Saturday, December 9, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ሕግ የማስከበር የመንግሥት ሥልጣን ከሕግ በላይ መሆን የለበትም!

ሕዝብን የማስተዳደር ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ሕግ የማስከበርና ፀጥታ የማስፈን ግዴታ አለበት፡፡ ይህንን ግዴታውን ሲወጣ ግን ለሕግ የበላይነት ትልቅ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል፡፡ በተለይ ሕግ ለማስከበር የማያሰማራቸው የፀጥታ ኃይሎች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባላቸው የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች መሠረት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ የአገሪቱ ሕገ መንግሥትም የሕይወት፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብትን በተመለከተ የደነገጋቸውን እንዲያከብሩ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ የሕግ የበላይነት ይከበር፡፡

በሕገ መንግሥቱ ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ ፍጡር በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብት አለው፡፡ ማንኛውም ሰው በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይወቱን አያጣም፡፡ ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት አለው፡፡ በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጪ ማንኛውም ሰው ነፃነቱን አያጣም፡፡ ማንኛውም ሰው በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጪ ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር አይችልም፡፡ ሕገ መንግሥቱ በሰብዓዊ መብቶች ላይ ካሰፈራቸው ድንጋጌዎች መካከል የሚጠቀሱት እነዚህ የዜጎች መብቶች፣ በፀጥታ አስከባሪዎች ሊከበሩ ይገባል፡፡ የግድ ነው፡፡

የሕግ የበላይነት የሚከበረው የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት ሲከበር ብቻ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ለሕጋዊነት አለመጨነቅ ልማድ እየሆነ ነው፡፡ ሕገወጥነትን ለመግታት በሚል በሚወሰዱ ዕርምጃዎች፣ የራስን ሕግ አክባሪነት የውኃ ልክ ከማስገመት በላይ በመንግሥት በራሱ ላይ ተደጋጋሚ ወቀሳዎችና ክሶች ተሰምተዋል፡፡ ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች የሕግ ጥሰት ፈጽመዋል ሲባል ከአያያዛቸው ጀምሮ እስከ ክስ ሒደታቸው ድረስ ያሉ ሥርዓቶች ሕጋዊ ሊሆኑ ይገባል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በሠፈሩ ድንጋጌዎች አማካይነት ተግባራዊ መሆን አለባቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ግን በተጨባጭ የሚታዩት ማተራመስ፣ ግርግር መፍጠርና ሰላማዊውን ድባብ የሚረብሹ በሕጋዊነት ስም የሚወሰዱ ሕገወጥ ዕርምጃዎች ናቸው፡፡ የሕግ የበላይነት በሌለበት ውጤቱ ጥፋት ነው፡፡

ወደኋላ ሄደን ኢሕአዴግ የዛሬ ሃያ አምስት ዓመት ገደማ የገባበትን ወቅት ስናስታውስ፣ በዝርፊያና በተቃውሞ ምክንያት የተፈጸሙ ድርጊቶችን አንረሳም፡፡ በወቅቱ ዝርፊያና ተቃውሞ በመታየታቸው የሰዓት  እላፊ ሲታወጅ እንደ መቀጣጫ ዕርምጃ ነበር የታየው፡፡ ዝርፊያውና ተቃውሞው ሲደጋገም ሰላማዊውን ከነውጠኛው ጋር አሳስቶ በጥይት የሚያስቀነድብ ሆነ፡፡ በወቅቱ ከበረሃ የመጡት የኢሕአዴግ ታጋዮች የሌባ መድኃኒትነት (መንትፎ የሚሮጠውን አይምሬነታቸውና የሰረቀውን ዕቃ አሸክመው ማዞራቸው) እንደ ዝና ተቆጥሮ በርካታ በደሎች ተፈጽመዋል፡፡ በሕግ መዳኘት ሲቻል የግለሰቦች ውሳኔ ለሰው ሕይወት መጥፋትና ለአካል መጉደል ምክንያት ሆኗል፡፡ የሕግ የበላይነት አልነበረምና፡፡

ከዚያም በኋላ ታኅሳስ 28 ቀን 1985 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከግቢያቸው ወጥተው ባደረጉት ተቃውሞ ከተፈጠረው ችግር ጀምሮ፣ ታኅሳስ 6 ቀን 1996 ዓ.ም. በጋምቤላ ብሔራዊ ክልል የተከሰተው ደም አፋሳሽ ግጭትና በ1997 ዓ.ም. ድኅረ ምርጫ ምክንያት በደረሰው የዜጎች ግድያ ምክንያት የተቋቋሙት አጣሪ ኮሚሽኖች የምንነጋገርባቸው ክሶችና ወቀሳዎች ማስረጃ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ክስተቶች በኋላም ምንም እንኳ አጣሪ ኮሚሽኖች ባይቋቋሙም ለበርካታ ዜጎች ሕልፈት፣ አካል መጉደልና ከመኖሪያቸው መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ድርጊቶች ተፈጽመዋል፡፡ በሕግ ማስከበር ስም የተፈጸሙ በርካታ መጣራት ያለባቸው ድርጊቶች አሉ፡፡ ለሕግ የበላይነት ሲባል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከድሮ ጀምሮ ‹‹እንቢ ላለ ሰው ጥይት አጉርሰው›› የሚባል ልማድ አለ፡፡ ይህ ዓይነቱ ልማድ ጠመንጃ ያልያዘን ተቃውሞ በጥይት እየደበደቡ ሳይጠየቁ መኖር ይቻላል የሚለውን አንድምታ የሚያሳይ ነው፡፡ የተቃውሞ ሠልፍን ወይም ስብሰባን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እስኪበተንና ዝምታና ፍርኃት እስኪነግስ ድረስ የሚካሄድ የፀጥታ ማስፈን ሥራ፣ ከመጠን ያለፈ ኃይል በመጠቀም ክቡር በሆነው የሰው ልጆች ሕይወት ላይ አደጋ ሲያደርስ ቆይቷል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎችም ሆነ በዋና ከተማው አዲስ አበባ በተለያዩ ጊዜያት ተስተውሏል፡፡ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በተነሳው ተቃውሞ የበርካታ ዜጎች ሕይወት ማለፉም ይታወሳል፡፡ ለሕግ የበላይነት ሲባል ችግሩ እንዳይደገም ጥረት ያስፈልጋል፡፡ የሕግ የበላይነት ጉዳይ መቼም ቢሆን ችላ መባል የለበትም፡፡

ሁሌም እንደምንለው የአገሪቱ ዋልታና ማገር መሆን ያለበት የሕግ የበላይነት ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ችግሮች ሲፈጠሩ ቅድሚያ ሊሰጥ የሚገባው ለሕግ የበላይነት ብቻ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት አንድ አገር በሕግ ጥላ ሥር የሚተዳደር መሆኑን ማሳያ መርህ ነው፡፡ ችግሮች ሲያጋጥሙ እንኳ ሕገወጥነት የበላይነት እንዳያገኝና የሕግ የበላይነት ችግር እንዳያጋጥመው ማንኛውም ዓይነት መስዋዕትነት መከፈል አለበት፡፡ በማናቸውም ጊዜ ችግር ሲፈጠር መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ሁልጊዜም ተመጣጣኝ የሆነ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወስዱ፣ ከመጠን ካለፈ የኃይል ተግባር እንዲቆጠቡ፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት እንዳለባቸው ሊያሠለጥናቸው ይገባል፡፡ በተቻለ መጠን ከጭካኔና ሰብዓዊነት ከጎደላቸው ሕገወጥ ተግባራት እንዲታቀቡ ማድረግ ግዴታው ነው፡፡ የፀጥታ አስከባሪዎች አለቆችም የበታቾቻቸውን እንቅስቃሴ መቆጣጠር፣ ሕግ በሚገባ እየተከበረ መሆኑን ማረጋገጥና ሪፖርት የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ካላጋጠመ በስተቀር የጦር መሣሪያ ባልያዙ ሲቪሎች ላይ በቀጥታ መተኮስ ሕገወጥ ተግባር በመሆኑ ይኼ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ከሕግ የበላይነት የተሻለ ምንም ነገር የለም፡፡

በፀጥታ አስከባሪዎች በተለይም በፖሊሶች አካባቢ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታዩ ተግባራት በጣም አደገኛ እየሆኑ ነው፡፡ አንዳንድ የፖሊስ ባልደረቦች በቁጥጥር ሥር ያዋሉዋቸውን ግለሰቦች ይደበድባሉ፣ ያሰቃያሉ፡፡ ከዚያም አልፈው ተርፈው በጦር መሣሪያ ይገድላሉ፡፡ ይህም በተለያዩ ጊዜያት የመገናኛ ብዙኃን የዜና ፍጆታ ሆኗል፡፡ የፖሊስ ባልደረቦች በሥራ ላይ እያሉም ሆነ በትርፍ ጊዜያቸው የሚፈጽሟቸው ሕገወጥ ተግባራት፣ የፀጥታ ተቋማቱንና በአገልጋይነት መንፈስ ኃላፊነታቸውን የሚወጡ ባልደረቦቻቸውን ሞራል ከመጉዳታቸውም በላይ፣ ዜጎች በሕግ የበላይነት ላይ ያላቸው ዕምነት እንዲጠፋ ያደርጋሉ፡፡ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ቅራኔ ይፈጥራሉ፡፡ ሕግ ለማስከበር የቆመ የፀጥታ ሠራተኛ ሕጉን ሲገረስሰው አገርም ጤና ታጣለች፡፡ መንግሥት በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ እዘምታለሁ ሲልም ይህንንም በአንክሮ ማየት አለበት፡፡ የሕግ የበላይነት መኖር ማሳያ ነውና፡፡

በአጠቃላይ የሕግ የበላይነት የሌለበት አገር የወንበዴ ዋሻ ነው የሚሆነው፡፡ ፍትሕ የሚፈልገው በገንዘብ እንዲገዛ ይገደዳል፡፡ የሕግ ከለላ የሚሻው የማፍያዎች ሰለባ ይሆናል፡፡ ሕዝብ እንዲያገለግል ሥልጣን የተሰጠው ሕዝቡን መልሶ ተገዢ ያደርጋል፡፡ በጥቅም የተሳሰሩ ኃይሎች የአገር ሀብት ይዘርፋሉ፡፡ ብዙኃኑን ሕዝብ እያደኸዩ ከቢጤዎቻቸው ጋር ይከብራሉ፡፡ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች በስፋት ስለሚጣሱ ሕዝቡ ይመረራል፡፡ በእነዚህ ሕገወጥ ድርጊቶች የተመረረ ሕዝብ ደግሞ እንቢ አሻፈረኝ ብሎ ሲነሳ የማይቀለብሱት ሁከት ይፈጠርና ሥርዓተ አልበኝነት ይነግሳል፡፡ በግብታዊነት የተነሳ መሪ አልባ አብዮት ውጤቱ ዕልቂትና ውድመት ነው፡፡  የሕግ የበላይነት የአንድ ማኅበረሰብ መመኪያ ሲሆን ግን ሰላም ይሰፍናል፡፡ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ይኖራል፡፡ ዴሞክራሲ በተግባር ይረጋገጣል፡፡ የግለሰቦችና የቡድኖቻቸው ጀብደኝነት ልክ ይገባል፡፡ በሥልጣን ያላግባብ እየተገለገሉ እንደፈለጉ መሆን ያቆማል፡፡ ይህ ደግሞ ለአገር ህልውና በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ስለዚህ ሕግ የማስከበር የመንግሥት ሥልጣን ከሕግ በላይ መሆን የለበትም!      

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...