Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ጉዞ ወደ ተፈጥሮ›› አረንጓዴው ፌሽታ

‹‹ጉዞ ወደ ተፈጥሮ›› አረንጓዴው ፌሽታ

ቀን:

የተለያዩ አገሮች የአየር ንብረት ለውጥ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮቻቸው ላይ እያደረሰ ያለውን ከፍተኛ ጉዳት ለመከላከል ይችሉ ዘንድ በአረንጓዴ ልማትና በተፈጥሮ ጥበቃ ላይ ያተኮረ ፖሊሲ ቀርፀዋል፡፡ እንዲሁም ሕዝብ በንቃት የሚያሳትፍባቸውን ተፈጥሮን በመንከባከብ ላይ ያተኮሩ፣ እያዝናኑ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ የስፖርትና ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶችን በማከናወን ጉዳቱን ለመከላከልና በዘላቂነት ከችግሩ ለመዳን የዜጎቻቸውን ግንዛቤ በማስፋት ላይ በትኩረት እየሠሩ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ኢትዮጵያም በዚህ መልኩ በንቃት እየተሳተፉ ከሚገኙት አገሮች ተርታ በዋናነት ትጠቀሳለች፡፡ ይሁን እንጂ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ማኅበረሰቡ ያለው ግንዛቤ አናሳ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም ከመንግሥትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ድርጅቶች፣ እንዲሁም ከተቋማት ጋር አብሮ በመሥራትና የሚኖርበትን አካባቢ ፅዱና አረንጓዴ በማድረግ ረገድ እያሳየ ያለው እንቅስቃሴ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

ይህን የግንዛቤ እጥረት ለመቅረፍ ከመንግሥትና ከተለያዩ ድርጅቶች ጎን በመቆም ማኅበረሰቡን እያዝናና አዳዲስ መንገድ እያሳየ በመሄድ በኩል ኪነ ጥበብና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡

በዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ ከጀመሩ የኪነ ጥበብ ድርጅቶች መካከል ‹‹ኪነ ምስሎች›› ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ይገኝበታል፡፡ ድርጅቱ ተፈጥሮን ማልማትና መንከባከብን አስመልክቶ ለማኅበረሰቡ በአዲስ መንገድ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚረዳ ‹‹ኢትዮ አረንጓዴ ፌሽታ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው በዓይነቱ ልዩ የሆነ የሰባት ቀናት ፌስቲቫል አዘጋጅቷል፡፡

የኪነ ምስሎች ኢቬንት ሥራ አስኪያጅ ወጣት ታደሰ ልብሰመንግሥት እንደገለጸው፣ ‹‹ጉዞ ወደ ተፈጥሮ›› በሚል ርዕስ ከሰኔ 28 ቀን እስከ ሐምሌ 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄደው ይህ ፌስቲቫል በየዕለቱ የሚከናወኑ ሰባት ዓይነት ፕሮግራሞችን አካትቷል፡፡

ከተካተቱትም ፕሮግራሞች መካከል አንደኛው ትምህርት ቤቶች ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር መልሰው ጥቅም ላይ በሚውሉ የተለያዩ ቁሳቁሶች የሠሯቸውን መገልገያዎች የሚያሳዩበትና የሚያስተዋውቁበት ፕሮግራም ይገኝበታል፡፡

ይህም ፕሮግራም የትምህርት ቤቶችን ገጽታ ለመቀየርና ታዳጊዎች የትምህርት ቤታቸውን ግቢ በተፈጥሮ በማስዋብ፣ ስለተፈጥሮ የተሻለ ግንዛቤ ይዘው እንዲያድጉ የበኩሉን ዕገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ታዳሚዎች ችግኝ በመግዛት የሚሳተፉበትና ‹‹ኢትዮ አረንጓዴ ፌሽታ›› መነሻና መድረሻው ዳያስፖራ አደባባይ የሆነ የሰባት ኪሎ ሜትር ሩጫ፣ እንዲሁም ‹‹እኔ ለምወደው›› በሚል ስያሜ በከተማ በሚገኙ ፓርኮች ውስጥ በአንዱና በአደባባዮች ላይ በሚወዱት ሰው ስም ችግኝ የመትከል ሥራ፣ በተፈጥሮ እንክብካቤና በከተማ ግብርና ላይ ለተሰማሩ ከተለያዩ ቦታ ለሚመጡ ወጣቶች ሥልጠና መስጠት፣ የከተማ ፅዳትና ተፈጥሮን ማልማት አስመልክቶ በኢትዮጵያ የተከናወኑ ሥራዎችንና ከተለያዩ አገሮች የተወሰዱ ልምዶችን የሚያሳይ የፎቶ ዓውደ ርዕይ ማካሄድ በፌስቲቫሉ ከታቀፉት ፕሮግራሞች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ከወጣት ታደሰ ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው በኤድናሞል አደባባይ ‹‹አረንጓዴ ፋሽን ሾው›› እንዲሁም በፓርክ ውስጥ ለታዳጊዎች እያዝናኑ የሚያስተምሩ ልዩ ልዩ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች፣ ዕውቅ ድምፃውያን የሚሳተፉበት የሙዚቃ ዝግጅት ይኖራል፡፡

በግዮን ሆቴል ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ጀምሮ የሚካሄደው የሙዚቃ፣ ፕሮግራም የፌስቲቫሉ ማጠቃለያ መሆኑን ጠቁመው፣ ታዳሚዎች ‹‹አረንጓዴ ፌሽታ›› ተብሎ የተጻፈበትን ቲሸርት በመግዛት የፕሮግራሙ ተሳታፊ እንደሚሆኑ አስረድተዋል፡፡

ኪነ ምስሎች ይህንን ፌስቲቫል የሚያካሂደው በአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ሥር ከተቋቋመውና በደን ልማት ዙሪያ ላይ ከሚሠራው ‹‹ሬድ ፕላስ›› ከተባለው ተቋምና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ቢሮና ከተለያዩ የግል ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ነው፡፡  

የፌስቲቫሉ ፋይዳ በአገሪቱ እየተደረገ ያለውን የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ በመደገፍና በአንፃሩም የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ጉዳት በማስገንዘብ ኅብረተሰቡ ከመንግሥትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጎን በመቆም አካባቢውን በመንከባከብ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ የሚያደርግ ነው፡፡ ዓላማው ደግሞ የማኅበረሰቡ ተፈጥሮን ማልማትና መንከባከብ የዕለት ተዕለት ተግባሩ እንዲሆን ግንዛቤቸውን ማስፋትና አዳዲስ ልምድ ይዘው እንዲሄዱ ማድረግና ማነሳሳት መሆኑ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...