– ፍርደኛው እስክንድር ነጋ የመከላከያ ምስክርነቱን አሰማ
በሽብር ድርጊት ወንጀል ተጠርጥረው ክስ በተመሠረተባቸው የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች በነበሩትና በነፃ በተሰናበቱበት የክስ መዝገብ የተካተቱት በእነዘለዓለም ወርቅአገኘሁ በመከላከያ ምስክርነት የተቆጠሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ የካቲት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀርበው እንዲመሰክሩ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ዓርብ ጥር 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ትዕዛዝ ሰጠ፡፡
በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሠተባቸውና ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ ያስረዱልኛል ያላቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች አቅርቦባቸው እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠባቸው ዘለዓለም ወርቅአገኘሁ፣ ዮናታን ወልዴ፣ ሰለሞን ግርማ፣ ባህሩ ደጉና ተስፋዬ ተፈሪ ሲሆኑ፣ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ ተሰናብተውና ይግባኝ ተብሎባቸው ከእስር ሳይለቀቁ በመከራከር ላይ የሚገኙት ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺ፣ አብርሃ ደስታ፣ የሺዋስ አሰፋና አብርሃም ሰለሞን መሆናቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
እንዲከላከሉ ብይን ያረፈባቸው እነዘለዓለም በመከላከያ ምስክርነት የቆጠሩት 18 ዓመታት በእስር እንዲቀጣ የተፈረደበትን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን፣ የግንቦት ሰባት ከፍተኛ አመራር የነበሩትንና ከየመን ሰንዓ አውሮፕላን ማረፊያ ተይዘው ወደ ኢትዮጵያ የመጡትን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌንና ሌሎች ምስክሮችን ነው፡፡
ጥር 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ቀርቦ የመከላከያ ምስክርነቱን ቃል አሰምቷል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ የሆነው ዘለዓለም ወርቅአገኘሁ ጋዜጠኛ እስክንድርን ጡመራ ምን ማለት እንደሆነና ከወንጀል ጋር ስላለው ግንኙነት፣ የሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ ሥልጠና ስለሚሰጡ ድርጅቶችና ስለሥልጠናው ይዘት እንዲያስረዳለት ጭብጥ አስይዟል፡፡ ጭብጡን ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በመቃወሙ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ጋዜጠኛ እስክንድር ጡመራ ምን እንደሆነና ከወንጀል ጋር ስላለው ግንኙነት እንዲያስረዳ በተከሳሹ የቀረበውን ጭብጥ በማለፍ፣ ስለዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት ስለሚሰጥ ሥልጠናና አሠልጣኝ ተቋማት ብቻ እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡
ጋዜጠኛ እስክንድር እንዲያስረዳ ስለተፈቀደለት ጭብጥ ከማስረዳቱ በፊት ስለማንነቱና ከየት እንደመጣ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ከመታሰሩ በፊት ጋዜጠኛ እንደነበር የገለጸው እስክንድር፣ አሁን ስላለበት ሁኔታ ሲጠየቅ ‹‹የህሊና እስረኛ ነኝ፤›› ብሏል፡፡ እንዲያብራራ ስለተፈቀደለት ስለሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲ ሥልጠናና አሠልጣኝ ተቋማት እንዳስረዳው፣ ሥልጠናውን የሚሰጡት ዓለም አቀፍ ተቋማት ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አገሮች ሥልጠናው ይሰጣል፡፡ ሥልጠናው ስለሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ ስለሚዲያና ሊከተላቸው ስለሚገቡ ሥነ ምግባሮች፣ እንዲሁም ስለዴሞክራሲ እንደሚሰጥ ገልጿል፡፡ ተቋማቱ የተለያዩ ሲሆኑ በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ ያላቸው መርህ ተመሳሳይ መሆኑንና የሚገኙትም በምዕራቡ ዓለም መሆናቸውን አስረድቷል፡፡
አሠልጣኝ ተቋማቱን በስም እንዲገልጽ የተጠየቀው ጋዜጠኛ እስክንድር ሲፒጄ፣ ፍሪደም ሀውስ፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ አርቲክል 19 እና የመሳሰሉት መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡ ስለሰብዓዊ መብት፣ ስለሚዲያና ስለዴሞክራሲ የሚሰጥ ሥልጠና መሆኑን፣ እሱም አዲስ አበባ ውስጥ በተሰጠ ሥልጠና ላይ መካፈሉን ጠቁሞ፣ ሥልጠናው ከሽብር ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ገልጿል፡፡ ሥልጠናው ማስረጃ ሆኖ በተከሳሾች ላይ መቅረቡ ኢትዮጵያን ትዝብት ላይ የሚጥልና አሳዛኝ መሆኑን በማስረዳት ምስክርነቱን አጠናቋል፡፡
የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የመከላከያ ምስክርነት ተሰምቶ እንደተጠናቀቀ ተከሳሽ ዘለዓለም ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ሌላው መከላከያ ምስክር ሆነው እንዲቀርቡለት በተደጋጋሚ ለፍርድ ቤቱ ያመለከተው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ቢሆንም ሊቀርቡለት እንዳልቻሉ አመልክቷል፡፡ በመሆኑም መንግሥት አቶ አንዳርጋቸው ቀርበው እንዲመሰክሩ ካልፈለገ፣ ዓቃቤ ሕግ ከአቶ አንዳርጋቸው ጋር በተገናኘ የመሠረተበትን የክስ ፍሬ ነገር ቀሪ አድርጐ በቀሪዎቹ ክሶች ላይ ብይን እንዲሰጥበት አመልክቷል፡፡
ነገር ግን መንግሥት በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ሲፈለጉ የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በፀረ ሽብር ግብረ ኃይል ከየመን ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ሲገልጽ እንደነበር በማስታወስ፣ ፍርድ ቤቱ ግለሰቡ ቀርበው ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ እንዲያዝለት ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የተከሳሹን አቤቱታ በመቀበል አቶ አንዳርጋቸው የካቲት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀርበው እንዲመሰክሩ መጥሪያ ለፌዴራል ማረሚያ ቤት እንዲጻፍ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሌሎች በሽብር ወንጀል ተግባር ተጠርጥረው ክስ በተመሠረተባቸው በእነዘመኑ ካሴ የክስ መዝገብ፣ በተደጋጋሚ ለመከላከያ ምስክርነት ተጠርተው ማረሚያ ቤት ‹‹እኔ ዘንድ የሉም›› የሚል መልስ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ግን ለሰበር ሰሚ ችሎት፣ ‹‹አቶ አንዳርጋቸው የዕድሜ ልክና የሞት ፍርደኛ ስለሆኑ በምስክርነት ሊቀርቡ አይችሉም፤›› ብሎ ያቀረበውን አቤቱታ ተቀብሎ፣ ‹‹ትርጉም ይሰጥበታል›› በማለት ለውሳኔ መቅጠሩን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡