Sunday, April 21, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለሙስና የተሰመረው ቀይ መስመር እንዳይረገጥ ኤሌክትሪክ ያለው ሽቦ ሊቀመጥ ይገባል

በልዑል አ.

የራስ ያልሆነውን ገንዘብና ሀብት ሳይፈቀድ በተጭበረበረ መንገድ መውሰድ ሌብነት ነው፡፡ አንድ ሰው የሚፈልገውን ጉዳይ ለማስፈጸም፣ የሚፈልገው ጉዳይ እንዲሆንለት፣ በጉዳዩ ላይ የሚፈለገው ውሳኔ እንዲሰጥ አገልግሎት ለሚሰጥ ሰው የሚሰጠው ገንዘብ ወይም ጥቅም ጉቦ ነው፡፡ በመንግሥት እንዲጠብቅ የተሰጠውን ሀብትና ንብረት ሰርቆ ለራሱ የሚያደርገው ደግሞ ርካሽ ሌባ ነው፡፡ እንዲሁም በሕዝብና መንግሥት የተሰጠውን ሥልጣን በመጠቀም ትንሽ ጥቅም በማግኘት የሚያውቀው ሰው እንዲጠቀም፣ ሀብት እንዲያገኝ፣ የማይፈቀድ ሕገወጥ ተግባር እንዲፈጸም ማድረግ ሌብነት ነው፡፡ ሰነድ በመደለዝ ወይም የሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀም የማይገባውን ጥቅም ማግኘት ማጭበርበር ነው፡፡ እነዚህንና ሌሎች ሌብነቶችን ጠቅልሎ የሚይዘው ደግሞ ሙስና የሚለው ቃል ነው፡፡

የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ለራስ ጥቅም ማዋል ወይም ሌላ እንዲጠቀም መፍቀድ ሙስና መሆኑን የዓለም ባንክ ጽሕፈት ቤት የሰጠው ትርጉም ይገልጻል፡፡ በአገራችን ደግሞ ሙስና የሚለው ቃል የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ተብሏል፡፡ አክራሪነት፣ ጠባብነትና ጽንፈኝነት በሚል ቃል ትርጉምም ተሰጥቶታል፡፡ በጣም ደስ የሚለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ በተገኙበት መድረክ ሁሉ እነዚህን ቃላት የማይጠቀሙ መሆናቸው ነው፡፡ ሙስናን ብቻ ሌብነት ብለውታል፡፡ የመደናገሪያ ቃሎች ስለሆኑ አለመጠቀማቸው ያስመሰግናቸዋል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነት የሚለው ጥሬ ትርጉሙ በአንድ ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨመር ጥቅም ማግኘት ነው፡፡ በገበያ ላይ ያለውን የአቅርቦትና ፍላጎት መካከል የሚፈጠረውን ክፍተት በተለይም የአቅርቦት ማነስ ክፍተትን በመጠቀም ዕቃ ላይ ዋጋ በመጨመር ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ኪራይ ሰብሳቢነት የሚለውን ትርጉም እንዲያገኝ ያደርጋል፡፡ በመንግሥት ተቋማት ውስጥም ለሚከፈለው ደመወዝ ተመጣጣኝ አገልግሎት ሳይሰጥ ሌላ ተጨማሪ ገቢ መቆዘም ኪራይ ሰብሳቢነት ትርጉም እንዲያገኝ ያደርጋል፡፡ ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨምር ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ያሰበውን ካደረገና ከተገበረ ሌባ ወይም ሙስኛ ይሆናል፡፡ የኪራይ ሰብሳቢነትን አስተሳሰብ ሰብአዊ ፍጡር የሆነው ሰው ሁሉ የሚያስበው ስለሆነ እንደ አጋንንት ጠላት ተደርጎ እርግማን ማውረድ ተገቢ አይሆንም፡፡ በአጠቃላይ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ የሌለበት ሰው የለም፡፡ ወደ ተግባር ሲለውጥ ግን ሌባ ይሆናል፡፡

ወደ ተነሳሁበት ርዕስ ስመለስ ሙስና የሚለው ቃል በውስጥ ጉቦ መስጠትና መቀበል፣ መዝረፍ፣ መስረቅ፣ ማጭበርበር፣ ማዳላት፣ ሥልጣን ያላግባብ መጠቀም፣ ያለችሎታ መቀጠር፣ ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀም ሥራ መቀጠር፣ የሥራ ፈቃፍ ማውጣት፣ ወዘተ ትርጉሞችን ጠቅልሎ የያዘ ቃል ሲሆን፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ውስጥ ይህ ተግባር ይፈጸማል፡፡ በተለይ መንግሥታዊ ተቋማት ደግሞ የበለጠ የሙስና ተጠቂ ናቸው፡፡

ሙስና ጥቃቅንና ከፍተኛ ሙስና ተብሎ ይታወቃል፡፡ ጥቃቅን ሙስና የሚባለው የገንዘብ መጠኑ አነስተኛ የሆነ ሆኖ በሁሉም የመንግሥት ተቋማት ውስጥ በተለይም ከተገልጋይ ጋር ግንኙነት ባላቸው የግንባር አመራርና ሠራተኞች፣ የመንግሥት ሀብትና ንብረት ላይ የማዘዝ ሥልጣን ያላቸው የሚፈጸም ሙስና ሲሆን፣ የሚወሰደው ገንዘብ አነስተኛ ሆኖ የመጨረሻ ውጤቱ ከፍተኛ ሊሆን የሚችል ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ኬላ ላይ ለሚጠብቅ የጥበቃ አባል 1,000 ብር ጉቦ ሰጥቶ የያዘውን ዕቃ ካሳለፈ በኋላ ያሳለፈውን ዕቃ ሲጠቀም ይህ ዕቃ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የአንድ ወር ደመወዝ ለቀጣሪ በመልቀቅ የሚቀጠር ሠራተኛ የትምህርት ማስረጃው ሐሰተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ያለዕውቀቱ ብዙ ዜጎችን ያጉላላል፣ ያበሳጫል፡፡ ሐሰተኛ ሰነድ የሚያዘጋጁት ሰዎች ለዝግጅት ሥራው ብር 1,500 እስከ 2,000 ብቻ ተቀብለው የሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ሰነድ አዘጋጅተው ይሰጣሉ፡፡ ይህን ሐሰተኛ ሰነድ ተጠቃሚ ተቀጥሮ ይሠራል፣ የሥራ ፈቃድ አውጥቶ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የሚሰጠው አገልግሎት ግን ጥራቱን ያልጠበቀ ለምሳሌ ምሕንድስናና ሕክምና ሙያ ሲሆን የባሰ ኅብረተሰቡን ለችግር የሚዳርግ ሊሆን ይችላል፡፡ በአገራችን በጣም እየተስፋፋ የመጣው የጥቃቅን ሙስና ወንጀል መሆኑን የተካሄዱ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ይህን ሙስና መቆጣጠር በጣም ከባድና ብዙ መስዋዕትነትን የሚጠይቅ ነው፡፡

ከፍተኛ የሙስና ወንጀል ሌላው የሙስና ዓይነት ነው፡፡ ይህ ሙስና የገንዘብ መጠኑም በጣም ከፍተኛ ሲሆን፣ ይህን ሙስና የሚሠሩት በከፍተኛ የመንግሥት ገንዘብና ንብረት ላይ የማዘዝ ሥልጣን ያላቸው የመንግሥት ሹመኞች ናቸው፡፡ በተለይም ከፍተኛ የመንግሥት የዕቃና አገልግሎት ግዥ ላይ ይህ ሙስና ይፈጸማል፡፡ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የግንባታ ሥራዎች ሲሠሩ፣ ከፍተኛ የሆነ የዕቃ ግዥ ሲፈጸም በዕቃ አቅራቢውና በመንግሥት ሹመኛ መካከል የሚፈጸም ስምምነት የሚፈጸም ሲሆን፣ ዕቃ አቅራቢው ወይም ግንባታ ፈጻሚው የራሱን ድርሻ በጠበቀ መልኩ በመንግሥት ገንዘብ ላይ እንዲፈረድ የሚደረግበት ነው፡፡ ከፍተኛ ሙስና ወንጀል በአገራችን አለ፡፡ ግን ለመቆጣጠር የሚቻል ነው፡፡

ሌላው ሙስና የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሙስና ይባላል፡፡ ፖለቲካ ሙስና የሚባለው በምርጫ ሒደት ላይ ምርጫን ለማሸነፍ ሲባል በተመራጭና በመራጭ መካከል የሚከናወን ሙስና አብላጫውን የፖለቲካ ሙስና ትርጉም ሲኖረው፣ በተለይም ተፎካካሪና ተወዳዳሪን ለማሸነፍ ሲባል ከምርጫ ቅስቀሳ ጀምሮ መራጩን ሕዝብ በገንዘብ መደለልና ምርጫውን ማሸነፍ፣ ወይም ከተፎካካሪው በበለጠ ለመንቀሳቀስ አቅም ማጎልበት ሲሆን፣ የፖለቲካ ሥልጣንን በመጠቀም ሕገወጥ ተግባራት እንዲፈጸሙ ማስገደድና ማስተግበርም ትርጉም ይሆናል፡፡ የምርጫ ካርድ መሰወር ወይም ማታለል የፖለቲካ ሙስና ይባላል፡፡ የኢኮኖሚ ሙስና የሚባለው ደግሞ ከላይ እንደተገለጸው በመንግሥትና በሕዝብ ገንዘብና ንብረት ላይ የሚፈጸም የጥቃቅንና ከፍተኛ ሙስናዎችን ትርጉም የያዘ ነው፡፡

ስለ ትርጉም ይህን ያህል ካልን ደግሞ የአገራችን ሙስና ምን ይመስላል? የሚለውን በዝርዝር እንየው፡፡ በአገራችን ሙስና በብዛት የሚሠራባቸው ተቋማት መኖራቸውን የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽንና በዓለም ባንክ አስተባባሪነት  የተካሄዱ የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ እነዚህ ተቋማት በአገራችን ከፍተኛ ሀብትና ንብረት የሚያንቀሳቀሱ፣ ለአገሪቱ በጀት ከፍተኛ የገቢ ምንጭነት የሚያገለግሉ፣ በየዕለቱ ብዙ ተገልጋይ የሚፈለግባቸው የመንግሥት ተቋማት ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት በፌዴራልና ክልል ውስጥ ያሉ በመሆናቸው በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ከሚያገለግሉት ውስጥ በተለይም ለተገልጋይ ግንባር ላይ ያሉ አመራርና ሠራተኞች ሙስና ይሠራሉ፡፡ ለሚሰጡት አገልግሎት ጉቦ ይጠይቃሉ፡፡ በጓደኝነት፣ በዝምድና በጉርብትና አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ከእነዚህ ተቋማት ውጪ ደግሞ ከፍተኛ የግንባታ ሥራዎችን የሚያስተዳድሩ፣ በበጀት ዓመት ከፍተኛ ዕቃ ግዥ የሚፈጸምባቸው ተቋማት ውስጥ በግዥ ሒደት ላይ ከፍተኛ ሙስና ይፈጽማሉ፡፡ ባንኮች ውስጥ ሚስጢራዊ የይለፍ ቃል ተጠቅመው የሕዝብ ገንዘብ ወደ ራሳቸው ሒሳብ በማዛወር ሙስና ይሠራሉ፡፡ በመንግሥት ተሽከርካሪ ጥገና ሰበብ የመንግሥት ገንዘብ ይዘርፋሉ፡፡ በቢሮ ኪራይ ሰበብ የመንግሥት ገንዘብ ይዘርፋሉ፡፡ መብራት ሆን ብለው በማጥፋት ለመልቀቅ ጉቦ ይወስዳሉ፡፡ ባልተሟላና በተጭበረበረ ሰነድ፣ የንግድና ሥራ ፈቃድ በሙስና ይሰጣሉ፡፡ ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የመንግሥት ተሽከርካሪና ነዳጅ ብዙም የማይታወቅ የሙስና ወንጀል የሚፈጸምበት ዘርፍ ነው፡፡ በሌለ ዶላር ተገዝቶ የመጣውን ነዳጅ ለግለሰቦች ጉዳይ ማስፈጸሚያ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ በአገራችን ውስጥ ሀብታም ከሆኑት ሰዎች ውስጥ ከመንግሥት ኃላፊዎችና ሠራተኞች ከመንግሥት በጀት ላይ በተሰጣቸው ቸርነት የበለፀጉ ብዙ ናቸው፡፡ ይህም የታለመ ሀቅ ነው፡፡

በዝርዝር የተገለጹት ችግሮች በአገራችን ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ሲመጣ፣ ደሃ የነበሩ ሰዎች በአንድ ጊዜ ምንጩ ባልታወቀ ሀብት ወደ ላይ መምጠቅ ሲጀምሩ ነበር፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽንን መንግሥት ያቋቋመው፡፡ በፌዴራል ላይ ብቻ በዚያ አላበቃም በክልሎችም የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ የፌዴራልና የክልል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች መቋቋማቸው ሙስና በአገሪቱ እንዳይንሰራፋ ሊገቱት አልቻሉም፡፡ እንዲያውም  የጥቃቅን የሙስና ወንጀል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል፡፡ የከፍተኛ ሙስና ወንጀል ጥቆማዎች ለኮሚሽኖቹ ብዙ ስለማይመጥኑ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በአጭሩ የተቋቋሙ የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች የመፈጸም ብቃትና ክህሎት የሚያንሳቸው መሆኑ ነው፡፡ ፌዴራልና ክልል መንግሥታትም ኮሚሽኖችን የበለጠ በማጠናከር ለሥራቸው በቂ ክትትልና ድጋፍ አለማድረጋቸው የመጀመርያ ችግር ነበር፡፡ የኮሚሽኖች ሠራተኞች በአገሪቱ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ከሚከፈለው የደመወዝ መጠን የተሻለ አይከፈላቸውም፡፡ በሌሎች ፀረ ሙስና ኮሚሽንን ባደራጁ አገሮች ከፍተኛ የደመወዝ ተከፋይ የሚሆኑት የፀረ ሙስና ተቋማት ሠራተኞች መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ሩቅ ሳይኬድ የኬንያ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ለአመራርና ሠራተኞች የሚከፍለውን የደመወዝ መጠን በጉግል ጎልግሎ ማየት ይቻላል፡፡

ኮሚሽኖቹ በሥራቸው ላይ የመንግሥት ኃላፊዎች እጃቸውን ሲዘረጉ ከለላ አልተደረገላቸውም፡፡ የጥቃት ሰለባ ሲሆኑ ለምን እየተባለ አይደለም፡፡ ስለሆነም በተለይም የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ከ2009 ዓ.ም. በፊት የምርመራና ዓቃቤ ሕግ ሥራ ሲሠራ በነበረበት ወቅት የመንግሥት ድጋፍና ዕገዛ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ በሕዝቡ ጥቆማ የቀረበባቸው ሰዎች ለመንግሥት ሹመት ሲታጩ የተጀመረው የሙስና ወንጀል እንዲያቋርጥ በከፍተኛ መንግሥት አመራር ይታዘዝ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ሙስና ፈጽመው የሙስና ወንጀል ጥቆማ ቀርቦባቸው የምርመራ ሥራ እንዲቋረጥ የተደረገባቸው ሰዎች አሁንም ድረስ በሥልጣን ላይ አሉ፡፡ የመንግሥት ኃላፊዎች የሚፈልጉት ባለሀብት ወይም ሌላ ሰው በፈጸመው የሙስና ተጠርጣሪነት በኮሚሽኖቹ በቁጥጥር ሥር እንዲውል ሲደረግ እንዲለቀቅ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡ መንግሥት በዚህ ዙሪያም ድጋፍ አያደርግም ነበር፡፡

ለሙስና ተጋላጭ በመሆናቸው አሠራሩን እንዲያሻሽሉ ሲጠየቁ ፈቃደኛ የማይሆኑ የመንግሥት ኃላፊዎች ላይ የሚወሰድ ዕርምጃ አለመኖር ለሙስና መባበስና ኃላፊዎች የልብ ልብ እንዲያገኙ አድርጎታል፡፡ ኮሚሽኑ በሕግ ሀብታቸውን እንዲያስመዝግቡ የሚገባቸው ሰዎች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ሲያደርግ ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑት ተቋማትና ሰዎች በመኖራቸው የተመዘገበውን ሀብት ለማሳየት ፈርቷል የሚባል ጉምጉምታም አለ፡፡ ተከታትሎ እንዲያስመዘግቡ ባለማድረጉ ሊደርስበት የሚችለውን በመፍራት በዚህ ሀብታቸውን ያላስመዘገቡ፣ ነገር ግን ሕዝቡ ሊያያቸው የሚፈልጋቸው የመንግሥት ኃላፊዎች እንዳሉ ከኮሚሽኑ የውስጥ አዋቂ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በአንድ ወቅት መንግሥት ለሙስና ትግል ያለውን ቁርጠኝነት በትክክል የተረዱት የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ሠራተኞች ኮሚሽኑ እየለቀቁ ጠበቃ ለመሆን የሥራ ፈቃድ በማውጣት ዘመቻ ጀመሩ፡፡ አብዛኛዎቹ ደግሞ ኮሚሽኑ በነበሩበት ወቅት ለሚያውቁት የሙስና ወንጀል ጉዳይ ከውጭ ሆነው የጥብቅና ሥራ መሥራት አዋጪ መሆኑን ስለተረዱ ፊታቸውን ወደ ሙስና ተጠርጣሪ ጥብቅና አዞሩ፡፡ በዚያ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የሆነ ሰው ለሙስና ተጠርጣሪዎች ጥብቅና እንዲቆም በባትሪ ጭምር ይፈለግ ነበር፡፡ ጓደኛው በኮሚሽኑ በኩል ለፍርድ ቤት ለሚያቀርባቸው የሙስና ወንጀል ክስ ቀደም ሲል ኮሚሽኑ ውስጥ ዓቃቤ ሕግ ሆኖ ሲሠራ የነበረው ጠበቃ ሆኖ ይቀርባል፡፡ ለሥራቸው ሥምረት ውሏቸውን ኮሚሽኑ አድርገው እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ሚስቱ ጠበቃ ባሏ ደግሞ ዓቃቤ ሕግ እንደነበሩም ማስታወስ ይቻላል፡፡ የጥብቅና ፈቃድ አውጥቶ የሚሠራው ጠበቃ ገቢ ስለሚፈልግ ለሥራው መሳካት የኮሚሽኑን መርማሪና ዓቃቤ ሕግ የሚያገኙ ደላሎችን ማሠማራት ጀመሩ፡፡ በዚህም በዚያም የጠበቃዎችና ደላሎች መሯሯጥ ሥራው የአገር ሙስናና ወንጀል መከላከል መሆኑ ቀርቶ የግለሰቦች ኪስ ማደለቢያ መሆን ሲጀምር ኅብረተሰቡ በኮሚሽኑ የፀረ ሙስና ትግል ላይ ጥያቄ ማንሳት ጀመረ፡፡ ለኮሚሽኑ ሌላ ኮሚሽን መቋቋም እንደሚያስፈልግ በየመድረኩ መነገር ጀመረ፡፡ መንግሥትም የኅብረተሰቡን ችግር የተረዳውና የሰማ መሰለኝ በአዋጅ የምርመራና ዓቃቤ ሕግ ሥራዎችን ለፖሊስና ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ለኮሚሽኑ በአብዛኛው የሚቀርበው በጥቃቅን ሙስና ወንጀል ላይ ያተኮረ ጥቆማ ስለነበር የምርመራና ዓቃቤ ሕግ ሥራም በአብዛኛው በጥቃቅን የሙስና ወንጀል ላይ ያተኮረ ነበር፡፡

ሆነም ቀረ አሁን ደግሞ ክቡር ዶ/ር ዓብይ ለ60 የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ክሳቸው ተቋርጦ በምሕረት እንዲለቀቁ አድርገዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሙስና ላይ አምርረው እየተናገሩ እንዴት የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎችን በምሕረት ይለቃሉ ሲባል ከተማው ውስጥ በስፋት ይወራል፡፡ የመረጃ እጥረት ይመስላል፡፡ መታወቅ ያለበት በከፍተኛ ሙስና ወንጀል ተርጣርጣሪ የሆኑት እነ መላኩ ፈንታም ሆኑ ሌሎች ሰኔ 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በሙስና ወንጀል የታሰሩት ሰዎች የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ወይም ፌዴራል ፖሊስ የሙስና ወንጀል ምርመራ ቢሮ የሙስና ወንጀል ጥቆማ ቀርቦባቸውና ምርመራ ተካሄዶባቸው የታሰሩና የተከሰሱ ሰዎች አይደሉም፡፡ እነ መላኩ ፈንታ እኮ ሲታሰሩ ኮሚሽኑ በፍፁም አያውቅም ነበር፡፡ ኮሚሽኑ ያወቀው እንደማንም ዜጋ ዓርብ ማታ ግንቦት 5 ቀን 2005 ዓ.ም. በሚዲያ ሲነገር፣ ለዚያውም የፌዴራል ፖሊስ ለመረጃ የሕዝቡን ዕገዛ ሊጠይቅ ባስተላለፈው ዘገባ ሲሆን፣ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሙስና ወንጀል ምርመራ ሥራ ሙያው ስለሆነ ብቻ ሰዎቹ ከታሰሩ በኋላ ሰነዶችን የመመርመርና ክስ የመመሠረት ሥራ ሠርቷል፡፡ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ክሱን ተከታትሏል፡፡

በሰኔ ወር 2009 ዓ.ም.  የታሰሩት የሙስና ተጠርጣሪዎች በፌዴራል ፖሊስ የሙስና ወንጀል ምርመራ ቢሮ በደረሰው የሙስና ወንጀል ጥቆማ በተካሄደው ምርመራ ሥራ ሳይሆን መንግሥት በራሱ መንገድ ሄዶበት ሙስና ሠርተዋል ብሎ በማሰቡ እንዲታሰሩ ካደረገ በኋላ የምርመራ ሥራው በፌዴራል ፖሊስ የሙስና ወንጀል መርማሪዎች እንዲካሄድ፣ የክስ ሥራ ደግሞ በጠቅላይ ዓቃቤ እንዲከናወን የተደረገ ስለሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ ምሕረት ማድረጋቸው ትክክል ናቸው፡፡ እነዚህ በትክክል የሙስና ወንጀል በመሥራታቸው ከሕዝብ የሙስና ወንጀል ጥቆማ ቀርቦባቸው ሳይሆን፣ መንግሥት በራሱ መረጃ ደኅንነት በማጣራት ባረጋገጠው መንገድ በማሰር ምርመራ እንዲካሄድና ክስ እንዲመሠረት የተደረገ ስለሆነ ምሕረቱ ይገባቸዋል ባይ ነኝ፡፡

በአገሪቱ የሙስና ወንጀል ላይ ዕርምጃ ይህን ሥራ እንዲሠራ በሕግ የተቋቋመ ተቋም እያለ በሌላ አካል ይህን ሥራ ማሠራት ተገቢ ስለማይሆን መንግሥት ይህን ማስተካከል ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለሙስና ተጠርጣሪዎች በተሰጠው ምሕረት ምክንያት ቀጣይ የፀረ ሙስና ትግል እንቅስቃሴ መስተጓጎል የለበትም፡፡ የሙስና በአገር ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት አኳያ ሲታይ ሰላም የሚነሳ የካንሰር በሽታ ስለሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስቀመጡት አቅጣጫ ቀይ መስመር ሆኖ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ማንም ቀይ መስመሩን መርገጥ የለበትም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ባለው ሁኔታ ቀይ መስመር ይፈራል ተብሎ ስለማይታሰብ የረገጠው ሰው እንዲደነግጥና እንዲያዝ ኤሌክትሪክ ያለው አደገኛ ሽቦ ሊደረግ ይገባል፡፡ ቀይ መስመር ሲረገጥ ብቻ ተሳስተሃል የሚል ነጭ ምልክት ማሳየት ብቻውን በቂ አይሆንም፡፡

የፌዴራልና የክልል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽኖችም ያለባቸውን ችግሮች አሁን በዶ/ር ዓብይ እየተፈጠረ ያለውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዕውቀትና ክህሎት ባላቸው የሰው ኃይል እንደገና በማደራጀትና ቁሳቁስ አሟልተው በመንቀሳቀስ ለውጥ የሚያመጣ የፀረ ሙስና ትግል ተግባራትን ከኅብረተሰብ ጋር በመሆን በንቃት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኅብረተሰቡን ሙስና በራስ ላይ ባይደርስም በገር ልማት ዕድገት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ ራሱን ከሙስና ከመቆጠብ ሙስና የሚሠሩትን ሰዎች ባገኘው አጋጣሚ በሙሉ ማጋለጥ ይጠበቃል፡፡ መንግሥትም ያስቀመጠው ቀይ መስመር አለመነካቱን በየጊዜው በሚያካሄደው ጠንካራ ክትትልና ሥራ ማረጋገጥና ቀይ መስመሩ ሳይረገጥ እንደተጠበቀ መሆኑ ለኅብረተሰቡ ማረጋገጫ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ እንዲሁም ሙስና የሚያጋልጡ ሰዎች በሙሰኞች በምንም ተዓምር እንዳይጠቁ ከለላ መስጠቱን ማጠናከርና በሙስና መከላከልና መዋጋት ላይ ተሰማርተው ትግል የሚያካሄዱ ዜጎች በተለይም የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን አመራርና ሠራተኞች እንዲበረታቱ በልዩ ሁኔታ የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም ወጪዎችን በበቂ ሁኔታ መመደብ ይኖርበታል፡፡ በተቋማቱ ውስጥ የሚመደቡ አመራርና ሠራተኞችም በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው መሆን ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles