Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ግዙፉ የቻይና የኮንስትራክሽን ኩባንያ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ተማርሬያለሁ አለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ባለሥልጣኑ ምሬቱ የተጋነነ ነው ብሏል

በአገሪቱ በመካሄድ ላይ በሚገኙት ግዙፍ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው የቻይናው ኮሙዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ (ሲሲሲሲ)፣ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መማረሩን ተናገረ፡፡

ኩባንያው ምሬቱን የገለጸው ጥር 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ባለሥልጣኑ ‹‹መልካም አስተዳደር በልማታዊ ታክስ ሥርዓት ግንባታ›› በሚል መሪ ቃል፣ ከፍተኛ ግብር ከፋዮችን በግዮን ሆቴል ለግማሽ ቀን ባወያየበት ወቅት ነው፡፡

ኩባንያውን በመወከል በውይይቱ ላይ የተሳተፉት አቶ በሽር የሱፍ እንደገለጹት፣ ኩባንያው ከፍተኛ ታክስ ከፋይ ነው፡፡ ለማሳያ ያህል እ.ኤ.አ. በ2013/2014 በጀት ዓመት 560 ሚሊዮን ብር ታክስ መክፈሉን ተናግረዋል፡፡

ኩባንያው ለፕሮጀክቶች የተለያዩ ግብዓቶችን የሚያቀርብ በመሆኑ ከሚከፍለው ታክስ ላይ ተቀናሽ ተደርጐ ተመላሽ እንዲደረግለት ጥያቄ ማቅረብ የሚችለው፣ ‹‹ከቫት በፊት ነው ወይስ በኋላ›› የሚለውን የአሠራር ዘዴ እንዲነገረው ለባለሥልጣኑ ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ እንደተነፈገው አስረድተዋል፡፡

ኩባንያው በቻይናዎች የሚመራ መሆኑን የጠቆሙት ተወካዩ፣ እ.ኤ.አ. ሴፕቴምበር 17 ቀን 2015 በደብዳቤ ጥያቄውን ያቀረበ ቢሆንም፣ ላለፉት ስድስት ወራት ምላሽ ማግኘት ባለመቻሉ ኃላፊዎቹ መማረራቸውንና ተስፋ መቁረጣቸውን አስረድተዋል፡፡

በአገራቸው በቻይና ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበው በሰባት ቀናት ውስጥ ምላሽ ካላገኙ ክስ መመሥረት እንደሚችሉ ተወካዩ ገልጸው፣ ላለፉት ስድስት ወራት ከባለሥልጣኑ ምንም ምላሽ በማጣታቸው ተስፋ መቁረጣቸውን እየገለጹ መሆኑን ተወካዩ ጠቁመዋል፡፡ የሚመለከታቸው የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ጉዳዩን አጽንኦት እንዲሰጡትም ጠይቀዋል፡፡

በቻይናው ኩባንያ የቀረበው ቅሬታ የተጋነነ መሆኑንና ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ ምላሽ የሰጡት፣ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረጄ መኰንን ናቸው፡፡ ባለሥልጣኑ ከሁሉም የድርጅቱ ሠራተኞች ጋር ጥሩ ግንኙነት አለው ብለዋል፡፡ ኩባንያው ታክስ በወቅቱ ከፍሎ ቻይና ለሚገኘው እናት ኩባንያው ታክስ ስለመክፈሉ ደብዳቤ እንዲጻፍለት ሲጠይቅ፣ ተገቢ ባይሆንም አገሪቱ ውስጥ ከሚሠራቸው በርካታና ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንፃር ለመተባበር ሲባል እንደሚጻፍለት አስረድተዋል፡፡ ኩባንያው ብዙ ሥራዎች ለሰብ ኮንትራክተሮች ስለሚሰጥና ሰብ ኮንትራክተሮቹ በተለይ በደረሰኝ ስለሚያጭበረብሩት፣ የተጭበረበረበትን ደረሰኝ ወደ ባለሥልጣኑ በማምጣት ተመላሽ እንደሚጠይቅ አስታውቀዋል፡፡

‹‹የኩባንያው ኃላፊዎችም ሆኑ ኩባንያው ባለማወቅ ጥያቄውን ስለሚያቀርቡ እንጂ፣ ኢትዮጵያዊ ኩባንያ ቢሆን ምን ልናደርገው እንደምንችል ግልጽ ነው፤›› ያሉት አቶ ደረጄ፣ በተወካዩ የቀረበው አቤቱታ የተጋነነ በመሆኑ እንዲታረም ጠይቀዋል፡፡ ችግር ካለ ተቀራርበው እንደሚያዩትና እንደሚፈቱትም አክለዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች በነጋዴዎቹ የቀረቡ ሲሆን፣ በተለይ ለባለሥልጣኑ ሠራተኞች ማበረታቻ የሚሰጥበት መንገድ በባለሥልጣኑ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ቢደረግላቸው የተፋጠነና ከጉቦና ከብልሹ አሠራር የፀዳ አገልግሎት ማግኘት እንደሚቻል ሐሳብ ቀርቧል፡፡ በተገልጋዩ ነጋዴና በባለሥልጣኑ ሠራተኞች (ከታች ሠራተኛ እስከ ከፍተኛ ኃላፊዎች ድረስ) የሥነ ምግባር ጉድለት እንዳለ በመጠቆም፣ ባለሥልጣኑ ወደኋላ ከሚሄድበት አሠራር ተላቆ ዓለም ወደደረሰበት ዘመናዊ አሠራር መሸጋገር እንዳለበትም ተነግሯል፡፡

በተለይ ከዋጋ በታች ደረሰኝ መስጠትን (አንደር ኢንቮይሲንግ)  በሚመለከት፣ ራሱ ጉምሩክ ሊፈትሽ እንደሚገባ የውይይቱ ተሳታፊዎች አሳስበዋል፡፡ ተቋሙ ለፖለቲካል ኢኮኖሚ ኪራይ ሰብሳቢነት የተመቸ በመሆኑ፣ ተገልጋዩም የተለያዩ የማጭበርበር ሥልቶችን የሚጠቀም መሆኑን የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ጠቁመው፣ ሁሉም ተባብሮ በመሥራት ግልጽነት የሰፈነበትና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ አሠራር ለመተግበር ተቋሙ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡  

የቻይናው ኮንስትራክሽን ኩባንያ የአዲስ አበባ-አዳማ የፍጥነት መንገድን ገንብቷል፡፡ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያን እየሠራ ነው፡፡ ከወልዲያ-ሃራ ገበያ-መቀሌ የሚዘረጋውን የባቡር መስመር እየገነባ ነው፡፡ ከደሴ-ኩታበር እንዲሁም ከኢንጂባራ፣ ቻግኒ ፕሮጀክትን ወስዶ እየሠራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች