Saturday, September 30, 2023

የዓለም ሩጫ ቀን በ24 የዓለም ከተሞች በተመሳሳይ ጊዜ በሩጫ ይከበራል

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የአዲስ አበባውን ሩጫ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በአምበልነት ይመራዋል

ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) ሰሞኑን ይፋ እንዳደረገው፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ 24 ከተሞችን የሚያስተሳስር የአንድ ማይል (1.6 ኪሎ ሜትር) ውድድር ረቡዕ ግንቦት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. (ጁን 6 ቀን 2018) በ10 ሰዓት ያደርጋል፡፡

በዓለም ዙሪያ የስፖርት ሚኒስቴሮች፣ የከተማ አስተዳደሮች፣ የውድድር አዘጋጆችና አባል ፌዴሬሽኖች አጋር የሚሆኑበት ውድድር ተመሳሳይ የጊዜ ቀመር በሚኖራቸው ሁለት ደርዘን ከተሞች በአንድ ጊዜ ውድድር የሚጀምሩት ለሩጫ ክብር ለመስጠት ነው፡፡

አይኤኤኤፍ በድረ ገጹ እንዳስታወቀው፣ ‹‹ሩጫ 24 በ1›› የተሰኘው ውድድር በኦክላንድ (ኒውዚላንድ) ኦሽያናን አቋርጦ በሲዲኒ፣ ከዚያም ወደ እስያዋ ቶኪዮ፣ አውሮፓም ተሻግሮ ሚኒስክ፣ አፍሪካዊቷ አዲስ አበባ በ10 ሰዓት፣ አትላንቲክን ተሻግሮ የአሜሪካዋ ሳዎ ፖሎና ቦነስ አይረስ፣ ከዚያም የመጨረሻው ሩጫ በምዕራብ ዳርቻ በምትገኘው ቫንኮቨር (ካናዳ) ይከናወናል፡፡ በየከተሞቹ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሯጮች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

‹‹ሩጫ ለሁሉም ተደራሽ መሆን አለበት፣ የሚዝናኑበት የሚወዳደሩበትም ነው፤›› ያሉት የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ፕሬዚዳንት ሰባስቲያን ኮ ‹‹ማኅበራዊም፣ የአንድነት መገለጫም ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡ 

በረቡዕ የዓለም ሩጫ ቀን በርካቶች በመሮጥ እንደሚያከብሩት እምነቱ እንደሆነ የገለጸው ዓለም አቀፉ ተቋም፣ በ24ቱም ከተሞች በተቀራራቢ ጊዜ የሚካሄደውን ውድድር በድረ ገጹና በማኅበራዊ ሚዲያ የቀጥታ ሥርጭት ይኖረዋል ብሏል፡፡

 በየከተሞቹ የሚካሄዱትን ውድድሮች የሚመሩት በከተማ አምበሎች (ካፒቴን) እንደሚሆን፣ እነሱም የቀድሞ ወይም የአሁን አትሌቶች ሊሆኑ እንደሚገባ የገለጸው መግለጫው የእነሱ መሮጥ አትሌቲክሳዊ ግንዛቤን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ያጎላዋል ብሏል፡፡

ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአዲስ አበባ በ10 ሰዓት መነሻና መድረሻውን በመገናኛ በማድረግ የሚከናወነውና ለሁሉም ክፍት የሆነውን ሩጫ ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በአምበልነት ይመራዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -