Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበፌዴሬሽኑ ያላለቀው ምርጫ

በፌዴሬሽኑ ያላለቀው ምርጫ

ቀን:

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ላለፉት ዘጠኝ ወራት በአመራር ምርጫ ውዝግብ ሲናጥ ቆይቷል፡፡ ብዙ ውጣ ውረዶችን ያለፈው ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንታዊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ግንቦት 26 ቀን 2010 ዓ.ም. በአፋር ስመራ  በተደረገው ምርጫ ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡ ከኦሮሚያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቀረቡት አቶ ኢሳያስ ጅራ ለቀጣዩ አራት ዓመታት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሆነው ሲመረጡ፤ ከኦሮሚያ ውጪ የቀሩት ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የቀረቡ አሥር አባላት ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት ተመርጠዋል፡፡

በእሑድ ግንቦት 26 ቀን የፌዴሬሽኑ አመራር ምርጫ ከሒደቱ ጎን ለጎን በተለይም የእግር ኳሱ ትልቅ የሥልጣን አካል ተብሎ የሚወሰደው የጠቅላላ ጉባዔ አባላት፤ ተቋሙ የሚመራባቸው ደንቦችና መመርያዎችን በቅጡና በወጉ ተረድቶ ለእግር ኳሱ የሚበጀውንና የሚጠቅመውን ሐሳብ ሙያዊ በሆነ አግባብ መግለጽ ሲገባ፤ በምርጫው ወቅት የታየው ግን እጅጉን የሚያስተዛዝብና በፌዴሬሽኑ ገና ያላለቀ ምርጫ መኖሩን ያመላከቱ ጉዳዮች ታይተዋል፡፡    

ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ሲተገበር የቆየውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብ በአስመራጭ ኮሚቴውም ሆነ በጉባዔተኛው አለመታወቁ ወይም በምርጫ ወቅት ስለሚተገበሩ ሕጎችና አንቀጾች የነበረው ግንዛቤ የወረደ ብቻ ሳይሆን፣ እግር ኳሱን የሚመሩትና የሚያስተዳድሩት እነማን ናቸው የሚለው የታየበት አሳፋሪ የምርጫ መድረክ መሆኑ በአደባባይ ታይቷል፡፡ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) እና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የምርጫ ታዛቢዎች ከምርጫ ጋር ተያይዞ ውዝግቦች ሲፈጠሩ ይኼው ጉባዔ አምኖበት ያፀደቀውንና የሚሠራበትን መተዳደሪያ ደንብ በመጥቀስ ጉባዔው ትክክለኛውን አቅጣጫ እንዲከተል በተደጋጋሚ ሲዘክሩና ሲመክሩ ታይተዋል፡፡

በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ የተካተቱ ነገር ግን ዕውቅናና ተመልካች ሳያገኙ ካናቆሩ የምርጫ ሒደቱንም ካጓተቱ አሠራሮች አንዱ ለፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩ ዕጩዎች አሸናፊ ለመባል የመራጩን ጉባዔተኛ (50+1) ድምፅ ማግኘት እንደሚገባቸው በመተዳደሪያ ደንቡ ተቀምጦ ሳለ የውዝግብ መነሻ ሆኖ ታይቷል፡፡ ጉባዔተኛውም ራሱ ካስቀመጠው ደንብና መመርያ ይልቅ በጎጥና በወንዝ ተከፋፍሎ ታይቷል፡፡

ጉባዔውም ሆነ አስመራጨ ኮሚቴው ትዝብት ውስጥ የወደቁበት የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮችን የመምረጥ ሒደት ያሳዩዋቸው ክፍተቶች እንዲሁ በቀላሉ የሚታዩ አልነበሩም፡፡ የፊፋ ተወካይ በምርጫው ሥነ ሥርዓት ወቅት ባይኖሩ ኖሮ ሊከሰት የሚችለው አለመግባባት የለየለት ጡዘት ውስጥ መግባቱ አይቀሬ ነበር፡፡ ነገስ እንዴት መጓዝ ይቻላል? የሚል ሥጋት ከወዲሁ ማስነሳቱም አልቀረም፡፡

በአፋር ሰመራ የታደመው የሪፖርተር ዝግጅት ክፍል ምርጫውንና የመራጩን አጠቃላይ ሁኔታና አረዳድ ምን እንደሚመስል ለመታዘብ እንደሞከረው ከሆነ ለወራት ሲያወዛግብ የቆየው ምርጫ በሰመራው ጠቅላላ ጉባዔ ፍጻሜውን ቢያገኝም አሁንም ያላለቀ ምርጫ መኖሩን ነው፡፡

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 27 ንዑስ አንቀፅ ስድስት፣ እንዲሁም አንቀፅ 31 ንዑስ አንቀፅ ሰባት፤ አንድ ተመራጭ አሸነፈ ተብሎ በይፋ የሚነገርበት አግባብ፤ በምርጫ ወቅት ማለትም ክልሎችና የየከተማ አስተዳደሩ የሚሰጣቸው ውክልና ወይስ ድጋፍ፤ ለፕሬዚዳንታዊና ለሥራ አስፈጻሚ ምርጫ የሚቀርቡ ዕጩ ተወዳዳሪዎች የሚታዩበት የሕግ አግባብ ለምሳሌ በሰመራው ጉባዔ ኦሮሚያ ለፕሬዚዳንት ያቀረባቸው ዕጩ አሸናፊ መሆናቸው ከተረጋገጠ በኋላ፤ ክልሉ ለሥራ አስፈጻሚ ዕጩ ማቅረብ እንደማይችል አስመራጭ ኮሚቴው በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀፅ 31 ንዑስ ንቀፅ ሰባት መሠረት ሲከለክል፣ አሁንም በመተዳደሪያ ደንቡ ለፕሬዚዳንትነት ዕጩ ያቀረቡ ክልሎች ለሥራ አስፈጻሚነት ማቅረብ አይችሉም ብሎ የሚከለክለውን አንቀፅ በዝርዝር አይጠቅስም፡፡

አስመራጭ ኮሚቴውም ቢሆን መተዳደሪያ ደንቡ በዚህ በዚህ አግባብ ብሎ መተዳደሪያ ደንቡን ከመጀመርያ እስከ መጨረሻ ያለውን አንቀፅ በአንቀፅ ተረድቶ ኃላፊነቱን በሚመጥን መልኩ ሊያብራራው አልሞከረም፡፡ በዚህ ጉዳይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች ‹‹በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ ፕሬዚዳንትና ሥራ አስፈጽሚ በተቋሙ ያላቸው ኃላፊነት የተለያየ ነው፡፡ ለፕሬዚዳንትነት ዕጩ ያቀረበ ክልል ለሥራ አስፈጻሚነት እንዳያቀርብ በግልጽ ክልከላ የሚያደርግበት ገደብ የለውም፡፡ ምናልባትም በዚህ አግባብ የኦሮሚያ ክልል ተበዳይ መሆኑን ያሳያል፤›› በማለት መተዳደሪያ ደንቡ ምን ያህል እርስ በርሱ እንደሚጣረስ ያስረዳሉ፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን በኃላፊነት የተረከበው አዲሱ አመራር በቀጣይ ሊመለከታቸው ይገባል ብለው ከሚያምኑባቸው ጉዳዮች መካከል የተቋሙን መተዳደሪያ ደንብ እንደገና መከለስና ትክክለኛውን መልክ እንዲይዝ ማድረግ ምርጫና መሰል አከራካሪ ጉዳዮች ሲፈጠሩ ብቻ በደንብና መመርያ ላይ በመመርኮዝ ሳይሆን በስማ በለው አቧራ ሊያስነሳ የሚዳዳው የጠቅላላ ጉባዔ አባላትም ሆነ ሌላው ባለድርሻ አካላት የሚከራከርበትን አግባብና ልክ አውቆ እንዲከራከር አግባብ ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ መፍጠር፣ የስፖርቱ ባለድርሻ መነጋገርና መከራከርም ካለበት በእግር ኳሱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ እንዲሆን በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በማቆጥቆጥ ላይ የሚገኙ ‹‹ጎጠኝነት›› ስፖርቱን ወደ ባሰ አዘቅጥ የሚከት ስለመሆኑ አሳማኝ መድረኮችን መፍጠር፣ ይህ አመራር ከሁሉ በፊት ኃላፊነት እንደሚጠበቅበት የሕግ ባለሙያዎቹ ይመክራሉ፡፡

የፌዴሬሽኑ አዲሱ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በማጠቃለያ ንግግራቸው፣ የባለሙያተኞቹን ሐሳብ በመጋራት ፌዴሬሽኑ ወቅቱን የሚመጥን ተቋማዊ አደረጃጀት ይኖረው ዘንድ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ኢሳያስ ከሆነ፣ ካቢኔያቸው እጅግ ውስብስብና ፈታኝ ሥራ ይጠብቀዋል፡፡ እግር ኳሱ ለሰዎች የእርስ በርስ ግንኙነት መጠናከር መዋል ሲገባው አሁን አሁን ለከፍተኛ ንብረት ውድመትና ውድ ለሆነው የሰው ልጆች ሕይወት መጥፋት ምክንያት እየሆነ መምጣቱ ትክክል እንዳልሆነ ገልጸው፣ እስከዛሬ ለጠፋው ንብረትም ሆነ ሕይወት በተቋሙ ስም ጉባዔውን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

እግር ኳሱ በእሳቸው ካቢኔ ወይም በተወሰኑ የሰዎች ስብስብ ጥረት የትም መድረስ እንደማይችል የገለጹት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት፣ ከተቋሙ አደረጃጀት ጀምሮ የአገሪቱን እግር ኳስ ውጤታማ ለማድረግ መድረኮችን ፈጥረው ሙያተኞችን እንደሚያሳትፉ አስረድተዋል፡፡ በሰመራው ጉባዔ ለሥራ አስፈጻሚነት ከተመረጡት አመራሮች መካከል ከትግራይ የተወከሉት ከሎኔል አወል አብዱራሂም ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡ አቶ አበበ ገላጋይ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ አቶ አሊሚራህ መሐመድ ከአፋር፣ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ከደቡብ፣ አቶ ሰውነት ቢሻው ከአማራ፣ አቶ አብዱዛቅ ሐሰን ከኢትዮ ሱማሌ፣ ወ/ሮ ሶፍያ አልማሙን ከቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ አቶ ኢብራሂም መሐመድ ከሐረሪ፣ አቶ ቻን ጋትኮት ከጋምቤላ በሥራ አስፈጻሚ አባልነት ተመርጠዋል፡፡         

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...