የመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ለመንገድ ጥገና በየዓመቱ የሚመድበው በጀት ከፍተኛ ጉድለት ስላለበትና እያደገ የመጣውን የመንገድ ጥገና ፍላጐት ማሟላት የማይችል በመሆኑ፣ መንግሥት የመፍትሔ ዕርምጃ እንዲወስድ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጥያቄ ቀረበ፡፡ በትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ተፈርሞ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከአንድ ወር በፊት የቀረበው ደብዳቤ፣ የመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ከነዳጅ ሽያጭ ለመንገድ ጥገና የሚሰበስበው ፈንድ አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት ለመንገዶች ጥገና በቂ በጀት መመደብ ባለመቻሉ፣ መንግሥት የመፍትሔ ዕርምጃ እንዲወስድ ይጠይቃል፡፡ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ባረቀቀው የተቀናጀ ብሔራዊ የትራንስፖርት ፖሊሲ ረቂቅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥር 23 ቀን 2008 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል ባካሄደው ስብሰባ ላይ የተገኙ የትራንስፖርት ባለሙያዎች፣ ለመንገድ ጥገና ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠ ተናግረዋል፡፡ ‹‹መንግሥት ከፍተኛ ወጪ አውጥቶ መንገድ ይገነባል፡፡ በቂ በጀት ተመድቦ የጥገና ሥራ ካልተሠራ የተገነባው መንገድ ሊጠፋ ወይም ሊበላሽ ይችላል፤›› ብለዋል ባለሙያዎቹ፡፡ የመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ረሺድ መሐመድ ባለፉት 18 ዓመታት መንግሥት ለመንገዶች ግንባታ ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን ገልጸው፣ የዚህን ከ2.5 እስከ 3.5 በመቶ በዓመት ከአምስት እስከ ሰባት ቢሊዮን ብር ለመንገድ ጥገና መመደብ እንደነበረበት ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን በአማካይ በዓመት መመደብ የተቻለው አንድ ቢሊዮን ብር ብቻ በመሆኑ፣ የመንገዶችን ጥገና በአግባቡ ማካሄድ እንዳልተቻለ አስረድተዋል፡፡ አቶ ረሺድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ካለው የመንገድ ኔትወርክ በጥገና ፈንድ መሸፈን የተቻለው 35 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ስድሳ አምስት በመቶውን በበጀት እጥረት ምክንያት መሸፈን አልተቻለም፡፡ ‹‹17.5 ቢሊዮን ብር የጥገና በጀት በመመደብ የመንገድ ኔትወርኩን ደኅንነት መጠበቀ እንችላለን፡፡ ይህንን ካላደረግን ግን በመንገድ ጥገና ያልተሸፈነው 65 በመቶ የመንገድ ኔትወርክ ከአምስት ዓመት በኋላ 130 ቢሊዮን ብር ሊያስፈልገው ይችላል፤›› ብለዋል፡፡ የመንገድ ፈንድ ለመንገድ ጥገና የሚውል ከአንድ ሊትር ነዳጅ ሽያጭ 0.9 ሳንቲም በዓመት 1.2 ቢሊዮን ብር ይሰበስባል፡፡ አቶ ረሺድ ይህ ታሪፍ ከ18 ዓመት በፊት የወጣና ላለፉት ረዥም ዓመታት ክለሳ ባለመካሄዱ፣ በአሁኑ ወቅት የሚሰበሰበው ገንዘብ በቂ ሊሆን እንዳልቻለ አስረድተዋል፡፡ የጎረቤት ኬንያ መንገድ ፈንድ ከአንድ ሊትር ነዳጅ 0.10 ዶላር በዓመት 285 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሰበስብ አቶ ረሺድ አስረድተው፣ የታንዛኒያም ተመሳሳይ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ የመፍትሔ ዕርምጃ እንዲወሰድ የሚጠበቀው የፌደራል መንግሥት ሁለት አማራጭ እንዳለው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የትራንስፖርት ባለሙያ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹የመጀመሪያው አማራጭ ከነዳጅ ሽያጭ የሚሰበሰበውን የገንዘብ መጠን ማሻሻል ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ካልተቻለ ግን ከመንግሥት ተጨማሪ በጀት መመደብ አለበት፤›› ብለዋል የመስኩ ባለሙያ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን መንግሥት የተበላሹትን መንገዶች እንደ አዲስ ለመሥራት ለከፍተኛ ወጪ እንደሚዳረግ አሳስበዋል፡፡ መንግሥት በመንገድ ልማት ዘርፍ ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገቡ ይነገራል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት 48,000 ኪሎ ሜትር ብቻ የነበረው የመንገድ ኔትወርክ፣ በአሁኑ ወቅት 110,000 ኪሎ ሜትር ደርሷል፡፡ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት 200,000 ኪሎ ሜትር ለማድረስ እየተሠራ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ቀደም ሲል የመንገዶች ጥገና ለማካሄድ ዋነኛ ማነቆ የነበረው አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጭ አለመኖር ነበር፡፡ ‹‹የመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ከተቋቋመ በኋላ ችግሩ እየተቀረፈ መጥቷል፤›› ያሉት አቶ ሳምሶን፣ የመንገድ አውታር በከፍተኛ ደረጃ እየሰፋ በመምጣቱ የመንገድ ጥገና በጀት ፍላጎት በዚያው መጠን እያደገ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡ ‹‹የመንገድ ኔትወርክ ከ48,000 ኪሎ ሜትር ወደ 110,000 ኪሎ ሜትር ሲሰፋ የጥገና በጀት ፍላጎቱ በዚያው ልክ አድጓል፡፡ ይህን ያገናዘበ በጀት መመደብ አለበት፡፡ ከዚህ አኳያ የበጀት ምደባ ላይ የተወሰነ ክፍተት አለ፡፡ የእኛም አቋም ክፍተቱ መሟላት አለበት የሚል ነው፡፡ ችግሩ መቀረፍ ይኖርበታል፡፡ የሚመለከተው የመንግሥት አካል በጉዳዩ ላይ እየሠራበት ይገኛል፡፡ መፍትሔ እንደሚበጅለት እናምናለን፤›› ሲሉ አቶ ሳምሶን ገልጸዋል፡፡