Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
    - ማስታወቂያ -
    - ማስታወቂያ -

    አቢሲንያ ባንክ አዲስ ዓርማ ይፋ አደረገ

    - ማስታወቂያ -

    ተዛማጅ ፅሁፎች

    አቢሲኒያ ባንክ ከ22 ዓመታት በላይ በፋይናንስ ሥራ መስክ የቆየና ከደርግ መንግሥት በኋላ ኢንዱስትሪውን ከተቀላቀሉ ቀዳሚ የግል ባንኮች አንዱ ነው፡፡ ባንኩ ሥራ ሲጀምር መለያው ወይም የኩባንያው ብራንድ በማድረግ እስከ ዛሬ ሲገለገልበት የቆየውን ዓርማ አሻሽሏል፡፡ ከቅዳሜ፣ ግንቦት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በተሻሻለው አዲሱ ዓርማ መጠቀም መጀመሩን ይፋ አድርጓል፡፡

    ባንኩ ዓርማውን ከማሻሻሉ በተጨማሪ ለ20 ዓመታት ሲተዋወቅበት የቆየውን መሪ ቃልም ለውጧል፡፡ በአንጋፋው የማስታወቂያ ባለሙያ አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ አንደበት እየተነገረ በሚተላለፈው ‹‹አቢሲኒያ የትጉሃን መናኸሪያ›› የባንኩ የማስታወቂያ መሪ ቃል ለውጧል፡፡ አዲሱን ዓርማና መሪ ቃል አሁንም በማስተዋወቅ እንደሚዘልቁ የሚጠበቁት አቶ ውብሸት ‹‹አቢሲኒያ የትጉሃን መናኸሪያ›› የሚለውን ቀይረው ‹‹አቢሲኒያ የሁሉም›› በማለት የባንኩን እንቅስቃሴዎች ያስነግራሉ ተብሏል፡፡

    ባንኩ የዓርማ ማሻሻያውን ለማድረግ የወሰነበትን ምክንያት የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ አስማረ ሲናገሩ፣ ‹‹ባንኩን የበለጠ ለመግለጽ ተፈልጎ ነው፡፡ የባንኩን ራዕይ ለማሳካት ጉልህ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ተብሎ ከተቀመጡት ተግባራት ውስጥ አንዱ የባንኩን መለያ በአግባቡና ወጥነት ባለው መልኩ መጠቀም አስፈላጊ በመሆኑ የተወሰነ ነው፤›› ብለዋል፡፡

    ባንኩን በማማከር ድሎይት የተባለው ኩባንያ የተሳተፈ ሲሆን፣ አማካሪው ባደረገው የዳሰሳ ጥናትም፣ የአቢሲኒያ ባንክ መለያ አንድ ወጥ የመሆን ችግር እንዳለበት አመላክቷል፡፡

    የተዳሰሱት ሦስቱ ዓበይት ጉዳዮች

    ስለባንኩ ሲነሳ በደንበኞቹ አዕምሮ ውስጥ በፍጥነት ሊመጣ የሚችል ባንክ የትኛው እንደሆነ፣ አንጋፋ ባንክ ሲባልም ካሉት ባንኮች የትኛው ባንክ እንደሆነ በሰዎች በአዕምሮ እንደሚከሰትና ደንበኞች አሁን ከሚጠቀሙበት ባንክ ወደ ሌላ መቀየር ቢፈልጉ የትኛውን ባንክ ይመርጣሉ በሚሉ መመዘኛዎች መሠረት፣ የባንኩን መለያ ወይም ብራንድ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ የባንኩን ነባር ዓርማ በአዲስ እንዲቀየር መደረጉን የባንኩ መረጃ ያስረዳል፡፡ የአቢሲኒያ ባንክ አዲሱ ዓርማም ከነባሩ መጠነኛ የቀለምና የቅርፅ ለውጦች ተደርገውበት እንደተቀየረ የባንኩ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡

    መጠነኛ ማሻሻያ የተደረገባት፣ በነጭ መደብ ላይ ያረፈች፣ ባለ ስድስት ቅጠል ወርቃማ ቢጫ የአደይ አበባ የባንኩ ዓርማ ሆና ትቀጥላለች ያለው ባንኩ፣ የመጀመርያው የቀለም ምርጫው ወርቃማ ቢጫ በነጭ መደብ ያረፈ ዓርማ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ የመረጠው ደግሞ ልዩ ልዩ ቀለማት የተካተቱበት የዓደይ አበባዋ ዓርማ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ አቢሲኒያ ባንክም ዋነኛ ቀለሙን (ቢጫ ወይም ወርቃማ የዓደይ አበባ በነጭ መደብ) እንዲሁም ነጭ አበባ በቢጫ መደብና ቢጫ አበባ በጥቁር መደብ በማድረግ እንደአስፈላጊነታቸው የሚጠቀም ሲሆን፣ በተለያየ ቀለማት አንድ ዓይነት ዓርማ ይፋ አድርጓል፡፡

    ይህንን ዓርማ ለማስቅረጽ ዓለም አቀፍ ጨረታ እንዳወጣ የገለጹት አቶ ሙሉጌታ፣ በዘርፉ ልዩ ሙያ ያላቸው ዓለም አቀፍ አማካሪ ኩባንያዎችም ተሳትፈውበታል፡፡ የቴክኒክና የፋይናንስ ውድድር በኩባንያዎቹ መካከል በማድረግ፣ በጨረታው ያሸነፈው HKLM የተባለ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ አቶ ሙሉጌታ ኩባንያው በጨረታ ያሸነፈበትን ዋጋ ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ባንኩ ለኩባንያው አገልግሎት ወፍራም ክፍያ ተከፍሎታል ብለዋል፡፡

    አቢሲኒያ ባንክ በ1988 ዓ.ም. ሥራ ሲጀምር በ50 ሚሊዮን ብር ካፒታል የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን የተቀላቀለ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ የተፈቀደ ካፒታሉን አራት ቢሊዮን ብር በማድረስ እየሠራ የሚገኝ የግል ባንክ ነው፡፡

    ከዚህ ቀደም የዓርማ ለውጥ ካደረጉ ባንኮች መካከል ንብ ባንክ፣ ወጋገን ባንክ፣ ዳሸን ባንክ፣ አዋሽ ባንክ እንዲሁም የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ይጠቀሳሉ፡፡

    spot_img
    - Advertisement -spot_img

    የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

    - ማስታወቂያ -

    በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች