የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በመጪው ዓመት ኅዳር ወር በጋና በሚካሄደው 11ኛው የአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ ለማለፍ፣ የመጨረሻውን ማጣሪያ ግንቦት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. በአልጄሪያ ያካሂዳል፡፡ ‹‹ሉሲ›› በሚል ቅፅል ስም የሚታወቀው ብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያውን ማጣሪያ ከሊቢያ አቻው ጋር ባደረገው ግጥሚያ በደርሶ መልስ 15 ለ 0 ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል። በአሠልጣኝ ሰላም ዘርዓይ የሚሠለጥኑት ሉሲዎቹ የመልሱን ጨዋታ ሰኔ 3 ቀን በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚያደርጉ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ገልጿል፡፡ ሉሲዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ ተደጋጋሚ ተሳትፏቸው ትልቁ ውጤታቸው ግማሽ ፍታሜ ደርሰው አራተኛ የወጡበት ነው፡፡ የጋናው የአፍሪካ ዋንጫ ከኅዳር 8 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ሳምንት እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡