Sunday, December 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የደቡብ መለስ አካዴሚን ለመገንባት የወጣው ጨረታ ጥያቄ አስነሳ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚጠይቅ ለሚገመተው የደቡብ መለስ አመራር አካዴሚን ለመገንባት ለወጣው ጨረታ ተወዳዳሪ ተቋራጮች ያቀረቡት የፋይናንስ ዝርዝር የጨረታ ሰነድ ሳይከፈት ቀረ፡፡

  በደቡብ ክልል እንዲገነባ የታቀደው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መታሰቢያ የአመራሮች የሥልጠና አካዴሚን እንዲገነቡ ለተቋራጮች የወጣው ጨረታ ውጤት፣ ሚያዝያ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ተከፍቶ ውጤቱ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቅ ነበር፡፡ ስለዚሁ የጨረታ ሒደት የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ በጨረታው ለመወዳደር ከቀረቡት ተቋራጮች መካከል ሁለቱ የቴክኒክ ግምገማውን እንዳላሟሉ የተገለጸላቸው ሲሆን፣ ሦስቱ እንዳለፉ ተነገሯቸው ነበር፡፡ ሆኖም በቴክኒክ ግምገማው ውጤት ላይ ቅሬታ የነበራቸው ተጫራቾች፣ ውጤቱን በመቃወም ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት፣ በፋይናንስ መጠይቁ መሠረት ለጨረታ ያቀረቡት የዋጋ መወዳደሪያ ሰነድ እንዳይከፈት ተደርጓል፡፡

  ይህ ውሳኔ የጨረታውን ትክክለኛ አሠራር እንደሚቃረን የሚገልጹት ምንጮች፣ የጨረታው ሒደት እንዲፈተሽላቸው ጠይቀዋል፡፡ ጉዳዩን ለመመርመር የክልሉ የግዥ ኤጀንሲ መወዳደሪያውና ውጤቱ እንዳይከፈት አድርጓል፡፡

  በአሁኑ ወቅት እየተለመደ የመጣና የኮንስትራክሽን ዘርፉን የሚያንቋሽሽ፣ ፍትሐዊነት እንዳይኖር የሚያደርግ፣ የሕጋዊነት ከለላ ያለው በሚመስል አካሄድ የተጠና የተንኮል አሠራር እንደሚታይ የሚገልጹ ወገኖች፣ በዚህ ጨረታ ዙሪያም እንዲህ ያለው ተግባር ስለመታየቱ ይናገራሉ፡፡ 

  እንዲህ ያለው ድርጊት ከመነሻውም ጨረታውን እንዲያሸንፍ የተፈለገው አካል ወይም ሥራውን እንዲያገኝ የሚፈለገው ተቋራጭ ሆን ተብሎ የተዘጋጀ መስፈርት እንዲቀርብለት በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተደረገ ነው በማለት ተቋራጮች ስሞታ ያቀርባሉ፡፡ በዚህ ሒደት ሌሎች ተወዳዳሪዎች ከጨረታው በተለያዩ ዘዴዎች ከውድድሩ ውጪ እንዲሆኑ እንደሚደረጉና ጨረታውን እንዲወስድ የተፈለገውን አካል አሸናፊ የማድረግ አሠራር በግንባታ ሥራ የጨረታ ሒደቶች ላይ ስለሚታዩ፣ የመለስ አካዳሚ የጨረታ ሒደት ከዚህ እንዲፀዳ ይታይልን በማለት አቤቱታቸውን ያሰሙት የጨረታው ተሳታፊዎች ናቸው፡፡

  ጨረታውን እንዲያሸንፍ የተፈለገው አካል ማሸነፍ ሲያቅተው ደግሞ፣ ሕጋዊ ሒደት በማስመሰል ጨረታን በማን አለብኝነት መሰረዝም በጨረታዎች ሒደት ውስጥ የሚታይ ችግር እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ሥልት በርካታ ጨረታዎች መሰረዛቸውም እየተነገረ ነው፡፡ የደቡብ ክልል መለስ አካዴሚ የግንባታ ጨረታ እንዲህ ካለው አጠያያቂ ሒደት ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ሥጋታቸውን የገለጹት ተጫራቾች ሒደቱ እንዲጣራላቸውም አሳስበዋል፡፡

  ጨረታው ለደረጃ አንድ ተቋራጮች የወጣ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ማርች 26 ቀን 2018 አምስት ተወዳዳሪዎች የጨረታ ሰነዱን ሞልተው ቢያስገቡም፣ በማጣራት ሒደት የጨረታ መስፈርቱን አላሟሉም የተባሉ ሁለት ተጫራቾች ከውድድሩ ውጪ መደረጋቸው ቅሬታ አስነስቷል፡፡ የጨረታ ሕጉና መመርያው በሚፈቅደው መሠረት ለተነሳው ቅሬታ መልስ መስጠት ሲገባ፣ ምክንያት ፈልጎ ጨረታውን መሠረዝ አግባብ እንዳልሆነ ያመለክታሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪም ክስ ከቀረበ በኋላ ጨረታን መሰረዝ ተገቢነት እንደሌለው በመደንገጉ ይህ አሠራር ሊከበር እንደሚገባም ይጠይቃሉ፡፡

  በመሆኑም ጉዳዩ የሚመለከተው የክልሉ ኮንስትራክሽን ቢሮ፣ ጉዳዩን በጥልቀት የሚያውቀው በመሆኑ እንዲህ ዓይነቱን የመልካም አስተዳደር መጓደልና ኢፍትሐዊ አሠራር እንዲያስቆም፣ ጨረታውን እንዳሰኘው መሰረዝና ማስቆም እንደማይቻል ተገንዝቦ ተገቢውን የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡

  የደቡብ መለስ አመራር አካዴሚ ኃላፊዎች በተነሳው የጨረታ ቅሬታ ሒደት ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ሪፖርተር በስልክ ያነጋገራቸው የአካዴሚው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰላሙ ሱላ እንደገለጹት፣ ተጫራቾች በጨረታው ለመሳተፍ ያቀረቡት የመወዳደሪያ ዋጋ ሰነድ አልተከፈተም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ከተጫራቾቹ መካከል በቴክኒካል ምዘናው ወቅት ማለፍ እንዳልቻለ የተገለጸለት ተቋራጭ ቅሬታ በማቅረቡ ነው፡፡

  በሕጉ መሠረት በጨረታው ሒደት ወቅት፣ በቴክኒክ ምዘናው ምክንያት መውደቅ እንደማይገባው ቅሬታ ያቀረበ ተጫራች ሲኖር የጨረታውን መወዳደሪያ ዋናው ሰነድ (ፋይናንሱን የሚያመላክተው) መክፈት አይቻልም፡፡

  ይህ በመሆኑም በቅሬታው መሠረት ጉዳዩን እንዲመረምር የአካዴሚው ጨረታ ኮሚቴ ስለ ጨረታው ሒደት የደረሰበትን ድምዳሜና የእያንዳንዱን ተጫራች የምዘና  ውጤት የሚያሳይ መረጃ ለክልሉ ግዥ ኤጀንሲ እንዲቀርብ መደረጉ ተገልጿል፡፡ የግዥ ኤጀንሲው የሚሰጠውን ውሳኔ እየተጠባበቀ እንደሚገኝ የአካዴሚው አስተዳደር አስታውቋል፡፡ ተከታዩ የጨረታ ሒደት ምን መሆን እንዳለበት ውሳኔ የሚሰጠውም ኤጀንሲው እንደሆነ ተገልጿል፡፡

   በጨረታው ሒደት ለግንባታ የቀረበው የተጫራቾቹ ዋጋ ከታሸገበት ሰነድ ተከፍቶ ይታይ አሊያም በቀረበው ቅሬታ መሠረት በቴክኒክ ምዘና ወቅት የወደቁት ተቋራጮች መልሰው በጨረታው ይሳተፉ በሚለው ላይ  ኤጀንሲው ውሳኔ እንደሚሰጥ ይጠበቃል ተብሏል፡፡ ይህ በመሆኑም የጨረታው ሒደት ሕጉን ጠብቆ እየሄደ ስለመሆኑና ከሕግ ውጪ የሚፈጸም ነገር እንደሌለ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ አካዴሚው ጨረታውን ሊሰረዝ ስለሚችልበት ጉዳይ ተጠይቀው ምላሽ የሰጡት አቶ ሰላሙ፣ ጨረውታውን ለመሰረዝ የሕግ ድጋፍ እንዳለውም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች