Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፌዴራል መንግሥት የጋምቤላ ክልል የፀጥታ ኃይሎችን ትጥቅ አስፈታ

የፌዴራል መንግሥት የጋምቤላ ክልል የፀጥታ ኃይሎችን ትጥቅ አስፈታ

ቀን:

በጋምቤላ ክልል በተቀሰቀሰው የከፋ ግጭት የክልሉ ልዩ ኃይልና ፖሊስ ተሳትፎ እንደነበራቸው በመረጋገጡ፣ በመከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደርገው ትጥቃቸውን ፈቱ፡፡

የጋምቤላ ክልል የፀጥታ ኃይሎች የሆኑት ልዩ ኃይልና ፖሊስ ግጭቱ በተቀሰቀሰበት ወቅት ጎራ ለይተው መታኮሳቸው ተነግሯል፡፡

በዚህ ምክንያት የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት የክልሉን የፀጥታ መዋቅር ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ትጥቅ በማስፈታት፣ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች አባላት ካምፕ እንዲገቡ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

የፌዴራል ጉዳዮችና የአርብቶ አደር ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ውለታው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የክልሉ የፀጥታ ኃይል ጎራ ለይቶ በመታኮሱ  የዕርምት ዕርምጃ መወሰድ ስላለበት ትጥቅ እንዲፈታ ተደርጓል፡፡ ‹‹በመከላከያ ሠራዊት ካምፕ እንዲገቡ ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ሙሉጌታ እንዳሉት፣ መንግሥት በጋምቤላ ክልል የተቀሰቀሰውን ግጭት በተመለከተ አስቸኳይ ዕርምጃ ሊወሰድባቸው በሚገቡ ስድስት ጉዳዮች ላይ እየሠራ ነው፡፡

የመጀመርያው በርካታ ሕይወት የቀጠፈውና የንብረት ውድመት ያስከተለውን ግጭት ማስቆም ነው፡፡ ‹‹ሰፋ ያለ ግጭት ለማድረስ የታቀደ ነበር፤›› ያሉት አቶ ሙሉጌታ፣ ‹‹የፌዴራል መንግሥት በአሁኑ ወቅት ግጭቱን መቆጣጠር ችሏል፤›› ብለዋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው ነጥብ በጋምቤላ ክልል የጎረቤት አገር (ደቡብ ሱዳን) ድንበር አዋሳኝ በመሆኑ በርካታ የጦር መሣሪያ ወደ አገር ውስጥ ይገባል፡፡ በዚህ ምክንያት በጋምቤላ የሚገኙ ዜጎች መሣሪያ በብዛት የታጠቁ በመሆናቸው፣ መሣሪያው ለሌሎች አካባቢዎችም ጠንቅ መሆኑን አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ምክንያት መሣሪያ ያነገበውን ዜጋ ትጥቅ የማስፈታቱ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አቶ  ሙሉጌታ ጨምረው አመልክተዋል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው በክልሉ የሚገኙ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችና በማረሚያ ቤት የነበሩ በግጭቱ ምክንያት አምልጠው የተሰወሩትን፣ በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየተሠራ መሆኑን አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡

በአራተኛ ደረጃ የተቀመጠው ጥር 19 ቀን 2008 ዓ.ም.  በተነሳው ግጭት ምክንያት የተዘጉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማትና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ተከፍተው መደበኛ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ማድረግ እንደሆነ አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡ በክልሉ የተነሳው ግጭት በቁጥጥር ሥር መዋሉ ቢገለጽም ኅብረተሰቡ ተረጋግቶ የዕለት ተዕለት ሥራ ማከናወን ባለመቻሉ ተቋማት እስካለፈው ሳምንት መጨረሻ ዝግ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በአምስተኛ ደረጃ የተቀመጠው የክልሉ የፀጥታ መዋቅሮችን በቁጥጥር ሥር ማዋል ነው፡፡ በስድስተኛ ደረጃ የተቀመጠው እነዚህ ጉዳዮች ከተከናወኑ በኋላ፣ የውይይት መድረኮች በሰፊው እንዲካሄዱ ማድረግና በአገር ሽማግጌዎችና በሃይማኖት አባቶች አማካይነት እርቅ ማውረድ ነው፡፡

አቶ ሙሉጌታ እነዚህ አጀንዳዎች በአጭር ጊዜ ከተከናወኑ በኋላ፣ በክልሉ በየጊዜው የሚነሳውን ግጭት ለአንዴና ለመጨረሻ ለማስቆምና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የሚያስችሉ ሥራዎች እንደሚከናወኑም ገልጸዋል፡፡

ከጋምቤላ ከተማ እስከ ወረዳዎች ድረስ በዘለቀው ግጭት የበርካታ ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ ከመንግሥት በኩል የሟቾች ቁጥርን በይፋ ማወቅ ባይቻልም ቁጥሩን ከ50 በላይ የሚያደርሱ መረጃዎች አሉ፡፡

በግለሰቦች ተነስቶ የአኙዋና የኑዌር ብሔረሰቦችን የተሸጋገረው ግጭት፣ ከሁለቱም ወገኖች በፍፁም ሊሆን በማይገባው ደረጃ የሰው ሕይወት እንዲያልፍ አድርጓል በማለት አቶ ሙሉጌታ ቁጭታቸውን ተናግረዋል፡፡

የተቀሰቀሰው ግጭት ከቀናት በኋላ በቁጥጥር ሥር ቢውልም፣ በክልሉ ነዋሪዎች ዘንድ ግን ግጭቱ ዳግሞ ሊነሳ ይችላል የሚል ሥጋት መኖሩን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ጉዳዮችና የአርብቶ አደር ልማት ሚኒስቴር ጥር 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረበ ሲሆን፣ ይኼው የጋምቤላ ግጭት አንዱ ጉዳይ ነበር፡፡ በሚኒስቴሩ የግጭት መከላከልና አፈታት ዳይሬክቶሬት ጄኔራል አቶ ሲሳይ መለስ እንደገለጹት፣ ስለግጭቱ መነሻና  የመፍትሔ ዕርምጃዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...