Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአዲስ አበባና ዙሪያዋ ኢንፍሉዌንዛ መከሰቱ ተረጋገጠ

በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ኢንፍሉዌንዛ መከሰቱ ተረጋገጠ

ቀን:

– በዚካ ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች እንደነበሩ የሚያሳይ ፍንጭ አለ

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ ጉንፋን መሰል ኢንፍሉዌንዛ (A, B, H1N1) መከሰቱ በተደረጉ ሳምንታዊ ቅኝቶች መረጋገጡን፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዓርብ ጥር 27 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዳዲ ጂማ እንደተናገሩት፣ በጥር ወር በአዲስ አበባ በሚገኙ የተለያዩ የጤና ተቋማት ላይ ኢንስቲትዩቱ ባደረጋቸው ሳምንታዊ ቅኝቶች 32 ሰዎች በኢንፍሉዌንዛ መያዛቸው፣ ከእነዚህ ውስጥ አራቱ ሕይወታቸው ማለፉ ታውቋል፡፡ አራቱን ሰዎች ግን ለሕልፈት ያበቃቸው ኢንፍሉዌንዛው ብቻውን ሳይሆን፣ እንደ ሳንባና ስኳር ያሉ ሕመሞች ስለነበሩባቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የዚህ ዓይነቱ ኢንፍሉዌንዛ ከዚህ ቀደምም ወቅቱን እየጠበቀ ይከሰት እንደነበረው ዓይነት እንጂ፣ ምንም የተለየ ነገር አለመኖሩንም ዶ/ር ዳዲ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በኅብረተሰቡ  ብቻም ሳይሆን በሕክምና ባለሙያዎች በኩል ጭምር ሥጋትና መደናገጥ ታይቶ እንደነበር ዶ/ር ዳዲ አክለዋል፡፡ ዶ/ር ዳዲ ኢንፍሉዌንዛው ከዚህ ቀደምም የታየና ወቅት እየጠበቀ የሚከሰት ከሆነ የሕክምና ባለሙያዎችን ጭምር እንዴት ሊያደናግጥ ይችላል? የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ሲመልሱ፣ ‹‹በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የታዩና ኅብረተሰቡ ላይ ሥጋት የፈጠሩ መረጃዎች የሕክምና ባለሙያዎች ላይም ተፅዕኖ አሳድረዋል፤›› ብለዋል፡፡

የኢንፍሉዌንዛ መከሰትን ተከትሎ ለሕክምና ባለሙያዎች ሥልጠና መሰጠቱን የገለጹት ዶ/ር ዳዲ፣ አሁንም ቅኝቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም ናሙናዎች ለተጨማሪ ምርመራ አሜሪካ ወደሚገኘው ሴንተር ፎር ዲዚዝ ኮንትሮል (CDC) መላካቸውን ጠቁመዋል፡፡

ዶ/ር ዳዲ እንደገለጹት፣ ናሙናዎች መላካቸው ለዚህ ኢንፍሉዌንዛ ተብሎ ሳይሆን የተለመደ አሠራር ስለሆነ ነው፡፡ ከኢንፍሉዌንዛው ጋር በተያያዘ አስፈላጊውን ምርመራ ማድረግ የሚያስችል ላቦራቶሪ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡ ኢንፍሉዌንዛውን ለማከምም የሕክምና ባለሙያዎች የሚከተሉት መደበኛውን፣ አስፈላጊውንና መሠረታዊ በሽታ የመከላከል ፕሮቶኮል እንደሆነ ዶ/ር ዳዲ ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳ ኢንፍሉዌንዛው የተከሰተው አዲስ አበባና በዙሪያዋ መሆኑ ቢገለጽም፣ በቅኝቱ በኢንፍሉዌንዛ መያዛቸው ከተረጋገጠው 32 ሰዎች መካከል የተወሰኑት በሪፈራል ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ የመጡ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በሌላ በኩል ከቀናት በፊት የዓለም ጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ የጤና ሥጋት ነው ያለው የዚካ ቫይረስ፣ ከሁለት ዓመታት በፊት ለሌላ ምርመራ በተወሰዱ ናሙናዎች ላይ በተደረገ ምርመራ፣ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች እንደነበሩ ፍንጭ መገኘቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ አማካሪ ዶ/ር መርዓዊ አረጋዊ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡ በሽታውን የሚያስተላልፉ ትንኞች በማንኛውም ሞቃት የአየር ንብረት ክልል በብዛት የሚገኙ በመሆናቸው፣ በአፍሪካ ቫይረሱ ሊገኝ እንደሚችል ጥርጣሬ መኖሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት የተገኘው ፍንጭ በአሁኑ ወቅት ስላለው ሁኔታ የሚናገረው እንደሌለ የገለጹት ዶ/ር መርዓዊ፣ ኅብረተሰቡ በተለይም ነፍሰጡሮች ትንኝን መከላከል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ዶ/ር መርዓዊ እንደገለጹት ዚካ ቫይረስ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሥጋት ባይሆንም፣ የቫይረሱን መኖር አለመኖር መመርመር የሚያስችል ኬሚካል በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ አገር ውስጥ ይገባል ምርመራውን ማድረግም ይጀመራል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...