በቅጣት ውሳኔ ‹‹እጁ ከተያዘበት ቀን አንስቶ›› የሚለው በቁጥር ይገለጽ ተብሏል
እስረኛ በምርመራ ወቅት የቆየበት ጊዜ ካልተገለጸ ሬጅስትራር ፋይል አይከፈትም
የፍትሕ አካላት በጋራ ባስጠኑት የመግባቢያ ሰነድ ማለትም ቢፒአር መሠረት የሚከሰሱ ሰዎች በፖሊስ የተያዙበት ቀንና ቦታ፣ በእስር ላይ የቆዩበትና የተፈቱበት ቀናት ተጠቅሰው እንዲጻፉ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለፖሊስ ተቋማትና ለፍርድ ቤቶች ማሳሰቢያ ሰጠ፡፡
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ በላቸው አንሺሶ ተፈርሞ ለፌዴራል ፖሊስ፣ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ለሁሉም ችሎቶችና ምድብ ችሎቶች የተላለፈው የማሳሰቢያ ደብዳቤ፣ በሕገ መንግሥቱ የሰዎች መብት ማክበርና ማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ በቀዳሚነት የፍትሕ ተቋማት መሆኑ ይታወቃል ይላል፡፡
በመሆኑም የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆን፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ የተከሰሱ ወይም የተፈረደባቸው ሰዎች መብታቸው መከበር ስላበት ‹‹የታሰረው ታስቦ ይፈጸም›› የሚለው የቅጣት ውሳኔ ክፍተት የሚፈጥርና በፖሊስና በታራሚዎች መካከል አለመግባባትን እየፈጠረ የሚገኝ በመሆኑ፣ ቀኑ በቁጥር ተጽፎ እንዲቀመጥ ያሳስባል፡፡
ተከሳሹ የተያዘበት፣ በዋስ ከተፈታ የተፈታበት ቀን፣ የሚፈረድበት ከሆነም የተፈረደበት ቀን ተጠቅሶና ተሰልቶ ውሳኔ እንዲሰጥም ይገልጻል፡፡
ማሳሰቢያው ለተቋማቱ እንዲደርሳቸው በዋናነት ያስፈለገው፣ ተከሳሾችና ፍርደኞች በፖሊስ የታሰሩበት ቀን ተገልጾ እንዲጻፍላቸው ቤተሰቦቻቸው ጥያቄ ስለሚያቀርቡ ለተጨማሪ የመጻጻፍ ሥራ መብዛት፣ ለአቤቱታዎች መበራከትና ለመብት ጥሰት ምክንያት እየሆነ በመምጣቱ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዳዲስ ዓቃቢያነ ሕግ ወደ ተቋሙ በመቀላቀላቸው ክስ ሲመሠርቱ ቀናቱን ስለማይገልጹ፣ ዳኞችም ‹‹በፖሊስ ጣቢያ የታሰረው ታስቦ ይፈጸም›› ከማለት ውጪ፣ ከመቼ ጀምሮ በፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደቆዩ ስለማይገልጹ የታራሚዎቹ የመብት ጥያቄ እየተበራከተ በመምጣቱ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሬጂስትራሮችም አዳዲስ የወንጀል ጉዳይ ክስ መዝገቦች ሲከፍቱ፣ ስለተከሳሹ በፖሊስ ጣቢያ የታሰረበት ጊዜ ካልተጠቀሰ ፋይል እንዳይከፍቱም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡ ክሱ በቅድሚያ መስተካከል እንዳለበትም አክሏል፡፡ ይኼ ውሳኔም በፍትሕ አካላት ጥምር ኮሚቴ የተወሰነ መሆኑንና ወደ ጭቅጭቅ የሚወስዱ ክፍተቶችን ከወዲሁ ለማስቀረት ሊያግዝ እንደሚችል ማሳሰቢያው ይገልጻል፡፡