Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሃና ማርያም ተፈናቃዮች ከንቲባውን ማግኘት አልቻሉም

የሃና ማርያም ተፈናቃዮች ከንቲባውን ማግኘት አልቻሉም

ቀን:

በሕገወጥ መንገድ መሬት ወረው መኖርያ ቤት ገንብተዋል በሚል ምክንያት ከሚኖሩበት ቀዬ በኃይል የተፈናቀሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የሃና ማርያም ነዋሪዎች፣ ሰኞ ግንቦት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ከንቲባ ድሪባ ኩማ እንደሚያናግሯቸው ተገልጾላቸው ማዘጋጃ ቤቱን ቢያጥለቀልቁም ከንቲባው ሳያነጋግሯቸው ቀሩ፡፡

ተፈናቃዮች  ላቀረቡት ተደጋጋሚ ቅሬታ ምላሽ ባለማግኘታቸው ባለፈው ረቡዕና ሐሙስ ከንቲባውን ለማግኘት ተሰብስበው ማዘጋጃ ቤት ደርሰው ነበር፡፡ ነገር ግን ከንቲባውን ማግኘት ባለመቻላቸው እንደተሰበሰቡ ወደ አሜሪካ ኤምባሲ ሄደው ነበር፡፡

ነገር ግን በወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትን እንዲያነጋግሩ የመፍትሔ ሐሳብ ቀርቦላቸው፣ አራት ኪሎ ወደሚገኘው ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተጉዘዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የቅሬታ አቅራቢዎቹን አቤቱታ እንዲያቀርቡ ሰባት ሰዎች ተወክለው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር ወ/ሮ ደሚቱ ሐምቢሳን አነጋግረዋል፡፡ ወ/ሮ ደሚቱ ከተወካዮች ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ሰኞ ግንቦት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ከንቲባ ድሪባ ሁሉንም ተፈናቃዮች እንደሚያነጋግሩ በመግለጽ መልሰዋቸዋል፡፡

ከንቲባ ድሪባ እንደሚያነጋግሯቸው ተስፋ አድርገው ሰኞ ማለዳ ተፈናቃዮቹ ማዘጋጃ ቤት ቢደርሱም ከንቲባው እንደማያነጋግሯቸው፣ ይልቁኑም ሦስት ተወካዮች ውስጥ ገብተው የተፈናቃዮቹን ቅሬታ ማቅረብ እንደሚችሉ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ የከንቲባው አለመገኘት ተፈናቃዮቹን ያስቆጣ ቢሆንም፣ መጨረሻውን ለማወቅ በመጓጓት የውይይቱን ውጤት እዚያው ሆነው ሲጠብቁ ተስተውሏል፡፡

የተፈናቃዮቹን ሦስት ተወካዮች የከተማው አስተዳደር ሦስት ባለሥልጣናት አነጋግረዋል፡፡ ባለሥልጣናቱ የከንቲባ ጽሕፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አዳሙ አያና፣ አቶ ሀርጋሞ ሀማሞና የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ግዛው ናቸው፡፡

በተለይ በሐምሌ 2008 ዓ.ም. በቦሌ ወረገኑና አሁን አይለው የመጡት የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 እና ወረዳ 11 ነዋሪዎች ሲፈናቀሉ፣ አቶ አዳሙና አቶ ሀርጋሞ ባሉበት ሥልጣን ላይ አልነበሩም፡፡

ነገር ግን በውይይቱ የተሳተፉት የወረዳ አንድ ተፈናቃዮች ወኪል ወ/ሮ ኢትዮጵያ ገበየሁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከንቲባውን ለማግኘት ብዙ ቢለፉም ልፋታቸው ከንቱ ሆኖ ቀርቷል፡፡

‹‹ሰኞ ከንቲባው እንደሚገኙ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተገልጾላቸው ጉዳት የደረሰባቸው ነዋሪዎች በሙሉ ነቅለው ቢመጡም፣ ከንቲባው በድጋሚ አለመገኘታቸው አስገርሞኛል፤›› በማለት ወ/ሮ ኢትዮጵያ ሁኔታውን ገልጸዋል፡፡

ወ/ሮ ኢትዮጵያ ከሦስቱ ባለሥልጣናት ጋር የተደረገው ውይይት ተስፋ ሰጪ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ባለሥልጣናቱ ኮሚቴ አቋቁመው ታች ወርደው ያለውን ሁኔታ እንደሚያዩ ገልጸውልን ውይይቱ በመግባባት ተጠናቋል፤›› ብለዋል፡፡

ተፈናቃዮች በዋናነት የሚያነሱት ቅሬታ የተፈናቀሉት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ እንደሆነ ነው፡፡ ሕጉን ተከትለው ቤት ሠርተው፣ ኤሌክትሪክና ውኃ አስገብተው ኮብልስቶን መንገድ በማሠራት ላይ እንዳሉ፣ በኃይልና ደም አፋሳሽ በሆነ ግጭት መፈናቀላቸውንና ድርጊቱ አግባብ አይደለም ይላሉ፡፡

ከኖሩበት ቀዬ በመፈናቀላቸውም ለከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር መዳረጋቸውን የወረዳ 11 የተፈናቃዮች ወኪል የሆኑት አቶ ከተማ ኢጄራ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሐምሌ 2008 ዓ.ም. በተለይ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ወረገኑ አካባቢ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድና ወረዳ 11 የሚገኙ የተለያዩ መንደሮች በሕገወጥ መንገድ መሬት ወረው ቤት ገንብተዋል ያላቸውን ይዞታቸውን በኃይል በማፍረስ ቦታውን ማስለቀቁ ይታወሳል፡፡

ከዚያ በኋላ መሄጃ ያጡት ነዋሪዎች ላስቲክና ሸራ እየወጠሩ ኑሮአቸውን ለመግፋት ቢሞክሩም፣ ፖሊስና ደንብ ማስከበር እንደሚያፈርሱባቸው ገልጸዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ መንግሥት ችግራቸውን ተረድቶ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይም የወረገኑ ተፈናቃዮች አስተዳደራዊ መፍትሔ እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም እስካሁን ምላሽ አላገኙም፡፡ በሰኞው ስብሰባ የወረገኑ ተወካይ በውይይቱ ላይ መገኘታቸው ታውቋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስተያየት እንዲሰጥ የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...