Tuesday, December 6, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየፓርላማ አባላት በአገሪቱ የውጭ ዕዳ ክምችት ሥጋታቸውን ገለጹ

  የፓርላማ አባላት በአገሪቱ የውጭ ዕዳ ክምችት ሥጋታቸውን ገለጹ

  ቀን:

  የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ላይ የብድር ፖሊሲውን ቀየረ

  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በአገሪቱ የውጭ ዕዳ ክምችት ላይ ያላቸውን ሥጋት ገለጹ፡፡ የፓርላማ አባላቱ ሥጋታቸውን ጠንከር ብለው የገለጹት፣ ሐሙስ ግንቦት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ለምክር ቤቱ የቀረበውን የብድር አዋጅን ለማፅደቅ በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡

  ለምክር ቤቱ የቀረበው ለሁለት ፕሮጀክቶች መንግሥት ከዓለም ባንክ ጋር ያደረገው ስምምነት ቢሆንም የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ መንግሥት የፈቀደው ብድር በገበያ ዋጋ የሚተመን ወለድ የተጣለበት መሆኑ፣ የምክር ቤቱ አባላት ሥጋታቸውን እንዲያነሱ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡

  የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የኤሌክትሪፊኬሽን (የኤሌክትሪክ ኃይል ለሁሉም) ፕሮጀክትና ለመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች የፈቀደው 702 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 325 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው በገበያ ዋጋ በሚተመን የወለድ ምጣኔ በ30 ዓመት ውስጥ ተከፍሎ የሚያልቅ ነው፡፡

  የዓለም ባንክ ይህንን ከፍተኛ ወለድ ያለው የብድር ፖሊሲ በኢትዮጵያ ላይ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው በቅርብ ጊዜ ሲሆን፣ ምክንያቱ ደግሞ የአገሪቱ የውጭ ዕዳ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ነው፡፡

  የዓለም ባንክ ከሁለት ወራት በፊት ባፀደቀው የብድር ስትራቴጂ መሠረት፣ ኢትዮጵያ በገበያ የወለድ ምጣኔ መበደር የምትችለውን የገንዘብ መጠን ጣሪያ አስቀምጧል፡፡ ለዚህም ከፍተኛ የወለድ ምጣኔ የሚጣልበትን (Non-concessional Loan) መጠን ከ400 ሚሊዮን ዶላር እንዳይበልጥ ወስኗል፡፡

  ‹‹የአገሪቱ ኢኮኖሚ በብድር ላይ የተንጠለጠለ እየሆነ ነው፡፡ ብድሩን ማግኘታችንን ብቻ ሳይሆን እንዴት ነው የምንከፍለው የሚለውን ማየት አለብን፤›› ሲሉ አንድ የምክር ቤት አባል ጠይቀዋል፡፡ ሌላ አንድ አባል በበኩላቸው፣ ወለዱ በገበያ የወለድ ምጣኔ መሠረት አዋጭ ስለመሆኑ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡

  የምክር ቤቱ የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ዕዳ ወደማይከፍሉ አገሮች ተርታ እየተጠጋች መሆኑንና አንዳንድ በብድር የሚሠሩ ፕሮጀክቶች ፈቀቅ ሳይሉ ወለድ መከፈል መጀመሩን ገልጸው፣ በብድር የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ውጤታማነት ላይ ክትትል እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡

  በተመሳሳይ አስተያየታቸውን የሰጡት ሌላው የምክር ቤቱ አባል መስፍን ቸርነት (አምባሳደር) አገሪቱ ከፍተኛ ዕዳ ያለባቸው አገሮች ተርታ መግባቷን ገልጸው፣ ‹‹እንዴት ነው እዚህ ደረጃ የደረስነው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

  ‹‹በሚገኙ ብድሮች ላይ ከሚመለከተው አካል ጋር በትክክል መነጋገር አለብን፡፡ ምክንያቱም ለትውልድ ዕዳ እያስረከብን ነው፤›› ብለዋል፡፡ የበጀትና የፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በምክር ቤቱ አባላት የተነሱትን ሐሳቦች እንደሚጋራ አስታውቋል፡፡

  የብድሮችን ውጤታማነት መከታተል እንደጀመሩ የተናገሩት የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ነጋልኝ ዮሴፍ፣ በቅርቡ ቋሚ ኮሚቴው በ37 ፕሮጀክቶች ላይ ክትትል ማድረጉንና ከእነዚህ ውስጥ ብድሩ ተገኝቶ ያልተጀመሩ፣ ተጀምረው በደካማ አፈጻጸም ላይ የሚገኙ መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡

  ምክር ቤቱ በተነሳው አንገብጋቢ ጉዳይ ላይ ተስማምቶ የቀረበው ብድር ግን አስፈላጊ በመሆኑ እንዲፀድቅ ወስኗል፡፡ የመጀመሪያው የኤሌክትሪፊኬሽን ብድር አዋጅ በአንድ ተቃውሞ ሲፀድቅ፣ ሁለተኛው የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ብድር ደግሞ በአንድ ተቃውሞና በአሥር ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...