደረገው ግንኙነት ዋና ዓላማ ሶማሊላንድ እንደ አንድ ነፃና ሉዓላዊ አገር ዕውቅና የምታገኝበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር እነማንን ለማግኘት አስባችኋል? የውትወታ ሥራ ለመሥራትስ አስባችኋል?

ዶ/ር ሳአድ አሊ ሽሬ፡- ጉባዔውን የሚታደሙ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ለማግኘት ጠይቀናል፡፡ የስዊዚላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን አግኝተናል፡፡ ከኬንያ፣ ከጂቡቲና ከጋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘናል፡፡ የቤኒንና የቶጎን ጨምሮ የሌሎች የአፍሪካ አገሮችን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለማግኘትም ተስፋ አድርገናል፡፡ ዓለማችን ግልጽ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ለሶማሊላንድ ዕውቅና አይሰጡም፡፡ ከሶማሊያ ጋር ያምታቱናል፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያው ዓለማችን ሶማሊላንድን ለአፍሪካና ለተቀረው ዓለም ማስተዋወቅ ነው፡፡ የሶማሊላንድና የሶማሊያ ጉዳይ በመሠረቱ አፍሪካዊ ጉዳይ ነው ብለን እናምናለን፡፡

ስለዚህ የአፍሪካ ኅብረት ለችግሩ መፍትሔ በመሻት አጋር እንደሚሆን እናምናለን፡፡ በተጨማሪም አሁን በሶማሊላንድ ስላለው ተጨባጭ ሁኔታ ለሦስተኛ ወገኖች መረጃ መስጠት እንፈልጋለን፡፡ በፀጥታና በደኅንነት፣ በፖለቲካና በዴሞክራሲ፣ በጤና፣ በትምህርትና በልማት ተጨባጭ መሻሻሎችን አሳይተናል፡፡ ስለሶማሊላንድ ታሪክም ማስተማር እንፈልጋለን፡፡ ሶማሊላንድ ከሶማሊያ ለመገንጠል የሚጥር የአገሪቱ ክፍል ብቻ ሳይሆን፣ ከውህደቱ በፊት የራሱ ህልውና የነበረው ክፍል ነው፡፡ ሶማሊላንድ የራሱ የሆነ ቅድመ ቅኝ ግዛትና የቅኝ ግዛት ታሪክ ያለው፣ ቅድመ ውህደት ህልውና የነበረውና ባለፉት 25 ዓመታት ደግሞ ራሱን ችሎ የኖረ የአፍሪካ አገር ስለመሆኑ ዓለም እንድገነዘብ እንፈልጋለን፡፡

አንድ ሉዓላዊ አገር ማሟላት ያለበትን ቅድመ ሁኔታዎች በሙሉ ይዘናል፡፡ ብሪታኒያ ከጣሊያን፣ ከኢትዮጵያና ከፈረንሣይ ጋር ባደረገችው ስምምነት አማካይነት ሶማሊላንድ በውል የተለየና ድንበሩ የታወቀ ግዛት አላት፡፡ በምርጫ ወደ ሥልጣን የመጣ መንግሥትና በፓርላማ፣ በፕሬዚዳንታዊ ምርጫና በተዋረድ ምክር ቤቶች የሚገለጽ ዴሞክራሲም አለን፡፡ እንደ ጤና፣ ትምህርት፣ ፀጥታና ደኅንነት ያሉ መሠረታዊ አገልግሎቶችን የሚሰጥና መሠረተ ልማቶችን የሚገነባ መንግሥትም አላት፡፡ ስለዚህ እ.ኤ.አ. በ1933 በተፈረመው የሞንቴ ቪዲዮ ስምምነት መሠረት አንድ ለመሆን ሁሉንም መሥፈርቶች ታሟላለች፡፡ ስለዚህ ራሳችን በራሳችን ለማስተዳደር ስንጠይቅ መነሻችን ምን እንደሆነ ማብራራት እንፈልጋለን፡፡    

ሪፖርተር፡- ከሶማሊያ መንግሥት ጋር በቀጥታ በመደራደር መገንጠል ምርጫችሁ ነበር፡፡ ነገር ግን የሶማሊያ መንግሥት ለረጅም ጊዜ የተረጋጋ ባለመሆኑ ይህን ዕቅድ በተግባር ልትተረጉሙ አልቻላችሁም፡፡ አሁን ሶማሊያ እንደ አገር እያገገመች ከመሆኑ አንፃር ከሶማሊያ ጋር ያላችሁ ድርድር ምን ላይ ይገኛል?

ዶ/ር ሳአድ አሊ ሽሬ፡- ከሶማሊያ ጋር እ.ኤ.አ. ከየካቲት 2012 ጀምሮ ድርድር ላይ ነበርን፡፡ ዘጠኝ ዙር ውይይቶች ቢካሄዱም ስምምነት ላይ መድረስ አልቻልንም፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ የሶማሊያ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት አልሰጠም፡፡ በዚህ የተነሳ ጠንከር ያለ ውሳኔ መወሰን አልቻለም፡፡ አሁንም ለጉዳዩ ትግል ላይ ነን፡፡ የአሁኑ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሲመረጥ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ተስፋ ጥሎበት ነበር፡፡ ከሶማሊላንድ ጋር የሚደረገውን ውይይት ጨምሮ በአገሪቱ ጉዳይ ላይ ሙሉ ቁጥጥር ከየት ለውጥ ያመጣል ተብሎ ተጠብቆ ነበር፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ እስካሁን ለውጥ አልመጣም፡፡ አሁንም በውይይት ለውጥ ይመጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ይህ ማለት ግን ሌላ አጋር አንፈልግም ማለት አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከሶማሊያ ጋር የነበረው ውይይት ለምን ውጤታማ አልሆነም?

ዶ/ር ሳአድ አሊ ሽሬ፡- ውይይቱ በሶማሊላንድና በሶማሊያ መካከል መሆን ነበረበት፡፡ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ግን በላከው ልዑክ ቡድን ውስጥ በሶማሊያ የሚኖሩ ሶማሊላንዳዊያንን አካተተ፡፡ ይኼ የውይይቱን ዓላማ የሚፃረር ነው፡፡ ይህ የሶማሊያ መንግሥት ጉዳዩን በቁም ነገር እንዳልያዘው ምልክት ይሰጣል፡፡ እኛ ግን ውይይቱ ውጤታማ እንዲሆን ቁርጠኛ ነበርን፡፡

ሪፖርተር፡- ሶማሊላንዳዊያን የሶማሊያ ፌዴሬሽን አንድ አካል ይሆናሉ የሚሉ አሉ፡፡ የዚህ ሒደት አካል ናችሁ? ጉዳዩን እንደ አማራጭ የማየት ፍላጎትስ አላችሁ?

ዶ/ር ሳአድ አሊ ሽሬ፡- የሶማሊያ ፌዴሬሽን ጉዳይ ከበርካታ ዓመታት በፊት የተጀመረ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ሒደት ውስጥ ሶማሊላንድ ተሳታፊ ሆና አታውቅም፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው የፌዴራል መዋቅር አካል አይደለንም፡፡ እ.ኤ.አ. በ2016 ሊካሄድ የታቀደው የሶማሊያ ምርጫም እኛን አይመለከትም፡፡ የምክክር ሒደቱ ውስጥም የለንም፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 የራሳችንን ምርጫ እናካሂዳለን፡፡ ሁለታችንም ለየቅል ነው ጉዳያችንን የምንፈጽመው፡፡ ከሶማሊያ ጋር ያለን ግንኙነት በአቻነት በሁለት አገሮች መካከል ያለ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ነገር ግን በሒደቱ ውስጥ ሶማሊላንድን የወከለ ቡድን እንዳለ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ ቡድን ማነው? ተቃዋሚ ቡድን ነው?

ዶ/ር ሳአድ አሊ ሽሬ፡- በሶማሊላንድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያለ ሲሆን፣ ሦስት ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወዳድረው አንዱ መንግሥት ሲሆን ሁለቱ ተቃዋሚ ሆነው ቀጥለዋል፡፡ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎቹ በሒደቱ ተሳታፊ አይደሉም፡፡ በኬንያ፣ በኢትዮጵያና በሌሎች አገሮች እንዳሉት ሶማሊላንዳዊያን በሶማሊያ የሚኖሩም አሉ፡፡ እነሱ በሒደቱ ውስጥ መሳተፍ ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡ ከሶማሊላንድ ግን እንደ አገር የለንበትም፡፡

ሪፖርተር፡- ለችግሩ ሕጋዊ መፍትሔ ለማግኘት እያሰባችሁ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ከሶማሊያ መንግሥት ጋር የምታደርጉትን ንግግር ተዋችሁት ማለት ነው?

ዶ/ር ሳአድ አሊ ሽሬ፡- ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ከምናደርገው ድርድር ጎን ለጎን ራሳችን በራሳችን ለማስተዳደር የሕግ አግባብ ለመከተል ጥሩ ዕድል እንዳለን እናስባለን፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከሶማሊያ ጋር የምናደርገውን ድርድር እንቀጥላለን፡፡ ከፖለቲካ ውጪ በኢኮኖሚ፣ በፀጥታ፣ በደኅንነትና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ከሶማሊያ ጋር እንነጋገራለን፡፡ እያንዳንዱ አገር እኮ ከጎረቤቱ ጋር መነጋገር ይኖርበታል፡፡ የሕግ መንገድ መከተላችን ይህን ከማድረግ አያግደንም፡፡ 

ሪፖርተር፡- የሶማሊላንድ የምርጫ ኮሚሽን ምርጫው እ.ኤ.አ. በ2017 እንዲካሄድ ወስኗል፡፡ ምርጫው ለምን ተዛወረ? አሁንስ በተያዘለት ቀጠሮ የሚካሄድ ይመስልዎታል?

ዶ/ር ሳአድ አሊ ሽሬ፡- አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት አምስት ዓመት የሞላው እ.ኤ.አ. በ2015 ነበር፡፡ ምርጫውም በዚያው ዓመት መደረግ ነበረበት፡፡ ነገር ግን የምርጫው ጊዜ ሲቀርብ ስለነበረው ዝግጁነት መግሥትና በፓርላማ መቀመጫ ያላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገምግመው ነበር፡፡ ግምገማው ያሳየው ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ምርጫው እ.ኤ.አ. ለ2017 ተዛውሯል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ከመራጮች ምዝገባ ጀምሮ ነገሮች በጥሩ ሁኔታ እየተጓዙ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከፀጥታና ከደኅንነት አንፃር ሶማሊላንድ ከሶማሊያው አልሸባብ፣ ከባህር ውንብድናና ከአክራሪ ኃይሎች ጫና እንደሚፈጠርበት ይነገራል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመቆጣጠር ምን እየሠራችሁ ነው?

ዶ/ር ሳአድ አሊ ሽሬ፡- እነዚህ የፀጥታና የደኅንነት ችግሮች የሶማሊላንድ ብቻ ሳይሆኑ አጠቃላይ የክልሉ ችግሮች ናቸው፡፡ ነገር ግን ችግሮቹን ለመቅረፍ ሶማሊላንድ በከፍተኛ ትኩረት እየሠራች ነው፡፡ ለዚህም ነው ከአጠቃላይ በጀታችን ውስጥ ግማሽ ያህሉን ለወታደራዊ ኃይል፣ ለፖሊስ፣ ለፍትሕ አካላትና ለመሳሰሉት የፀጥታና የደኅንነት ዘርፎች የምንመድበው፡፡ ሕዝባችን በሰላማዊና በተረጋጋ ሁኔታ እንዲኖር የምናደርገው ጥበቃም ውጤታማ ነው፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ የፀጥታና የደኅንነት ችግር የገጠመን እ.ኤ.አ. በ2008 ነበር፡፡ የእኛ ሰላማዊ መሆን ኢትዮጵያንና ጂቡቲን ጨምሮ ለአካባቢው ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር አብረን ከምንሠራቸው መካከል ይኼው የፀጥታና የደኅንነት ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ የሁለቱም አገሮች የጋራ ፍላጎት ስለሆነ መረጃ እየተለዋወጥን አብረን እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ሶማሊላንድ የፀጥታና የደኅንነት ተግዳሮት የሚገጥማት ከሆነ ምንጩ ከየት የሚሆን ይመስልዎታል?

ዶ/ር ሳአድ አሊ ሽሬ፡- በሌሎች የአካባቢው አገሮች እንዳለው ሁሉ ዋናው ተግዳሮት ከአክራሪ ኃይሎች የሚመጣ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የሶማሊላንድ ኢኮኖሚ በበርበራ ወደብ ላይ ጥገኛ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህን ለማስፋት ጥረት ስታደርጉ ነበር፡፡ ጥረታችሁ ምን ያህል ውጤታማ ሆኗል?

ዶ/ር ሳአድ አሊ ሽሬ፡- በዋነኛነት የመንግሥት ገቢ የሚገኘው ከግብርና ከታክስ ነው፡፡ ከጉምሩክ ቀረጥና ከገቢና ወጪ ንግድ ግብርና ታክስ የሚገኘው ገቢ ወሳኝ ነው፡፡ እንደተባለው በርበራ የአገሪቱ ትልቁ ወደብ በመሆኑ ዋናው ገቢ የሚገኘው ከእሱ ነው፡፡ ይሁንና በአንድ የገቢ ምንጭ ላይ ጥገኛ መሆን የራሱ አደጋ ስላለው የገቢ መሠረቱን ማስፋት ያስፈልጋል በሚለው ላይ ስምምነት ተደርሷል፡፡ የአገር ውስጥ ገቢን የማሳደግ ሥራ እየሠራን ነው፡፡ የመንግሥት የፋይናንስ ሥርዓት ላይም ማሻሻያ እያደረግን ነው፡፡ አንዱ የማሻሻያው ክፍል ራሱን የቻለ የአገር ውስጥ ገቢ ታክስ ኤጀንሲ ማቋቋም ነው፡፡ የሶማሊላንድ ኢኮኖሚ መደበኛ ባልሆኑ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የበላይነት ሥር መሆኑ በእርግጥ ትልቅ ተግዳሮት ነው፡፡ ይኼ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር እንዳናደርግ አግዶናል፡፡ ይህን ለመለወጥ ከሕግ ማሻሻያ ጎን ለጎን ሕዝቡን የማስተማር ሥራም እየተከናወነ ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- ሶማሊላንድ ወደፊት ኤክስፖርት የምታደርጋቸው ምንድን ናቸው?

ዶ/ር ሳአድ አሊ ሽሬ፡- በአሁኑ ጊዜ በዋነኛነት ሶማሊላንድ ኤክስፖርት የምታደርጋቸው የቁም ከብቶች፣ ቆዳና ሌጦና ዕጣን ናቸው፡፡ ከቁም ከብት የምናገኘው ገቢ ይጨምራል ብለን እንገምታለን፡፡ የቁም ከብት ከመላክ የሥጋ ምርቶችን ብንልክ የበለጠ ተጠቃሚ እንሆናለን፡፡ ይህንን ለእስያ፣ ለአውሮፓና ለመካከለኛው ምሥራቅ ገበያ ለማቅረብ መሠረት የማስፋት ዕቅዳችንን ለማሳካት እንጥራለን፡፡ ቆዳና ሌጦውንም ወደ ቆዳ ምርቶች ብንቀይረው እንዲሁ እንጠቀማለን፡፡ ይኼ አሁን ኢትዮጵያ እያደረገችው ያለ ነገር ነው፡፡ ይኼ የውጭ ንግድ ምርቶችን ብቻ ሳይሆን ገበያዎችንም ለማስፋት ይጠቅማል፡፡ የዓሳ ምርቶችን ኤክስፖርት የማድረገ አቅሙም አለን፡፡ አንዱ ገበያ ኢትዮጵያ ልትሆን ትችላለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የማዕድን ዘርፉና ቱሪዝም እንዲሁ የወጪ ንግዳችንን የማጠናከር አቅም አላቸው፡፡ አዲስ መሠረት በመፍጠርና ባሉት ላይ እሴት በመጨመር ኤክስፖርት የማድረግ ዕቅድ አለን፡፡ 

ሪፖርተር፡- የበርበራ ወደብን በመሸጥ የመዝናኛ ማዕከልና ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ የማድረግ ዕቅድ ነበር፡፡ ይህ ዕቅድ ከምን ደረሰ?

ዶ/ር ሳአድ አሊ ሽሬ፡- አዎ ወደቡን ለቱሪዝም የመጠቀም አቅም አለን፡፡ ዕቅዱ ግን ገና በጅምር ያለ ነው፡፡ እጅግ ውብ የሆነ የባህር ዳርቻ አለን፡፡ ብዙ ኢትዮጵያዊያን መጥተው እንዲዝናኑ እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን ዘርፉ እንደ ሆቴሎችና ትራንስፖርት ያሉ ልማቶችን የሚጠይቅ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ዘርፉን ለማዳበር ያልተሠሩ ሥራዎች አሉን፡፡

ሪፖርተር፡- የበርበራ ወደብን ለማልማት የሶማሊላንድ መንግሥት ኩባንያዎችን ሊቀጥር እንደሆነም ተሰምቶ ነበር፡፡ ይህ ዕቅድ ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው?

ዶ/ር ሳአድ አሊ ሽሬ፡- ይኼ ለበርካታ ዓመታት ሒደት ላይ የነበረ ሥራ ነው፡፡ አሁን ለሥራው አራት ኩባንያዎች ተመርጠዋል፡፡ ከዓለም ባንክና ከአማካሪዎቻችን ጋር በመመካከር አንዱን እንመርጣለን፡፡ በያዝነው የአውሮፓውያን ዓመት አጋማሽ ላይ ሥራው ይጠናቀቃል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የወደቡን አቅም የማሳደግ ሥራ ይሠራል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም የሒደቱ ባለድርሻ ይሆናል፡፡ ከቶጎጫሌ እስከ በርበራ ድረስ ያለው የመንገድ ግንባታ በኢትዮጵያ ይፈጸማል፡፡ በቆይታዬ አንዱ የምንመክርበት ጉዳይም ይኼ ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -