Sunday, January 29, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ፖለቲካው ውስጥ የበቀለው ዓረም ለአገር አይበጅም!

ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ መልካም አጋጣሚዎቹን በማበላሸት ወደር የለውም፡፡ ሌላው ቢቀር ከ1953 ዓ.ም. መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እስከ ምርጫ 97 ድረስ ኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚዎች ያመለጧት ዕድለ ቢስ አገር ናት፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እርግማን ያለ ይመስል ከውይይት ይልቅ መተናነቅ፣ ከተፎካካሪነት ይልቅ መጠላለፍ፣ ከመደማመጥ ይልቅ መጯጯህ፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ መጠፋፋት ዋናዎቹ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ሥልጣን ላይ የሚወጡትም ሆኑ ለሥልጣን የሚታገሉት በአንደበታቸው ለዴሞክራሲ ቢዘምሩም በተግባር የሚታየው ግን ተቃራኒውን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያዊያን እርስ በርስ ባደረጉት ግጭት ሞት፣ እስራት፣ ስደትና እንግልት ዕጣ ፈንታቸው ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተንሰራፍቶ የበቀለው ዓረም ጥላቻና ቂመኝነትን እያባባሰ በርካቶች መከራ ዓይተዋል፡፡ እጅግ በጣም የተከበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ያኖራቸው የጋራ እሴቶቹና አገር በቀል ዕውቀቶቹ እየተናዱ፣ በባዕዳን ርዕዮተ ዓለም የተጠመቁ ፖለቲከኞች በታሪክና በትውልድ የሚያስጠይቅ ጥፋት ፈጽመዋል፡፡ የጥፋቱን መጠንና ክብደት ደግሞ አገር ያውቀዋል፡፡ የጎራ ፖለቲካ ውስጥ ተሰንቅሮ ራስን ብፁዕ የማድረግና ሌላውን የማሰይጠን ልማድ፣ ፖለቲካው ውስጥ የበቀለው ዓረም መገለጫ ነው፡፡ ይህ ዓረም መወገድ አለበት፡፡

ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሰየሙት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ባለፉት ሁለት ወራት ይህ ዓረም ተወግዶ አገር በአዲስ መንፈስ እንድትነሳሳ ሙከራ አሳይተዋል፡፡ ቂምና ቁርሾን በማስወገድ ይቅር መባባል እንደሚያስፈልግ በአደባባይ እየሰበኩ ነው፡፡ ይህ መልካም ተነሳሽነት በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድም ተቀባይነት እያገኘ ነው፡፡ ይሁንና ከዚያ አሳዛኝ የመጠፋፋት ስሜት ውስጥ መውጣት ያቃታቸው ደግሞ፣ ቀናውን ጎዳና ለማሰናከል ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፡፡ በአንዳንድ ወገኖች በማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ የሚንፀባረቀው የነውጠኝነት ባህሪ አሁንም ገና የሚቀር ሥራ እንዳለ አመላካች ነው፡፡ ሰላማዊ ነን እያሉ ሰላም ለማደፍረስ የሚተጉ፣ በዴሞክራሲ ስም እየማሉ የሌላውን መብት የሚጋፉ፣ የሁሉም ነገር ሰጪና ከልካይ ለመሆን የሚዳዳቸውና ዘመኑ ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ጋር እኩል መራመድ የተሳናቸው እዚህም እዚያም እየታዩ ነው፡፡ አገር ከቂምና ከጥላቻ አስተሳሰብ ተላቃ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በፍትሐዊነት የሚስተናገዱበት ዓውድ እንዳይፈጠር፣ ዛሬም አክራሪ ብሔርተኝነትን ሙጥኝ ያሉ አሉ፡፡ ጥላቻ እስከ አንገታቸው ድረስ የዋጣቸው ደግሞ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያለያይ አደገኛ የዘር ልዩነት ቅስቀሳ ያካሂዳሉ፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ በዓረም የተሞላ ፖለቲካ ምክንያት ነው ዛሬም መልካም አጋጣሚዎች እንዳይመክኑ ጥረት መደረግ አለበት የሚባለው፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ የወረረውን ዓረም አስወግዶ ሥልጡን ጎዳና መያዝ የሚችለው፣ ለዓመታት ከተጣባው በሽታ መገላገል ሲችል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ሥልጣን የሚያዘው በነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ምርጫ ብቻ መሆን እንዳለበት ሲታመን ነው፡፡ ይህ ዕውን ይሆን ዘንድ ደግሞ የፖለቲካ ምኅዳሩ ወለል ብሎ ተከፍቶ፣ በነፃነት መወዳደር የሚቻልበት አስተማማኝ ሕጋዊ ማዕቀፍ መኖር አለበት፡፡ በሕግ ዋስትና ያገኙ መሠረታዊ መብቶች መከበር አለባቸው፡፡ በአገር ውስም ሆነ በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ድርጅቶች ሕጋዊ ዋስትና አግኝተው መንቀሳቀስ መቻል አለባቸው፡፡ መብትና ነፃነትን ከሚጋፉ ሕጎች የሚስተካከሉት ተስተካክለው፣ የማያስፈልጉት ደግሞ ተጥለው ኢትዮጵያዊያን በሕግ የበላይነት ሥር ነፃነታቸውን እንዲያጣጥሙ የሚያስችሉ ዕርምጃዎች መወሰድ ይኖርባቸዋል፡፡ ሕጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የማንም ጣልቃ ገብነት ሳይኖርበት በነፃነት ማካሄድ የሚቻለው በቅድሚያ ሰላም ሲሰፍን ነው፡፡ ይህ ሰላም ይሰፍን ዘንድ ደግሞ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በቅንነት መነሳት አለባቸው፡፡ ዓረም የዋጠው ፖለቲካ ለዚህ ዘመን አይመጥንም፡፡

ሌላው መሠረታዊ ችግር የኃላፊነት ስሜት መጥፋት ነው፡፡ አገርንና ሕዝብን ማዕከል ያላደረጉ ነገር ግን ሁሌም ከብሽሽቅና ከፋይዳ ቢስ ተቃርኖ መውጣት የማይፈልጉ አሉ፡፡ ለአንዳንዶቹ ይህ ድርጊት ከህልውና ጋር የተያያዘ ንግድ ስለሆነ፣ አገር ውስጥ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሲጀመር አይመቻቸውም፡፡ ሥልጣኑ ከመዳፉ ውስጥ ያፈተለከበት የሚመስለው ለአገር የማያስብ ስብስብና ዕድሜ ልኩን ተቃውሞን የእንጀራ ገመዱ ያደረገ ቡድን፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መልካም ጅምር ሲታይ ያቃዣቸዋል፡፡ ሕዝብ የሚፈልገው ምንድነው በማለት በጥልቀት ከመፈተሽ ይልቅ፣ የራስንና የቡድንን ጥቅም በማስቀደም የሚናውዙ ወገኖች ከከበባቸው ዓረም መገላገል ይኖርባቸዋል፡፡ እየተነጋገርን ያለነው ስለአገር ህልውናና ደኅንነት ስለሆነ፣ ለአገር ሲባል ደግሞ ማናቸውም ዓይነት መስዋዕትነት ተከፍሎ ከአጥፊ ድርጊት መራቅ ይገባል፡፡ ሥልጣንንና ጥቅምን ብቻ ታሳቢ ያደረገ የክፋት ፖለቲካ አገር ያጠፋል እንጂ ፋይዳ የለውም፡፡ ጊዜያቸውን የብሽሽቅ ፖለቲካ ላይ ያዋሉ ኃይሎችም ይታቀቡ፡፡ ብሽሽቅ ለቧልት እንጂ ለአገር አይፈይድም፡፡

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች ከአኩራፊነትና ከቀቢፀ ተስፋ በመላቀቅ፣ ከወቅቱ የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ራሳቸውን ሊመረምሩ ይገባል፡፡ ተወደደም ተጠላም አገሪቱ ባለፉት ዓመታት በርካታ ለውጦች ታይተውባታል፡፡ የአገሪቱ የመሠረተ ልማትና የኢኮኖሚ ይዞታ ብቻ ሳይሆን፣ የአዲሱ ትውልድ ፍላጎትም ከበፊቱ በጣም የተለየ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ ከ100 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ሲኖራት፣ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ታዳጊና ወጣት ነው፡፡ ይህ ትውልድ ባለፉት 27 ዓመታት የተገኘ ነው፡፡ በዚህ ትውልድና ያ ትውልድ በሚባለው መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ፡፡ ይኼንን ልዩነት ማዕከል ያላደረገ የፖለቲካ ትግል ችግር ያጋጥመዋል፡፡ የአሁኑ ትውልድ ጠያቂና ሞጋች ስለሆነ በከንቱ እየተደለለ መፈክር አይሸከምም፡፡ በኮርኳሪና በስሜት ቀስቃሽ አደናጋሪ ቅስቀሳዎች አይታለልም፡፡ ዕድሜ ለዘመኑ ቴክኖሎጂ የሚሻለውን ከማይሻለው የመለየት ክህሎቱ እያደገ ነው፡፡ ስለዚህ ያንን ያረጀና ያፈጀ በጥቀርሻ የተሞላ የዓረም ፖለቲካ መገላገል ያስፈልጋል፡፡ ዘመኑን አይመጥንምና፡፡

ፍጥነት ቁጥጥር ካልተደረገበት ለአደጋ እንደሚዳርግ ሁሉ፣ በስሜታዊነትና በግብታዊነት የሚመራ ፖለቲካም ኪሳራው የበዛ ነው፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃ የተጠና፣ ወቅቱን ያገናዘበ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን የጋራ ፍላጎት ያማከለና የጋራ መግባባት የሚፈጥር መሆን አለበት፡፡ እንደ ትናንትና ዜጎች ወገብ ላይ ቆሞ ረግጦ መግዛት እንደማይቻለው፣ በሐሰተኛና በጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ተመርዞ ፖለቲካው ውስጥ መደበቅም አይታሰብም፡፡ በተለይ ለሰጥቶ መቀበል መርህ የማይገዙና በቅድመ ሁኔታዎች ካልሆነ በስተቀር ለመነጋገር አሻፈረኝ የሚሉ ግትሮች፣ ለአዲሱ ትውልድ ሥፍራውን በመልቀቅ ለአገር ውለታ ቢፈጽሙ ይሻላቸዋል፡፡ አገር ውስጥም ሆነ አሜሪካ፣ እንዲሁም አውሮፓ ተቀምጦ በዛገ አስተሳሰብ ሰላምን ማደፍረስ ጊዜው አልፎበታል፡፡ ይልቁንም አገራቸውን የሚጠቅሙ ብሩህ አስተሳሰብ ያላቸው ሀቀኛ ወገኖች ዋስትና አግኝተው ከስደት ተመልሰው እንዲመጡ፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ ያሉት ደግሞ መብታቸው ተከብሮ በነፃነት እንዲሠሩ ሕጋዊ ማዕቀፉን ማመቻቸት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲና ብልፅግና ማሸጋገር የሚቻለው በልጆቿ አንድነት ስለሆነ፣ ለዚህ በጎ ዓላማ መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ፀጉር እየሰነጠቁ የአገሪቱን መልካም ዕድል ማበላሸት ይብቃ፡፡ በዓረም የተሞላው ፖለቲካ ለአገር ፋይዳ የለውም! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ከውጭ ይገቡ የነበሩ 38 ዓይነት ምርቶች እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 38 ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ዕገዳ...

የአየር መንገድ ተጓዦች በሻንጣ የሚያስገቡትን የልብስና የጫማ ብዛት የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎች 87 በመቶ እንዲቀንሱ ተደርጓል መንገደኞች...

አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...

ለልማት ፕሮጀክቶች የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተፈቀደ

የገንዘብ ሚኒስቴር በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በሎጀስቲክስ፣ በኮንስትራክሽን፣ የባለኮከብ ሆቴሎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...

ፖለቲካና ሃይማኖትን እየቀላቀሉ በእሳት መጫወት አይቻልም!

ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚሹ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሃይማኖት ነው፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ ለተቋማቱና ለምዕመናኑ ብቻ የተተወ ነው፡፡ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥትም መንግሥትና ሃይማኖት...

አገር የጥፋት ቤተ ሙከራ አትሁን!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የሚለዋወጡ ስትራቴጂዎች እንደሚኖሩት ዕውን ቢሆንም፣ በየጊዜው መዋቅሮችንና ፖሊሲዎችን መለዋወጥ ግን አይችልም፡፡ ‹‹ሁሉን መርምሩ የተሻለውን ያዙ›› የሚለው መጽሐፍ...