Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ የገነባቸው የልህቀት ማዕከላት ሥራ ጀመሩ

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተጨማሪ የገነባቸው የልህቀት ማዕከላት ሥራ ጀመሩ

ቀን:

ከቅድመ ወደ ድኅረ ምረቃ ፕሮግራም ለመሸጋገር የሚያስችሉትን እንቅስቃሴዎች በማከናወን ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥሩ የሚገኙ የልህቀት ማዕከላትን ቁጥር አምስት ማድረሱን የዩኒቨርሲቲው የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ኃላፊ ፕሮፌሰር ዘሪሁን ወልዱ አስታውቀዋል፡፡

ኮሌጁ የሰብአዊ መብቶች ማዕከል በሰብዓዊ መብቶች ትምህርት፣ ምርምርና የሕዝብ አገልግሎት ላይ ትኩረት ያደረገውን አዲሱን ፕሮጀክት ይፋ ባደረገበት ሥነ ሥርዓት ላይ ፕሮፌሰር ዘሪሁን እንደገለጹት፣ የተቋቋሙትም ማዕከላት የሰብአዊ መብትና የማይግሬሽን፣ የሬልዌይ ኢንጂነሪንግ፣ የውኃ ማኔጅመንትና የመድኃኒት ምረት ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡

ከአምስቱ መካከል ሦስቱ የልህቀት ማዕከላት የተቋቋሙት ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ ነው፡፡ የማዕከላቱ መቋቋም ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የሚመጡ ተማሪዎችን እየተቀበሉ እንዲያስተምሩና ልምድ የመለዋወጥ አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ዩኒቨርሲቲው የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር አሊያንስ (ኅብረት) አባል መሆንም ችሏል፡፡ የማዕከላቱ መቋቋምም አንድ ዩኒቨርሲቲ የአሊያንስ አባል ከሆነ በውስጡ የልቀት ማዕከላትን እንዲኖሩት ግድ ይላል የሚለውን መሥፈርት እንዲያሟላ አስችሎታል፡፡  

ዩኒቨርሲቲው የአሊያንሱ አባል በመሆኑም ለሚያካሄደው የምርምር፣ የመማርና የማስተማር ሥራ ከሚያስፈልገው ወጪ ውስጥ ከፊሉን ራሱ እንዲሸፍን፣ ከአሊያንሱ ደግሞ ተወሰነ ድጋፍ እንዲያገኝ ያስችለዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም የመምህራን ልውውጥና የአቅም ግንባታ ሥራም ይኖራል፡፡

‹‹ከብዛት ወደ ጥራት እየተሸጋገርኩ ነው›› የሚለው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች ቅበላው መጠን እየቀነሰ ይገኛል፡፡ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን የመቀበል ኃላፊነቱንም በሌሎች ታዳጊ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ እየጣለ እንደሚገኝ፣ የመሰል ዩኒቨርሲቲዎችን አቅም የመገንባት ሥራም እየሠራ እንደሚገኝ፣ ራሱ ግን ወደ ምርምርና ድኅረ ምረቃ ጥናት ዘርፍ በመሸጋገር ሒደት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ከታዳጊ ዩኒቨርሲቲዎች የሚወጡ መምህራንም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለማግኘት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ‹‹ድኅረ ምረቃ ማለት ምርምር እንደመሆኑ መጠን በቅርቡ ይፀድቃል ተብሎ በሚጠበቀው አዲሱ ደንብ መሠረት እያንዳንዱ የድኅረ ምረቃ ተመራማሪ ለመመረቅ ቢያንስ ሁለት የምርምር ጽሑፎችን ማሳተም ይኖርበታል፤›› ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎችን የኅትመትና የምርምር አቅምን አስመልክቶ በ2008 ዓ.ም. በተካሄደው ግምገማ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 16ኛ፣ ከምሥራቅ አፍሪካ ደግሞ ከማካሬሪ ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ ሁለተኛ ወጥቷል፡፡ በሚቀጥሉት ሰባት ዓመታት ማለትም በ2017 ዓ.ም. ከአህጉሩ አሥረኛ፣ ከምሥራቅ አፍሪካ ደግሞ አንደኛ ለመሆን የሚያስችለውን ስትራቴጂ ቀርፆ ለተግባራዊነቱ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴዎች በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

‹‹በሰባት ዓመታት ውስጥ ማካሬሪንና የግብፅ ዩኒቨርሲቲዎችን ቀድመን እንደምንሄድ ነው፤ የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ግን በልጦ ለመገኘት ብዙ ድካም ያስፈልጋል፤›› ያሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኦፍ ሎው ኤንድ ገቨርናንስ ስተዲስ የሰብአዊ መብቶች ማዕከል ኃላፊ ዶ/ር ወንድማገኝ ታደሰ ናቸው፡፡

በቢዝነስና ፋይናንስ ፋኩልቲ በሚገኘው እሸቱ ጮሌ ጉባዔ አዳራሽ በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ ይፋ የተደረገው አዲሱ ፕሮጀክቱ ለችግር ተጋላጭ በሆኑ የኅብረተሰቡ ክፍሎች (ሴቶች፣ ሕፃናት፣ ስደተኞችና አካል ጉዳተኞች) ነፃ የሕግ ድጋፍ፣ ሥልጠና፣ ወዘተ አገልግሎት ይሰጣል፡፡

ዶ/ር ወንድማገኝ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ የማስተማር የምርምርና የሕዝብ አገልግሎትን ያካተተ ነው፡፡ ለተግባራዊነቱም ኖርዌይና የስዊድን ልማት ተራድኦ ድርጅት የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

ድጋፉ የሚዘልቀው ከ2010 ዓ.ም. እስከ 2013 ዓ.ም. ድረስ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹የድጋፉን መጠን ለመግለጽ አጋሮቻችን ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ ድጋፉ ግን በዋናነት በፋይናንስ ላይ የተመሠረተ ቢሆንም ማዕከሉ በዓይነት የሚፈልገው ካለ ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው፡፡ በተለይ ስዊድን የሚገኘው የጆአንበርግ ኢንስቲትዩት መምህራንን በመላክ፣ የእኛ ተማሪዎች እዚያ ሄደው ምርምር እንዲያካሂዱ ይፈቅዳል፤›› ብለዋል፡፡

የሰብአዊ መብቶች ማዕከል በአሁኑ ጊዜ በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የማስተርስና የዶክትሬት ዲግሪ ፕሮግራም እንዳለው፣ ከመማር ማስተማሩ ሥራ በተጨማሪም ከተለያዩ አጋሮች ጋር በመቀናጀት ለማኅበረሰቡ ልዩ ልዩ የማኅበራዊ አገልግሎቶች እየሰጠ፣ ለችግር ለተጋለጡ ማኅበረሰቦች ደግሞ በሰብአዊ መብት ዙሪያ ሥልጠናና የማማከር ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ከዶ/ር ወንድማገኝ ማብራሪያ ለመረዳት ችሏል፡፡  

‹‹በትምህርት ዘርፍ ፍላጎት አለን ብለን በምናስበው ዙሪያ አዳዲስ የሰብአዊ መብቶች ድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞችን የመክፈት ሐሳብ አለን፡፡ በምርምር ዙሪያ ደግሞ ለሰብአዊ መብት ችግሮች መፍትሔ መስጠት እንፈልጋለን፡፡ የመፍትሔ ሐሳብም የምናቀርበው ጥናትና ምርምር ካካሄድን በኋላ ነው፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...