‹‹ፍቅር ካለ የቁንጫ ቆዳ ለሺሕ ይበቃል፡፡ ጠጋ ጠጋ እያላችሁ ቁጭ በሉ፤›› እያለ ወያላው መጠቅጠቁን ቀጠለ፡፡ የተቃወሙትን ሁሉ እንዳልሰማ አልፎ ሌላ የቸኮለ ተሳፋሪ ይጣራል፡፡ በነገራችን ላይ ጉዟችን ከመካኒሳ ሜክሲኮ ያደርሰናል፡፡ ከወንበር በላይ የጫነው ወያላ፣ ‹‹የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ ዓብይ ላይ ጥላችሁ ፈታ ብላችሁ ተቀመጡ፤›› የሚል መልዕክት አስተላለፈ፡፡ በተጨባጭ እንኳንስ ፈታ ለማለት በአግባብ ያልተቀመጡ በርካታ ነበሩ፡፡ ሁኔታው ያበሳጨው፣ የሚባለውና እየሆነ ያለው ነገር ያልገጠመለት የሚመስል አንድ ሰው፣ ‹‹ስለምንድነው የምትቀባጥረው?›› በማለት ወያላውን ጠየቀው፡፡ ወያላው የለበጣ ሳቅ ፈገግ አለ፡፡ ሰውዬው ቀጠለ፣ ‹‹ጠጠር መጣያ በሌለበት ታክሲ ውስጥ ሰፋ በሉ ትለናለህ እንዴ?›› በማለት ሞገተው፡፡ ወያላውም፣ ‹‹ብራዘር ስለፖለቲካ ምንም ‹አይዲያ› የለሽም ማለት ነው?›› በማለት በአጭሩ መለሰለት፡፡
ይኼኔ ሰውዬው፣ ‹‹አንተም አሁን ስለፖለቲካ አውቃለሁ እያልከኝ ነው?›› በማለት ሲጠይቀው፡፡ ወያላው መልሶ፣ ‹‹ዓብይ ከመጣ በኋላ ፖለቲከኛ ያልሆነ ሰው ካለ፣ ያ ሰው አደባባይ ላይ ይውጣና በትልቅ ስክሪን እስከ ዛሬ ዓብይ የተናገራቸውን ንግግሮች እንዲያደምጥ ይወሰንበት፤›› አለው፡፡ ወይ ዘንድሮ? አንዳንዱ እኮ አነጋገሩን እንዴት እንደተካነው ግራ ያጋባል፡፡
አንድ እናት በበኩላቸው፣ ‹‹አገራችን ሰላም ከሆነችልን የፈለገ ፖለቲከኛ፣ ያሻው ነጋዴ፣ ሌላው ደግሞ እንደ በዝንባሌው መሰማራት ይችላል፤›› በማለት አጠር ያለ ማማብራሪያ ሰጡ፡፡ ከኋላ የተቀመጠ አንድ ጎልማሳ፣ ‹‹ምነው ይህን ያህል ዓብይ መንግሥት ያልነበረባት አገር ላይ የተሾመ አስመሰላችሁት?›› በማለት ትንሽ አወዛጋቢ ሐሳብ አነሳ፡፡ መንግሥት እንደነበራት ወደ ኋላ ዞር ብሎ ለማሰብ የፈለገ ሰው ያለ አይመስልም ነበር፡፡ ለዚህ ጥያቄ አንድ ሰው መልስ ሲሰጥ፣ ‹‹ከዓብይ በፊት መንግሥት ኖራትም አልኖራትም ያለፈውን ትተን የአሁኑንና የወደፊቱን እናውራ፤›› በማለት ትንታኔ መሰል ማብራሪያ ሞከረ፡፡ ሰውዬው ግን ቁጣውን በመቀጠል፣ ‹‹ያለፈውን በመዘንጋት የአሁኑንም ሆነ የወደፊቱን ማሰብ ስኬታችንን ሙሉ አያደርገውም፤›› በማለት አስረዳ፡፡
ወሬውን በጥሞና ሲያዳምጥ የነበረ ሌላ ሰው ተቀላቀለ፣ ‹‹ምንም ችግር የለውም እኮ ስላለፈው ማውራት? የትኛው እንዲወራልህ ነው የምትፈልገው?›› ብሎ ከጠየቀው በኋላ የእሱን መልስ ሳይጠብቅ፣ ‹‹የቱን ልንገርህ በየመሥሪያ ቤቱ የነበረውን ሙስና፣ በየመንግሥት ተቋማት የነበረውን መጉላላት፣ ወይስ ያላግባብ የነበረውን የሀብት ክፍፍል? የትኛውን ላውራልህ?›› እያለ ሌላ ጉዳይ ውስጥ ሰተት ብሎ ገባ፡፡
ወያላው ግራ ገብቶታል፡፡ ወሬው ወዳላሰበውና ወዳልጠበቀው አቅጣጫ አቅንቶበታል፡፡ ‹‹ማንንም መወንጀል የለብንም፡፡ ዘመኑ እኮ የይቅርታና የምሕረት ነው፤›› ሲል ሾፌሩ ተቀበለውና፣ ‹‹እንዴት ነህ እንዴት ነህ አንባባልም ወይ፣ ሰው ከአባቱ ገዳይ ይታረቅ የለም ወይ?›› እያለ ማንጎራጎ ሲጀምር ወያላው፣ ‹‹ሸጌ እንዴት ነሽ አንቺ እንዴት ነሽ . . . ›› እያለ አጀበው በጎርናና ለዘፈን በማይመች የወያላ ድምፅ፡፡ ይኼን ጊዜ ሾፌሩ፣ ‹‹ይህንን ዕድል ተጠቅመህ በዚህ ድምፅ ዘፈንክበት? መቼም አሁን የታመመ ሰው አይጠፋም፤›› በማለት አላገጠበት፡፡ በእርግጥ የወያላው ድምፅ የጆሮዋችንን ታምቡር ሊበሳው ጥቂት ቀርቶት ነበር፡፡
ወያላው ለሾፌሩ፣ ‹‹አዋጅ የለ ወራጅ የለ፣ ዝም ብለህ ንዳው . . . ›› በማለት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹ገና ቤተ መንግሥት ገብተን የሙዚቃ ሥራችንን እናቀርባለን፤›› በማለት ቀለደ፡፡ ይኼን ጊዜ በአነጋገሩ አፍረን ሳቃችንን ዋጥ አደረግን፡፡ ሾፌሩ ግን እስከ መጨረሻው ክትክት ብሎ ሳቀበት፡፡ ወያላው ግን፣ ‹‹ምን ያስቅሃል? ባለፈው ሰሞን በሚሊኒየም አዳራሽ ተገኝተው ሙዚቃ ሲኮመኩም እንደነበር አልሰማህም ማለት ነው?›› በማለት ቤተ መንግሥት ገብቼ አቀነቅናለሁ በሚለው ሐሳቡ ገፋበት፡፡ ሾፌሩም፣ ‹‹ገና ለገና የሆነ ሽግሽግ አለ ብለህ ሥራ ልትፈልግ ካልሆነ በስተቀር፣ በአንተ ድምፅ እንኳን ቤተ መንግሥት ልትጋበዝ ቤተሰብህ ራሱ የሚቀበለው ድምፅ አይደለም ያለህ፤›› በማለት ቀለደበት፡፡
ቀደም ሲል ሰውዬው፣ ከዚያ ወያላውና ሾፌሩ ያበረዱት ታክሲ ውስጥ ተመልሶ ውጥረት መስፈን ጀመረ፡፡ አንዱ በተከፋ ስሜት፣ ‹‹ሰውን ግን ምን ነክቶታል?›› በማለት ላነሳው ጥያቄ ወያላው ከአፉ ላይ መንጭቆ፣ ‹‹ያው ዓብይ የሚባል የፍቅር፣ የሰላምና የእርቅ አምባሳደር ልቡን ነክቶታል፤›› በማለት ለሰውዬው ጥያቄ መልስ ሰጠው፡፡ ይኼን ጊዜ ሰውዬው፣ ‹‹አንተ ምን ጥልቅ ያደርግሃል?›› ሲለው ወያላው በፍጥነት፣ ‹‹አንተ ወሬ ውስጥ መግባቴ ሲገርምህ ገና ቤተ መንግሥት ጥልቅ እላለሁ፤›› በማለት መለሰለት፡፡ ‹‹ሰውዬው በምን እንደተናደደ ባናውቅም ምናልባት በሕዝቡ ወይም ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተማሮ ሊሆን ይችላል (ተባሮ ሊሆን ይችላል) የሚል ጥርጣሬ ቢጤ እየገባኝ ነው . . . ›› የሚለኝ አጠገቤ የተቀመጠው ነው፡፡
ከሰውዬው ጋር አብሮ የተቀመጠው ጓደኛው ወሬ ጀመረ፣ ‹‹መንግሥት አልተለወጠም እኮ ድሮም የሚመራው ኢሕአዴግ ነበር፡፡ አሁንም እየመራ ያለው ራሱ ነው፤›› በማለት ጓደኛውን ለመደገፍ ሙከራ አደረገ፡፡ ይኼን ጊዜ አዲስ ተሳፋሪ አስተናገድን፡፡ ይህቺ ወጣት ገና ከመግባቷ መናገር ጀመረች፡፡ ‹‹ድሮ በርግጥ ኢሕአዴግ ሊሆን ይችላል ሲመራን የነበረው፡፡ አሁን ግን እየመራን ያለው ዓብይ ነው፤›› በማለት ዓብይ የሚል ሰንደቅ ከፍ አድርጋ አውለበለበች፡፡ በዚህ መሀል አድፍጦ ወሬውን ሲያዳምጥ የነበረ ወጣት፣ ‹‹ኢሕአዴግ እስከ ዛሬ በብዛት ራሱ ላይ ሲሠራ ቆይቶ ነበር፡፡ አሁን እንግዲህ ከወትሮ በተሻለ መንገድ ሰዎችን ለማገልገል ቆርጦ ተነስቷል፡፡ እሰየው ነው . . . ›› ሲል ከሁለቱ ሰዎች አንደኛው፣ ‹‹ድሮም በሥራ ላይ ነበረ፣ አሁንም በሥራ ላይ ነው፡፡ ወደፊትም ቢሆን እንደዚያው፤›› በማለት ተቆጥተው ተናገሩ፡፡ ይኼን ጊዜ በዚህ ሐሳብ ያልተስማማችው ወጣት ድጋሚ መናገር ጀመረች፡፡ ‹‹የወደፊቱን እርግጠኛ ሆነን መናገር ባንችል እንኳን አሁን ግን እየመራን ያለው ዓብይ ነው፤›› ስትል የግል ሐሳቧን አንፀባረቀች፡፡ ‹‹ይህች ጉብል ኢሕአዴግ ግዙፍ የሆነ መንግሥት መሆኑን የዘነጋች ትመስላለች፡፡ ከቤተ መንግሥት እስከ ቀበሌ ድረስ ሁሉንም ነገር የሚዘውረው ዓብይ ነው ብላ የምታምን ቢጤ ናት . . . ›› አለኝ አሁንም አጠገቤ የተቀመጠው፡፡
ሆኖም በሁለቱ ሰዎች ሁኔታ ብዙዎች የታክሲው ተሳፋሪዎች አልተደሰቱም፣ ወያላና ሾፌሩም እንደዚሁ፡፡ ይኼን ጊዜ ሾፌሩ እንደዚህ አለ ለወያላው፣ ‹‹አንዳንድ ሰዎች ተማረው ካናገሩህ . . . ›› አለው ወያላውም፣ ‹‹እሺ?›› በማለት ወሬውን ተቀበለው ወሬው ባያስቅ እንኳን እንዲሁ አሽሙር እንደሆነ ገብቶት ለመሳቅ እያቀባበለ ነበር፡፡ ሾፌሩም ቀጠለ፣ ‹‹ . . . ተባረው ሊሆን ይችላል፤›› ብሎ ሳይጨርስ ወያላው ያቀባበለውን ሳቅ ለቀቀው፡፡
ወያላው አዲሱን የታክሲ ታሪፍ ጭማሪ ዓብይ ያመጣው መስሎታል፡፡ ሁሉም ነገር ዓብይ፣ ዓብይ ሆነዋል፡፡ ‹‹ወደፊት አንድ ቀን ምን ያጋጥመናል ብዬ እንደምገምት ታውቃለህ?›› በማለት ሾፌሩን ጠየቀው፡፡ ሾፌሩም፣ ‹‹ሰሞኑን ደግሞ ልትሞት ነው መሰለኝ ምኞት አብዝተሃል . . . ›› ካለው በኋላ፣ ‹‹ደግሞ ዛሬ ምን ተመኘህ?›› ሲለው፣ ‹‹አንድ ጠዋት ግን ታክሲያችን ውስጥ ጠቅላዩን እንዳላገኛቸው እሠጋለሁ፤›› በማለት ያሰበውን ነገረው፡፡ እኛም ምኞት እንደሆነ አይከለከልም በማለት ወደ መጨረሻችን ደርሰን ስለነበር፣ ከታክሲው ወርደን ወደ ሜክሲኮ የሰው ትርምስምስ ውስጥ ገብተን በየአቅጣጫችን ስንበታተን የምኞታችንን ነገር እያሰላሰልን ነበር፡፡ መልካም ጉዞ!