ከአራት ዓመታት በላይ ዕግድ ተጥሎበትና ሕጉ ጭምር ተቀይሮ መሥፈርቱን ለሚያሟሉ ለውጭ አገር ሥራና አሠሪ አገናኝ ኤጀንሲዎች ሕጋዊ ፈቃድ መስጠት ሲገባቸው፣ መሥፈርቱን ላላሟሉ ኤጀንሲዎች ፈቃድ እንዲያገኙ ባደረጉት ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ እንደሚወስዱ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሯ ሒሩት ወልደ ማርያም (ዶ/ር) ግንቦት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. በሥራቸው ካሉ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ዳይሬክተሮችና ሌሎች የተለያዩ የክፍል ኃላፊ ሠራተኞች ጋር በመሆን፣ የውጭ አገር ሥራና አሠሪ አገናኝ ኤጀንሲዎች ባለቤቶችና ወኪሎችን ማነጋገራቸው ታውቋል፡፡ ሦስት ጊዜና ከዚያ በላይ ዕገዳ የተጣለባቸው ኤጀንሲዎች መሰረዝ ሲገባቸው ፈቃድ መሰጠቱን፣ በሕጉ መሠረት የተቀመጠውን መሥፈርት ሳያሟሉ እንዳሟሉ ተደርጎ ፈቃድ የተሰጣቸው ኤጀንሲዎች መኖራቸውን ሲገለጽላቸው፣ የሚመለከታቸው የፈቃድ ክፍል ሠራተኞች መጠየቃቸውንና ምላሽ መስጠታቸውን ጠቁመው፣ ተጣርቶም ዕርምጃ ይወሰድባቸዋል ማለታቸውን፣ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ ኃላፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትሯ ዘርፉን ከማንኛውም ስህተት በመጠበቅ በዜጎች ላይ የሚደርስ ጉዳትና እንግልትን በሚያስቀር መንገድ እንዲቀጥል እንደሚያደርጉና ተነሳሽነቱም እንዳላቸው ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ ሚኒስቴሩ አሠራሩን በማሻሻል ኢትዮጵያውያን ተፈልገውና ዋጋ አማርጠው የሚሠሩበት ሁኔታ ለመፍጠር ሥራውን በደንብ ከሚያውቁት፣ ሕግን ከሚያከብሩና ከማናቸውም የሚኒስቴሩ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር በጥቅም ያልተሳሰረ አገልግሎት መስጠት ከሚችሉ ኤጀንሲ ባለቤቶች ጋር መመካከርና ችግሮችን ነቅሶ ለማውጣት መወያየት አስፈላጊ መሆኑን እንደተናገሩ ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም በዕለቱ ከተገኙ የኤጀንሲዎች ባለቤቶችና ተወካዮች ጋር ሲወያዩ፣ በፈቃድ አሰጣጥ ላይ ጠንከር ያለ ጥያቄ መቅረቡን ኃላፊዎቹ አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ላልሆኑ ዜጎች ፈቃድ መስጠት፣ ሥራው ሳይጀመርና በተለይ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር ያለው የሁለትዮሽ ስምምነት ተፈርሞ ሳይፀድቅ ፈቃድ የተሰጣቸው ኤጀንሲዎች ለምልመላ ማስታወቂያ መሥራታቸው ስህተት መሆኑን እንዳስረዱ ተገልጿል፡፡ የቁጥጥር ክፍሉ ዕርምጃ ባለመውሰዱ በዜጎች ላይ አሁንም ችግር እየደረሰ መሆኑን፣ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር ስምምነት ሳይደረግ ፈቃድ መሰጠቱ በግለሰቦች ፍላጎትና ከጥቅም ጋር የተሳሰረ እንደሆነ እንደተገለጸ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ ድርጊቱ ሕገወጥነት ያጋለጠና ለዜጎች መጎሳቆል፣ ሞትና አስከፊ ስቃይ ያደረገው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑንም አክለዋል፡፡
ኤጀንሲዎቹ ቀደም ብለው ሲሠሩ ሦስትና ከዚያ በላይ ዕገዳ ከተጣለባቸው መሰረዝ እንዳለባቸው ሕጉ ስለሚደነግግ እንዲጣራ የኮሚቴ አባላት የተመደቡ ቢሆንም፣ ገለልተኛና ባለመሆናቸው ቀደም ባለው ጊዜና ሕግ ዕግድ ሲጥሉ የነበሩ ኃላፊዎች የአጣሪ ኮሚቴ አባል ሆነው በመመረጣቸው፣ ሦስትና ከዚያ በላይ ዕግድ የነበረባቸውን ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረጋቸውንም ለሚኒስትሯ እንደተነገራቸው ኃላፊዎቹ አስረድተዋል፡፡
ኤጀንሲዎቹ አሠራሩን በደንብ የሚረዱና የሚያውቁ ግለሰቦች መርጠው እየሠሩ ባሉበት ሁኔታ፣ አዲስ ማኅበር እንዲቋቋም መደረጉ ስህተት መሆኑን የኤጀንሲዎቹ ተወካዮች ማስረዳታቸውንም ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡
አዲሱ ማኅበር ቢሮ ሳይኖረውና ማሟላት የሚገባውን በርካታ መሥፈርቶች ሳያሟላ እንዲቋቋም የተደረገው ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ጋር የጥቅም ትስስር በመፍጠርና ነባሩ ማኅበር እንዲዳከም ለማድረግ መሆኑን ማከላቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ሌላው የኤጀንሲ ባለቤቶች ተወካዮች ያነሱት ጥያቄ፣ በአዲሱ ሕግ ፈቃድ የሚያወጣ ኤጀንሲ ወደፈለገው አገር ሠራተኞች ቢልክ 100 ሺሕ ዶላር ተቀማጭ እንዲያደርግ ደንግጎ እያለ፣ ‹‹ለሁለት አገሮች ብቻ ነው›› መባሉ ሕግን ያልተከተለና መደረግም ካለበት ሕጉ መሻሻል ያለበት መሆኑን መግለጻቸውን አስረድተዋል፡፡ ሚኒስትሯም በቀጣይ እንደሚታይ ምላሽ መስጠታቸውን ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡
ከሚኒስትሯ ሒሩት (ዶ/ር) እና ሌሎች የሚኒስቴሩ ባለሥልጣናትና ኃላፊዎች ጋር ውይይት ያደረጉትን የኤጀንሲዎች ባለቤቶችና ተወካዮችን አስተያየት ለማካተት ሪፖርተር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡