Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናቻይናዊው የኦሞ ኩራዝ አምስት ስኳር ፕሮጀክት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሳቸው በገለልተኛ አካል እንዲታይ...

ቻይናዊው የኦሞ ኩራዝ አምስት ስኳር ፕሮጀክት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሳቸው በገለልተኛ አካል እንዲታይ ጥያቄ አቀረቡ  

ቀን:

የኩባንያው ተወካዮች ፕሮጀክቱ አደጋ እንደተጋረጠበት አስታውቀዋል

በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው እ.ኤ.አ. ጁላይ 25 ቀን 2017 በቁጥጥር ሥር የዋሉትና ክስ ተመሥርቶባቸው በእስር ላይ የሚገኙት የኦሞ ኩራዝ አምስት ስኳር ፕሮጀክት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚኒተር ዩዋን ጂያሊን፣ የተመሠረተባቸው ክስ በገለልተኛ አካል እንዲታይላቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በደብዳቤ ጥያቄ አቀረቡ፡፡

መቀመጫው ቻይና የሆነው ጂያንጊዚ ጃንግሊያን ዓለም አቀፍ ኢንጂነሪንግ ካምፓኒ ሊትድ (ጄጄአይኢሲ) የኢትዮጵያ ተወካይ ሚስተር ዩዋን ጂያሊን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ እንዳብራሩት፣ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው እ.ኤ.አ. ጁላይ 25 ቀን 2017 በፌዴራል ፖሊስ ተይዘው ታስረዋል፡፡ በመቀጠልም የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶባቸውና ዋስትና ተከልክለው ላለፉት አሥር ወራት በእስር ላይ በቂሊንጦ ማቆያ ቤት እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያና ቻይና ባላቸው የቢዝነስና የልማት የሁለትዮሽ ስምምነት፣ ጄጄአይኢሲ የኦሞ ኩራዝ አምስት ስኳር ፕሮጀክት ለማከናወን እ.ኤ.አ. ሜይ 30 ቀን 2016 ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ ኮንትራት መፈራረሙን ጠቁመዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የሚፈጀው ካፒታልም 550 ሚሊዮን ዶላር መሆኑንና ይኼም ከቻይና ባንክ አይሲቢሲ የተገኘ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ጄጄአይኢሲ ደረጃውን የጠበቀና ተወዳዳሪነት ያለው የግዥ ሥርዓት ተከትሎ ምንም ዓይነት የሙስና ድርጊት ሳይኖር ግዥዎችን ሲፈጽም መቆየቱን ዳይሬክተሩ ጠቁመው፣ ነገር ግን በተደረገ ምርመራ ምንም ዓይነት ሙስና መፈጸሙ ሳይረጋገጥ መታሰራቸውን አስረድተዋል፡፡

የድርጅቱ ኃላፊዎች በበኩላቸው ምናልባት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ የፈጸሙት የሙስና ተግባር ካለ ብለው ለማረጋገጥ የሕግ ባለሙያ ቀጥረው ጉዳዩን (ክሱን) እየተከታተሉ መሆኑንም፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ አስታውቀዋል፡፡ የኦሞ ኩራዝ አምስት ማኔጂንግ ዳይሬክተር በፌዴራል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውለው ይደረግባቸው የነበረ ምርመራና ብርበራ አግባብነት በጎደለው ሁኔታ እንደነበረ፣ በዚህም ምክንያት የአካልና የአዕምሮ ጉዳት ሊደርስባቸው እንደቻለም ገልጸዋል፡፡

በወቅቱ በሕግ አማካሪያቸው፣ በሥራ ባልደረቦቻቸውና በቤተሰቦቻቸው እንዳይጠየቁ ተደርገው እንደነበርና ይኼንንም የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ላይ ቢያቀርቡም ተገቢ የሆነ ምላሽ አለማግኘታቸውንም አስረድተዋል፡፡ የቀረበባቸው የሰነድ ማስረጃም በሐሰት የተዘጋጀ መሆኑን አክለዋል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግም ሁሉንም ሰነድ በመቀበል ክስ እንደመሠረተባቸው፣ በፍርድ ቤት ተቀባይነት ያጡትን ማስረጃዎች  እንደገና እንደ አዲስ ለማዘጋጀት ረዥም ቀጠሮ በመጠየቅ እየተፈቀደለት በመሆኑ፣ የተፋጠነ ፍትሕ ማጣታቸውን አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ እንዲያውቁላቸው የፈለጉት፣ የኦሞ ኩራዝ አምስት ስኳር ፕሮጀክት በጄጄአይኢሲ ተወካዮች እ.ኤ.አ. ሜይ 23 ቀን 2018 ባደረጉት ጉብኝት፣ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም አደጋ ውስጥ መሆኑንና የመንግሥትን ተጠቃሚነት የሚያሳጣና የነበራቸውን የሁለትዮሽ ስምምነት የሚያስቀር መሆኑን ተገንዝበው፣ የተፋጠነ ፍትሕ እንዲያገኙ እንዲያደርጉላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሰየሙበት ቀን ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር በፍትሕ ዘርፉ ያለውን ችግር እንዲስተካከል እንደሚሠሩ በገለጹት መሠረት፣ የእሳቸው ክስ በገለልተኛ አካል ተመርምሮ አፋጣኝ ፍትሕ እንዲሰጣቸው እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...