Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርኢትዮጵያዊነት ኃይል ነው

ኢትዮጵያዊነት ኃይል ነው

ቀን:

በወልደ አማኑኤል ጉዲሶ

በአገራችን ረም ዕድሜ ካስቆጠሩት ህያው አባባሎች አንዱ ‹‹ዕድሜ መስታወት ነው››፣ በመሆኑም ብዙ ነገር ያሳያል የሚለው ነው፡፡ አባባሉ ለሁላችንም ባይሆንም ለብዙዎቻችን ብዙ ጊዜ ከታላላቆቻችን የምንሰማው አባባል ስለሆነ፣ አዲስ ይሆናል ብዬ አልገምትም፡፡ በእርግጥም ዕድሜ በጊዜ ሒደት ብዙ ነገሮችን ያሳያል፡፡ መልካምና መልካም ያልሆኑ ነገሮችን ያሰማል፣ ያስተናግዳልም፡፡ አንድ ሰው ዕድሜው በቆየ ቁጥር ከራሱ አልፎ ለሌሎች በተለይም ደግሞ ለወጣቱ ትውልድ ግንዛቤ መፍጠሪያ፣ ያለፈውን ታሪክ ማገናዘቢያ ህያው ምስክርነቶችን በተለያዩ መንገዶች ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ወደድንም ጠላን ተፈጥሯዊ ሕግ ነውና እውነታውን እንቀበለዋለን፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንበረ ሥልጣናቸውን በይፋ ከተረከቡ በኋላ ለተወካዮች ምክር ቤትና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያደረጉት ንግግር፣ የበርካታዎቻችንን ልብ የሚጠግንና የሚፈውስ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ስሜት የእኔ ብቻ ሳይሆን የብዙዎች ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት እንደሆነ ደፍሬ መናገር እችላለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን፤›› ያሉትን አኩሪና ይፋዊ መልዕክት እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በቴሌቪዥን እከታተል በነበረበት ወቅት፣ የመልዕክቱ ጠንካራነት ውስጣዊና ውጫዊ የሰውነት ክፍሎቼን ሰርስሮና ዘልቆ በመግባት በደስታ እንዲሞሉ አድርጎኛል፡፡ ብሔራዊነት ‹‹እየደበዘዘ›› እና ብሔርተኝነት እየገዘፈ የመጣውን አገራዊ ስሜት ወደነበረበት ወደ ጋራ ቤታችን ኢትዮጵያ እንድንመለስ የሚያደርግ ጥሪ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ይህ ኢትዮጵያዊነት ለእኔ በግሌ የተለየ የሆነው ያለምክንያት አልነበረም፡፡ የሕይወቴ አንዱ ምዕራፍ ሆነና በወታደራዊ መንግሥት ዘመነ መንግሥት በአሰብ አስተዳደር የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ አገልጋይ ሆኜ እሠራ ስለነበር፣ በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ ይቀነቀኑ የነበሩ አዎንታዊ አብነቶችንና ያሳለፍኳቸውን የሕይወት ውጣ ውረዶች ወደ ኋላ መለስ ብዬ እንዳስታውስ አድርጎኛል፡፡ በወቅቱ ስለኢትዮጵያዊነት ይገለጹ ከነበሩ ማሳያዎች መካከል የምደግፋቸውና የማልደግፋቸው አመለካከቶች ቢኖሩም፣ አብዘኛዎቹ ዕይታዎች ግን ዛሬም ሆነ ነገ በቀላሉ ከአንደበቴ የሚፋቁ ሳይሆኑ በውስጣዊና ውጫዊ ስሜቶቼ ተቀርፀው የቀሩና እስከ ሕልፈተ ሞቴ አብረውኝ የሚዘልቁ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያችን የሁላችንም፣ ለሁላችንም መሆኗን አጉልተው የሚያሳዩ ነበሩና፡፡

ወታደራዊ መንግሥቱ ሁሉንም ነገር በወታደራዊ ኃይል ለመፍታት ያደረጋቸው የመፍትሔ አቅጣጫዎች በአገሪቱ ሀብት፣ ንብረትና የዜጎች ሕይወት ያደረሰው ጉዳት ከባድ አገራዊ ቀውስ አስከትሎ እንደነበረ ዕሙን ነው፡፡ ይህንኑ ቀውስ እንኳን ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ስለኢትዮጵያችን ሰላምና ደኅንነት የሚቆረቆሩ የውጭ አገር ዜጎች ሳይቀሩ የሚኮንኑት ሀቅ ነበር፡፡ (ለነገሩማ ወደ ሰላማዊ መድረክ መምጣት በአገራችን መልካም ፍላጎት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፣ ዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታም ብዙም አመቺ አልነበረምና) የእርስ በርስ ጦርነት ሆኖ እርስ በርስ ተዋጋን፣ ተሟሟትን፡፡

ከ17 ዓመታት በላይ በፈጀው የእርስ በርስ ጦርነት አሸናፊውም ተሸናፊውም እኛው በኛው፣ ለኛው ሆንን፡፡ እኛው በኛው ተኩራራን፣ እኛው በኛው ተኮራረፍን፡፡ እኛው በኛው ተመፃደቅን፡፡ አንዱ ሲያጎነብስ ሌላው ራሱን የተለየ ዜጋ በማስመሰል ደረቱን ገልብጦ መሄድ ጀመረ፡፡ አንዳንዶቹ በኢትዮጵዊነታችን ዙሪያ ልዩነትን የሚያሰፉና የአንድነትን ድባብ የሚገፉ አስተሳሰቦች ነበሩባቸው፡፡ ይህንኑ ታሪካዊ ሒደት ወደ ሥልጣን መቆናጠጫና ጥቅማ ጥቅም ማሳደጃ ልዩ አጋጣሚ ወይም ዕድል አድርገው የተጠቀሙም ነበሩ፣ አሉም፡፡ ሁሉም ባይሆኑም በርካታዎች ‹‹ከባለጊዜዎቹ›› ጋር ቁርኝት በመፍጠር የውሸት ፅዋ አብረው መጠጣት በመጀመራቸው ያለ ችሎታቸውና ዕውቀታቸው ሌሎችን ዜጎች ያለ አግባብ አሳዳጆች፣ ተጠቃሚዎች፣ ፈላጮችና ቆራጮች ሆኑ፡፡ ዘረኝነትንና ቂመኝነትን መሬት ላይ ዘርተው እስከ ማብቀል ደረሱ፣ ኮትኩተውም አፋፉ፣ አሳደጉም፡፡ ልማት በጥፋት ላይ ጊዜውን ጠብቆ ሚዛን መድፋቱ አይቀሬ ቢሆንም፣ ልማትና ጥፋት እርስ በርስ ሳይዋደዱ ጎን ለጎን መሄድ ጀመሩ፡፡     

በእነዚህም የትግል ዓመታት የአንድ አገር ዜጎች የሆንን ወንድማማቾችና እህትማማቾች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አብረን ብንወድቅም አብረን ተነስተናል፡፡ አብሮ የመውደቅን መራር ፅዋ ወደ ኋላ ትተን አብሮ የመነሳትን ጠቀሜታ የበለጠ እያጎላን መጥተናል፣ አጣጥመናልም፡፡ በማሸነፍና በመሸነፍ ሒደት የነበሩ መነሻዎችና መዳረሻዎች ወዴት ሊያመሩን እንደነበረ በጋራ በማጤን ፊታችንን ወደ አገራዊ ልማትና ግንባታ አዙረናል፡፡ እንደ ገና ተዋግተን ሉዓላዊነታችንን እንድናስከብር ያስገደዱንን ‹‹ጠላቶቻችንን››  በጋራ መዋጋት ነበረብንና በጋራ ተዋግተን መክተን፣ አሸንፈናቸዋልም፡፡

‹‹ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር›› የሚለው መፈክር ሁሉም ነገር ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ማሸነፍ በሚል የተባበረ ልማታዊ እንቅስቃሴ ተተክቷል፡፡ ጉልበታችንንና ዕውቀታችንን አስተባብረንና በሙሉ ቁርጠኝነት የገባንበት ጉዞም ስለነበረ ሁለንተናዊ ውጤት አስመዘገብን፡፡ ለዚህም በአገር ውስጥና በውጭ አገር በተጨባጭ መረጃ የተደገፈ ምስክርነት ተሰጠን፡፡ ትግሉ፣ ድሉ፣ ውጤቱና ጣፋጭነቱ ወደፊት መገስገስን፣ ዘላቂነትንና የማያቋርጥ መሆኑን በማሳየት ተነሳሽነትን ፈጠረ፡፡ ይህ ሁሉ ጉዞ በልዩነት ውስጥ አብሮነት፣ በአብሮነት ውስጥ ልዩነት መኖርን አስተማረን፡፡ ይህንኑ ልማታዊ እንቅስቃሴ እንደ አገር ስናካሂድ ደግሞ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖዎች አልነበሩብንም ወይም የሉንም ማለት አይደለም፡፡ ከፊትም ከኋላም፣ ከግራም ከቀኝም እጃችንን ሊጠመዝዙ የሚሞክሩ ተፅዕኖዎች ነበሩብን፡፡ ጣልቃ ገብነቶች ማለቱ ሳይሻል አይቀርምና እስኪ ከእነዚህ ተፅዕኖዎች መካከል አንዳንድ ጭብጦችን በትንሹ እንመልከት፡፡

ካለፉት 50 እና 60 ዓመታት ወዲህ የዓለም ሕዝቦች ለሰላም፣ ለልማትና ለዴሞክራሲ ማበብ የሰጡት ትኩረት ዝቅተኛ ነው ባይባልም፣ በየአገሮቹ ‹‹ታቅደው›› እና  እንደ እሳተ ገሞራ ድንገት በሚፈነዱ ጦርነቶች ሳቢያ የወደመው ሀብትና የሰው ልጆች ሕይወት እጅግ አስደንጋጭና አሳፋሪም ነበር፡፡ በእርግጥም ያስደነግጣል፣ ያሳፍራልም፡፡ በእኔም ሆነ በብዙዎች ዕይታ አስደንጋጭ የሚሆነው ለጦርነቶቹ የወጣው ወጪ ግዙፍነት ተወዳዳሪ የሌለው መሆኑ ሲሆን፣ አሳፋሪ የሚሆነው ደግሞ በብዙዎቹ የዓለም አገሮች በርካታ ዜጎች በተለይም ሴቶች፣ ወጣቶችና ሕፃናት በስደት፣ በረሃብና በመጠለያ ዕጦት እንደ ቅጠል እየረገፉ ባሉበት ሁኔታ ይኼው አሰቃቂ ድርጊት እንደ መፍትሔ ዕርምጃ መወሰዱ ነው፡፡ ሲወሰድም በተለይም ጡንቻ ባላቸው ኃያላን መንግሥታት ሳይቀር ዝም ተብሎ መታየቱ ነው፡፡

ለእነዚህ ሁሉ ጦርነቶች መከሰት በኃያላን መንግሥታት መካከል የተፈጠረው የርዕዮተ ዓለም ፍጥጫና የኑክሌር ጦር መሣሪያ የበላይነት ፉክክር ያስከተለው ቀዝቃዛ ጦርነት በተለየ ሁኔታ ዓለማችን በጦርነት ሥጋት ውስጥ እንድትገባ ቢያስገድዳትም፣ ዋነኛው አስገዳጅ ምክንያት ግን ድህነት እንደሆነ በተጫባጭ እየታየ ነው፡፡ ድህነት የሁሉም ችግሮች መነሻና መድረሻ ነው፡፡ ሚዛናዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል ያስከተለው የሕይወት ውጣ ውረድ ነው፡፡ ውጣ ውረዱ በአብዘኛዎቹ የዓለም አገሮች የማይሽር ጠባሳ አስከትሏል፡፡ እያስከተለም ይገኛል፡፡

ድህነት በሰው ልጆች መካከል ምን ዓይነት አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ገና ከጧቱ አጥብቆ የተገነዘበው አርስቶትል በሕይወት ዘመኑ ከተናገራቸው አባባሎች አንዱ፣ ‹‹ድህነት የብጥብጥና የወንጀል ወላጅ ነው›› (Poverty Is the Parent of Revolution and Crime) የሚለው ነው፡፡ ድህነት የጦርነት፣ ጦርነት ደግሞ የድህነት ወላጆች እየሆኑ የዓለምን ሰላምና ልማት እያቀጨጩ ናቸው፡፡ የወደፊቱን ልማታዊ እንቅስቃሴ ማደናቀፍ ብቻ ሳይሆን፣ በረዥም ጊዜ ጥረትና ሕዝቦች ድካም ፍሬ አፍርተው ወደ ዓለም ሀብትነት የተመዘገቡ እሴቶችም በዚሁ ሰበብ አሳዛኝ ውድመት ደርሶባቸዋል፡፡ ለዚህም አብነት በርካታ አገሮችን መጥቀስ የሚቻል ቢሆንም ሞሮኮ፣ ኢራቅ፣ ሊቢያ፣ የመንና ሌሎችንም የአፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮችን መግለጹ በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ እሴቶቹ በዓይን ከሚታዩበትና በእጅ ከሚዳሰሱበት ትዕይንት በመውደማቸው ወደ አፈ ታሪክነት ተቀይረዋል፡፡ የየአካባቢዎቹን ሀብት ለመቆጣጠር ሲሉ ኃያላን መንግሥታት የሚያካሂዱት የእጅ አዙር ስትራቴጂካዊ ጦርነት በመሆኑም የንፁኃን ሕይወት ጠፍቷል፣ ለአስከፊ ስደትም ተዳርገዋል፡፡ የሚዘገንን የሰብዓዊ መብት  ረገጣም ደርሶባቸዋል፡፡

በአገራችንም ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ዕድገቷን ወደኋላ የሚጎትቱ፣ በሰው ሕይወትና ንብረት ቀላል የማይባል አደጋ የሚያስከትሉ፣ ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ በሰላምና በነፃነት መዘዋወርን የሚገድቡና በተያያዝነው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ጉዟችን ተፅዕኖ የሚያሳድሩ እንቅስቃሴዎች (ይህንኑ እንቅስቃሴ የልማታዊ እንቅስቃሴ አዎንታዊ መገለጫ አድርገው የሚመለከቱ ወገኖች እንዳሉ ሆኖ ማለት ነው) መፈጠራቸው አልቀረም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ታሪካዊ ንግግርም ይኸው ሕዝባዊ ንቅናቄ የፈጠረው ክስተት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን፤›› ማለታቸው ከሶስት አሥርት ዓመታት ወዲህ ‹‹ተቀዛቅዞ›› የነበረውን የኢትዮጵያዊነት ትኩሳት አጉልቶና አግዝፎ ያሳየ ታሪካዊ መልዕክት ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊነትን እንደገና ያደሰና ያነሳሳ ንግግርም ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ የሚያነሷቸው ትልልቅ ሐሳቦች፣ ትልቅ የነበርነውን ኢትዮጵያውያን ወደ ትልቅነት የሚመልሱን ስለመሆናቸው ጥርጣሬ የለኝም፡፡

እነዚህ በአገር ውስጥ የተከሰቱ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች በወቅቱ ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎች ያስከተሏቸው መዘዞች ስለመሆናቸው መንግሥት በራሱ አምኖ፣ ሕዝቡን ይቅርታ የጠየቀባቸው መሆናቸውም ይታወቃል፡፡ በየጊዜው እያደገ ከመጣው የሕዝብ ፍላጎቶች ጋር ተደምሮ ሕዝብና መንግሥት ቅርብ ለቅርብ መወያየት ያለመቻል በተለይም የወጣቱን የልብ ትርታ ያለማዳመጥ የቅርብ ጊዜ ትዝታ የሆነውን ሕዝባዊ እምቢተኝነት አስከትሏል፡፡ ይህ እምቢተኝነት አሜሪካዊው ጀግና አባት አብርሃም ሊንከን በዘመኑ የተናገሩትን ታላቅ አባባል ከዛሬው ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንድናመሳስል እንገደዳለን፡፡ ይኸውም ‹‹ሕዝቡ እውነቱን ይወቀው፣ ከዚያ አገሪቷ ትረጋጋለች፤›› ማለታቸው ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በንግግራቸው ‹‹አገር ለሁሉም የሚበቃ ሀብት አላት፣ ሁሉም እንደ ልቡ የሚዘርፈው ሀብት ግን ሊኖራት አይችልም፤›› በማለት የማህተመ ጋንዲን ህያው ምሳሌ መናገራቸው ዶ/ሩ ተስፋ ሰንቀው፣ ራዕይ አንግበው፣ ብቁ አመራርነትን ተላብሰው ብቅ ያሉ ስለመሆናቸው ሌላ አብነት ሊጠቀስ የሚገባ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ‹‹የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል›› እንዲሉ ነውና፡፡  ከዛሬ 30ዎቹ ዓመታት ወዲህ ለተወለዱ ወጣቶች ወንድሞቼና እህቶቼ፣ ኢትዮጵያዊነትም ሆነ የሰላምና ጦርነት ትርጉም ብዙም ላይታወቃቸው ይችል ይሆናል፡፡ ሰላምን እንጂ ጦርነትን በተግባር ስለማያውቁ (እንዲያውቁም አልመኝም) ብዙም ላይጨነቁ ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ኃይል ነው ሲባል መፈክር ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ቀላል የቅስቀሳ ቋንቋም የሚመስላቸው ይኖራሉ፡፡ የመልዕክቱ ይዘት ግን ከዚያ ሁሉ በላይ የአገርና የሕዝብ ዓብይ አጀንዳ ነው፡፡ ቀኑ ይመሻል፣ ሌሊቱም ይነጋል፡፡ ክረምትና በጋም በየጊዜው ይፈራረቃሉ፡፡ በየትኛውም ሁኔታ ኢትዮጵያዊነት የማንሸሸውና ለማንም አሳልፈን የማንሰጠው ክብራችን፣ መለያችንና መገለጫችንም ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ለኛ ኃይል ነው፡፡ ሰላምና ደኅንነት ነው፡፡ ወሳኝ፣ ዘላቂና የማያቋርጥ ዕድገትም ነው፡፡ ይህች በአፍሪካ ጠንካራና ግዙፍ ኢኮኖሚ እየገነባች ያለችው ጥንታዊቷ ገናና አገር ኢትዮጵያችን መጠንከር ለእኛ ለዜጎቿ ታላቅ ኃይል ነው፡፡ ዋስትና ነው፡፡ ኩራትም ነው፡፡ አጥብቀን ልንይዘውና ልንንከባከበው ይገባል፡፡  

እንደ ዜጋ በዓይናችን ከምናያቸውና በእጃችን ከምንዳስሳቸው ልማታዊ እንቅስቃሴዎቻችን በተጨማሪ፣ በዓለም አቀፍ መድረኮችና ግዙፍ ሚዲያዎች ጭምር ስለልማታዊ እንቅስቃሴያችን ውጤታማነት እየሰማን ባለንባቸው ዓመታት የተከሰቱ ንቅናቄዎች ያሳዩት ነገር ቢኖር ከእኛነት ይልቅ የእኔነት፣ ከኅብረ ብሔራዊነት ይልቅ አካባቢያዊነት፣ ከአገራዊ ልማት ይልቅ ግለሰባዊ ብልፅግና፣ ከሁሉም በላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ንግግር ደግሞ ‹‹የሕዝቡን ብሶት ካጋጋሉት ከዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ሙስና ነው››፡፡ ለዚህ አገራዊ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ጉዞ እያንዳንዱ ሙያ፣ የእያንዳንዱ ሙያ ባለቤት የሆነው  ግለሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ በአጭሩ እያንዳንዱ ዜጋ አገራዊ ግዴታ ነውና ተገቢውን ሚና ሊጫወት ይገባል፡፡ ለእኔ እንደ ባለሙያ ለእያንዳንዱ ሙያ የሚሰጠው ክብርና አድናቆት እንዳለ ሆኖ፣ መረጃዎችን ወደ ኅብረተሰቡ በማሠራጨቱ ሒደት መገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች (ባለሙያዎች) ትልቅ አገራዊ ተልዕኮ አላቸው፡፡ ለዚህም ነው ማርክ ቱዌን የተባለ አሜሪካዊው ደራሲ ‹‹ብርሃንን ወደ ሁሉም የዓለም ዳርቻዎች የሚያደርሱ ሁለት ኃይሎች አሉ፡፡ እነሱም የሰማይዋ ፀሐይና እዚህ ታች አሶሼትድ ፕሬስ ናቸው፡፡

እንደዚያ ሁሉ የብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች ባለሙያዎች የሚጠቀሙባቸው ቃላት በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ ትልቅ ኃይልና አንጋፋ ተልዕኮ ያላቸው መሣሪያዎች ናቸው፡፡ ቃላት ሕይወት ይፈጥራሉ፣ ሕይወት ያጠፋሉ፣ ያስጠፋሉ፡፡ ቃላትን በአግባቡ ካልተጠቀምን እውነታን አጉልተው የሚያሳዩ ብቻ ሳይሆኑ የሚያደበዝዙም ይሆናሉ፡፡ ይበታትኑናልም፡፡ ቃላት ያገናኙናል፣ ያለያዩናልም፡፡ ቃላት መረጃዎች ናቸውና በአንድነታችን ፀንተን እንድንቆይ ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ቃላት ቁጣን ይቀሰቅሳሉ፣ ጥርጣሬ ያነግሣሉ፣ ያለመተማመንን ይፈጥራሉ፣ ዕልቂትን ያስከትላሉ (የሩዋንዳ የእርስ በርስ ፍጅት ትዝ ይሏል)፡፡ ቃላት መከባበርን ያሰርፃሉ፣ ልማትን ያበረታታሉ፣ ህሊናችንን ይገነባሉ፣ የዚያኑ ያህል ያቆስላሉ፣ ጥላቻን ይወልዳሉ፣ ያፈርሳሉ፡፡ ቃላት ሀቅን ያደበዝዛሉ፣ ውሸትን ያናፍሳሉ፡፡ አንዱን ያስቃሉ ሌላውን ያስለቅሳሉ፡፡ ቃላት መረጃዎች ናቸውና የአንድነትንና የእውነትን ታሪክና ሐውልት ይገነባሉ፣ የዕድገት መሠረት ይጥላሉ፡፡ መረጃዎች ናቸውና በአግባቡ ከተጠቀምናቸው የጋራ መግባባትን፣ መቻቻልን፣ ይቅር መባባልን፣ አርቆ ማስተዋልን፣ መተማመንን፣ ግልጽነትንና ባለራዕይነትን ያስታጥቃሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ከተጠቀምናቸው ግን ውጤቱም ግቡም ተቃራኒ ይሆናል፡፡ አሉታዊነት እየተተካ አፍራሽነት ያመዝናል፡፡ መረጃ ኃይል ነው፣ መረጃ ዕውቀት ነው፣ መረጃ ከጥይት የበለጠ ፍጥነትና ድምፅ አለው፡፡ መረጃ የአመለካከት መቅረጫ መሣሪያ ነው፡፡ መረጃ የአዕምሮ ምግብ ነው፡፡ ሚዲያ ደግሞ መረጃ አቀባይ በመሆኑ ዜናው፣ ፕሮግራሙ፣ መጣጥፉ መቼ ቀርቦ በተመገብነው ሊያሰኝ የሚችል መሆን አለበት፡፡ እንደዚያ ማድረግ ከቻልን የኢትዮጵያዊነትን ኃያልነት እናረጋግጣለን፡፡ መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያዊነትን ሁሌም በመገንባት ሒደት ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡ የመገናኛ ብዙኃንን ሚና የሚያናንቅ ሕዝብ የመረጃ ደሃ ይሆናል፡፡ የመረጃ ድህነት የሀብት ድህነትን ያስከትላል፡፡  የመረጃ ድህነት የዕውቀት ድህነትን ያስከትላል፡፡ የመረጃ ድህነት የቴክኖሎጂ ድህነትን ያመጣል፡፡ ስለዘመኑ ቴክኖሎጂ በቂና ተመጣጣኝ  መረጃ ያለመኖር ዓለም አቀፋዊነትን ያደበዝዛል፡፡ የሚዲያን ሚና የሚያናንቅ መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ልማታዊ መሆን አይችልም፡፡ ራሱን መልሶ የሚያይበት መስታወት አይኖረውም፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ የምንደራደር አይደለንም፡፡ አልነበርንም፡፡ ወደፊትም አናደርገውም፡፡ ፈጽሞ አንፈቅድምም፡፡ የሚፈቅድና የተፈቀደ ታሪክም የለንም፡፡ ወደፊትም አይኖረንም፡፡ ለዚህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወደ ኋላ የማይቀለበስ የኢትዮጵያዊነት ቃለ መሃላ ማደስ አለበት፡፡ ከኢትዮጵዊነታችን የምናገኘው እንጂ የምናጣው ነገር ሊኖር አይገባም፡፡ አንድ ከሆንን አናጣም፡፡ ዛሬ ያጣነውን ነገር ተስፋ ባለ መቁረጥ ነገ እናገኛለን፡፡ ነገ ባናገኝ ከነገ ወዲያ እንደርስበታለን፡፡ ይህ ባለ ራዕይ ዕርምጃችን ተስፋ ሳይሆን ሙሉ እምነት ይዘን መኖርና ለቀጣዩ ትውልድ ማውረስ አገራዊ ስሜት መሆን ይገባዋል፡፡

አገራዊ ስሜት ስንገነባ አንድ ልብ ልንል የሚገባን ትልቅ ቁም ነገር መረሳት የለበትም፡፡ ይኸውም ላለፉት ታሪካዊ ክንዋኔዎች ተገቢውን ቦታ መስጠትን ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ከቻልን የወጣቱን፣ የጎልማሳውንና በዕድሜ የገፉ ዜጎችን ድጋፍና አድናቆት እናገኛለን፡፡ በሠለጠነ መንገድ ለአገራዊው ጥሪ ከመንግሥት ጎን እንዲሠለፉ እናደርጋለን፡፡ በአገራዊው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ቀድመው ይሠለፋሉ፡፡ የኃይልን፣ የቁስንና የስበትን ኃይል ሚስጥር በማግኘት ለዓለም ታላቅ ባለውለታና ሊቅ የሆነው አልበርት አንስታይን በዘመኑ አንድ ነገር ተናግሮ ነበር ይባላል፡፡ ይኸውም፣ ‹‹ማንኛውም ችግር ያንኑ ችግር በፈጠረው ንቃተ ህሊና አይፈታም፣ አዲስ የሆነ ዓለም ማየት አለብን፡፡›› ስለዚህም ለነገ ብሩህ ተስፋ እንዲኖር ከተፈለገ የትናንትናውን እውነታ ማደብዘዝ የለብንም፡፡ ችግሮችን በአንድ ሌሊት የሚቀረፉ አድርገን አጉልተን ማሳየትም ሆነ ማየትም አንዳንድ ጊዜ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዘነ ይሆናልና ጊዜ መስጠት ይገባል፡፡ ፖርቹጋላዊው ክሪስቶፎር ኮሎምቦስ የዛሬዋን አሜሪካ ከማግኘቱ በፊት አብረውት የነበሩ መርከበኞች ከውኃ በስተቀር መሬት ማግኘት እንደማይችሉ አድርገው ተስፋ እየቆረጡ ሲያስቸግሩት፣ ‹‹ዛሬ ካላየን ነገ እንደርስበታለን›› እያለ ያበረታታ እንደነበር ይነገራል፡፡ በዛሬ ዘመን የማይሆነውን ነገር እንደሚሆን ለሕዝብ ቃል መግባትም እምነትን ወደ ኋላ  እየሸረሸረ የሚያመጣ በመሆኑ ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡

በመጨረሻም ይህንን መጣጥፍ በማዘጋጅበት ወቅት ሁለት ደስ የሚሉ አጋጣሚዎችንና ፕሮግራሞችን በቴሌቪዥን ስክሪን በጥንቃቄ ተከታትያለሁ፡፡ እነዚህም በኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ተላልፎ የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ  የሚሌኒየም አዳራሹ ‹‹የአስተሳሰብ መገንቢያና ማነቃቂያ መድረክ›› ንግግርና በቢቢሲ ቻናል ላይ የተሠራጨው የእንግሊዙ ልዑል የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ ሁለቱንም አደነቅኳቸው፡፡ ለምን ቢሉኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለወጣቶች በተለይም ባለራዕይ ለሆኑ ወጣቶች የሰጡት ተስፋ ዕውን ቢደረግ፣ በእርግጥም ዕውን ይሆናል ብዬ እጠብቃለሁ:: የአገራችንን ወጣቶች ለተወዳዳሪነትና ለአገር ገንቢነት የሚያነሳሳ መሆኑ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ እኛም በእውነት እንዲህ የዓለምን ሕዝብ በጉጉት የሚያስጠብቁና ነባር ባህሎችን በአንድ ልብና በኢትዮጵያዊነት ስሜት ጋር ተደማሪ አድርገን ብንጠቀም የሚለው ነው፡፡ እንዲህ ማለቴ ግን የዓለምን ሕዝብ የሚያስደምምና አኩሪ ባህል የለንም ማለት  አይደለም፡፡ ሌሎችንም ነባርና አዳዲስ እሴቶቻችንን አንዱ ሌላውን ሳይንቅ፣ ሳያሳንስ፣ በመከባበርና በመቻቻል እናድንቅ ለማለት ነው፡፡ በሚቀጥለው እንገናኝ፡፡ ለእኛም ለአገራችንም ሰላም ተመኘሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...