Thursday, May 30, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ትልቅ ሀብት ለማፍሰስ ለተዘጋጀ ባለሀብት የመሬት አቅርቦት ማሻሻል ያስፈልጋል››

አቶ ካሳዬ ለማ፣ የሴንቸሪ ሞል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከተሞች በፍጥነት በማደግ ላይ ይገኛሉ፡፡ የሕዝብ ቁጥርም የዚያኑ ያህል እየጨመረ በመሆኑ ከኢኮኖሚ ዕድገቱ ጋር ተያይዞም የአገልግሎት ጥራት ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል፡፡ በተለይ ከኒዮርክና ከብራስልስ ቀጥሎ ሦስተኛዋ የዓለም የዲፕሎማቲክ ብሎም የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ በፍጥነት በማደግ ላይ ትገኛለች፡፡ ከተማዋ በአሁኑ ሰዓት እንኳ 26 ሺሕ የሚሆን ግንባታ እያካሄደች ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ በሠንጋ ተራ አካባቢ የሚካሄዱ ስምንት ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች ይገኙበታል፡፡ ከነዚህ ግንባታዎች የፋይናንስ ተቋማት የሚገነቧቸው ሲሆኑ፣ በጥቂት ባለሀብቶች ደግሞ ሁሉን ያካተተ ዘመናዊ አገልግሎት መስጫ ተቋሞች ገንብተዋል፡፡ እየገነቡም ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ተጠቃሽ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ከገነቡት መካከል ኔህኮ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ተጠቃሽ ነው፡፡ ኔህኮ ከመገናኛ ወደ አያት በሚስደው ዋና መንገድ ጉርድ ሾላ ከመድረሱ በፊት ሴንቸሪ ሞል የተሰኘ ግዙፍ አገልግሎት መስጫ ገንብቶ ጥር 2009 ዓ.ም. ለአገልግሎት ክፍት አድርጎታል፡፡ ኩባንያው ኔህኮ ከዚህም በጥልቀት በመሄድ ከቻይና ኢንቨስተሮች ጋር በጋራ በመሀል አዲስ አበባ ሁሉን ያካተተ ዘመናዊ ኮምፕሌክስ ለመገንባት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 20 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቦ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኔህኮ ገንብቶ ለአገልግሎት ከፍት ያደረገው ሴንቸሪ ሞል የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች እንዲሁም አዲስ ያቀደው ግዙፍ ፕሮጀክት ይዘት ምን እንደሚመስል ውድነህ ዘነበ ከኔህኮ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ካሳዬ ለማ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ አቶ ካሳዬ ተወልደው ያደጉት ሰሜን ሸዋ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ የመጀመርያ ዲግሪ ከእንግሊዝ ኦፕን ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የሴንቸሪ ሞል ግንባታ እንዴት ሊፀነስ ቻለ?

አቶ ካሳዬ፡- ባለፉት 15 ዓመታት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ወስደን ትልቅ ሥራ ለመሥራት ከፍተኛ ጥረት ብናደርግም ጥረቶቹ አልተሳኩም፡፡ ፍላጎታችን የነበረው አሥር ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ወስደን ከዚህ የገዘፈ ትልቅ የገበያና የመዝናኛ ማዕከል ያጣመረ ተመራጭ የጉብኝትና የግብይት ሥፍራ መገንባት ነበር፡፡ ሆኖም ግን የፈለግነውን ያህል ቦታ ባናገኝም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሊዝ ጨረታ ሲያወጣ ተወዳድረን አሸነፍን ይህንን ሴንቸሪ ሞል ልንገነባ ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡- ቦታውን በምን መንገድ አገኛችሁት?

አቶ ካሳዬ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2003 ዓ.ም. ባወጣው ስምንተኛው ዙር ሊዝ ጨረታ ተወዳድረን አሸንፈን ይህን አምስት ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት አገኘን፡፡ ከኛ ጋር በአጠቃላይ 17 ተጫራቾች ተወዳድረው ነበር፡፡ እኛ ከፍተኛ ዋጋ በማቅረባችን አሸናፊ ሆነን ቦታውን ተረክበናል፡፡

ሪፖርተር፡- የሴንቸሪ ሞል ሕንፃን ዲዛይን የሠራው ማነው? በግንባታው የተሳተፉ ኩባንያዎችስ እነማን ናቸው?

አቶ ካሳዬ፡- የሕንፃውን ግንባታ አማካሪ ሆኖ የሠራው ጌሬታ ሕንፃ ኮንስትራክሽን አማካሪ ድርጅት ነው፡፡ የሕንፃውን የውስጥ ዲዛይን የሠሩት ደግሞ የደቡብ አፍሪካ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ግንባታውን ያካሄደው ባማኮን ኢንጂነሪንግ፣ የማጠናቀቂያ ግንባታውን ዊንዳል ቢውልዲንግና ሲስተምስ ቴክኖሎጂ፣ የሴራሚክ ሥራውን ያዕቆብ ሕንፃ ተቋራጭ፣ በአጠቃላይ በሴንቸሪ ሞል የግንባታ ሒደት ከ70 በላይ ኩባንያዎች ተሳታፊ ነበሩ፡፡

ሪፖርተር፡- ሴንቸሪ ሞል ዘመናዊና ትልቅ ሕንፃ ነው ካልን በውስጡ ምን ምን አካቶ ይገኛል?

አቶ ካሳዬ፡- ሴንቸሪ ሞል በአምስት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሦስት መሠረቶች ያሉት በአጠቃላይ ባለ 16 ወለል ሕንፃ ነው፡፡ በአጠቃላይ በሕንፃው 43 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡ ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡ ሰፊውን ቦታ የሚይዘው የገበያ ማዕከሉ ነው፡፡ 800 ታዳሚ የሚይዙ ሦስት ዘመናዊ ፊልም ቤቶች፣ በአንድ ጊዜ 1,200 ሕፃናት የማስተናገድ አቅም ያለው የልጆች መዝናኛ ማዕከል፣ 1,500 ካሬ ሜትር ቦታ የያዘ ዘመናዊ የምግብ አገልግሎት የሚሰጥ ፉድ ከርት፣ 3,500 ካሬ ሜትር ቦታ የያዙ የቢሮ ክፍሎች፣ ዘመናዊ ሐይፐር ማርኬት፣ በተለይ የሕንፃው መጫወቻና ሲኒማ ቤቶቹ ማዕከል ዘመናዊ የአየር ሙቀት መቆጣጠሪያ አላቸው፡፡ ሕንፃው ሁለት ግዙፍ ጄነሬተሮች አሉት፡፡ የራሱ የጉድጓድ ውኃ አለው፣ አራት አሳንሰሮች፣ አሥር አስክሌተሮች፣ ከሕንፃው ሥር የሚገኙ ትልልቅና ዘመናዊ ከ300 በላይ ተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታዎች (ፓርኪንግ)፣ በአጠቃላይ የሕንፃውንና የአካባቢውን እንቅስቃሴ መቆጣጠሪያ ከ120 በላይ ዘመናዊ ካሜራዎች የተገጠሙለት ሕንፃ ነው፡፡ አንድ የሕንፃው ጎብኝዎች በሕንፃው ውስጥ ባሉ ሰፋፊ መተላለፊያዎች ሳይጨናነቁ የሚፈልጉትን አግኝተው የሚወጡበት ሕንፃ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ግንባታው ምን ያህል ፈጀ? የሕንፃው ባለቤትስ ማነው?

አቶ ካሳዬ፡- የሴንቸሪ ሞል ሕንፃ በድምሩ 541 ሚሊዮን ብር ወጥቶበታል፡፡ ይህ ወጪ ሦስቱን ሲኒማ ቤቶችና የሕፃናት ማጫወቻውን ይጨምራል፡፡ ግንባታው ከራስ ፋይናንስና ከባንክ በተገኘ ብድር የተካሄደ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ካለፉት 60 ዓመታት በላይ ጉልህ ሥፍራ ካላቸው ቤተሰቦች የተገኙ የገነቡት ሕንፃ ነው፡፡ ቤተሰቡ የጀመረው ንግድ ቀጥሎ ወደ ኢንቨስትመንት የተለወጠ ሲሆን፣ አዲሶቹ የቤተሰቡ ፍሬዎች አዲስ አበባ ተወልደው ያደጉ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ ከወላጆቻቸው ያገኙትን ልምድ በማሳደግ በአገሪቱ ኢኮኖሚ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው፡፡ ባለሀብቶቹ ከሴንቸሪ ሞል በተጨማሪ የሲቲሊ አርአምአይና የኦፖሎ ሚስማር ፋብሪካ ባለቤቶች  ናቸው፡፡ እህት ኩባንያዎቹን ጨምሮ በአራት ድርጅቶቻቸው ከ3,800 በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች ያስተዳድራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ሴንቸሪ ሞል ለምን ያህል ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጠረ? በአጠቃላይ ሴንቸሪ ሞልና እህት ድርጅቶቹ በሥራ ፈጠራ ያላቸው ዕቅድ ምን ይመስላል?

አቶ ካሳዬ፡- በሴንቸሪ ሞል ሁለት መቶ ዜጎች በላይ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ በተመሳሳይ ዘርፍ ቀጣዩ ፕሮጀክት አሁን ከመንግሥት የጠየቅነው መሬት ዕውን ሲሆን በአገልግሎት ዘርፍ ብቻ ለሁለት ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል የሚል ግምት አለን፡፡ በአጠቃላይ በአራቱ ኩባንያዎች 3,800 ዜጎች የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ሲሆን፣ በአጠቃይ በሁሉም ዘርፎች በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለአሥር ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ለማከናወን ትልቅ ዕቅድ ይዘናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ብዙ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የሕንፃ ግንባታዎች ደረጃቸውን የጠበቁ አይደሉም ይባላል?

አቶ ካሳዬ፡- ይህን ሕንፃ በአውሮፓ ስታንዳርድ ሠርቶ በዚህ ደረጃ ለአገልግሎት ማብቃቱ በመጀመርያ አገራችን የደረሰችበትን የዕድገት ደረጃ ያሳያል፡፡ ይህ ሕንፃ የአገር ሀብት በመሆኑ ለሁሉም ወገን ኩራት ነው የሚል እምነት አለን፡፡ አዲስ አበባ ከኒውዮርክና ከብራስልስ ቀጥሎ የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ናት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ ይህ ጅምር ነው፡፡ ‹‹የት ሄደን እንገበያይ? የትስ ቦታ ልጆቻችንን እናዝናና? ለሚሉ ኢትዮጵያውያንም ሆነ የውጭ ዜጎች መልስ የሚሰጥ ለወገንም ለአገርም መጣቀሻ ቦታ ነው ሴንቸሪ ሞል፡፡

      አንድ ከተማ ለመዝናናትም ሆነ ለመገበያየት የተለያዩ አማራጮችን የያዘ ሆኖ መገኘት አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ነው አንድ ከተማ አድጓል የሚባለው፡፡ የልጆች አዕምሮ እንዲጎለብት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዙ መጫወቻዎች፣ ለመዝናናትና ትምህርት ለመቅሰም ዘመኑ ባፈራቸው ፊልም መመልከቻዎች፣ ድምፅ ማስተጋቢያ መሣሪያዎች አገር በቀልና የውጭ ፊልም እንዲያዩ በማድረግ ሁሉንም ኅብረተሰብ የሚያገለግል ሕንፃ ነው፡፡ ከልጆች እስከ አዋቂ የተለያዩ አልባሳት የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶች፣ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች እንዲሁም የተለያዩ ዕቃዎች የሚገኙበት ማዕከል በአንድ ቦታ ላይ አካቶ የሚገኝ በመሆኑ ለከተማው አማራጭ ሆኖ ቀርቧል፡፡ ይህንን ስንል ከደንበኞችና ከጎብኝዎች የተሰጡ አስተያየቶችን ብናካትት ደስ ይለኛል፡፡ ‹‹ይህ ሕንፃ የአገር ሀብት እንጂ የባለቤቶቹ አይደለም፡፡ እውነትም ሌሎች የደረሱበትን አስተሳሰብ የኢትዮጵያውያን አሉ ማለት ነው፡፡ ባይገበያዩም ለማየት ብቻ የሚመጡበት ሕንፃ ነው፡፡ ሌሎቹም ደስ የሚሉና ገንቢ አስተያየቶች ኅብረተሰቡ እየሰጠን ነው፡፡ የሕንፃው አሠራር፣ አጨራረስ ውበትና የመተላለፊያ ስፋት ሕንፃውን ልዩ ያደርገዋል፡፡ የሲኒማና የልጆች መጫወቻ ምቹ መሆን ተመራጭ አድርጎታል፤›› የሚሉ አስተያየቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ሕንፃ በምትገነቡበት ወቅት በመንግሥት የተደረገላችሁ ድጋፍ አለ?

አቶ ካሳዬ፡- መንግሥት ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ እንደሚታወቀው ይህ ሕንፃ የተገነባው መንግሥት በዘረጋው መሠረተ ልማት (መንገድ፣ ውኃና መብራት) በዘረጋበት ሥፍራ ነው፡፡ ይህ እንደ ድጋፍ ሊታይ ይችላል፡፡ ነገር ግን መደረግ ያለበት ድጋፍ ከዚህ ማለፍ የለበትም ወይ? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ትልቅ ሀብት ለማፍሰስ ለተዘጋጀ ባለሀብት የተጠየቀውን መሬት አቅርቦት ማሻሻል ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ግዙፍ ኢንቨስትመንት ስናካሂድ ከቀረጥ ነፃ መብት ድጋፍ አልተደረገም፡፡ ሆኖም ከቀረጥ ነፃና የመሳሰሉ ቢመቻቹ የበለጠ ያበረታታል፡፡ ይህ ዘርፍ በሌሎች አገሮች እንደ ቱሪስት መስህብና መዝናኛ ማዕከል የሚቆጠር በመሆኑ በመንግሥት በኩል ሊመቻቹ የሚገባቸው ድጋፎች ሊደረጉ ይገባል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የወደፊት ዕቅዳችሁ ምንድነው? በመሀል ከተማ ካዛንቺስ አካባቢ አንድ ግዙፍ ፕሮጀክት ለመጀመር ማቀዳችሁ ይነገራል፡፡ ምንድነው ፕሮጀክቱ?

አቶ ካሳዬ፡- በተመሳሳይ ዘርፍ ይበልጥ ለመሥራት ዕቅድ አለን፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካዛንቺስ አካባቢ 20 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ እንዲሰጠን ጥያቄ አቅርበናል፡፡ ሲፈቀድልን ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ ነን፡፡ ቁርጠኛም ነን፡፡ ከምንሠራው ሥራ አንፃር ያቀድነውን ለመፈጸም ማንም ይጠረጥረናል ብዬ አልገምትም፡፡ ካዛንቺስ አካባቢ ለመሥራት ያቀድነው ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብና ቱሪስት ጭምር ሊያመጣ የሚችል ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ሞል፣ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል፣ አፓርትመንት፣ ሲኒማ ቤቶች፣ የልጆች መጫወቻዎችና የቢሮ ሕንፃዎችን ያካትታል፡፡ ይህንን ሕንፃ ከቻይና ኢንቨስተሮች ጋር በሽርክና ለመሥራት ነው ያቀድነው በአጠቃላይ ለዚህ ፕሮጀክት 2.7 ቢሊዮን ብር ይወጣል ተብሎ ታስቧል፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ተመሳሳይ ግንባታዎች ተገንብተው የበለጠ ውድድር ያለበትና ከሠራነው የበለጠ ሕንፃ በትልቅነትም ሆነ በዘመናዊነት የተሻለ አገልግሎት የሚሰጡ እንዲኖሩና እኛም እንድንወዳደር እንፈልጋለን፡፡ አማራጮች ሲኖሩ ሁላችንም ለላቀ ነገር ተግተን እንድንሠራ ያግዘናል፡፡ ኔህኮ ትሬዲንግ ባለሀብቶች በአገር ውስጥ የተጀመረውን የገበያና የመዝናኛ ማዕከል ጅምሮ በማየት ወደዚህ ደረጃ በማድረሳቸው ሊመሰገኑ ይገባል፡፡  

ሪፖርተር፡- ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ያበረከታችሁት ወይም እያበረከታችሁት ያላችሁት አስተዋጽኦ አለ?

አቶ ካሳዬ፡- ሁለት የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን አንዱን በሰሜን ሸዋ አንዱን በቢሾፍቱ ከተማ ከእህት ኩባንያ ጋር በመሆን ገንብተን አስረክበናል፡፡ 380 ሕፃናትና አረጋውያን ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት 14 ዓመታት ሙሉ በሙሉ ወጪያቸውን በመቻል በማኖር ላይ እንገኛለን፡፡ ይህ በቂ ነው ብለን ስለማናምን ወደፊት ከዚህ የበለጠ ድጋፍ ለማድረግ ዕቅድ አለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

የሳባ መንደር

ሼባ ግሩፕ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሼባ/ሳባ የጉዞ ወኪል በ1960ዎቹ የተመሠረተና በርካታ እህት ኩባንያዎችን ያፈራ ነው፡፡ ሼባ ግሩፕ በቢሾፍቱ ከተማ በ350 ሚሊዮን ብር ወጪ...

ከዕውቀት እስከ ሕይወት ክህሎት

ዋርካ አካዴሚ ከትምህርት አመራርና ፔዳጎጂ፣ ከሳይኮሎጂ፣ ከዓለም አቀፍ ኪነ ጥበብ፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ከባንኪንግና ዓለም አቀፍ ፋይናንስ አመራር ሙያዎች በተውጣጡ ባለሙያዎች የተቋቋመ የትምህርት ተቋም ነው፡፡...

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...